“Our true nationality is mankind.”H.G.

የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

ኧረ እቴ የምዕራባውያን እንዲህ እላይ እታች የሚሉት ምን ሆነው ነው!? ይቺስ ነገር አላት። እንዲህ የሚቅበዘበዙት ለማን ተቆርቁረው ይሆን አላስተኛ አላስቆም ያላቸው!? የቀረባቸው ነገርማ ግን አለ!
ይሄ ሁሉ መቅበዝበዝ ለዲሞክራሲያቸው ነው!? ለነገሩ ነው እንጂ የትኛው ዲሞክራሲያቸው!? የማይሰራው we are 99 ነው!? ንጉሣዊው ዲሞክራሲ(monarchial democracy)!? ብዙ ያደጉት ምዕራባዊ ሀገሮች ንጉሳዊ ሥርዓቱን ዛሬም ይከውኑት እንደሆነ እያየን ሳለ ስለ እኩልነት እንዴትስ ሊያወሩ ቻሉ!? ንጉሣዊ ሥርዓት ጥሩ ነው ለማለት ሳይሆን አፍሪካ ሲሆን ንጉሣዊ ሥርዓት እንደ ኃላቀርነት፣ እንደ አሳፈሪ ጉዳይ፣ እነሱጋር ሲሆን እንደጸጋ ተደርጎ ለምን ይታያል/ይቀርባል!
ሰዎች በቀለም ዛሬ ድረስ ተለይተው አንዳንድ ቦታ ደግሞ እንዳይገቡ የማይፈቅድላቸው የአፓርታይድ መሰል ሥርዓት የሚታይበት ሰፈሮች – የነጮች ሰፈር፣ የአይሪሾች ሰፈር፣ የላቲኖች ሰፈር፣ የጥቁሮች ሰፈርና ከተማ፣ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲዎች ሳይቀሩ በቀለም የሚለዩባቸው ሀገራት ለምሳሌ በአሜሪካ እንደሚታይ እንዳለ በጹሑፎች ያሉና እዛው የሚኖሩ፣ ደርሰው የመጡ የሚያውቁት እውነት አይደለም ወይ!? ይሄ እየታወቀ ግን ለነሱ ሲሆን የዴሞክራሲ መስፈሪያው ምን ይሆን!? ለኛ ከሚነግሩን ለምንድን ነው የተለየባቸው!?
Majority rule!? መሆኑ ነው በቁጥር አናሳ የሆኑ ዜጎችን ረግጦ የያዘ ዴሞክራሲ የገነቡት!? የራሳቸውን ወሳኝ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ትተው ምነው ስለኛ ሲሆን ተሰማቸው!? ስለእኛ የተጨነቁበት ጉዳዩ ግን ሌላ ይመስላል። የእነሱ የትኛው ጥቅማቸው ተነክቶ ነው ግን እንዲህ ያንዘረዘራቸው!? ምነው የሚሆኑትን መላ ቅጡ ጠፋባቸው!? ከድህነት ለመውጣት የምናደርገውን ጥረት ለምንስ እንዲህ አንጨረጨራቸው!? ፍትሀዊነት ለእነሱ እኛ እየተራብን መኖራችንና የነሱን ቁራሽ እንድንለምን ወይም እየጠበቅን እንድንኖር ነው!? ድብቅ ዓላማቸውስ ግን ምን ይሆን!?
ስለታላቁ የአትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ አሁን እንዲህ የሚሆኑት ለግብጽ ብለው ነው ወይስ ለሱዳን ተቆርቋሪ መሆናቸው ይሆን!? ግድቡ ግብጽንም ይሁን ሱዳንን አይጎዳም! በቃ!።
ስለህዳሴ ጉዳይስ ቢሆን ታዲያ በኛ በራሳችን ጉዳይ ምነው እንደዚህ አላዘኑብን!? ምነው አዛኝ መሰሉ!?የሚያዝኑትስ ለማን ነው!? በውስጣችን ጉዳይ ምነው ያገባናል አሉ!? እኛ በእነሱ የውስጥ ጉዳይ ያገባናል ማለት እንችል ይሆን!? ምንድን ነው እንደዚህ ያበገናቸው!?
በእንግሊዛዊያን ወይም ጀርመናዊያን ጉዳይ ሀገሮቹ ጣልቃ እንዲገባባቸው ይፈቅዳሉ!? ሌላውስ በካሊፎርኒያና በአጎራባች አንድ የሆነ ክልል የተፈጠረን ጉዳይ ካናዳ ወይም ሜክሲኮ ወይ ሌላ ሀገር ጣልቃ ልግባ ማለት ይችሉ ይሆን!? ወይ ሩሲያ ወይ ቻይና ወይ ፈረንሣይ ወይ ጀርመን ይሄን በአሜሪካ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ቢፈልጉ ይቻላቸው ይሆን!?
የጸጥታው ምክር ቤትስ ቢሆን በአሜሪካ ጉዳይ ምን አይነት ስብሰባ ይጠራ ይሆን!? (እንበልና በአሜሪካ በሁለት ግዛቶች መካከል የተፈጠረ ችግር ቢኖር…) “የማይመስል ነገር ለሚስትህ አትንገር አሉ” እቴ!
ቀደም በሀገራችን ስንት ደባ ሲሰራ አይተው እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ ሲሆኑ ከርመው ዛሬ ላይ ምነው ተቃጠሉሳ!?
ባለፉት ጥቂት ወራቶች ውስጥ እንኳን በትግራይ ክልል በሀገር ሰራዊት ላይ ወንጀል ሲፈጸም ዝም ብለው ሲያበቁ ሰብዓዊ መብት ተጣሰ ብለው ለፈፉ፣ የህዝባችን መከራና ስቃይ ለኛ የሚያመን ሆኖ ሳለ ለትግራይ ህዝብ ስቃይ ምክንያት የሆነውን የህወሓት የወንበዴና የትምክት ቡድን ለመወቀስ እንኳን መች ዳዳቸው!?
ለትግራይ ህዝባችን መንግስት የእህልና ሸቀጣሸቀጥ አድርሶ ለህዝቡ ሲደርስ ምነው የዚያን ግዜ አፋቸው ተለጎመሳ!?
ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ስትወር ዝምታን ለምን መረጡ!? ሲመረጡ፣ ግብጽ የህዳሴ ግድቡን እንድትመታ ብለው በኛ ላይ እልቂት ሲያውጁ ዝም ብለው፣ እንኳን ለህዝቡ ዕርዳታ ሊሰጠው ይገባል፤ ህዝቡ ተራበ ሲሉ ከርመው ትንሽ ቁና የማትሞላ ድጋፍ አደረግን ብለው ነው የአዛኝ ቅቤ አንጓች የሆኑት!?
የድሮውን ባርነት በእጅ አዙር ጥለውብን ሲያበቁ እኛ ከድህነት አዘቅጥ ውስጥ ለመውጣት የምናደረገው ጥረት ምነው አበገናቸው!? ቆይ ከአጅ አዙር ግዞታቸው ለመላቀቅ የምናደረገው ብርቱ ጥረት ይሆን እንዲህ ያንገበገባቸው!? በእርግጥ ወሰን የሌለው ፍላጎታቸው ተነካባቸዋ!
በሀሰት ዜናቸው ለምንስ ያደነቁሩናል!? እነሱ ከሳሽ፣ እነሱ ምስክር እነሱ ፈራጅ!? ምን አለባቸውና ነው በእርግጥ!?
“ፌክ” እየሰሩን “ፌክ ኒውስ” ይሉናል። መቼስ የኛ ነገር በጎ በጎው አያታያቸው!? የእነሱ ተላላኪ ካልሆን በስተቀር መች ጎሽ ይሉናል!?
ለጠላት መቼም ደስ አይበለው!
የሀገራችን ህልም በልጆቿ ጥረት እውን ይሆናል! ደጃችንን ለከፋፋዮችና ለጠላት መዝጋት አለብን። እናውቃለን ትንሿን ልዩነቶቻችንን በጥናት፣ በስኮላርሽፕ፣ የነሱ ተመጽዋች አድርገው በማይገል በማይሽር እርዳታቸው ሰበብ እየመጡ እኛኑ እንድንኮንን፣ የበላይነታቸውን እንድንቀበል እያስደገደጉን በግዞት ሊያኖሩን ይተጋሉ።
ክብራችን ግን ሀገራችን እንጂ የእነሱ ሀብት አይደለም። ጫና የሚያሳድሩብን ተቋሞቻቸውም በኛ ድህነት የሚሳለቁ፣ የኛን መናኛነት የሚናገሩና በእኛ ሞት የሚነግዱ ሆነው መገኘታቸውን አሁን ላይ በውል ተገንዝበናል።
ለጠላት መቸም ደስ አይበለውና የሀገራችን ትንሣዔ በልጆቿ ይረጋገጣል! የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት እንዳለ ግን ልብ ያለው ልብ ይበል!?
ሠላም ትሁን ኢትዮጵያችን!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቅ!
(ከሠላም ለሀገሬ የፌስቡክ ገጽ የተወሰደ)

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የተላላኪው ጠበቃዎች
0Shares
0