“Our true nationality is mankind.”H.G.

በኦክስጅን እጥረት !! ዴልሂ ህይወት ምን ይመስላል?

የዴልሂ ሆስፒታሎች ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር የኦክስጂን እጥረት ያጋጥማቸው የጀመረው። ቀውሱ የመቀነስ ምልክት አላሳየም።

ቅዳሜ ብቻ በአንድ ታዋቂ ሆስፒታል ኦክስጅንን በማለቁ ሐኪምን ጨምሮ ቢያንስ 12 ታካሚዎች ሞተዋል።

ከሆስፒታሎች ውጭ አልጋ ማግኘት የማይችሉ የሕመምተኞች ቤተሰቦች ተንቀሳቃሽ ሲሊንደሮችን ለማግኘት እየታገሉ ነው። አንዳንድ ጊዜ ለ12 ሰዓታት ድረስ ወረፋ ለመጠበቅ ይገደዳሉ። የዴልሂ ትልልቅ ሆስፒታሎች በየቀኑ በሚታደል የኦክስጅን እደላ ነው እየሰሩ የሚገኙት።

አንድ ዶክተር ሁኔታውን አስፈሪ እንደሆነ ገልጸዋል። “ዋናውን ሲሊንደር አንዴ ከተጠቀሙ በኋላ የሚቀየርበት ምንም ነገር የለም” ብለዋል፡፡የማጠራቀሚያ ታንከሮች በሌላቸው እና በትላልቅ ሲሊንደሮች በሚሠሩ አነስተኛ ሆስፒታሎች ሁኔታው የከፋ ነው። እሁድ ዕለት በዴልሂ ብቻ ከ25 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 412 ሰዎች መሞታቸውን ተዘግቧል። ሕንድ በ24 ሰዓት ውስጥ ከ 400ሺህ በላይ አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን በማስመዝገብ የመጀመሪያዋ አገር ሆናለች።

‘የዕለት ተዕለት ውጊያ ነው’

የሽሪ ራም ሲንግ ሆስፒታልን አስተዳዳሪው ዶ/ር ጋውታም ሲንግ 16 የጽኑ ህሙማን እና 50 የኮቪድ ህሙማን አልጋዎች እንዳላቸው ገልጸዋል። የኦክስጅን አቅርቦት ዋስትና ስለሌላቸው ህሙማንን ለመቀበል ግን ፈቃደኛ አይደሉም። ሕይወት ለማትረፍ ኦክስጅን እንዲሰጣቸው በማሰብ ባለፉት ጥቂት ቀናት በርካታ የድረሱልን ጥሪዎችን አድርገዋል።

“በየዕለቱ የምናደርገው ውጊያ ነው። ግማሾቹ የሆስፒታል ሠራተኞች ከቦታ ወደ ቦታ በመሄድ ሲሊንደሮች ለመሙላት በየቀኑ ሲንገላቱ ይውላሉ።” በሆስፒታሉ በኦክስጅን እጥረት የሚሞቱ ህመምተኞች ጉዳይ እንቅልፍ እንደሚነሳቸው ዶ/ር ሲንግ ይገልጻሉ።

Related stories   በህንድ በኮቪድ 19 ምክንያት በሁለት ቀናት ውስጥ ከስምንት ሺህ ሰው በላይ ለህልፈት ተዳረገ

“ታካሚዎቼን ስለማከም እንጂ ኦክስጅን ለማግኘት መንገላታት አልነበረብኝም” ብለዋል። የሌሎች የሆስፒታሎችም እጣ ፈንታ ተመሳሳይ ነው።

ሰዎች የኦክስጅን ስሊንደር ለማስሞላት እስከ 12 ሰዓታት ወረፋ ይጠብቃሉ።

የፎቶው ባለመብት,GETTY IMAGES ምስሉ መግለጫ, ሰዎች የኦክስጅን ስሊንደር ለማስሞላት እስከ 12 ሰዓታት ወረፋ ይጠብቃሉ።

ቤተሰቧ ዴልሂ ውስጥ ሆስፒታል ያላቸው አንዲት ግለሰብም ቀውሱ ሲጀመር በባለስልጣናት መካከል ቅንጅት እንደሌለ ትናገራለች።

“በእነዚያ ጥቂት ቀናት ውስጥ የሚመለከተው አካል ማን እንደሆነ እና ጉዳዩን የሚፈታው ማን እንደሆነ አናውቅም ነበር” ትላለች።

ሁኔታው “አሁን በመጠኑ ተሻሽሏል” ትላለች። ይሁን እንጂ የኦክስጅን አቅርቦቱ ላይ እርግጠኛ መሆን ስለማይቻል ሆስፒታሎች ብዙ ታካሚዎችን የመቀበል አቅማቸው ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል።

“የኦክስጅን አልጋ አለሽ ወይ ብለው ሲጠይቁኝ የለኝም በማለት ስመለስ በጣም ይሰማኛል” ትላለች።

ኦክስጅን የሚያከፋፍለው የፌደራል መንግስት ነው። የደልሂ ዋና ሚኒስትር አርቪንድ ኬጅሪዋል ከተማዋ በቂ ኦክስጅንን እያገኘች አይደለም ሲሉ በተደጋጋሚ ተናግረዋል።

የፌዴራል ባለሥልጣናት ደግሞ የኦክስጅን እጥረት የለም የቸገረን የትራንስፖርቱ ጉዳይ ነው ይላሉ።

‘ሰዎች ዋጋ እየከፈሉ ነው’

በመሬት ላይ ያለው ሁኔታ ግን አሁንም አስከፊ ነው።

“በግዛቶች እና በፌዴራል መንግሥት መካከል በተፈጠረው የፖለቲካ ውዝግብ ሰዎች ዋጋ እየከፈሉ ነው። አንዳንድ ጊዜ ህይወታቸውን ነው የሚከፍሉት” ብለዋል አንድ ተንታኝ።

በኦክስጅን እጥረት ምክንያት አልጋ ያገኙ ቤተሰቦችም በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ናቸው።

ያለፉት 48 ሰዓታቶች ለአልታፍ ሻምሲ አሰቃቂ የሚባሉ ናቸው።

እሱ እና መላው ቤተሰቡ ባለፈው ሳምንት ተመርምረው ኮቪድ -19 አለባችሁ ተባሉ። ነፍሰ ጡር ሚስቱ በጠና ታማ ሆስፒታል ተወሰደች። አርብ ዕለት ሴት ልጅ ተገላገለች። በተወሳሰበ ወሊድ ምክንያት ከጥቂት ሰዓታት በኋላ በመታመሟ ቬንትሌተር የተገጠመላት ሲሆን አሁን በአስጊ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች።

Related stories   ሁለት የተለያዩ የኮቪድ-19 ክትባቶችን ብንወስድ ምን እንሆናለን?

አልታፍ አባቱ በሌላ ሆስፒታል ህይወታቸው እንዳለፈ ተነገረው። በጽኑ ህሙማን ማቆያ ውስጥ የሚገኙት ሚስቱ እና ሕጻኗ የሚገኙበት ሆስፒታል ኦክስጅን እያለቀ ነው ሲል አሳውቋቸዋል።

ሆስፒታሉ ለአንድ ቀን የሚሆን ኦክስጅን ቢያገኝም አልታፍ ግን ዘላቂ መፍትሔ ባለመሆኑ እንደተጨነቀ ነው።

“ነገ ምን እንደሚፈጠር ማን ያውቃል?” ይላል።

ከኦክስጅን እጥረቱ በተጨማሪ ሆስፒታሉ በቂ የሰው ኃይል የለኝም በሚል ባለቤቱን ወደ ሌላ ተቋም እንዲያዛውር እየጠየቀው ነው።

በዚህም ራሱ የባለቤቱን የኦክስጅን መጠን እና ትኩሳት ለመከታተል ተገደደ።

“እያሳለፍኩ ያለሁትን ስቃይ መገመት እንኳን አትችሉም” ይላል።

ሕንድ

የፎቶው ባለመብት,GETTY IMAGES

‘የአባቴ ኦክስጅን እያለቀ ነው’

በዴልሂ በከባድ ሁኔታ ውስጥ ላሉት ታካሚዎች የሆስፒታል አልጋ ካላገኙ በቤታቸው ተንቀሳቃሽ የኦክስጂን ሲሊንደሮች መጠቀማው ብቸኛው መንገድ ነው።

የአቢሼክ ሻርማ አባት የኦክስጅን መጠን ከቅዳሜ ጀምሮ እየወረደ ነው። ሲሊንደር ለመግዛት ወደ ገበያ በፍጥነት አቀና።

ከደርዘን በላይ ሱቆችን ጎብኝቶ ለስድስት ሰዓታት ብቻ የሚቆይ ሲሊንደር አገኘ። በኋላ አንድ ትልቅ ሲሊንደር በ944 ዶላር ቢገዛም ባዶ ነበር። ሲሊንደሩን ለማስሞላት ወደ ብዙ መሙያ ጣቢያዎች ወስዶ አንዱ ብቻ ሊረዳው ፈቃደኛ የነበረ ቢሆንም ወረፋው በጣም ረጅም ነበር።

Related stories   ሁለት የተለያዩ የኮቪድ-19 ክትባቶችን ብንወስድ ምን እንሆናለን?

“በወረፋው በቆምኩበት እያንዳንዱ ደቂቃው አባቴ ኦክስጂን እያለቀ ነበር። ሁሉም ሰው በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ስለነበረ እንዲያስቀድሙኝ ማንንም መጠየቅ አልቻልኩም ነበር። ሲሊንደሩን ከስድስት ሰዓታት በኋላ አስሞላሁ። ነገም ደግሞ ደጋሚ መሰለፍ አለብኝ” ይላል።

የህዝብ ፖሊሲ እና የጤና ስርዓት ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ቻንድራካንት ላሃሪያ መንግስት “ሊመጣ ስለሚችለው ቀውስ” ሕዝቡን ቢያስጠነቅቅም ምንም እርምጃ አልተወሰደም ይላሉ።

የአገሪቱ ፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ በህዳር ወር ስለ ኦክስጅን አቅርቦት እና “በቂ ስላልሆነው የመንግሥት ሆስፒታል አልጋዎች ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር።

እንደ ዶ/ር ላሃሪያ ከሆነ በሕንድ የተከሰተው የህክምና ኦክስጅን ቀውስ፤ የስርጭት እና የትራንስፖርት ኔትወርክን የማስተካከል ዕቅድ ባለመኖሩ ነው።

‘የጦርነት ክፍል አዘጋጅተናል’

በችግር ወቅት ዜጎች በችግር ውስጥ ያሉትን ለመርዳት ቅድሚያ ይሰጣሉ።

ድጋፍ ከሰጡት ታዋቂ ሰዎች መካከል ማህበራዊ ጉዳይ ተሟጋች እና ፖለቲከኛው ተህሴን ፖናዋላ፣ ፖለቲከኛው ዲሊፕ ፓንዴይ፣ አክቲቪስት እና ፖለቲከኛ ስሪኒቫስ ቢ ቪ እና ተዋናይ ሶኑ ሶድ ይገኙበታል።

ፖናዋላ መለስተኛ ሆስፒታሎች ኦክስጂን ሲያልቅባቸው ሲያግዙ ቆይተዋል። “የቸገራቸውን ለመርዳት ከሚችሉ ጋር እያገናኘሁ ነው” ብለዋል።

“አንድ ትንሽ ቡድን ከእኔ ጋር አብሮ የሚሰራበትን የውጊያ ክፍል አቋቁመናል። የማውቃቸውን ሰዎች ጋር ብቻ እየደወልኩ ነው። አንዳንዶቹ በሌሎች ግዛቶች ቢኖሩም ለመርዳት ዝግጁ ናቸው” ይላሉ።

“በእያንዳንዱ ቀን ሁኔታው ይበልጥ አስከፊ እየሆነ ነው። እንደ እኔ ያሉ ሰዎች እያንዳንዱን ሰው ወይም የተቸገረን ሆስፒታል ለማገዝ የሚረዳ ሃብት ስለሌላቸው መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ኃላፊነቱን መውሰድ አለበት” ብለዋል።

BBC AMHARIC 

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0