እነማን ዘጉ፣ እነማን ተዘጋባቸው፣ እነማን ሲበራላቸው ለነማን ጨለመ፣ እነማን ሲሽሩ እነማን ለመኑ፣ እነማን ጠግበው ሲያገሱ እነማን ጠኔ ደፋቸው፣ እነማን ሲለብሱ እነማን ተራቆቱ፣ እነማን ሲያብረቀርቁ እነማን አመድ ነፋባቸው፣ እነማን  ሲያብቡ እነማን ከሰሙ፣ እነማን ሲያሽካኩ እነማን አነቡ…. ለቅሶ፣ ሃዘን፣ ድብታ፣ የተሰበረ መንፈስ፣ የራበው አንጀት፣ ያዘነ ህሊና፣ ያኮረፈ መንጋ፣ የባሰበት፣ ያልባሰበት፣ ግድ የለሽ፣…የተመቻቸው፣ የሚነዱ፣ የሚያሽካኩ፣ የሚፈልጡ፣ ያበጡ፣ የተዋቡ፣ የሚታጀቡ፣ ለምና የነጋላቸው፣ ለመቀፈፍ የጠባላቸው፣ ሹማምንት፣ ተላላኪዎች፣ ባለመደብሮች፣ ባለወርቅቤቶች፣ ባለ ድርጅቶች፣ …… ሁሉም ዓይነት ሰዎች ይታያሉ። ቄስ፣ ሼኽ፣ …. መምሬ አብደላ፣ ሼኽ ገብረ ማሪያም የደሴ ውህደት!!!

ፒያሳ በጠዋት ሲፈትገው ላደረው፣ ጠግቦ ሲያስታውክ ለነጋበት፣ ተከፍታለች። ደላሎች ብቅ ብቅ እያሉ ጊዮርጊስን በሩቁ ይሳለማሉ። ቀኑን “ ላራዳው ጊዮርጊስ ባደራ የሚያስረክቡም አሉ ” ትንሽ ሲያገኙ  ወደ ጊዮርጊስ ደጅ የሚሮጡ ብዙ ናቸው። ደላላው ሳቀ። በኩሉ ደልሎ ያገኘውን ሳይዘረዝር አራዳ ጊዮርጊስ ገብቶ ግብር ሳያስገባ ለራሱ አይጠቀምም ነበር። …. ብቻ ነግቷል። ሰው የሚያስማሙ፣ ሰው የሚሸጡ፣ የድሃ ንብረት ላይ የሚፈርዱ ፣ ደላላ መስለው የሚሰልሉ፣ የሚሰለሉ፣ ደላላ መስለው የሚመነትፉ፣ የሚመነተፉ፣ የሚስቁ የሚያለቅሱ፣ አውቶቡስ የሚጋፉ፣ አዲስ አበባን ባቡር እስኪንበሸበሽባት  በትግስት የሚጠብቁ እግረኞች ይራወጣሉ። በታቦት ስም የሚለምኑ፣ ያራዳ ልጅ፣ ጀለስ፣ ፍሬንድ … የሚሉ ቄንጠኛ ለማኞች ይበዛሉ።  ቀኑ መጀመሩ ነው። ያበደውም ነግቶለታል።

ያበደው በጠዋት ከቤቱ ሲወጣ መመሪያ ተቀብሏል። ባለቤቱ ቦሰና “ ድህነትን  ተረትና ታሪክ  ሳታደርግ  እንዳትመጣ ” ብላዋለች። ማብራሪያዋም አስገራሚ ነው። ድህነትን  ታሪክ ማድረግ መልካም ነው። ድህነትን ታሪክና ተረት ማድረግ ግን በቀደመው ድህነት እንደ ተረት መቀለድንም ስለሚያካትት ታሪክ የሚሆን ባለጠግነት ብቻ ሳይሆን ፣ ተረት የሚሆን  ድህነት …. ”  ባለቤቱ ቦሰና “ ልማታዊ ናት ” ውሃ ማቆር፣ አርብቶ አደር፣ ግብርና መር፣ ውጤት ተኮር፣ ኢንቬስተር፣ አጥር ማጠር፣ ፀረ ሽብር ፣ ግምገማ፣ ጥርነፋ፣ ተሃድሶ፣ ፋይዳ፣ ማተራመስ፣ ነውጥ፣ ጎጥ፣ ….. ስለሚሉት ፓኬጆች  በቂ ግንዛቤ አላት። ነቅታለች!!

አንዳንዴ የሰራችው ምግብ ውር ውር የሚል ስጋ ካለው “ ዛሬ ውጤት ተኮር ነው ”፣ ውሃ ውሃ የሚል ከሆነ “ ዛሬ ውሃ ማቆር ነወ ”፣ ቆሎና በቆሎ ከሆነ “ ግብርና መር ነው ”፣… ትላለች። “ ቦንድ ” ነብሷ ነው። “ አዳሜ ሲስቅ፣ ሲያላግጥ  ግድቡ ተሰርቶ ሊያልቅ ነው። አሁን ስራው ሲጀምር ሲያንቋሽሹ የነበሩ ምን ሊሉ ነው ” የቦንድን ጥቅም ለማስረዳት ቦሰና ታወራለች። ያበደው እንዲህ ያለ ቀልድ  ቢያጥወለውለውም፣ ቦሰናን ላለመቃወም ታቅቦ ይመርጣል።

አዎ!! ማን ያውቃል አባይ ተገድቦ አፍሪካ ስታበራና ስታብረቀርቅ፣ አባይ ተገድቦ የሁመራና የመተማ ሜዳ በምርት ሲምበሸበሽ፣ ባባይ ስንጠመቅ፣ ባባይ ስንጠግብ፣ ረሃብን ስናራግፍ፣ አባይን ከመርገም መለስ ብለን ስናወድስ…… ያበደው ጎመጀ። ሳያስበው “ የኢትዮጵያ አምላክ ” አለ። ኢትዮጵያ አገሬ ተራራሽ አየሩ ተብሎ ሲዘፈን፣ ወንዝሽ ሸንተረርሽ  እየተባለ ግጥም ሲደረደር፣ ያበደው ተራራ፣ ወንዝ፣ ሸንተረር፣ ሸለቆ፣ ለም መሬት፣ ውብ አየር… ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ያለ ይመስለው ነበር። በዚህ መልክ የተሸወዱ ብዙ ናቸው። እግሂአብሔሩ ራሱ ከኢትዮጵያ ሌላ አገር፣ ከእኛ ሌላ ህዝብ የማያውቅ፣ መቀመጫው አዲሳባ የሚመስለን አለን። ያበደው ተናደደ!!

ወግ ይገላል። ሰው በወግ እስከመቼ ይኖራል። ባዶ አገር፣ የራበው ህዝብ፣ ራቁት የሚሄዱ ህዝቦች፣ ትራፊ ያረረበት አገር፣ ጠኔ የሚደፋቸው ህፃናት …. ይዘን ባዶ ጉራ። በተረት መኖር፤ እውነትን መካድ፣ ወግ፣ ወግ፣ ወግ፣ ወግ፣ ወግ፣…….. እንዲህ ያለ አገርና ህዝብ እየመሩ ጉራ፤ ያበደው ተቆጣ። ምራቁ አፉ ውስጥ ደነደነ። ያበደው ሲናደድ ምራቁ አረፋ ይሆናል። …… ያበደው የቦሰና ትዕዛዝ ታወሰው። ድህነትን ታሪክ ማድረግ!! ድህነትን ታሪክ ብቻ ሳይሆን መጪው ትውልድ ተረት አድርጎት እንዲዝናናበት….. ያበደው አሽካካ። ቦሰናን የሚያነቃት  ያ መከረኛ ቲቪ፣ ቀበሌ ያለው ጥላ ቢስ ታወሳት።

አሁን ኢቲቪን ይዘን፣ እንዲህ ያሉትን መሪዎች ይዘን ድህነት ታሪክና ተረት ሊሆን? …. ግን ግን ታሪክና ተረት ማንና ምን ናቸው ? ያበደው ሊቀናጣ አሰበ። ድህነትን ተረት ለማድረግ፣ አባይን ለመገደብ የተነሱ መሪዎች ከታሪክ ይልቅ ወደ ተረት ያተኩራሉ። ታሪክ ጊዜ ይወስዳል። ታሪክ ረጅም ነው። ታሪክ ስራ ያስተጓጉላል። ታሪክ የኢትዮጵያን ህዳሴ ያጓትታል። ታሪክ ባለታሪኮችን በማስታወስ በሃሳብ ያስቆዝማል፣ ማንነትን ይነግራል፣ ታሪክ ፀረ ልማት ነው፣ ታሪክ ……. ለውሸት አይመችም፤ ታሪክ ተናጋሪውን ሳይሆን ባለታሪኩን ስለሚያከብር ስብሰባ ያፋዝዛል።

ተረት ደስ ይላል። ተረት ለወሬ ይመቻል። ተረት “ አሉ ”  ነው። ተረት ጠያቂ የለውም። ተረት ለፓርላማ ሪፖርት ማድመቂያ፣ ለማይጠይቁና ለማይናገሩ ማዝናኛ ይሆናል። ተረት ጊዜ አይፈጅም። ተረት ልማት አይጓትትም። ተረት ለኢትዮጵያ ህዳሴ እንቅፋት አይሆንም፣  ተረት ለመተረት ይቀላል። ተረትን በመደጋገም አንድ ቀን እውነተኛ ማድረግ የተረት አስፈላጊነት “ ፓኬጅ ” ነው። ያበደው ከት ብሎ ሳቀ። ውሻው ደጎል ታወሰው። ደጎልና ያበደው ያወራሉ። ቦሰና ቲቪ ስትከፍት ደጎል ያበደውን ያየዋል። ጆሮውን እአዟዟረ “ እንውጣ ” አይነት ምልክት ያሳየዋል። …..

ያበደው ሲነጋ ከቤቱ የወጣው ድህነትን ታሪክና ተረት ለማድረግ ነው። ድህነት እንዴት ታሪክም ተረትም ይሆናል? የቤታቸውን ድህነት ታሪክ ያደረጉ አሉ። ልጆቻቸውም የቤታቸውን ድህነት ወደ ተረት ለውጠዋል።  ድህነትን “የጠረነፉ” ተረት ማውራት ጀምረዋል። የቤታቸው “ የልማት አርበኛ ” ናቸው። ያበደው በጀግና ትርጉም ላይ ማብራሪያ አይቀበልም። ሁሉም ለራሱ ጀግና ነው። በ15 ዓመት እድሜዋ ስጋዋን ለመሸጥ እናትዋን አስማምታ የቤተሰቦቿን ጉሮሮ ለመዝጋት የወሰነች “ የቤተሰቦቿ ጀግና ናት ”፤ ድህነት ሲፈጀው ማጅራት የሚመታ ለራሱ ጀግና ነው። ከደሃ ህዝብ ላይ የሚወስድ “ የመንግስት ሌባ ” የራሱ ጀግና ነው። የቀን ጀግና!! በሚመሩት ህዝብ ስም የተገኘውን የሚሰበስቡ ጀግኖች የበዙ ይመስላል።

ያበደው ሳያስበው አራት ኪሎ ደርሷል። አራት ኪሎ ወሬ ይፈጫል። እቅድ ይወጣል። ይቀደሳል። ይመናል። ጥበቃ ይታያል። ቤተመንግስት!! አዎ !! ቤተ መንግስት ድህነት ታሪክና ተረት የሆነበት ቦታ!!  እዛ የምትኖሩ ሰላም ይብዛላችሁ። የሌላውንም ሰላም አክብሩ። ከግቢው ውጪ ድህነት እንኳን ታሪክ ሊሆን ብሶበት ህዝቡን እያመሰው ነውና ለመዝናናት ስትወጡ እንዳትደነግጡ  የቀድሞውን ፊልም አከታትላችሁ ተመልከቱ። ፊልም ተረት ነው። ከተፈለገም ታሪክ ይሆናል፤ በታሪክና በተረት መካከል ያለው ልዩነት ያልገባቸው አሉ። የገባቸውም አሉ። ባይገባቸውም እንደገባቸው ሆነው የሚኖሩ አሉ። ለታሪክና ለተረት ደንታ ያጡ አሉ። ታሪክና ተረት ተጨፍልቀው ዳቦ ቢሆኑላቸው የሚመርጡ ጥቂት አይደሉም። የአክሱም ሃውልት ተቆራርጦ ዳቦ ቢሆን የሚወዱ አሉ።  ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የቆመው ሃውልት ሲነጋ የሚበላ ቢሆን የሚጨፍሩ አሉ። የእብደት መጀመሪያው ታሪክና ተረት ማደባለቅ ነው። ሃውልትን፣ ድንጋይን፣ ማስታወሻን ለመብላት መመኘት ነው። ደስ ሚል እብደት።  የራበው  ማሰብ ቢያቅተው በየትኛው አንቀፅ ይጠየቃል? ። የራበው ወንጀለኛ ቢባልና ቢታሰር ምን ይቀርበታል? የራበው ቢሞት ምን ይጎልበታል? ….

ያበደው የቦሰናን የቤት ስራ ሳይ ሰራ ዋለ። መሸበት። ቦሰና ጋር መመለስ አለመት። ቦሰናን አሰበ። ባዶ ቤት፣ ባዶ ኪስ። ቀልድ አሰበ። ገመድ ፈለገ። አንገቱ ላይ አስገባ። ሞትን አወጀ። ሸምቆቆውን ሳበው። አንገቱን አመመው። ከረከረው። ለካስ ለመሰቀል ገመዱ ከፍ ያለ ዛፍ ላይ መታሰር አለበት። እሱ እውነተኛው ሞት ነው። ያበደው ገመዱን ፈታና ሳቀ። ነገም ሌላ ቀን ነው……. ህይወት ይቀጥላል፤ ህይወተወ ወንዝ ነው፤ ህይወት ደራሽ ውሃ ይሆናል። ህይወት የጊዜ ባርያ ነው። ወግ የጊዜ ጠላቱ ነው። በባዶ ሜዳ ጉራ ……… ድህነትን ታሪክ ያደረጋችሁ ተርቱ፣ ያበደው ከታሪኩም ከተረቱም የለበትም። ጉራም አይወድም።  ፒኮክ አፕሬቲቭ ተወግቶ መግባት ከፈለገ መብቱ ነው። የሚኒስትሩ ልጅ ስፖንሰር ያደርገዋል። ያበደው ወደ ፒኮክ አመራ!! ፒኮክ ፖለቲካ ይበለታል። መኪና ውስጥ  ሁለት ሁለት ሆነው  የተጣመዱ የሚሰሩትን ማየት ኑሮ ያስረሳል። የመኪናዎቹ አሞርዛቶር ሲቆሙ መስራት የሚጀምር ይመስላል። አልኮል በበዛ ቁጥር መኪኖቹ ወደ ላይ ወደ ታች … አዲሳባ ተዥጎርጉራለች። ከዝግ ቤት የወጡ  ይወጋሉ።፡በርጫ፣ ሚርቃና ፣ ሚርቃና  ሰበራ፣ ከዛ ማሪንጌ ቻቻ፣ ቻቻ፤ ተለያይተናል፤ ልዩነቱ በዛ፤   ……. ቸር ሁኑ !!

Share and Enjoy !

0Shares
0

1 Comment

  1. I said woow. you took me back to Addis. ehhm, that is how we manage, politics, business and life, appreciate it.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *