አኬልዳማ ቁጥር 2:

ይህ ፅሁፍ የተገኘው ከ www.solidaritymovemenet.org  ድረ ገጽ ነው።

     በጋምቤላ የፉኝዶ ወረዳ የአንድ አባ ወራ አህያ ወደ ጎረቤቱ ዘልቆ አንዲት የሌላ አባወራ ንብረት የሆነች ሴት አህያ ላይ ይንጠላጠልና የልቡን ያደርሳል። የሴቷ አህያ ባለቤትም አህያዬ “ተደፈረችብኝ” በሚል ክስ ይመሰርታሉ። የወንዱ አህያ /ደፋሪው መሆኑ ነው/ ባለቤት ፖሊስ ዘንድ ይወሰዳሉ ክስ ይመሰረትባቸውና ይቀጣሉ።

የወረዳው የፍትህ አካላት ጠርተውን የክሱንና የፍርዱን ሂደት አስረዱን። እኛም በተነገረን መሰረት ዜና ሰራን። ኃላፊው መግለጫ ሲሰጡ እንዲህ ነበር ያሉት። የከሳሽንና የተከሳሽን ስም እየጠሩ “የተከሳሽ አህያ በሰላም ሳር እየጋጠች ያለችውን የተከሳሽ አህያ አጥር ጥሶ መድፈሩ በምስክር ተረጋግጧል። በመሆኑም ተከሳሽ የ 420 ብር ከ25 ሳንቲም መቀጫ ተበይኖበታል። ድርጊቱ የመብት ጥሰት በመሆኑ ለሌሎች ትምህርት እንዲሆን ሲባል ሰፊ የዜና ሽፋን እንድትሰጡት እንጠይቃለን . . . ”

“የመብት ጥሰት” ዜናውን ተቀብለን ስንመለስ ከስራ ባልደረባዬ ጋር ሳቅን፣ አዘንን፣ አደነቅን። የሳቅነው በጋምቤላ የሰው መብት የሚረግጡ ለአህያ መብት በመጨነቃቸው ነበር። ያዘነው በየመንገዱ የሚገደሉና የእገሌ ጎሳ ነው የገደለው እየተባለ አብሮ ለዘመናት የኖረ ህዝብ ገዳዩ ሳይታወቅ ሲረግፍ ዝም ተብሎ የአህያ የሜዳ ላይ ወሲብ የዜና ሽፋን እንዲሰጠው  በመታሰቡ ሲሆን ያደነቅነውና የተደነቅነው በገጠመኙ ነበር።

የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ አህያዋ መደፈር አለባት የሚል መከራከሪያ ለማቅረብ አትወድም። መደፈርም የለባትም። ለማስታወስ የምትወደው ትልቁ ነገር ግን ሰሞኑን አቶ በረከት ስምዖን የሂውማን ራይት ዎችን ሪፖርት ለመከላከል በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ህወሃት ያሰፈነው የፍትህ ስርዓት ምን ያህል ለመብት ተከራካሪ እንደሆነ ለማስረዳት የአህያዋን የፍርድ ሂደትና ብይን  ምሳሌ ስለመርሳታቸው ነው።

አቶ በረከት መንግስታቸው ለመብት መከበር ያለውን ቁርጠኛነት ለማሳየትና ሂይውማን ራይትስ ዎች ያወጣውን ሪፖርት ለመከላከል እንዲህ ያለውን ማሳያ መዘንጋታቸው ቢያስገመግማቸውም፣ ጊዜው ገና ስለሆነ እንደ “አኬልዳማ” አይነት ዘጋቢ ፊልም አዘጋጅተው “ለአቅመ አዳም ያልደረሱ አህዮች ሊመለከቱት የማይገባ” የሚል ማስጠንቀቂያ አስከትለው በትኩሱ እንዲያቀርቡት ምክር ቢጤ እሰነዝራለሁ። ስለ አህያዋና ስለ አህያዋ ዜና ጉዳይ ቀሪውን ቤትስራ አቶ በረከት ኮሚቴ አቋቁመው እንዲሰሩት ለሳቸው ልተወውና ወደ ሌላው ጉዳዬ ላምራ።

የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ጋምቤላ ለስራ በነበርኩበት ወቅት በርካታ አሳዛኝ ጉዳዮችን ለመታዘብ ችያለሁ። ማንም እንደሚረዳው ከጽዳት ሰራተኛ አንስቶ እስከ ከፍተኛው አመራር ድረስ የህወሃት አባል በሆኑበት በአንድ የዜና ተቋም ውስጥ እውነት መዘገብና የህዝብ አንደበት መሆን ስለማይቻል እንደማንም ዜጋ ከማዘን ውጭ ሌላ አማራጭ የለኝም ነበር።

ይህም ሆኖ ግን እኔና እኔን መሰል የስራ ባልደረቦቼ ከኛ የተሻለ የመጻፍ ነጻነት ላላቸውና ለሌሎች አግባብ ላላቸው ክፍሎች መረጃ በመስጠት የበኩላችንን ስናደርግ ኖረናል። አሁንም በተመሳሳይ መረጃ በማቀበል ስርዓቱን ውስጡ ሆነው የሚዋጉ አሉና የሚደበቅ ጉዳይ ይኖራል ብዬ አላስብም። ስለ ራሴ እዚህ ላይ ላብቃ። ከዚህ በላይ ካልኩ /ወደፊት ማለቴ አይቀርም/ አሁን ያለሁበትን የስደት አገር በረዶ ሊያቀልጥብኝ የሚችል ሙቀት እፈጥራለሁና!!

ወደ ጋምቤላ ልመልሳችሁና መቼም የጋምቤላ መሬት የሰጡትን የሚያበቅል አፈር የያዘ ስለመሆኑ ካሩቱሪና ሼክ መሐመድ ሁሴን አላሙዲ ሊነግሩኝ አይችሉም። ይልቁንም ያጠናክሩልኛል። በአንድ ወቅት የክልሉ ግብርና ቢሮ የሰራው ሰህተት ትዝ ይለኛል፣ ነገሩ እንዲህ ነዉ የግብርና ቢሮዉ ያለበቂ ስልጠና የእርሻ በሬዎችን ለአርብቶ አደር ነዋሪዎች በብድር አከፋፈለ። በሬዎቹን ካከፋፈለ በኋላ ግብርና ቢሮ ጉብኝትም፣ ስልጠናም፣ ምክርም ሳያከናውን ደብዛው ጠፋ። ከረጅም ጊዜ በኋላ  ቢሮው በሬ ገዝቶ ያከፋፈለበትን ገንዘብ ለማስከፈል መንቀሳቀስ ጀመረ። ከ”አርብቶ አደርነት ወደ አርሶ አደርነት ተቀየሩ” እያልን ዜና እንድናዘጋጅ ስንወተወትበት የኖርነው ጉዳይ አንድ አስቂኝ ድራማ ይዞ ከተፍ አለ። “በሬ የወሰዳችሁት በብድር ነው፤ የተበደራችሁትን ክፈሉ” ተባሉ። የግብርና ቢሮው ለጥያቄው የተሰጠው መልስ “በበሬ ማረስ ስለማናውቅ የተሰጡንን በሬዎች ለምግብነት አዋልናቸው” የሚል ነበር። ገጠርን ማዕከል ያደረገ፣ ግብርና መር የኢኮኖሚ ቀመር የሚከተል መንግስት፣ በግብርናው ማግኔታዊ የመመንጨቅ ሃይል ኢንዱስትሪውን አስፋፋለሁ የሚል ፓርቲ በሬ ለምግብ ዋለ፣ ለእርሻ ነው የሰጠውህ የሚል ቧልት ውስጥ ገብቶ ሲንቦጫረቅ  መስማት ካፈርኩ አይመልሰኝ ካልሆነ ምን ትርጉም አለው።

እውነት ለመናገር ጋምቤላ እንኳን ለዓመታት ለወራት መቀመጥ የሚችል ህሊና የሌለው ሰው ብቻ ነው። በጋምቤላ የቆይታ ጊዜዬ አልቅሻለሁ። እንደ ሴትነቴ የእህቶቼን ችግር ስመለከት መፈጠር የጠላሁበት ጊዜ ሁሉ ነበር። ምንም ያላጣ ህዝብ አለሁልህ ብሎ አቅጣጫ የሚያሳየው በማጣቱ እየገፋ ያለው መከራ ያንገፈግፋል።

“ዜናዊ ይሙት” እያሉ እንደሚምሉ የሚነገርላቸው አቶ በረከት ጋምቤላ ወፍጮ ተተከለ፣ መስኖ ተስፋፋ፣ ህክምና ተደራጀ… እያሉ ሲናገሩ መስማት እንደኔ ቦታው ላይ ለኖረ ያሳፍራል። ለቢቢሲ ጋዜጠኛ ከራሳቸው አንደበትና ከእውነት ጋር እየተጣሉ መልስ የሰጡት አቶ በረከት እሳቸው ለተናገሩት አንቀጠቀጠኝ። ሰውነቴን ወረረኝ። ሃያ ዓመት ውሸት ምን ያደርጋል? ደግሞስ አሁን ተሰራ ብለው የሚያወሩት “የወፍጮና የዱቄት” ልማት ትግራይን ካጥለቀለቋት ፋብሪካዎች ጋር ሲነጻጸር የጋምቤላ ተወላጆችን ብቻ ሳይሆን ንጹህ ህሊና ያላቸውን ሁሉ በስርዓቱ ላይ እንዲያምጹ የሚያነሳሳ ስለመሆኑም የዘነጉት ይመስላል። በትግራይ መልማት ማኩረፌ ሳይሆን ለትግራይ ልማት ጋምቤላ ኋላ መቅረት አለባት የሚል እምነት ሊኖር እንደማይገባ ለመጠቆም ነው። ትግራይና የትግራይ ህዝብም ቢሆን ከሌሎች ጋር በማያቃርናቸው መልኩ ፋብሪካም ሆነ ከቻሉ የአውቶሚክ ኢነርጂ ቢሰሩ የተሻለ ይመስለኛል። ወደ ጋምቤላ ልመለስ።

የጋምቤላ ህዝብ በውሃ ወለድ በሽታዎችና በወባ ክፉኛ የሚጠቃ ህዝብ ነው። ክሊኒክና ንጹህ ውሃ የሚታሰብለት ዛሬ መሆኑ በራሱ የመንግስታቸውና ክልሉ ላይ የተሰየሙትን  ሹመኞች ሃጢያት የሚያሳይ ከመሆን ያልፋል ብለው አቶ በረከት ራሳቸው እንደማያምኑ ርግጠኛ ነኝ። እንግዲህ ይህንን እውነት አስቀምጠው ነው አቶ በረከት በጋምቤላ ልማት ሞልቶ ፈሷል በሚል “ወፍጮ፣ ዱቄት….” እያሉ እንደ እድር እቃ የዘረዘሩልን። እንግዲህ በሳቸው ቤት የሂውማን ራይትስ ዎችን ዘገባ ማስተባበላቸው ነው።

የውጭ አገር ጋዜጠኞች ገብተው በነጻነት እንዳይሰሩ መከልከሉ፣ የርዳታ ድርጅቶችና የሲቪክ ተቋማት ባገሪቱ ውስጥ እንዳይንቀሳቀሱ በአዋጅ መከልከሉ፣ የአገር ውስጥ ጠንካራ ጋዜጦችን አገር ጥለው እንዲወጡ  መደረጉና የተቀሩት መሰደድ ያልቻሉት አገር ቤት ታስረው የሚማቅቁት ስርዓቱ የሚፈጽመው ተግባር የሚያስበረግገው በመሆኑ ነው። የሃጢያት ክምር ስላለበት ነው።

የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ቃል በቃል የሂውማን ራይትስ ዎችን ሪፖርት ከአቶ በረከት ምላሽ ጋር መነጻጸር ባለመሆኑ ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ አልገባም። ግን ተቋሙ ባቀረበው በመረጃ የተደገፈ ሪፖርት የህወሃትን  እርቃን ሲያሳየን፣ አቶ በረከት እቁብ ሰብስበው ሰዎች በየመቶ ሜትር የሚተክሉትን “የናፍጣ ወፍጮ ተክለናልና ዱቄት ተፈጨ” ማለታቸው ፍየል ወዲህ እንዲሉ ሆነብኝ። በከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰትና ወንጀል ለሚከሳቸው ሪፖርት አቶ በረከት በወፍጮና በዱቄት ሊያጣፉት ሲሞክሩ መስማት ያስቃል። መሬት እየቸበቸብክ ነው ሲባሉ “ገና የምንቸበችበው በሚሊዮን ሄክታር የሚቆጠር መሬት አለን” የሚለውን  መከራከሪያ ማቅረብም ሌላው አስደማሚው የአቶ በረከት መልስ ነው።

ከሁሉም በላይ ሙስና እንደ ርእደ መሬት የመታት ጋምቤላ፣ ሰዎች በየስርቻው በሚወድቁባት ጋምቤላ፣ ሰፈራ ተብሎ በመከላከያ ሃይል ብረት ተወድሮባቸው ዜጎች ከኖሩበት ቀበሌ በሚፈናቀሉባት ጋምቤላ፣ አሳሪውና ፍርድ ሰጪው ሳይለይ አቤት የሚባልበት በሌለባት ጋምቤላ፣ ንጹሃን በግፍ በተጨፈጨፉባት ጋምቤላ፣ ቅርሷ እየተቸበቸበና እየተወረረች ባለችው ጋምቤላ . . . እየተፈጸሙ ያሉት አስነዋሪ ተግባሮች እንዴት ማሻሻል እንደሚቻል ከመነጋገር ይልቅ  ችግሩ ላይ ቤኒዚን ማርከፍከፍ የተመረጠበት መንገድ ከቶውንም ሊገባኝ አይችልም።

“. . . ዘረኛ አትበሉኝና የጋምቤላ ህዝብ የትግራይን አንጡራ ሃብት አግዞ ይሆን? የጋምቤላ የጥንት ነገስታት ትግራይ ድረስ ዘልቀው ገብተው ደን ጨፍጭፈው ይሆን? የጋምቤላ ቀደምት አባቶች ስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት የአቶ መለስን ዘሮች መርጠው ሲተናኮሉ ነበር? በአገር ላይ ባንዳነትና ክህደት ፈጽመው ነበር? ፈላስፋዎቹ መሪዎቻችን ለኛ የማይታየን ይታያቸዋልና ይንገሩን። እንመንና እኛም በጋምቤላ ላይ እንዝመት።. . .” ለዝግጅት ክፍላችን ከተላከ ደብዳቤ የወሰድኩት ነው። አስተያየቱን የላከው ሰው ለጽሁፉ የሰጠው ርዕስ “ምድር ተናገሪ” የሚል ነበር። ክቡሩ ሰው አውሬ ሲሆንና በአውሬነት ሲተካ፣ ከግዑዝ ነገር ጋር መሟገቱ አይገርምም። ደብዳቤው ይቀጥላል . . .

“. . . አብረው ለዘመናት የኖሩ ህዝቦች በማናከስ በልዩነት ውስጥ ማበብ እውቀት የመሰላቸው  አንዱ ጎሳ ሌላው መንደር ሄዶ ጫማ እንኳን ማስጠረግ የማይችልበት ደረጃ አድርሰውታል። ይህ ሁሉ የልዩነት መርዝ የሚረጭበት ምስኪን ህዝብ በድህነቱ ኮርቶ መኖር ሲያቅተው ዝም የምንል ሁሉ በትውልድ የምንጠየቅበትና የመከራውን አረም ለተተኪዎች ለማስተላለፍ በመስማማታችን ከህሊና ወቀሳ የምንድን አይመስለኝም” ደብዳቤው በከፍተኛ የሃዘን ስሜት የገለጸው ሌላው አንቀጽ ነው።

ስለ ሰፈራና ስለ ሰብአዊ መብት ረገጣ ተጨማሪ ጽሁፍ በቅርቡ አዘጋጃለሁ። ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ በተለያዩ ጊዚያት የሚያስነብባቸውን ጽሁፎች የምከታተል ነኝ። እስካሁን ዝምታ በመምረጤ በጋምቤላ ህዝቦች ስም ይቅርታ ይደረግልኝ። አቶ በረከትና በስማቸው የሚምሉባቸው  ጠቅላይ ሚኒስትር ተመካክረው “ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ውርንጭላዎች የማይመለከቱት ፊልም” ከማሳተማቸው በፊት ውርንጭላዎቹን ነጻ በማውጣት አህያዎቹም ሳይሸማቀቁ  የሚኖሩበት ጊዜ እንዲመጣ እንተባበር።

 አዜብ ሃይሉ፤ጥር 142004

ahailu20@yahoo.com

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *