በተደጋጋሚ ” የአፃፋ ተመጣጣኝ ርምጃ ” በሚል ከኢትዮጵያ በኩል  በተደጋጋሚ ጥቃት መድረሱ ይታወቃል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ድንበር አልፎ በመሄድ ያደረሰው ጉዳት የከፋ እንደሆነ በተለያዩ ወገኖች ተረጋግጧል። ይሁን እንጂ በኤርትራ በኩል የተወሰደ ርምጃ አልነበረም። ባልተጠበቀና ባልተለመደ ሁኔታ የኤርትራ መንግስት ወደ ክስና አቤቱታ ነበር ያመዘነው። በተለይ ባለፈው ሳምንት በድጋሚ የኢትዮጵያ ጦር በድጋሚ ድንበር አልፎ በኤርትራ ሃይል ላይ ጥቃት ወስዷል። በጥቃቱም የደረሰው ቁሳዊና ሰብአዊ ጉዳት በዝርዝር ባይቀርብም ጉዳቱ የተመረጠ እንደ ነበር ለመከላከያ ቅርበት ያላቸው በተለያዩ ብሎጎች ጽፈዋል። ይህ በእንዲህ እያለ ነው የዘወትር የመረጃ ምንጫችን ሪፖርተር የኤርትራ መንግስት ጥቃት ማድረሱን የሚጠቁም ዜና አሰራጭቷል። ዝርዝር የሌለው ሪፖርተር ዜና የኤርትራ መንግስት ባደረሰው ጥቃት በሰው ህይወት ላይ ጉዳት እንዳላስከተለ አስታውቋል።አንዳንድ  መረጃዎች  ባድሜ አከባቢ የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማና ቁስለኞች  መታየታቸውን እየተናገሩ ነው። ዜናው  

 የኤርትራ ጦር በባድመ አንድ ትምህርት ቤትና አንድ አውቶብስ አቃጠለ

የኢትዮጵያ ሠራዊት በቅርቡ በባድመ ግንባር የኤርትራ ግዛት ውስጥ በመግባት በሦስት ወታደራዊ ካምፖች ላይ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ፣ የኤርትራ ጦር በባድመ ውስጥ የሚገኘውን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና አንድ አውቶብስ ማቃጠሉን ምንጮች ጠቆሙ፡፡ የአካባቢው የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ ባለፈው እሑድ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በባድመ ግንባር የሚገኘው የኤርትራ ጦር ኃይል በከባድ መሣርያ (ተወንጫፊ) ባደረሰው ጥቃት፣ ‹‹ባድመ ቀዳማይ ብርኪ ቤት ትምህርቲ›› (ባድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት) ሙሉ ለሙሉ በመቃጠሉ ከጥቅም ውጪ ሆኗል፡፡ ትናንት ደግሞ በከተማዋ ውስጥ ቆሞ በነበረ አንድ አውቶብስ ላይ በተመሳሳይ በደረሰው ጥቃት ሙሉ ለሙሉ ተቃጥሏል፡፡ በሁለቱም ጥቃቶች በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት የለም ተብሏል፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ኤርትራ የነፃነት በዓል በማክበር ላይ ሳለች ድንበር ጥሶ በመግባት በባድመ ግንባር በሚገኝ አንድ ብርጌድ ላይ ጥቃት ያደረሰው፣ ከዚያ ቀደም ሲል የኤርትራ ጦር የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ በመግባት በባህላዊ መንገድ የወርቅ ማውጣት ሥራ ላይ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያንን በተደጋጋሚ እያፈነ በመውሰዱ ምክንያት ነው፡፡

ባለፈው ዓመት በኤርትራ ላይ ያለውን ፖሊሲ ‹‹ከመከላከል ወደ ተመሳሳይ ዕርምጃ መውሰድ›› የለወጠው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በአፋር አካባቢ በኢትዮጵያውያንና በአውሮፓውያን ቱሪስቶች ላይ ከኤርትራ በኩል ጥቃት በመሰንዘሩ አፀፋ ወታደራዊ ዕርምጃ መውሰዱ የሚታወስ ነው፡፡http://www.ethiopianreporter.com/news/293-news/6588-2012-06-06-06-22-30.html

የኢትዮጵያ ሠራዊት በኤርትራ ጦር ላይ ጥቃት ፈጸመ

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ባለፈው ሳምንት ኤርትራ የነፃነት ቀኗን ስታከብር በነበረበት ዕለት፣ ባድመ በሚገኘው የኤርትራ ጦር ላይ ጥቃት ማድረሱን ወታደራዊ ምንጮች ገለጹ፡፡ ጥቃቱ በትግራይ አካባቢ በቅርቡ በኤርትራ ጦር ታፍነው ለተወሰዱ ኢትዮጵያውያን አጸፋዊ ምላሽ ነው ተብሏል፡፡
ማንነታቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የመከላከያ ሠራዊት ምንጮች እንደገለጹት፣ ግንቦት 16 ቀን 2004 ዓ.ም. የኤርትራን ድንበር ጥሶ የገባው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ባድመ አካባቢ በሰፈረው በአንድ ብርጌድ የኤርትራ ጦር ላይ ድንገተኛ ጥቃት ሰንዝሮ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡
በጥቃቱ በርካታ የኤርትራ ወታደሮች የመቁሰልና የሞት አደጋ የደረሰባቸው መሆኑን፣ እስከ ሻለቃ ማዕረግ ያላቸው በርካታ የኤርትራ ጦር አመራሮችም እጃቸውን የሰጡ መሆናቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከወራት በፊት በተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፣ የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚፈጽመው የሽብር ጥቃት ተመጣጣኝ ምላሽ እንደሚሰጥ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
በያዝነው ዓመት ጥር ወር ላይ አፋር ክልል ውስጥ የተገደሉትና ታፍነው የተወሰዱትን የአውሮፓውያን ቱሪስቶች ሴራ ያቀነባበረው የኤርትራ መንግሥት ነው ብሎ ያመነው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የመከላከያ ሠራዊቱ የኤርትራን ድንበር ጥሶ በመግባት ሽብርተኞች የሚንቀሳቀሱባቸው ናቸው ባላቸው ሦስት የጦር ካምፖች ላይ ጥቃት ፈጽሟል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ጥቃት ካካሄደ በኋላም ግን ትግራይ አካባቢ በማዕድን ፍለጋ ላይ የተሰማሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን በየጊዜው በኤርትራ ጦር እየታፈኑ እንደሚወሰዱ በተቃዋሚዎችም ሆነ በመንግሥት በኩል ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
የመከላከያ ምንጮች እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ጦር ሰሞኑን በኤርትራ ላይ የወሰደው ወታደራዊ ጥቃት የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ አካባቢ ለሚፈጽሙት አፈና አጸፋዊ ምላሽ ለመስጠት ነው፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የወሰደውን ዕርምጃ በማስመልከት ከኤርትራ በኩል የተገለጸ ነገር የለም፡፡

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *