Imageሰሞኑን ፕሬዚዳንት ኢሳያስን አስመልክቶ  የሚናፈሰው ወሬ ከታማኝ የዜና ምንጮች ማስተባበያ ባይሰጥበትም በህይወት የመቆየታቸውና የመኖራቸውን  ጉዳይ የመጨረሻው ቁርጥ  መቃረቡን  የሚያመላክቱ  መረጃዎች ወጥተዋል።የኢሬና  ታማኝ ምንጮች እንደሚሉት ደግሞ ኤርትራ እንዴት ትቀጥል በሚለው ጉዳይ ጀነራሎች ስብሰባ ተቀምጠው ውሳኔ ማስተላለፋቸውን ተናግረዋል።ራዲዮ ኢሬና / ERENA / በመባል የሚታወቀው የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚ  ሚዲያ  በዛሬው እለት በየሰዓቱ በሚያስተላልፈው ዜና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ኮማ ውስጥ እንዳሉ እየገለፀ ይገኛል። 

ኢሬና በተደጋጋሚ እንደዘገበው  የኤርትራ ጀነራሎች በትናንትናው እለት አስቸኳይ ስብሰባ ተቀምጠው ታሪካዊ የተባለ ውሳኔና ሹመት  አካሂደዋል። በዚሁ  ስብሰባ ፕሬዚዳንቱ በጊዚያዊነት አገር እንዲያስተዳድሩ የሰየሙዋቸው ጀነራል ተክሌ ማንጁስ ውክልናቸውን ተነስቷል። በዚሁ ውሳኔ መሰረት  ጀነራል ስብሃት ኤፍሬም ጦሩን እንዲመሩ፣ የማነ ቻርሊ የፕሬዚዳንቱን ጽ/ቤት እንዲያስተዳድሩ፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ የማነ ገብረ አብ የፖለቲካ ጉዳዮችን በበላይነት እንዲቆጣጠሩ ሃላፊነት ሰጥቷል።

ጀነራሎቹ ቀጣዩን የኤርትራ ጉዳይ “ አገራዊ መግባባት “ በሚሰፍንበት መልኩ ለማስተቀጠል ይቻል ዘንድ በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፉወርቂ ላይ ኩዴታ ለማካሄድ ሲያሴሩ ተደርሶባቸዋል በሚል በእስር ላይ ያሉት ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲፈቱ ወስኗል። የሞቱም ካሉ ለቤተሰቦቻቸው እንዲነገር ከስምምነት ላይ ተደረሷል ሲል ኢሬና አስታውቋል።

በኢትዮጵያ የስደት መንግስት ያቋቋሙትን የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚዎች ስብስብ “ የኤርትራን ነፃ አገርነት አሳልፈው የሸጡ ከዳተኞች “ በማለት የሚጠራው ይህ ራዲዮ በቅርቡ በአየር ሃይል ውስጥ ከፍተኛ ሃላፊነት ስለተሰጣቸው        የፕሬዚዳንት  ኢሳያስ ልጅ  ያለው በግልፅ የሰጠው አስተያየት የለም።

ጀነራሎቹ ያሳለፉትን ውሳኔ  ከኩዴታ ጋር ያያዘው ኢሬና ራዲዮ የፕሬዚዳንት ኢሳያስን ጤንነት አስመልክቶ ከኳታር ወደ ዱባይ መዛወራቸውን ምንጮቹን በመጥቀስ አስታውቋል። በዘገባው በተደጋጋሚ ፕሬዚዳንቱ ራሳቸውን እንደማያውቁ አመልክቷል።በማያያዝም ወደ ዱባይ የተዛወሩት ለጉበት ለውጥ መሆኑንም ተናግሯል።

ክትትል እያደረገ በየሰዓቱ መረጃ የሚያቀብለው ሬዲዮ የኢትዮጵያ መንግስት በኤርትራ ጉዳይ ጣልቃ መግባት እንደሌለበት እየወተወተ ነው። ከኢትዮጵያ በኩል ምንም ዓይነት መረጃ እስካሁን ድረስ ባይሰጥም በኢትዮጵያ መንግስት ሙሉ በሙሉ የሚደገፈው  የተቃዋሚዎች ህብረት በትናንትናው እለት ባወጣው መግለጫ በኤርትራ አስተማማኝ ሰላምና ዴሞክራሲ የሚሰፍንበት ቀን መቃረቡን የገለፀው ህዝቡን በመማፀን ነው።

Related stories   The Root Causes of Ethiopian Political Crisis:—Beyond Ethiopian Nationalism and Ethnicity

ቀደም ሲል ለነፃነት የተደረገውን መስዋዕትነትና የትግሉን ሰማዕታት ገድል በማስታወስ የኤርትራ ህዝብ የነፃነት ፍራውን የሚያጣጥምበት ወቅት እንደሚያጣጥም አመልክቷል። ይፋ ካልወጡ መረጃዎች ለመረዳት እንደተቻለው ኢህአዴግ የኤርትራን ቀጣይ እጣ ፈንታ በተመለከተ የቀይ ባህር ጉዳይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየመከረ እንደሆነ ተሰምቷል። የኢህአዴግ ርምጃ እንግዳ ባይሆንም በስውር የሚደረገው ግንኙነት የኤርትራን ጀነራሎች የያዘ ስለመሆኑ የታወቀ ነገር የለም።

የፕሬዚዳንቱ ጉዳይ እልባት ባላገኘበት በአሁኑ ሰዓት በኤርትራ ውስጥ ሊፈጠር የሚችለው የፖለቲካ ለውጥ፣ ከክልሉ  ልዩ ጸባይና  በሌሎች ተመሳሳይ የፖለቲካ ትግል አኳያ  ሁሉንም ወገኖች ያጓጓ መሆኑ አብዛኞች የሚስማሙበት ቢሆንም  ኢሳያስን አስመልክቶ ከገለልተኛ ወገን የተሰጠ ነገር የለም።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *