. በሙስና የተገኘን ሀብት ማገድ፤ ማስመለስ እና የማካካሻ ምንነት
በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተመዘበረ ሀብት ማስመለስ ጽንሰ ሀሳብ መነሻ በሙስና ወንጀል፤ በታክስ ማጭበርበር ፤ በህገ ወጥ መንገድ የተገኘን ሃብት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ፤ ህገ ወጥ የሰዎች ዝዉዉር እና በሰዎች መንገድ ሌሎች በርካታ ወንጀሎች አማካኝነት የተገኘን ሀብት ለማስመለስ ቡዙ የህግ ማእቀፎች ቢደነገጉም በዚህ አጭር ጽሁፍ ከ በሙስና ወንጀሎች የተመዘበሩ ሀብት ማስመለስን ከሙስና ወንጀሎች አንፃር ብቻ ለማየት ተሞክሯል፡፡
የሙስና ወንጀል የሚፈፀመው ህገወጥ ጥቅም ለራስ ለማግኘት፣ ለሌሎች ለማስገኘት ወይም በሌሎች ሰዎች መብትና ጥቅም ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ ሲሆን መንግስት እና ግለሰብ የወንጀሉ ዋና ተጎጂ ይሆናሉ፡፡
በመሆኑም በሙስና ወንጀል ፈፃሚዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው አጥፊዎችን መርምሮና ከሶ በማስቀጣት ብቻ ሳይሆን በወንጀሉ የተገኘውን የወንጀል ፍሬ በመውረስ እንዲሁም በወንጀሉ ምክንያት ጉዳት የደረሰበትን አካል እንዲካስ በማድረግ ነው፡፡
ይህም በዋናነት ሶስት አላማዎችን የሚያሳካ ሲሆን የመጀመሪያው ዓላማ በሙስና ወንጀል የተገኘውን ሀብት በማስመለስ ሙስና አስከፊና አትራፊ አለመሆኑን ለአጥፊውም ለሌሎችም ማስተማሪያ ማድረግ ሁለተኛው ደግሞ በህገወጥ መንገድ የተገኘውን ንብረትና ገንዘብ ከጤናማው ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውጪ በማድረግ ህጋዊ ስራዎች፤ ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲበረታታ ማድረግ ነው፡፡
ሶስተኛው አላማ ወንጀል ፈፃሚዎችን የወንጀሉን ፍሬ በማሳጣትና የወንጀሉን ምንጭ በማድረቅ ተጨማሪ ወንጀል የመፈፀም አቅማቸውን ማሳጣት ነው፡፡
በአዋጅ ቁ 434/97 በአዋጅ ቁ 882/07 እንደተሻሻለዉ ከአንቀጽ 7 ጀምሮ ያሉት ተከታዮች ድንጋጌዎች በወንጀል የተገኘውን ሃብት ማስመለስ ሲባል የወንጀል ፍሬ አስቀድሞ በመያዝ ህጋዊ በሆነ መንገድ በፍ/ቤት እና በአስተዳደር መ/ቤት መንገድ እንዲወረስ ወይም ለህጋዊ ባለቤቱ እንዲመለስ ማድረግን፣ በሙስና ወንጀሉ የተገኘው ሃብት የአጥፊውን ንብረት አፈላልጎ በመሸጥ ተመጣጣኝ የሆነ ማካካሻ ለመንግስት ወይም ጉዳቱ ለደሰበት አካል ገቢ የማድረግ ትርጉምን ይሰጣል፡፡
2. የሚታገዱ እና የማይታገዱ የሀብት አይነቶች የሙስና ወንጀል አፈጻጸሙ እጅግ ዉስብስብ፤ በተቀናጀና በተጠና መንገድ የሚፈጸም በመሆኑ በሙስና የተገኘ ህብትን ለማስመለስ ዋነኛዉ ቁልፍ ተግባር ንብረቱ ከመሸሹ በፊት አስቀድሞ ሚስጥራዊ በሆነ ስልት ጥናት በማድረግ ንብረቱን ለይቶ ማገድ ሲሆን በቂ እና አሳማኝ ማስረጃ በማቅረብ ተገቢዉን ክስ አቅርቦ በፍ/ቤት ዉሳኔ እንዲወረሱ ማድረግ ነዉ ፡፡
የሚታገደዉ ንብረት ሁለት አይነት ሲሆን አንደኛው በአዋጅ ቁ. 434/97 አንቀፅ 8 መሰረት የወንጀል ፍሬ የሚባለው ሲሆን ይህ አይነቱ ንብረት በቀጥታ የወንጀል ፍሬ መሆኑ በመርማሪ ወይም በዐቃቤ ህግ በቃለ መሃላ ተደግፎ ሲቀርብ የሚታገድ ሆኖ በማስረጃ ሲረጋገጥ በፍርድ ቤት ውሳኔ ሲወረስ ሁለተኛው በዚሁ አዋጅ ቀ. 434/97 አንቀፅ 9 መሰረት የማካካሻ ንብረት ሲሆን የወንጀሉ ፍሬ የተባለው ሃብት ማስረጃ ባይቀርብበትም በምርመራ ላይ ወይም በክስ ላይ እንዳለ በቃለ መሃላ ተደግፎ ሲቀርብ በሙስና ወንጀሉ ምክንያት የደረሰ ጉዳት/ጥቅም ካለ ለደረሰው ጉዳት ወይም ለተገኘው ጥቅም ማካካሻ እንዲሆን የተከሳሹ ወይም የቅርብ ቤተሰብ ተመጣጣኝ ንብረት ተሸጦ በማካካሻነት የሚውልበት ሁኔታ ይኖራል፡፡
የቅርብ ቤተሰብ ሲል ባል፤ሚስት እና 18 ዓመት ያልሞላዉ ልጅ ሃብትን የሚያካትት ሲሆን በአብዛኛዉ የወንጀሉ ትስስር ከዚህ ቤተሰብ ዉጭ ባሉ የቅርብ ዘመዶች ጭምር ተሳትፎ ያለዉ በመሆኑ ህጉ በሰፊዉ ቢመለከተዉ ይመከራል፡፡
በሌላ በኩል ፍ/ቤቱ የተለየ ትእዛዝ ካልሰጠ በቀር ተከሳሽ በሌለበት የሚሰጥ ዕግድ የጸና እንደሚሆን በአዋጁ አንቀጽ 12/3/ ስር ተጠቅሷል፡፡ እስከ መቼ ይጸናል የሚለዉ እንደተጠበቀ ሆኖ ምርመራዉ በሌለበት የተካሄደበት እንዲሁም በሌለበት ክስ የቀረበበት ሰዉ በምን ሁኔታዎች እና ምክንያቶች እግዱ ሊነሳለት እንደሚችል ቅድመ ሁኔታዎች በአዋጁ አልተቀመጠም ፡፡
ምንአልባት በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 197 ፤ 198 እና 199 በሌለበት የተሰጠ ፍርድ የሚስተናገድበትን አግብባ በዚህም አዋጁ በተመሳሳይ የሚተገበር ስለመሆኑ አመላካች ነገር አልተቀመጠም ፡፡
በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 10 (1- 4 ) ስር የማይታገዱ ንብረቶች ዉስጥ ለተከሳሹ ወይም ቤተሰቡ የሚሆኑ ለእለት ኑሮ የሚገለግሉ ልብሶች፤ምግብ ማብሰያ ቁሳቁሶች፤ አልጋ እና የአልጋ ልብሶች ፤ከሶስት ወር የማይበልጥ ስንቅ ፤ ለእለት ኑሮ የሚጠቅሙ ቀላል እቃዎች ፡ ከታገደዉ ንብረት ዉጭ ሌላ አማራጭ ገቢ ከሌለ ፍ/ቤት በቂ ነዉ ብሎ ያመነዉን ገቢ አይታገዱም ፡፡
ምን አልባት በተሸሻለዉ የቤተሰብ ህግ አዋጅ ቁ 213/1992 ቤተሰብ የሚለዉ ትርጉምና ደረጃ የሰፊዉ ማህበረሰብ መገኛን የሚያካትት ሰፊ ትረጉም ያለዉ መሆኑ ሲታይ በዚህ ህግ ቤተሰብ ሲል በየትኛዉ በኩል ያለዉን የዝምድና ሀረግ ወይም ግንኙነት ወይም እስከ ስንት ደረጃ ያለዉን ትስስር እንደሆነ በገልጽ ባለመቀመጡ የ3ኛ ወገን ንብረት አላግባብ እንዲታገድ ወይም እንዲለቀቅ ለትርጉም በር ከፋች ሊያደርገዉ ይችላል፡፡
በተግባር ያለዉ አሰራር የቤተሰብ ንብረት ማለት የባል ፤ የሚስት ፤ የልጅ አድረጎ በመዉሰድ ንብረቶች የሚለቀቁበት እንዲሁም የሚታገዱበት ሁኔታ አለ፡፡
ዐቃቤ ህግ ወይም መርማሪዉ ለማሳገድ ምርመራዉን የደረሰበትን ደረጃ፤ ተጠርጣሪዉ አገኘ የተባለዉን ጥቅም ወይም አደረሰ የተባለዉን ጉዳት የሚያሳዩ አሳማኝ ምክንያቶች፤ንብረቶቹ የሚገኙበትን አድራሻ እና ዝርዝሮቹን በቃለ መሃላ በተደገፈ እና ግልጽ በሆነ ሁኔታ ማቅረብ አለበት፡፡
ንብረቱ ከመታገዱ በፊትና በኋላ ሊደረጉ የሚገቡ ጥንቃቄዎች የተጠርጣሪን ወይም ግንኙነት ያለዉን ንብረት ማጥናት፣ ከፍ/ቤት የማሳገጃ ትእዛዝ ማዉጣት ማሳገድ ፤ለንብረቱ ደህንነት ሲባል የንብረት ጠባቂ እንዲሾም ማድረግ፣በአዋጁ አስተዳደራዊ ውርስ የሚያስፈልጋቸዉ ከሆነ ወደ ፍርድ ቤት መሄድ ሳያስፈልግ የተመዘበረ ንብረት በቀጥታ በአስተዳደራዊ አካል ዉሳኔ ተመላሽ ይደረጋል፡፡ በዉሳኔዉ ቅሬታ ያለዉ አካል በይግባኝ ወደ ፍርድ ቤት ሊሄድ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡
ፍ/ቤት ሲል ጉዳዩን ለማየት ሥልጣን ያለዉ አካል መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ በቀላሉ ሊበላሹ ወይም ሊጠፉ የሚችሉ ካሉ የታገደዉን ንብረት ለፍርድ ቤቱ በማመልከት በአግባቡ እንዲሸጥና ሽያጩ እንዲቀመጥ ይደረጋል፡፡ በወንጀል ፍሬ እና ማካካሻ ንብረት መካከል ያለዉ ልዩነት የታገደው ንብረት የወንጀል ፍሬ ከሆነ ተከሳሽ /ተጠርጣሪዉ የመጠቀም መብቱን የሚከለከል ሲሆን የታገደው ንብረት ማካካሻ በሚል የታገደ ከሆነ ግን በመርህ ደረጃ የመጠቀም መብትን ስለማይከለክል ንብረቱ እንደታገደ የታገደበት ሰው እንዲጠቀምበት በአዋጅ ቁ 434/97 በአዋጅ ቁ 882/07 እንደተሸሻለ አንቀጽ 9/2/ ሥር ይደነግጋል፡፡
የማይበላሽ ንብረት ከሆነ መጨረሻ ላይ በፍርድ ቤት ውሳኔ ሲያገኝ ንብረቱን በመሸጥ ወይም በአይነት ለመንግስት ወይም ጉዳት ለደረሰበት አካል በመስጠት የህዝብና የመንግስትን ጥቅም ማስከበር፤ የወንጀል ምንጮችን ማድረቅ፤ አጥፊዎች ተገቢዉን ቅጣት እና እርማት እንዲያገኙ በማድረግ ሌሎች ትምህርት እንዲያገኙ ማስቻል ተቀዳሚ ግቡ እንዲሆን ይሆናል፡፡
3. የሚወረሰዉ እና የሚመለሰዉ ንብረት በአዋጅ ቁ 434/97 በአዋጅ ቁ 882/07 እንተሻሻለዉ በአንቀጽ 34/1/ እና /2/ የሚወረሰዉ እና የሚመለሰዉ ንብረት በወንጀል የተገኘዉን ንብረት ወይም ተመጣጣኙ( fruits, fruits of the fruits and corresponding value) ፤ ተከሳሽ ካገኘዉ ጥቅም ወይም ያገኛል ተብሎ ከሚገመተዉ ያላለፈ መሆን እንዳለበት ይደነግጋል፡፡
4. ሀብትን ለማገድ፤ ክስ ለማቅረብ ፤ለማስመለስ እና ዉሳኔ ለመስጠት ሥልጣን ያለዉ አካል ከሙስና ወንጀል ጋር በተገናኘ ጉዳዩን ለማየት የፀረ ሙስና ልዩ የስነ ሥርዓት እና የማስረጃ ህግ አዋጅ ቁ 434/97፣882/2007 እንደተሻሻለዉ አንቀፅ 7(1) እና (4) የማገድ፤ የዋስትና ጥያቄ የማስተናገድ ፤ በዳኝነት የማየት በተለይ ከአንቀፅ 8 እስከ 34 ባሉት ድንጋጌዎች የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ሥልጣን ያለዉ ሲሆን ፡ ምርመራ እና ክሱን የማቅረብ ሥልጣን ቀድሞ የፌዴራል ሥነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሥልጣኑ የተሰጠ ቢሆንም ፌ/ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁ 943/2008 አንቀጽ 3/3/ ሥር በፌዴራል ሥር ያሉ የወንጀል ጉዳዮችን ለጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የተሰጡ በመሆኑ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ምርመራን ማስጀመር ፤መምራት ፤ ማሳገድ እንዲሁም ክስ ማቅረብ ፤ እና ዉሳኔ የማሰጠት ስልጣን አለዉ፡፡
ፌ/ጠቅላይ ዐቃቤ ወይም የክልል ጠቅላይ ዐቃቤ በወንጀል ስነ ሥረዓት ህግ ቁጥር 111 እና 112 ተከታዮቹ ድንጋጌዎች በሚያዘዉ የክስ አቀራረብ መሰረት0. የተጣሰዉን የሙስና ወንጀል እንዲሁም ሌሎች ተደራራቢ ወንጀሎች ካሉ በክሱ ግልጽ በሆነ መንገድ ጠቅሶ የዉርስ አቤቱታን ከክሱ ጋር አያይዞ ሥልጣኑ ለሚፈቅደዉ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀርባል ይከራከራል፡፡
ፍ/ቤቱ በተከሳሹ ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ እና ዉሳኔ ካስተላለፈ አዋጅ ቁ. 434/97 አንቀፅ 29 ጥፋተኝነትን መሰረት ያደረገ የውርስ (Conviction based confiscation or criminal confiscation) አቤቱታ መሰረት ዐቃቤ ህግ ፍ/ቤቱ ትእዛዝ እንዲሰጥለት በማሳሰብ ንብረቱን ማስመለስ የሚቻል ሲሆን ከክሱ ጋር የዉርስ አቤቱታ ያልቀረበ ከሆነ አዲስ አቤቱታ በማቅረብ በወንጀል የተገኘዉ ሃብት በዉሳኔዉ መሰረት ለተገቢዉ አካል እንዲመለስ ያደርጋል፡፡
ነገር ግን የሙስና ወንጀል የፈፀመዉን ሰውን በተለያየ ምክንያት በወንጀል ተከሶ ጥፋተኛ ማስባል ሳይቻል የቀረ እንደሆነ የጥፋተኝነት ውሳኔ ባይኖርም የወንጀል ፍሬ በሆነው ንብረት ወይም ድርጅት ላይ ክስ አቅርቦ ንብረቱ የሚመለስበት አግባብ አዋጅ ቁ. 434/97 አንቀፅ 35 (3) በጥፋተኝነት ላይ ያልተመሰረተ ውርስ (Non-conviction based confiscation or civil confiscation) አቅርቦ ማስመለስ እንደሚቻል ተደንግጎ ይገኛል ፡፡
አፈጻጸሙ ሲታይ ሙስናን ለመደንገግ የወጡ አዋጆችም ሆኑ በልዩ ስነ ስርዓት እና ማስረጃ ህጎች በግልጽ የሚመራበት ሂደት ስላልተቀመጠ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስቸግር ይሆናል፡፡ እስከማዉቀዉ ድረስ ይህን የዉርስ መንገድ ተከትሎ የተመለሰ ሃብት መኖሩን ማረጋገጫ አላገኘሁም ፡፡ በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በወንጀል የተገኘን ንብረት መመርመር እና ማስመለስ ዳይሬክቶሬት ጄኔራል በጥፋተኝነት ላይ ያልተመሰረተ የውርስ አቤቱታን በመከተል በሰፊዉ እየሄደበት መሆኑን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡
በአብዛኛዉ የሙስና ወንጀል ፈጻሚዎችን በአካል {physically} በመያዝ ለፍርድ ለማቅረብ አስቸጋሪ ስለሚሆን ለምሳሌ ከፍትህ ቢሰወር፤ በሞት ምክንያት ባይገኝ በንብረቱ ወይም በድርጅቱ ክስ አቅርቦ ተገቢዊን ማካከሻ ወይም ዉርስ ለማግኘት ለዚህ አይነቱ አማራጭ የአፈጻጸም ደንብ እና መመሪያ በማዉጣት ስራ ማዋል ይገባል፡፡
ሌላዉ የሃብት ማስመለሻ ዋነኛዉ መንገድ አዋጅ ቁ.882/2007 አንቀፅ 32 እንደተገለጸዉ የፍትሐብሔር ክስ (civil action) በማቅረብ ንብረትን ማስመለስ ነዉ፡፡ ተከሳሹ በነፃ ቢሰናበት፣ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 42(1) (ሀ) ለክስ የሚያበቃ በቂ ማስረጃ ባለመገኘቱ ለጊዜዉ ቢዘጋ ወይም በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 23) (2) መሰረት ወንጀል አለመፈጸሙ ቢረጋገጥና የምርመራ መዝገቡ የአያስከስስም ዉሳኔ ቢሰጠዉ የፍትሀብሄር ክስ አቅረቦ ማስመለስ ይቻላል፡፡
የከሳሽነት ስልጣኑን ያገባኛል የሚል የመንግስት አካል ወይም ጥቅሜ ተጎዳ የሚል አካል ሊያቀርብ እንደሚችል በአዋጁ ተጠቅሷል ፡፡ ዐቃቤ ህግ ወይም የዉርሱን አቤቱታ ያቀረበዉ አካል ከላይ በተጠቀሰዉ ህጋዊ መንገዶች ንብረቱ እንዲወረስ ወይም ለማካካሻ እንዲዉል ማድረግ ካልቻለ የታገደዉ የተከሳሹ ንብረት እግዱ እንዲነሳና ንብረቱ ለባለቤቱ እንዲመለስ ማድረግ አለበት፡፡
5. የሃብት ማስመለስ የህጎች ተፈጻሚነት ወሰን እና ተግዳሮቶቹ ከሙስና ወንጀሎች ጋር በተያያዘ ንብረት ማሳገድ ፤ ማስመለስ እና ማስወረስ ጋር በተያያዘ ሙስና ለመደንገግ የወጡ አዋጆች 214/74፣ በአዋጅ ቁ 881/2007 እንደተሻሻለ) እስካልተቃረኑ የፀረ ሙስና ልዩ የስነ ሥርዓት እና የማስረጃ ህግ ( አዋጅ ቁ 434/97፣882/2007)፣ የሙስና ተቋማትን ለማቋቋም የወጡ አዋጅ ቁ 433/97፣ በአዋጅ ቁ 883/2007 እንደተሻሻለ)፤ የወንጀል ህግ (1996) የወንጀል ሥነ ሥርዓት እና የፍትሀብሄር ህግ እና ሥነ ሥርዓት ህግ፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሀብት ምዝገባ አዋጅ ፤ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ሌሎች አግባብነት ያላቸው ህጎች ተፈፃሚ እንደሚሆኑ ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም ይህንን ድንጋጌ በሙስና ወንጀል ከተመዘበረ ሀብት ማሳገድ ፤ ማስመለስ፡ ማስወረስ እና ማካካስ አንፃር ስናየው ለሀብት ማስመለስ ተብለው ከተደነገጉት የእግድ፣ የንብረት ጠባቂ እና የውርስ ድንጋጌዎች በተጨማሪ ሌሎች ህጎችም ተፈፃሚነት የሚኖራቸው በመሆኑ ህገወጥ የሆነዉን ንብረት በመያዝ ሃብቱን ለህዝብ እና ለመንግስት ጥቅም ለማዋል በተወሰነ መልኩ የህግ ማዕቀፍ መኖሩን ያመላክታል፡፡
ተመዝብረዉ ወደ ዉጭ የሸሹ ንብረቶችን ለማስመለስ ኢትዮጵያ ፈርማ ያጸደቀቻቸዉ አሃጉር ዐቀፍ እና አለም ዓቀፍ ህግጋቶች እንደአግባብነታቸዉ ተፈጻሚ ይሆናሉ ፡፡ በጥቅሉ የሙስና አዋጆች ከሀብት ማስመለስ አንጻር ሲታዩ ከሙስና ዉጭ ባሉ ወንጀሎች የተገኙን ህገ ወጥ ንብረቶች ለማስመለስ የማይችሉ መሆኑ (no centeralized asset recovery law)፤ የሶስተኛ ወገኖች ጥቅም ወይም በቅን ገዢዎች ንብረት ዕግድ ሲወጣ ከዉሳኔ በፊት ንብረቱ ተጣርቶ የሚመለስበትና የሚስተናገድበትን ሥርዓት አለማስቀመጡ፡ አንድ ንብረት ከፍርድ ቤት ዉሳኔ በኋላ ወይም በፊት ታግዶ የሚቆይበት ምክንያታዊ ጊዜ አለማስቀመጡ፤ በአስተዳደር አካላት ንብረትን ለ48 ሰዓት የማገድ ስልጣን መሰጠቱ ስልጣንን አላግባብ ለመጠቀም (abusal} የተጋለጠ መሆኑ፤ ብቃት ያለው የንብረት አስተዳደር በመንግስት ይሁን የግል ተቋም አለመኖሩ፤ ለንብረት ጠባቂው የሚከፈለው ክፍያ በፍርድ ቤቱ ይወሰናል ወይስ በድርድር አለመገለጹ፡ የውርስ አቤቱታ ሲቀርብ ወለድ (interest) አብሮ ሊጠየቅ የሚገባ መሆን/ አለመሆኑን አለመጠቀሱ፡ የውርሱ ዉጤት በፌዴራል ፍ/ቤቶች የፍርድ አፈፃፀም ዳይሬክቶሬት እንዲፈጸም መደረጉ ረጅም ጊዜ የሚወስድ መሆኑ ፤ የጥቅምና የጉዳት አሰላል ሂደቶች ሙያዊ እና ወቅታዊ በሆነ ስሌት ባለመሰራቱ ግልጽ ችግሮች መኖራቸዉ፤ ወዘተ በወንጀል የተገኘን ሃብት ለማስመለስ እና ለማስወረስ ተገዳሮት ሆነዉ ቆይተዋል፡፡
በአጠቃላይ እነዚህ የህግ ክፍተቶች እና የአሰራር ተግዳሮቶች የሃብት ማስመለስ ሥራዉን ለማሳለጥ እንቅፋት ስለሚሆኑ ህጉን በማሻሻል ፤ ደንብ እና የአሰራር ማኑዋሎችን እንዲወጡ በማድረግ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይገባል፡፡
ከአቃቤ ህግ ፌስ ቡክ የተወሰደ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   በቡድን ተደራጅተው የውንብድና ወንጀል የፈጸሙት ተከሳሾች ከ18 እስከ 20 ዓመት በሚደርስ እስራት ተቀጡ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *