ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

በሰሜን የኤርትራና ሶማሊያ ወታደሮች ጣልቃ ገብተዋል መባሉን መንግስት ” ፈጠራ የሮኬት ተኳሹ ወሬ” አለው

” ጉዳዩን ቀጠናዊ ማድረግና የሌሎችን ጣልቃ ገብነት ለመጋበዘ የሚደረግ ነው። ይህንንም የሚያደረገው ወደ አስመራ ሮኬት ሲጥል የነበረው ሃይል ነው” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ አስታወቁ።
አቶ ዲና ሙፍቲ ይህን ያሉት ዛሬ በውቅታዊ የሱዳንና ኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሲሰጡ ነው። በመግለጫቸው በሰሜን ኢትዮጵያ የኤርትራና ሶማሊያ ወታደሮች እንደገቡ ተደርጎ የሚራገበው ወሬም ከእውነት የራቀ እንደሆነ አመልክተዋል። አያይዘውም ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር በድንበር ጉዳይ ያላትን ልዩነት ያለሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት በውይይትና በድርድር ለመፍታት ዝግጁ መሆኗንና ሱዳንም የኢትዮጵያን አቋም ልትቀበለው እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ቃል አቀባዩ እንዳሉት ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያለውን ልዩነት ያለሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ለመነጋገርና በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እሳቸውን ጠቅሶ እንደዘገበው ኢትዮጵያ ፍቃደኛ እስከሆነች ድረስ የሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት አያስፈልግም፡፡ በፊትም በድንበሩ ጉዳይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ውይይት ሲደረግ እንደነበር አስታውሰው፤ የሱዳን ኃይል ወደ ነበረበት ቦታ እንዲመለስና ውይይቱ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ፍላጎት መሆኑን ነው አምባሳደር ዲና የገለጹት፡፡
ለማስታረቅና ለማሸማገል ፍላጎት ያሳዩ ሀገራት ችግሩ በሰላም እንዲፈታ ካላቸው ፍላጎት በመሆኑ እናደንቃለን ብለዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ለመነጋገር ዝግጁ ናት፤ ለውይይቱም የሚመቸው በራሳችን ውይይት ተደርጎ ቢፈታ ነው›› ብለዋል፡፡
ሁለታችንም ተነጋግረን ብንፈታው ዘለቄታ ይኖረዋል፤ በተጽዕኖ የሚደረግ ሽምግልና ብዙ ጊዜ ውጤቱ ዘላቂ እንደማይሆንም ነው የጠቆሙት፡፡
የኢትዮጵያና ሱዳን ግንኙነት ጥልቅ፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ በተለይም የችግር ዘመናትን ሁሉ የዋጀ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡ የሁለቱ ሀገራት ትስስር አንዱ የአንዱን ጥቅምም ጉዳትም የሚጋራበት ግንኙነት መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
የኢትዮጵያ አመራር ለሱዳን ሰላምና መረጋጋት በርካታ ጥረቶች ማድረጉን በማስታወስ በሰላም ማስከበርና በሱዳን ያሉትን የፖለቲካ ኃይሎች አንድ ላይ ለማምጣት በኢትዮጵያ አመራር የተደረገው ጥረት በሱዳን ህዝብ ጭምር ከበሬታ ያገኘ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በታሪክም ሁለቱ አገራት ከመደጋገፍ ይልቅ ወደ ግጭት የሚሄድ ጉዳይ እንዳልነበረ በመጠቆም፤ የሁለቱ አገራት መናቆር ሁለቱንም እንደሚጎዳ እናምናለን ብለዋል፡፡ ሂደቱም የሱዳን ህዝብ ፍላጎት ነው ብለን አናምንም ሲሉም ነው አምባሳደሩ የተናገሩት፡፡ ነገር ግን የድንበሩን ጉዳይ እያራገቡ ሁለቱን አገራት በማባላት በመሃል የራሳቸውን ጥቅም መፍጠር የሚፈልጉ አገራት እንደሚሰሩ እናምናለን ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ህግ ለማስከበር ፊቱን ባዞረበት አጋጣሚ በድንበር አካባቢ ለሁለቱም አገራት የማይመቹ ነገሮች እንዳይሰሩና ሌሎች እንቅስቃሴዎች እንዳይደረጉ በኢትዮጵያ አመራር አደራ ተሰጥቶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ወደ ድንበር እንዲገቡ አልፈውም የእኛ ነው እንዲሉ የተባለ ነገር አልነበረም›› ብለዋል፡፡
‹‹ድንበራችሁን ዝጉ እኛ የህግ ማስከበር ስራ እየሰራን ነን፣ አጋጣሚውን ተጠቅመው ወደ እናንተ ገብተው ከናንተ ተመልሰው ሊያጠቁና ሊበጠብጡ የሚችሉ ሰዎች እንዳይኖሩ፣ እንዳያጋጩንና በሁለታችን መካከል አለመግባባት እንዳይፈጥሩብን ጠብቁ ነው የተባሉት›› ሲሉም አስታውሰዋል፡፡
የኤርትራና ሶማሊያ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ጋር ሆነው ይወጉናል በሚል እየተናፈሰ ያለው መሰረተ ቢስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ዳር ድንበሩን ከማንም ወራሪ ሃይል ጠብቆ የቆየ ሃይል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አልፎም በሩዋንዳ፣ በብሩንዲ፣ በኮንጎ፣ በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳን ትልቅ ገድል የሰራ ሃይል መሆኑን ነው ያስታወሱት፡፡
በአገር ውስጥ የህግ የበላይነትን ለማስከበር አቅምና ብቃት እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ ማንንም አገር የሚጠራ አይደለም፣ የተጠራ አገር የለም ሊጠራ አይገባም፣ አይፈልግምም ብለዋል፡፡ ይህንን የሚያስወራው ጉዳዩን ቀጠናዊ ለማድረግ፣ የሌላውን ጣልቃ ገብነት ለመጋበዝ የሚፈልግ ሃይል ነው፣ ይሄ ሃይል በተግባር ሮኬት ወደ አስመራ ሲለቅ የነበረ ነው ብለዋል፡፡
ዘላለም ግዛው

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ዶክተር አብራሃም በላይ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳድር ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነው ተሾሙ!
0Shares
0
Read previous post:
ኢትዮጵያ በወታደራዊ ኃይል ጥንካሬ ከአፍሪካ 6ኛ ከዓለም 60ኛ ሆነች

ግሎባል ፋየር ፓወር በዓለም ዙሪያ ካሉ አገራት መካከል ባደረገው የወታደራዊ ጥንካሬ ምዘና፣ ከ50 በላይ መመዘኛዎችን...

Close