በውጭ ወራሪም ሆነ በውስጥ ባንዳ ተባባሪ ያልተሞከረብን የለም። በየዘመናቱ እንቁ የኢትዮጵያ ልጆችን ገብረናል ፣ ቆስለናል ፣ ደምተናል ፣ ሞተናል። እኛ ኢትዮጵያዊያን እኮ ተፈትነን እንጂ ወድቀን አናውቅም ። ምክንያቱም በዓይነቱ የተለየ መሣሪያ ታጥቀናልና ነው።
ቀለብ እየተሰፈረለት የገዛ ሀገሩን ለመበጥበጥ የለፋና የደከመው እልፍ ነው ፣ አንዱ በአንዱ ላይ እንዲነሣ ለፍተው የተሳካላቸው መስሏቸው ጮቤ የረገጡት ተቆጥረው አያልቁም ። እኩይ ተልዕኳቸውን እውን አድርገው ፍርስራሿን ለማየት ቋምጠው ዞር ብለው ሲያዩ ዓርማዋ በሠንደቋ ላይ ሆኖ ከፍ ብሎ ሲውብለበለብ ይመለከቱና በድንጋጤ ክው ይላሉ ። ምክንያቱም የአገራችንን የአኬልዳማነት ድግስ በያዝነው የተለየ መሣሪያ ገና ድሮ ነውና የመከትነው።
ስለተለየው ትጥቃችን ሲነሳ በተለይም ከባድነቱ ብዙዎች ብዙ ግምት እንዲሰጡ ሊያደርግ ይችላል። የተብላላ ኒውክሊየር ፣ ተወንጫፊ ወይም ባላስቲክ ሚሳኤል ፣ ሰው አልባ ድሮኖች ፣ በብርሃን ፍጥነት ኢላማን ዶግአመድ የሚያደርጉ እጅግ ዘመናዊ ጄቶች ፣ ባህር ሰርጓጅ ፣ ታንኮች ፣ ረጅም ርቀት መቺ መድፎች ብቻ ምን አለፋችሁ እስካሁን ያልታዩና የተለዩ ወታደራዊ ግኝቶች የተሞሉባቸው የነፍስ ወከፍና የቡድን መሣሪያዎችን ሊገምት ይችላል ።በፍፁም ግን አይደለም ። ነገሩ ወዲህ ነው።

እኛ የታጠቅነው መሣሪያ ረብጣ ዶላሮችን ማፍሰስ ስለቻሉ ብቻ ገበያ ላይ የሚገዙት ፣ በሀያላኑ ወይም በወዳጅ አገራት በብድር ፣ በእርዳታም ሆነ በትብብር መታጠቅ የሚቻል አይደለም ፤ የሚፈታና የሚገጠም ፣ በስልጠና ብዛት አጠቃቀሙን የምንካነውም አይደለም።
በተቆጠረለት ልክ እናት አገር ከፍተኛ ማዕረግ ሠጥታው ሀይል ይገነባልኛል ፣ ይመራልኛል ፣ ይጠብቀኛል ፣ ያስጠብቀኛል ያለችው ጄኔራል መኮንን እንደ ተሾመበት አላማ ሳይሆን ከመሪ መርህ ውጭ በጁንታዊ ደባ ናውዞ ፥ ከህሊናው ተጣልቶ ከወታደራዊው ሙያዊ ስነምግባር አፈንግጦ ያደረገውን አድርጏል ።


እኛ የታጠቅነው መሣሪያ ከሁሉም በእጅጉ ይለያል እሱም “ኢትዮጵያዊ ስነልቦና” ነው። ያውም ጥንት አበው በከበረ የደም ዋጋ አቅልመው ያወረሱን የአልደፈርና የአልሸነፍ ባይነት ታሪክ ፣ ለትልቋ ሀገር ዘላቂ ህልውና ትንሹን ሰብአዊ ፣ ግላዊና ጥቅማዊ ፍላጎት ወደ ጎን ትቶ ስለ ህብራዊ የአንድነት ክብር በፍቅር የመሞት ማንነታዊ የውርስ ስነልቦና ነው።
ብዙዎች ጥልቁን የአናብስት ምድር ግዙፍ መሣሪያ ትተው በሠው ሠራሽ የትጥቅ ጋጋታ ይገምቱናል ። ኋላቀር ደካማ ናቸው ብለው በተነሱ ቁጥር የማይታየውን የኢትዮጵያዊ ስነልቦና ቃታችንን እየሳብን ከነ ድንፋታቸው በመጡበት አስቀርተናቸዋል።
ለዚህ ደግሞ የጥቁር ክንድ መስካሪው የአድዋ ገድል ፣ የፋኖነታችን ማሳያው የካራማራ ድል አብነቶች ቢሆኑም ፣ የየዘመኑ ጠላቶቻችን ወደፊት እንጂ ወደኃላ አይመለከቱም ።
እኛ ኢትዮጵያዊያን ዛሬም ሆነ ነገ ልክ እንደ ትናንቱ ለሚነሱብን ሁሉ የነበረን የተለየ መሣሪያ ከፊት ቀድሞ ይጠብቃቸዋል።
አዎ የማንሸነፈው የተለየ መሣሪያ ስለታጠቅን ነው።
ሻምበል ፈይሳ ናኔቻ