የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር የአገር ሕልውናን ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች መስማማታቸውን አስታወቀ።
ባለፈው ዓመት ሰላም ሚኒስቴር፣ እርቀ ሰላም ኮሚሽን፣ ዴስቲኒ ኢትዮጵያና የሃሳብ ማዕድን ጨምሮ በአጠቃላይ ሰባት ድርጅቶች በጋራ የመሰረቱት ‘ማይንድ ኢትዮጵያ’ ሁሉን አቀፍ የምክክር አጀንዳዎች መካከል ብሔራዊ መግባባት አንዱ ነው።
‘ማይንድ ኢትዮጵያ’ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ከሚያከናውናቸው የልሂቃን ተኮር የምክክር መድረኮች መካከል የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክክር መድረክ ይገኝበታል።
ባለፈው ሳምንት ገዥውን ፓርቲ ብልጽግናን ጨምሮ የተለያዩ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ያሰባሰበው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በአገራዊ መግባባት ላይ የሶስት ቀናት ምክክር በዝግ አካሂዷል።
የጋራ ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ግርማ በቀለ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በመድረኩ ቅድመ እና ድሕረ ምርጫ በሚሉ አጀንዳዎች ላይ ከመግባባት ተደርሷል።
በዚህም ከምርጫ በፊት 12 የአጭር ጊዜ አጀንዳዎች እንዲሁም ከምርጫ በኋላ 5 በረጅም ጊዜ የሚፈቱ አጀንዳዎች ለይቶ ወደ ስራ ለመግባት ስምምነት ላይ መድረሱን ገልጸዋል።
ከነዚህም መካከል የምርጫ ቦርድና የሚዲያ ገለልተኝነት፣ የሕግ የበላይነት፣ ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች እንዲሁም ሕገ መንግስታዊና የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የረጅም ጊዜ አጀንዳዎች ለአብነት ጠቅሰዋል።
ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር በምክክር መድረኩ በተለዩ አጀንዳዎች ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች መለየታቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ህልውና ለማስቀጠል ብሔራዊ መግባባት መፍጠር እንደሚያስፈልግ የገለጹት አቶ ግርማ፤ ፓርቲዎች የጋራ መግባባት ለመፍጠር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል።
የሶስት ቀናቱ ውይይት ከዚህ በፊት ከተደረጉ ሌሎች መድረኮች የተለየ አካሄድ የተከተለና መደማመጥ፣ መቀራረብና መግባባት የተደረሰበት መድረክ እንደነበረም አንስተዋል።
በቀጣይ አገራዊ መግባባት በመፍጠር የአገር ህልውናን ለማስቀጠል አስፈላጊ በመሆኑ ልዩነቶችን አስታርቆ ማስኬድ የሚያስችል መድረክ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪ አቅርበዋል።
ጥር 13 ቀን 2013 (ኢዜአ)

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   በሳሊቫኪርና በሪክ ማቻር መካከል እያገረሸ ያለውን ቅራኔ እየተባባሰ በመምጣቱ በደቡብ ሱዳን አዲስ ግጭት እንዳያገረሽ ተሰግቷል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *