ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል!!

 አርባ ሁለት ኪሎ  ነበረች።መሰረት ደፋርንና ጥሩነሽ ዲባባን አራውጣ ካሸነፈች በሁዋላ አዲስ አበባ ቤተሰቦቿ ዘንድ ለእረፍት በመጣችበት ወቅት ቃለ ምልልስ ለማድረግ እድሉን አግኝቼ ነበር።ንፋስ የሚወስዳት የምትመስለው አትሌት ካገር ለመሰደድ እንዴት እንደወሰነች ለማስረዳት የሰጠችው መልስ አስገረመኝ።

“አገሬ ያሉ ሲያቀሉኝ የቱርክ መንግስት አከበረኝ።ቱርኮች ስላከበሩኝ እኔም አከበርኳቸው።አሁን እኔ የማስበው ስለቱርክ ነው።ምክንያቱም ቱርኮች ባያከብሩኝ ኖሮ ባገሬ የተነፈኩትን ይህንን እድልና እውቅና አላገኝም ነበር።ኢትዮጵያ አገሬ ናት እወዳታለሁ።ግን አሁን አገሬ ቱርክ ነች።እኔም የቱርክ ዜጋ ነኝ”በማለት የሚያስደምም፣የሚያሳዝን፣የሚያስደነግጥ ብሎም የሚያስፈራ መልስ የሰጠችኝ ሄዋን አብይ ለገሰ ወይም ኤልቫን አብይ ለገሰ በትውልድ ኢትዮጵያዊ፣በዜግነት ቱርካዊ የሆነችው የ5000 እና የ10,000 ሜትር የኦሎምፒክና የዓለም ሻምፒዮና ባለሜዳል ናት።

“ነገሮች ሲስተካከሉ አንድ ቀን ላገሬና ለባንዲራዬ እሮጣለሁ።አታስፈልጊም ስላሉኝ ለባህሪን ለመሮጥ ተገደድኩ።የተሰደድኩት አገሬን ጠልቼ ሳይሆን እድሉን በማጣቴ ነው…”በማለት የተናገረችው የ1500ና የ3000 ሜትር ታዋቂ አትሌት መሪም የሱፍ  ናት።ኢትዮጵያ በርቀቱ አትሌት ማግኘት ተስኗት አንድ ብትገኝ “አታስፈልጊም” ተብላ ለመሰደድ የተገደደች አትሌት !!

“የኢትዮጵያ ህዝብ አድምጠኝ።ብራስልስ ለቅሶ ተቀምጫለሁ።ያገሬ ህዝቦች ሳልፈልግ አገሬን ትቼ እንድሄድ እየተደረኩ ነው።ለቅሶ ላይ ነኝ…”በማለት የድረሱልኝ ጥሪ ያቀረበችው አትሌት ብርሃኔ አደሬ ነበረች።አቴንስ ኦሊምፒክ ላይ በተሰራባት ደባና እሷን አስቀምጠው ብቃት የሌላት አትሌት በማወዳደር ሽንፈት መድረሱን ተከትሎ ለምን አስተያየት ሰጠሽ ተብላ በብራስል ትጥቋን ለብሳ ለመወዳደር ትራክ ላይ ስትቆም መታገዷ ሲነገራት ነበር ቅሬታዋንና ሃዘኗን ለአገሯ ህዝቦች ያቀረበችው።

እየተደበቁ ተጨማሪ ልምምድ የሚሰጣቸው አትሌቶች/ስም ጠቅሳለች/ነበሩ።ህዝብ እንደየው በውድድሩ ላይ ሁለቱ ተደብቀው እኔ ብቻ ውድድሩን እንድመራ መመሪያ ተሰጥቶኝ ተቃጠልኩ።ብንረዳዳ ኖሮ የቻይናዋ አትሌት እየተራመደች አታሸንፈንም ነበር።እንዲህ ያለው ደባ እኔን ሳይሆን አገርን አዋረደ….”ስትል በወቅቱ ተናግራለች።

“ሚኒማ አለኝ።በሚኒማ የሚበልጠኝ የለም።ሳላውቀው ከብሄራዊ የማራቶን ውድድር ተቀንሻለሁ።ለተሰራብኝ ግፍ ህዝብና መንግስት ይፍረዱኝ”በማለት አትሌት ሃይሌ ገ/ስላሴ፣አሰፋ መዝገቡ፣ጌጤ ዋሚ፣ስለሺ ስህንና ሌሎች ታዋቂ አትሌቶች በተገኙበት በመኖሪያዋ ቤቷ ላገር ውስጥና ለውጭ አገር ጋዜጠኞች መግለጫ የሰጠችው የገዛሃኝ አበራ ባለቤት እልፍነሽ አለሙ ነበረች።

ለመነሻ ይህን ያህል ካልኩ ማንም ስለማያውቀውና በድብቅ ተገንዞ ስለተቀበረው የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር እንዴትና ማን እንዳፈረሰው ጥያቄ ላቅርብ።ማህበሩ የተቋቋመው አትሌቶች ላይ የሚደርሰው በደል እያየለ በመሄዱ ነበር።ፍትሃዊ ምርጫና ብይን በመጓደሉ ታዋቂ አትሌቶች ተሰባሰቡ።በዱቤ ጅሎና ደራርቱ ቱሉ የሚመራው ተለጣፊ ማህበር አትሌቶችን ወክሎ በፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ ድምጽ ቢኖረውም ደራርቱና ዱቤ የአትሌቶች መብት ተሟጋች ሊሆኑ ባለመቻላቸው እንደነበር በምስረታው ላይ ተሳታፊ ስለነበርኩ ግንዛቤው አለኝ።

ሃይሌ የዓለም አትሌቶች ተወካይ በመሆን በዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ባለድምጽ አባልና የገዘፈ ክብርም ስላለው “ብሶት የወለደው”የአትሌቶች ማህበር ሊቀመንበር ሆነ።ጌጤ ዋሚና አሰፋ መዝገቡ ምክትል ሊቀመንበርና ጸሃፊ ተደረጉ።እነ ስለሺ ስህን ተካተው ሰባት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተሰየመ።ለጊዜው በሚል ሃይሌ ዓለም ህንጻ ሲኒማ አዳራሹ ጎን ቢሮ ፈቀደ።ኮምፒውተርና የቢሮ እቃ ተደራጅቶ ስራ ተጀመረ።

ማህበሩ ስራ ሲጀምር የመጀመሪያው ስራው ፌዴሬሽኑ ያቋቋመው የአትሌቶች ማህበርና አመራሮቹ በትክክል የኢትዮጵያን አትሌቶች እንደማይወክሉ ለዓለም አቀፉና ለአህጉሩ የአትሌቶች ማህበራት በማሳወቅ የፌዴሬሽኑን ተለጣፊ ማህበር ማስወገድ ነበር።አነሳሱ አስፈሪ የነበረውና ፌዴሬሽኑ ውስጥ አብዮት ያቀጣጥላል በሚል ከፍተኛ ድጋፍ አግኝቶ የነበረው ማህበር ስለ አነሳሱ በተወራ ማግስት መሽመድመዱ መወራት ጀመረ።

የፖለቲካ ተጽዕኖ የማይፈቅደው ፊፋ ኢትዮጵያን  ያገደበት ወቅት ስለነበር አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ላይም ተመሳሳይ ርምጃ ይወሰዳል የሚል ፍርሃቻ ያደረባቸው ክፍሎች የማክሸፋ ሚሳይል ለመተኮስ ሩጫ ጀመሩ።ስማቸውን የማልጠቅሳቸው የወቅቱ ታዳጊ አትሌቶች የግራውን ክንፍ ተከትለው “ዱቤ ወይም ሞት”እንዲሉ ተደረገ።በፖለቲካ ሹመታቸው ፌዴሬሽኑን እንዲመሩ የተመደቡት ባለስልጣናት ትዕዛዝ በማስተላለፍ ተጠመዱ።ባልተጠበቀ ሁኔታ “ታላቁ ሩጫ ታገደ”የሚለው ዜና ሰበር ዜና ሆነ።ለወትሮው ለመረጃ ዝግ የነበረው ፌዴሬሽን ስለታላቁ ሩጫ መግለጫ ለመስጠት በሩን ከመክፈት አልፎ ግድግዳውን ጭምር አሰፋው። ሳምንት እንገፋበታለን እስከዛው ሰላም።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *