በቀጣዩ ዓመት በሚካሄደው የአዲስ አበባ ምርጫ ለመሳተፍ ገና አልተወሰነም

ስድስት ፓርቲዎችን በአባልነት የያዘው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ግንባር ለመሆን በሚያስችለው ጉዳይ ላይ እየመከረ ነው። 12 አባላት ያሉት የስድስቱ ፓርቲዎች ተወካዮች በዛሬው ዕለት የመድረክ የፓርቲዎች ስብስብ ወደ ግንባር እንዲያድግ የሚያስችለውን የጋራ ጠቅላላ ጉባኤ የሚካሄድበትን ቀን ጨምሮ በሌሎች ልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተው ውሳኔ ያሳልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ እና ደቡብ ኅብረት ፓርቲዎች በወቅቱ ከገንዘብ እጥረት ጋር በተያያዘ ጠቅላላ ጉባኤ መጥራት ባለመቻላቸው “መድረክን” ከተራ ቅንጅት ወደ “ግንባር” ለማሳደግ የነበረው ኀሳብ ሲጓተት መቆየቱ አይዘነጋም። ሆኖም ሁለቱ ፓርቲዎች ባለፈው ሰኔ 16 እና 17 ቀን 2004 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤ ከጠሩ በኋላ መድረክን ግንባር ለማድረግ የተያዘው አጀንዳ ላይ ውይይት ተጀምሯል።
ለመድረክ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት፤ መድረክ በቀጣዮቹ ሁለትና ሦስት ሳምንታት ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ ሊጠራ እንደሚችል ገልፀዋል። መድረክ ግንባር የመሆኑ ዕድል በመጓተቱ የተደራጁና ወጥነት ያላቸው ተግባራት ለማከናወን አዳጋች መሆኑን ምንጫችን የጠቀሱ ሲሆን፤ አሁን ችግሩ ተፈትቶ ወደ ተግባር እየገባን ነው ብለዋል።
መድረክ ግንባር ሲሆን በሦስት ወሩ ይቀያየር የነበረውን አመራር ወደ ሁለት ዓመት፣ የስድስቱ ፓርቲዎች ጽ/ቤቶች የመድረክ ቅርጫፍ ጽ/ቤቶች እንዲሆኑ በማድረግ አንድ ዋና ጽ/ቤት መረጣ የሚካሄድ ሲሆን በተለያዩ ቁመና ላይ የሚገኙ ፓርቲዎች የተመጋገበ እንቅሰቃሴ በማካሄድ ግንባሩ እንደሚጠነክር ምንጫችን ገልጿል።
መድረክ ግንባር በሚሆንበት ወቅት የፓርቲው የስም ለውጥ እንደማይኖር በአመራሮቹ መካከል መግባባት መደረሱን፣ የጋራ ሀብትና እዳ እንደሚኖረውና ሁሉንም ፓርቲዎች የሚመሩበት የጋራ ሕገ-ደንብ እየተዘጋጀና በሕገ-ደንቡም ላይ የፓርቲው አመራሮች ከተወያዩበት በኋላ ወደ ተራ አባላት የሚደርስበት ሁኔታ እንዲመቻችም ምንጫችን ገልጿል።
በተያያዘ ዜና መድረክ በቀጣዩ ዓመት በሚካሄደው በአዲስ አበባ አስተዳደር ምርጫ ላይ ለመሳተፍ እስካሁን አለመወሰኑም ምንጫችን ገልጿል። ቀደም ሲል የመድረክ አባል የሆነው አንድነት ፓርቲ በአዲስ አበባው ምርጫ ለመሳተፍ ልዩ ልዩ ቅድመ ዝግጅቶች ሲያካሂድ ቆይቷል። ሆኖም መድረክ ግንባር ሲሆን፤ ምርጫው የአንድ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ መመዘኛ የሚያሟላ መሆኑ ከታየ በኋላ የሚገባበት እንደሚሆን ለመድረክ አመራሮች ቅርበት ያለው ምንጫችን ለዝግጅት ክፍላችን ገልጿል።
መድረክ የአዲስ አበባ አስተዳደርን ምርጫ እንደ ፖለቲካ ጥቅም (Advantage) ለማየት ማሰቡን የገለፀልን ምንጫችን፣ የአዲስ አበባው ምርጫ የኢህአዴግ ባህሪ የሚለካበትና መሻሻሎች ከታዩ ወደ ምርጫው የሚገባ መሆኑን ነገር ግን የኢህአዴግ ባህሪ እንዳለፉት ምርጫዎች ችግር ያለበት ከሆነ በምርጫው ባለመሳተፍ ኢህአዴግን ማጋለጥ እንደሚቻልም ገልፀዋል።

Source ሰንደቅ ጋዜጣ 7ኛ ዓመት ቁጥር 356 ረቡዕ ሰኔ 27/2004
——————————————————————————————————————————————————————–

               ሐዋሳ ከተማ ወደ ፌዴራል አስተዳደር አትገባም

የሃዋሳ ከተማ ግለት አልበረደም። የሃዋሳ ከተማ  በፌደራል መንግስት ስር እንድትተዳደር አይደረግም ሲል የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር እየወተወተ ይገኛል። ለውጥረቱ የተለያዩ ምክንያቶች ቢቀርቡም ሚኒስቴሩ የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ለችግሩ መንስኤ እንደሂነ ይናገራል።ያም ሆኖ ጸጥታው አስተማማኝ አለመሆኑን አክሏል የሰንደቅ ጋዜጣ ዜና ይህን ይመስላል።

ሰሞኑን የሐዋሳ ከተማ ወደ ፌዴራል አስተዳደር ትገባለች በሚል በከተማዋ ውጥረት ሰፍኖ ቆይቷል። የፌዴራልና የክልል ፖሊስ የተፈጠረውን ውጥረት ለመከላከል ወደ ከተማዋ መግባቱን እየተገለፀ ነው።

በሐዋሳ ከተማ የተፈጠረውን አለመረጋጋት በተመለከተ በፌዴራል ደረጃ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተውን የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴርን አነጋግረናል። የሚኒስቴር መስሪያቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ ወርቁ ሐዋሳ በፌዴራል ስርዓት ትተዳደራለች መባሉን አስተባብለዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በትላልቅ የክልል ከተሞች እየተንሰራፋ የመጣውን የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግሮች በፍጥነት እያደገ ካለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ አምስት የክልል ከተሞች በፌዴራል መንግስት ሥር ይተዳደራሉ የሚለው ውዥንብር የሚኒስቴር መስሪያቤቱ ህዝብ ግንኙነት አስተባብለዋል።
እንደ ሕዝብ ግንኙነቱ አገላለፅ በክልሎች ሕገ-መንግስት ሆነ በፌዴራል ህገ-መንግስት ላይ የፌዴራሉ መንግስት ከድሬዳዋ ከተማ በስተቀር በክልል ከተሞችን በሞግዚትነት የሚያስተዳድርበት የሕገ-መንግስትም ሆነ የሕግ አግባብ የለም ብለዋል።
የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የፌዴራል ስርዓቱን በህገ-መንግስቱ መሰረት እንዲፈፀም፣ በክልሎች መካከል ያለው ግንኙነት የሰመረ እንዲሆን እየሰራ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አበበ ሰሞኑን ለሐዋሳ ከተማ አለመረጋጋት በመንስኤነት ከሚነሱ ጉዳዮች አንዱ ሐዋሳ ከተማ በፌዴራል አስተዳደር ስር ትሆናለች መባሉ መሆኑን ሚኒስቴር መስሪያቤቱ መገንዘቡን ገልፀዋል።
‘‘ሕዝቡን ሊያነሳሱ የሚችሉ ውዥንብሮች አሉ። ከነዚህም ውዥንብሮች መካከል ሕዝቡን ለመቀስቀስ የተጠቀሙበት ሐዋሳ ከተማ በፌዴራል ስርዓት ትተዳደራለች የሚል መነሻ ህገ-ወጥ በራሪ ወረቀት ተፅፎ መበተኑ ነው’’ ያሉት አቶ አበበ ወርቁ ሐዋሳ ከተማም ሆነ ሌሎች የክልል ከተሞች ወደፌዴራል አስተዳደር አይገቡም፤ የተጠናም ነገር የለም ብለዋል።
በሰሞኑ የሐዋሳ ከተማ ውጥረት ላይ ሐዋሳ ከተማ በፌዴራል አስተዳደር ትገባለች ከሚለው ጉዳዩ በተጨማሪ የሐዋሳ አስተዳደር የሲዳማ ሕዝብን ብቻ እያስተዳደረ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችን ማግለል የለበትም የሚል ነው። የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሕዝብ ግንኙነት የሐዋሳ አስተዳደር ብሔር ብሔረሰቦች መካከል አድሎ ያደርጋል መባሉን ‘‘የሌለ ነገር ነው’’ ሲሉ ገልፀውታል። የደቡብ ክልል ዋና ከተማ ‘‘ወደ ወላይታ ይሄዳል’’ መባሉም ‘‘በሬ ወለደ’’ ወሬ ያሉት ሕዝብ ግንኙነት ጉዳዩ ሕዝቡን ወደግጭት እንዲገባ ለመቀስቀስ የተደረገ ሙከራ ነው ብለዋል።
የህገ-ወጥ በራሪ ወረቀቶች ምንጫቸው ከጥቂት ግለሰቦች መሆኑን ያወሱት አቶ አበበ በራሪ ወረቀትን ሊያባዙ ይችላሉ ተብለው ከተገመቱ ቡድኖች መካከል የክልል ጥያቄ እንዳለ አስመስለው የሚያነሱ ቡድኖችና ሌሎች ፀረ-ሰላም ኃይሎች መሆናቸውንም ህዝብ ግንኙነቱ ተናግረዋል።
በክልሉ ‘‘ክልል እንሁን’’ የሚል ጥያቄዎች ቀደም ሲል ይነሱ እንደነበር ያስታወሱት ህዝብ ግንኙነቱ ይህ ጥያቄ በክልሉ ‘‘ልዩ የብሔረሰብ ዞኖች’’ በመመስረት ችግሩ መፈታቱን ገልፀዋል። ጥያቄው ከተነሳ የክልሉና የፌዴራሉ ህገ-መንግስት ባስቀመጠው ስርዓት አማካኝነት እንጂ ግርግርና ረብሻ በመፍጠር አይደለም ብለዋል። ሆኖም ፌዴራል ጉዳዮች ‘‘ክልል እንሁን’’ የሚለው ጥያቄ የጥቂቶች እንጂ የሕዝቡ አለመሆኑን መረዳቱንም አያይዘው ገልፀዋል።

Source ሰንደቅ ጋዜጣ 7ኛ ዓመት ቁጥር 356 ረቡዕ ሰኔ 27/2004

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *