“Our true nationality is mankind.”H.G.

በለው! አፍርሰው! ቁጥር 1

( በላይ ባይሳ)
ደስ የሚለኝ ነገር ሁሉንም ነገር አላውቅም፣ ሁሉንም ማወቅ ቢቻልም እንኳ አልፈልግም!። ሁሉንም አግበስብሼ ለማወቅ ጥረት ለማድረግ አልባጅም፤ አልጃጃልም። ምክንያቴ ደግሞ አንድ ነው። እርሱም ስለማይቻል።
በምድር ላይ ካሉ ብዙ ነገሮች መካከል የውሃ ጠብታ ታህል እንኳ አላውቅም። እስከዛሬ ያወኩትን፣ ያየሁትን፣ የሰማሁትን እና ያደረኩትን ነገሮች ሁሉ በጊዜ ሂደት ባልረሳቸው ኖሮ አይምሮዬ ታጭቆና ተጨንቆ ጧ! ብሎ በፈነዳ ነበር።
“እውቀት ፈሳሽ ነው” የሚለውን አባባል ለዚህ ነው መሰለኝ እወደዋለሁ። ማለቴ ሲፈስ መንጠባጠቡ ስለማይቀር ማለቴ ነው።
ከዚህ አንፃር አይምሮዬም እግዜር ይስጠው ከስር ከስር ይረሳልኛል። ይህን የማመንና ያለማመን ጉዳይ ካልሆነ በስተቀረ አብዛኛው ሰው እንደዚሁ ይመስለኛል።
አንድ ሰው አከባቢውን ለመረዳትና ለማወቅ እንዲሁም ኑሮውን የተመቸ ለማድረግ ብዙ ጥረት ያደርጋል። አከባቢውን ለመረዳት በፅኑ ይሞክራል። ሙከራው ከሰዋዊነት የመነጨነውና ይጠበቃል።
ይሁንና ስለ አከባቢው ያወቀው ነገር የተሟላ ሳይሆን ቁንፅል እውቀት እና ትንሽ እውነት ነው የሚሆነው። የሰው ልጅ ስለ አንድ ነገር 100% አያውቅም ለማለት ነው። በመሰረቱ የሰው ልጅ እንኳን አከባቢውን ራሱንም በውል የሚያውቅ አይመስለኝም።
ይሁንና ሰው እንደ ማህበረሰብ ሲኖር በረጅም ጊዜ የህይወት ኑረት የተለመዱና የተቀሰሙ ግላዊ ልምድና ሞያን በማስተሳሰር፣ በማስተባበር እና በመቀመር የማህበረሰቡን ቁሳዊና መንፈሳዊ ማንነት ይፈጥራሉ፣ ይገነባሉ።
ማህበረሰቡ ደግሞ በሂደት የራሱን ቅርፅና ቀለም እየሰጣቸው የግለሰቦችን እውቀትና ልምድ በማቀናጀት የማህበረሰብ ሃብት ያደርጋቸዋል። የአንዱን ለሌላው በማዋስ ጉድለቶችን ይሞላበታል በሂደትም ያበለፅገውና የማህበረሰቡ ሃብት ያደርገዋል። “የእገሌ ነው” የሚባል ነገር የለም። ይልቁንም “የኛ ነው” መባል ይጀምራል።
አንዳንዴ ግን እነዚህን በጊዜ ሂደት የተገነቡ ቁሳዊ እና መንፈሳዊ ሃብቶች በማወቅም ባለማወቅም ለማፍረስ ይሞከራል። ይነቀነቃል።
ለአብነት ያክል ኢሃዴግ እንደገባ ደርግ ያቆመውን ሃውልቶችን በዶዘር ለማፍረስ ሞክሯል። ግን አልተሳካለትም።
በሌላ መልኩ ልጅ ሆነን እንኳን የሆነ ጥንዚዛ ወይም ሃምሳ እግር አልያም ሌላ ህይወት ያለው በራሪ ወይም ተሳቢ ነብሳት ስናይ ስጋታም ስለሆንን ወዲያው መግደል ነው የምንፈልገው። ምክንያቱ ደግሞ በለው! ርገጠው! ግደለው! አፍርሰው ተብለን ነዋ ያደግነው።
ግን ደግሞ በአንፃሩ እየው፣ ተመራመርበት፣ ስንት እግር አለው?፣ አይኑስ?፣ … ብለን ምንነቱን እንድንማርና እንድናውቀው እድል ቢሰጡን ኖሮ ከፍጥረቶቹ አንድ እውነት በተማርን ነበር። ግን አልሆነም።
ከዚህ የተነሳ ስለ አንድ ነገር ቆም ብለን ከማስብ እና ከማጥናት እንዲሁም ከታሪክ እና ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ለመማር ጥረት ማድረግ አንፈልግም። በራችንን ዝግ እናደርጋለን። ጆሮዋችንን አውቀን እንደፍናለን።
ስጋታችን ስለሚጨምር ስሜታም ሆነን በለው፣ አፍርሰው፣ ደምስሰው፣ ግደለው ማለት ለመደብንና ተቸገርን። ይህው እንዲህ ሆነን እስከዛሬ አለን።
ታድያ ይህ እንደ ማህበረሰብ ያስኬዳል?
ኤዲቶር – ጽሁፉ ሙሉ በሙሉ የጸጋፊው አሳብ ሲሆን የሽፋን ፎቶ – በዝግጅት ክፍሉ የተመረጠ ነው

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሻለቃ ሰከን ይበሉ እንጂ! – ባይሳ ዋቅ-ወያ
0Shares
0