ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

” ነጋሪ የሌለው ትውልድ “

‘‘የኢትዮጵያ ወጣትና የወደፊት ኃላፊነት’’

ከፕሮፌሰር መስፍን አንደበት

 ተጧሪ ትውልድ ነው!!

  “አርበኛውን የሚገድል ሕዝብ በሌላ ሀገር ያለ አይመስለኝም። ሀውልት ሊያቆምላቸው የሚባቸውን ሰዎች የሚገድል ሕዝብ በሌላ አለም ያለ አይመስለኝም ወይም አላውቅም፤ እኛ ግን ራስ አበበን ገድለናል። ራስ መስፍንን ገድለናል። በላይዘለቀን ገድለናል ማን ያልገደልነው አርበኛ አለ። ይሄንን የምጠቅሰው በዜግነትና በሎሌነት መካከል ያለውን ልዩነት በደንብ እንድንረዳ በማሰብ ነው። ትልቁ ነገር በዚህች ሀገር ታሪክ ዜግነት ሳይሆን ሎሌነት ነው። ፉከራውም እኔ ያንተ አሽከር፣ እኔ ያንተ ቡችላ ነው። ይህ ባህል ነው፤ በአንድ ትውልድ ቢኖርም ተላልፏል። አንዱ ትውልድ የሰራው ስህተት ሌላው ትውልድ ተረክቦ ያስተላልፈዋል። ሎሌነቱን ብቻ ሳይሆን ጌትነቱንም ጭምር ነው “

  

አሁን ከ40 አመት በታች ያለው ትውልድ ‘‘ግራ የጋባው’’ ያሉት ፕሮፌሰር ‘‘የሚቆምበት የሌለው መሰረት ያጣ፣ ጫት ካልሆነ በቀር መሰረት የሌለው፣ መቆሚያ ያጣ ተንጠልጥሎ በአየር ላይ የሚውረገረግ ነው። የዚህ ትውልድ ልጆች ወዴት እንደሚሄዱም አይታወቅም። ወደፊት የሚመጡት ትውልዶች ከእሱ የተሻሉ ወይስ የባሱ? አይታወቅም’’ ሲሉ የዚህን ዘመን ትውልድ ገልፀውታል። 

‘‘ሀይሉ አርአያ (ዶ/ር) አንድ የደርግ ካድሬ ላይ ከኋላ ሆኖ መንገድ ልቀቅልኝ ብሎ የመኪና ጡሩምባ ነፋበት፤ ያ የደርግ ካድሬ መኪናውን እንዳቆመ መጥቶ በጥፊ ወለወለው፤ በኃላ ኃይሉ ሄዶ የነሱ ሎሌ ሆነ፤ እና የማይገባን ነገር አለ። ጨቋኝ መሆን እስከፈለግን ድረስ ጭቆናን ማስወገድ አለብን። የጭቆና አስተሳሰብ በዜግነት ባለን እኩልነት መንፈስ ላይ ማፅናት አለብን’’

 ‘‘ውስጣችን ጨቋኝ የመሆን ጠንካራ ፍላጎት አለ። ሁላችንም ጨቋኝ መሆን እንፈልጋለን። ቢያጣ-ቢያጣ ባል ሚስቱን ይጨቁናል። ጨቋኝነትን ስለምንፈልግ በምትኩ ተጨቋኝ መሆንም እንችላለን። ጨቋኝ መሆን የሚቻለው በተጨቋኝነት መንገድ ላይ ነው። እሺ ብሎ፣ ሰግዶና አደግድጎ፣ ተልፈስፍሶ ይቆይና ሹመት ሲመጣ አንበሳ ነኝ ይላል። ይህ ጭቆና ተጨቋኝነት የተያያዙ ነገሮች ከመሆን አልፈው ባህላችን ሆኗል።’’

‘‘ከ30 እና 40 አመት በፊት እኔን ‘‘ይሄ ልጅ አስቸገረ’’ እባል ነበር። ዛሬ ደግሞ ‘‘ይሄ ሽማግሌ’’ እየተባልኩ ነው። ያኔ ከ40 አመት በፊት የነበሩ ሽማግሌዎች ልጆችን አልሰማ ብለው ለእነሱም ለሀገሪቱም የማይበጅ ሁኔታ ውስጥ ጥለውን ሄዱ። አሁን ደግሞ ያሉት ጨርሶ የሚነግራቸውም የለ። ዝግ ናቸው። ውስጥ እርስ በርሳቸው ብቻ እየተነጋገሩ ከውጪ የሚገባ ኀሳብ የለ፣ ሀሳባቸውን የሚያናፍስላቸው የለም። እና አሁን ቄስ የለ፣ ንስሃ አባት የለ፣ አባት የለ፣ ሽማግሌ የለ፣ የሚቆጣ የለ፣ ማን ምን ለማን ይናገር? ዝግ ነው’’

‘‘ወያኔ ነገሩ ገብቶት ነበር። ይሄ በፍጥነት የሰለጠነ ኃይል እንደማያኖረው አውቆት ስለነበር ገና እንደገባ በአንድ ጊዜ ቀጨው። አርባ መምህራንን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲያስወጣ ዩኒቨርሲቲው በወታደር ቋንቋ ‘‘ቁም’’ ከሚለው ባለፈ ወይም ‘‘ባለህበት ሂድ’’ ከሚባለውም አልፎ ‘‘ቀኝ ኋላ ዙር’’ ነው የሆነው። አሁን ያለው ዩኒቨርሲቲ አንድ ዩኒቨርሲቲ ሊኖረው የሚገባውን በነፃ ማሰብ፣ በነፃ መነጋገር፣ በነፃ መፃፍ፣ በነፃ መወያየት፣ በነፃ መደራጀት የሚባል ነገር የለውም’’ ብለዋል።

‘‘እስክንድር ነጋ ከአሜሪካ ኢትዮጵያ ከደረሰ ቀን ጀምሮ እንዲሁ ፍዳውን እንደበላ ነው። ከእስር ቤት ሲገባና ሲወጣ፣ እናቱ ፍዳዋን ስትበላ ባለቤቱ በያለበት እየዞረች ስታለቅስ ነው ያለችው። እስከዚህ ድረስ እስክንድር ምን አደረገ? በእርግጥ ይናገራል፣ የሚያምንበትን ይፅፋል፣ ይህ ትክክል አይደለም የሚል ሰው ካለ እንደሱ ንግግሩን በንግግር፣ ፅሁፉን በፅሁፍ መመከት ይችላል። ይህ ችሎታ የሌላቸው ሰዎች የሚቀናቸው ጉልበት ነው። ሀሳብን በሀሳብ መቋቋም የማይችሉ ሰዎች በጉልበት መጠቀም ይፈልጋሉ’’

በዘሪሁን ሙሉጌታ (ሰንደቅ ጋዜጣ)

አንጋፋው ኢትዮጵያዊ ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በቅርቡ 82ኛ አመት የልደት በአላቸውን አክብረዋል። ፕሮፌሰር መስፍን በዚህ ሁሉ ዘመናቸው ከአስር ያላነሱ ዘመን አይሽሬ መፃሕፍቶችና የተለያዩ የምርምር ፅሁፎችን አሳትመዋል። ፕሮፌሰሩ በቅርቡ በምስራቅ አፍሪካ ላይ ከሚያጠነጥነው መፃሕፋቸው በተጨማሪ በቀጣይም በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን መፅሐፍ በማዘጋጀት ላይ ናቸው።
አንጋፋው ምሁር በመፃሕፍት መልክ እያሳተሙ ከሚያመጡት ምሁራዊ ኀሳባቸው በተጨማሪ በየሳምንቱ በጋዜጣ ላይ አምደኛ በመሆን ተዝቆ የማያልቅ ኀሳባቸውን ለትውልዱ በማካፈል ላይ ይገኛሉ። ከዚህ ሁሉ ተግባራቸው በተጨማሪ በአንዳንድ መድረኮች ላይ ቀርበው በተወሰኑ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ይሰጣሉ። በሀገራችን የ82 አመት አዛውንት ቤት ተቀምጦ ታጧሪ በሚሆንበት ሁኔታ አንጋፋው ምሁር ግን ለትውልዱ በርካታ ቁም ነገሮችን ለማሳለፍ ከጊዜ ጋር ግብግብ የገጠሙ ይመስላሉ።
ባሳለፍነው እሁድ ሰኔ 24 ቀን 2004 ዓ.ም ሰማያዊ ፓርቲ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ተገኝተው ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ፕሮፌሰር መስፍን ሰፊውን ማብራሪያ የሰጡት ‘‘የኢትዮጵያ ወጣትና የወደፊት ኃላፊነት’’ በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ነበር።
በዕለቱም ወጣቱ በማንነት ቀውስ ውስጥ መዘፈቁ፣ ወጣቱ ከአካባቢው (ከዘውገኝነት) ባለፈ ሀገር የሌለው ይመስል የማንነት ቀውስ ውስጥ መግባቱን፣ ወጣቱ ነፃነት ማጣቱ፣ የኢኮኖሚ ጥገኛ መሆኑ፣ የታሪክ ትምህርት ባለመኖሩ፣ የሚቆምበት ማንነት ማጣቱና በኀሳብ መዋለሉ የትምህርት ተቋማት ወጣቱን በትምህርትና በኢትዮጵያዊ ማንነት ማነፅ ያለመቻላቸው ምስጢር፣ የአፄው ትውልድ፣ ያ ትውልድና አሁን ያለው ትውልድ ልዩነትና አንድነት ወዘተ በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የፕሮፌሰር መስፍንን ማብራሪያን ዘሪሁን ሙሉጌታ በሚከተለው መልኩ አደራጅቶታል።
* * *
ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም የዕለቱን ንግግራቸውን ጀምረው የነበሩት የአፄ ኃይለስላሴ ‘‘ሥህተት’’ን በማውሳት ነበር። በእርግጥ ‘‘በስህተት መጀመሬ እሳቸው [አፄ ኃይለስላሴ] ጥሩ ስራ አልሰሩም ማለቴ አይደለም። አንዱ ስህተታቸው እሳቸው ጥሩ ስራ ሰራሁ የሚሉት ነው’’ ብለዋል።
በፕሮፌሰር መስፍን እምነት የአፄው ስህተት ኢትዮጵያ ለማሰልጠን በስደት አውሮፓ ቆይተው እዛ ብዙ ነገር ከማየት ይጀምራል ብለዋል። ‘‘በዚህ ላይ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ደቁሳታለች። ኢጣሊያ የሰለጠነች በመሆኗ በጋዝ መርዝና በተለያዩ መሳሪያዎች ክፉኛ ደቁሳናለች። አዋርዳናለች፣ ተሸንፎና ተዋርዶ የማያውቅ ሕዝብ ውርደቱ ተሰምቶት ነበር። ክብሩም ተነክቶ ነበር። አፄውም ይሄ ስሜት ስለተሰማቸው ኢትዮጵያን ለማሰልጠን ከፍተኛ ፍላጐት ነበራቸው’’ ሲሉ አስታውሰዋል።
የአፄ ኃይለስላሴ ትውልድ በፕሮፌሰር አገላለፅ የአድዋ ድል ክብር ጀግንነት ልቡ ውስጥ ያለ ትውልድ ነው። ያ ትውልድ ክብርና ኩራት የነበረው ትውልድ ነበር። ነገር ግን ጣሊያን ተመልሶ አዋረደው። ይሄ ደግሞ በኃይል ማስቆጨቱን የጠቀሱት ፕሮፌሰር ቁጭት ስለተሰማቸው አፄ ኃይለስላሴ ከነፃነት በኋላ ሲመለሱ ለመሰልጠን ቸኩለው ነበር። በመቸኮላቸውም ትምህርት ቤቶች በማቋቋም ተማሪዎችን ካገኙበት እየሰበሰቡ አዳሪ እያደረጉ አስተማሩ ብለዋል።
አፄ ኃይለስላሴ ኢትዮጵያን በችኮላ በማሰልጠን ካላቸው ፍላጐት አንፃር አዳሪ ትምህርት ቤትና በውጪ ሀገር ተማሪዎችን ቢያሰለጥኑም ትምህርቱ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ምን አለ? ምን የወረስነው ነገር አለ? ካለፈው ትውልድ ምን የወረስው ነገር አለ? ብለው አልጠየቁም ብለዋል። ይሄንንም ይበልጥ ሲያብራሩ ‘‘ፈረንጅ አጠቃን። ስለዚህ ፈረንጅን የምናጠቃበትን ሙያ ቶሎ ቶሎ እንማር ብለው ፈረንጆችን ከያሉበት አስመጡ። ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ፣ ከካናዳ አስመጡ። በየተማሪ ቤቱ አስተማሪ አደረጉ (ዳይሬክተርም ሆኑ)፤ እና አስተማሩን፤ እኛም ተማርን የሰጡንን ሁሉ እየተቀበልን ተማርን። ሌላ ቀርቶ አማርኛ እነሱ አስተማሩን። እኔ በሃይስኩል አማርኛን ያስተማሩኝ ፈረንሳዊ ናቸው። እና የውርደቱ ደረጃ እዚህ ላይ ደርሶ ነበር። ይሄ ሁሉ ግን ቶሎ ለመሰልጠን ነበር። ይሄም አልበቃ ተብሎ ወደ ውጪ ተልከን ተማርን። ተምረን ስንመለስ እየተንከባከቡን ከአውሮፕላን ስንወርድ ትምህርት ሚኒስቴር ተቀብሎ እቴጌ ሆቴል ወስዶን እዛ ስራ እስክናገኝ ድረስ በልተን ጠጥተን አድረን፤ ስራ ሲገኝ ቀስብለን ቤት ተከራይተን እንወጣለን። ቤት ተከራይተን በምንወጣበት ጊዜ የቤት እቃ መግዣ ተብሎ 3ሺህ ብር መንግስት ያበድረናል። ይሄ ሁሉ ያንን ትውልድ ለማሰልጠንና ኢትዮጵያ የሰለጠነች ለማድረግ ነበር’’ ብለዋል።
‘‘እ.ኤ.አ በ1951 ዓ.ም ‘‘Life Megazine’’ የሚባል መፅሔት ‘‘ኢትዮጵያ አንድም ኢንጂነር የላትም’’ ብሎ ፅፎ ነበር’’ ሲሉ ያስታወሱት ፕሮፌሰር መስፍን በወቅቱ እሳቸውን ጨምሮ የጊዜው መንግስት ባለስልጣናትን በንዴት አሳርሮ ነበር ብለዋል። ይሄንንም ተከትሎ በርካታ ወጣቶች ፈረንጅ ሀገር ሄደው እንዲሰለጥኑ ከተደረገ በኋላ ብዙ ኢትዮጵያውያን ኢንጅነሮች ሆነው መጡ ሲሉ አስታውሰዋል። በዚያን ጊዜ በሁለተኛ ደረጃ ውጪ ተምረው የመጡት እነ ሀይሉ ሻውል ናቸው ብለዋል።
አሁን ደርሼ ስመለከተው የአፄ ኃይለስላሴ ‘‘ስህተት’’ ታይቶኛል ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን ሥህተቱ ምን እንደነበርም በሚከተለው መልኩ አብራርተውታል። ‘‘አፄ ኃይለስላሴ ቸኮሉ፣ ፈጠኑ፣ እነዛን ልጆች [እኔንም] ለማሰልጠን ቢያስቡም ኢትዮጵያዊ መሰረት አላስያዙንም። ሙሉ በሙሉ ፈረንጅ እንድንሆን አደረጉን። ፈረንጅ ሀገር ሄደን የፈረንጅን ነገር ሁሉ ተማርንና መጣን። ስንመጣ ሐበሻ-ሐበሻ ነበር። ኢትዮጵያም ኢትዮጵያ ነበረች። ምንም ፍንክች ብላ አልተለወጠችም። አስተዳደሩ ላይ ቁጭ ያሉት ሰዎች ‘‘የአድዋ ትውልድ ሰዎች’’ ናቸው። የአድዋ ትውልድ ስል ወያኔን ማለቴ አይደለም። በአድዋ ክብርና ድል ጊዜ የተወለዱትን ማለቴ ነው። እና ይሄ ትውልድ [የአፄ ኃይለስላሴ ትውልድ] እዛው ቁጭ ብሎ ጠበቀን። ያስብ የነበረውም እንደዛው እንደ አድዋው ጊዜ ነበር’’ ብለዋል።
በፕሮፌሰር መስፍን ማብራሪያ የአፄ ኃይለስላሴ ትውልድ ያስብ የነበረው ‘‘ጌታና አሽከር’’ን ነበር። የተማረውም ቢሆን የሰለጠነ አሽከር እንዲሆን ይፈለግ ስለነበር ተጨማሪ ስህተት መሰራቱንህ ያወሱት ፕሮፌሰር መስፍን በችኮላ ካስተማሩን በኋላ ተምረን ሲመጣ ‘‘አሽከር ሁኑ’’ አሉን በዚያን ጊዜ ትምህርት አሽከር ለመሆን አይደለም። በዚያን ጊዜ ትምህርት ‘‘በነፃነት መለወጥ’’ ማለት ነበር። እንኳን ፈረንጅ ሀገር የሄደው ቀርቶ ኢትዮጵያም ውስጥ የነበሩት በቀዳማዊ ኃይለስላሴ የነበሩት በሙሉ ነፃነት ነበር ያደጉት። በነፃነት እያሰቡ፣ በነፃነት እየፃፉ፣ በነፃነት እየተናገሩ በነፃነት እየጠየቁ ነበር ያደጉት ብለዋል።
ይሄ በነፃነት እየፃፈ፣ እየተናገረ፣ እየጠየቀ ያደገው ትውልድ፣ በዚህ ዘመን ባለው ትውልድ ‘‘ያ ትውልድ’’ የሚል መጠሪያ እንዳለው የጠቀሱት ፕሮፌሰር ‘‘ያ ትውልድ’’ በነፃነት አድጎና ተኮትኩቶ፣ ተንቀባሮ፣ አድጎ አሽከር መሆን ግን አቃተው ብለዋል።
‘‘አሽከርነት ብዙ ሰዎች ቃሉን እኔ የፈጠርኩት ይመስላቸዋል። በ1973 ዓመተምህረት ‘አዛዥ ሙሉሰው ምትኩ የሚባሉ ሰው የፃፉት መፅሐፍ በአጋጣሚ አንድ ሰው ሲያዞረው አገኘሁና በመቶ ብር ገዛሁት። በጣም ጠቃሚ መፅሐፍ ነው። መፅሐፉ ላይ ስም መጥቀስ ባያስፈልግም ‘እገሌ የልዑል አልጋ ወራሽ አሽከር፣ የራስ እገሌ አሽከር… የደጅ አዝማች አሽከር ወዘተ እያሉ ይጠቅሱ ነበር። እና የአሽከርነት ባህል ነበር። አሽከሮቹም አሽከር መሆናቸውን አይክዱም። አሁን አሁን መካድ መካካድ መጥቷል’’ ብለዋል።
እናም በአንድ ወቅት በአንድ መድረክ ላይ የአፄ ኃይለስላሴ ትውልድ ‘‘ የንጉሱ ሎሌዎች’’ ነበሩ በማለቴ የተናደዱ ነበሩ ሲሉ የሚያስታውሱት ፕሮፌሰር መስፍን ሀቁ ግን በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ሚኒስትሮቹ ሁሉ ሎሌዎች እንደነበሩ አስረድተዋል። እኔ ቃሉን ላሻሽለው ብዬ እንጂ ‘‘ባሪያም’’ ማለት እችል ነበር ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን። ይህንን አባባላቸውንም ሲያጠናክሩ ሚኒስትሮቹ በወቅቱ ለንጉሱ ደብዳቤ ሲፃፃፉ ‘‘ባሪያዎ’’ እያሉ እንደነበርም አስታውሰዋል። በመሆኑም የአፄ ኃይለስላሴው ትውልድ (የአድዋው ትውልድ)ም ሆነ ከዚያ በኋላ የመጣው ‘‘ያ ትውልድ’’ በሎሌነትና በዜግነት መካከል ያለውን ልዩነት አላወቁትም ብለዋል።
‘‘በሎሌነትና በዜግነት መካከል ምንም አይነት ልዩነት ሳይኖር በመቅረቱ ፋይዳችን ሁሉ ተደበላልቆ አርበኞቻችንን ገድለናል የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ ‘‘አርበኛውን የሚገድል ሕዝብ በሌላ ሀገር ያለ አይመስለኝም። ሀውልት ሊያቆምላቸው የሚባቸውን ሰዎች የሚገድል ሕዝብ በሌላ አለም ያለ አይመስለኝም ወይም አላውቅም፤ እኛ ግን ራስ አበበን ገድለናል። ራስ መስፍንን ገድለናል። በላይዘለቀን ገድለናል ማን ያልገደልነው አርበኛ አለ። ይሄንን የምጠቅሰው በዜግነትና በሎሌነት መካከል ያለውን ልዩነት በደንብ እንድንረዳ በማሰብ ነው። ትልቁ ነገር በዚህች ሀገር ታሪክ ዜግነት ሳይሆን ሎሌነት ነው። ፉከራውም እኔ ያንተ አሽከር፣ እኔ ያንተ ቡችላ ነው። ይህ ባህል ነው፤ በአንድ ትውልድ ቢኖርም ተላልፏል። አንዱ ትውልድ የሰራው ስህተት ሌላው ትውልድ ተረክቦ ያስተላልፈዋል። ሎሌነቱን ብቻ ሳይሆን ጌትነቱንም ጭምር ነው ‘‘ያ ትውልድ’’ የምትሉት ጌትነትን ለመረከብ ቢፈልግም፣ ሎሌነትን ግን እምቢ ብሎ ነበር፤ ነገር ግን ሎሌነትን እምቢ ብሎ ‘‘እኔ ጌታ ልሁን’’ አለ። ‘‘እኔ ልደቁስ’’ አለ። ነፃነቱን አበላሸው። ነፃነቱን ወደ ስድነት ለወጠው’’ ሲሉ አስረድተዋል።
የአፄ ኃይለስላሴ ትውልድ ‘‘ያ ትውልድ’’ን ማለትም ለፕሮፌሰር መስፍን ትውልድ ያሉበትን ትውልድ ለአሽከርነት ሲፈልገው፣ ‘‘ያ ትውልድ’’ ወይም በፕሮፌሰር መስፍን አገላለፅ የጠፋው ትውልድ በተራው ግራ የገባው ትውልድ ላይ መቆሙን ይህ ግራ የገባው ትውልድ በአብዛኛው የሞተ፣ የተሰደደ፣ የተገዳደለ፣ የተጫረሰና ከእሱ በኋላ የመጣውንም ትውልድ ያስጨረሰ ነው ብለውታል። አጫራሹም ተጫራሹም ሁለት ትውልድ የባከነ ትውልድ እንደሆነም ፕሮፌሰሩ በማብራሪያቸው ገልፀውታል።
አሁን ከ40 አመት በታች ያለው ትውልድ ‘‘ግራ የጋባው’’ ያሉት ፕሮፌሰር ‘‘የሚቆምበት የሌለው መሰረት ያጣ፣ ጫት ካልሆነ በቀር መሰረት የሌለው፣ መቆሚያ ያጣ ተንጠልጥሎ በአየር ላይ የሚውረገረግ ነው። የዚህ ትውልድ ልጆች ወዴት እንደሚሄዱም አይታወቅም። ወደፊት የሚመጡት ትውልዶች ከእሱ የተሻሉ ወይስ የባሱ? አይታወቅም’’ ሲሉ የዚህን ዘመን ትውልድ ገልፀውታል።
አፄ ኃይለስላሴ በዚህ ዘመን ‘‘ያ ትውልድ’’ የሚባለውን ወጣት እንደ አውሮፓ ለማድረግ ሞክረው አነሰም በዛም ‘‘ተማረ’’ የሚባል ሀይል ፈጥረው ማለፋቸውን የጠቀሱት ፕሮፌሰሩ ደርግ ሰክሮ ቢመጣም አፄው ያስተማሩትን ‘‘ተማረ’’ የተባለውን ኃይል ፈርቶት ተወው። ወያኔ ግን አልፈራውም ብለዋል።
‘‘ወያኔ ነገሩ ገብቶት ነበር። ይሄ በፍጥነት የሰለጠነ ኃይል እንደማያኖረው አውቆት ስለነበር ገና እንደገባ በአንድ ጊዜ ቀጨው። አርባ መምህራንን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲያስወጣ ዩኒቨርሲቲው በወታደር ቋንቋ ‘‘ቁም’’ ከሚለው ባለፈ ወይም ‘‘ባለህበት ሂድ’’ ከሚባለውም አልፎ ‘‘ቀኝ ኋላ ዙር’’ ነው የሆነው። አሁን ያለው ዩኒቨርሲቲ አንድ ዩኒቨርሲቲ ሊኖረው የሚገባውን በነፃ ማሰብ፣ በነፃ መነጋገር፣ በነፃ መፃፍ፣ በነፃ መወያየት፣ በነፃ መደራጀት የሚባል ነገር የለውም’’ ብለዋል።
ይሄንንም ገለፃቸውን በሚከተለው ማብራሪያ አስደግፈውታል። በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመን ሳንሱር ቢኖርም ዩኒቨርሲቲው አትሞ የሚያወጣው ነገር ግን ሳንሱር አልነበረበትም ብለዋል። ይሄም ዝም ብሎ ሳይሆን በትግልና በግጭት የመጣ እንደነበር አውስተው ዛሬ ግን በወያኔ ዘመን ሳንሱር ቢነሳም ወያኔ ግን ቂል አይደለም ብለዋል።
‘‘ወያኔ ሳንሱር በማንሳቱ ከአፄ ኃይለስላሴም ከደርግም ይሻላል። በአሁኑ ጊዜ ከምንጊዜውም በላይ ይፃፋል፣ ይታተማል፤ ይህ ባይካድም ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን እያየነው ነው። በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን ግን ዩኒቨርሲቲውን ሳንሱር አይነካውም። በዚህም ምክንያት ሕዝቡ ዩኒቨርሲቲውን ‘‘ቫቲካን’’ ብሎ ሰየመው። ጣሊያን ሀገር ውስጥ ቫቲካን ለብቻው እራሱን የቻለ ሀገር ሆኖ እንዳለው ሁሉ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ እንደ ቫቲካን የራሱን ነፃነት ነበረው’’ ሲሉ አስታውሰዋል።
ሌላው ታሪካችን ከጥንት ጀምሮ ያመጣብን ሌላ ችግር እንዳለም የጠቀሱት ፕሮፌሰር መስፍን ስልጣን ሁልጊዜ በጉልበት የሚገኝ መሆኑ ነው። በሀገረ-መንግስትነት (state) ኢትዮጵያ ብዙዎቹን የአውሮፓ አገሮች ትቀድማቸዋለች። ታላቋ ብሪታንያ ሀገር የተባለችው በ1707 አካባቢ ነው። ጀርመን ከ1815 እስከ 94 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ነው ሀገር የተባለችው። ኢጣሊያ በ1870 አካባቢ ነው ሀገረ-መንግስት የሆነችው። ፈረንሳይም በ18 መቶ ግድም ነው፤ ኢትዮጵያ በ525 ዓ.ም ሀገረ-መንግስት ከመሆን አልፋ ንጉስ ካሌብ የመንን የወረረበት ዘመን ነበር። እና ኢትዮጵያ ገና እንግሊዞች ሀገረ-መንግስት ለመሆን በሚፍጨረጨሩበት ጊዜ እኛ ግን ሀገረ-መንግስት ነበርን። እነሱ ‘‘ማግና ካርታ’’ የሚሉት በምዕራባውያን ለመጀመሪያው ጊዜ የመብት ጥያቄ ያነሱት እ.ኤ.አ በ1215 ዓ.ም ነበር። እኛ ኢትዮጵያውያን በ1215 ዓ.ም ግድም አቡነ ተክለሃይማኖት የዛጉዌን ስርወ መንግስት ወደ ሰሎሞን ስርወ-መንግስት የተለወጠበት ጊዜ ነበር። እኛ በዚያን ጊዜ የተደራጀን ሀገረ-መንግስት (state) ነበር። ሀገረ-መንግስት ማለት ደግሞ መሬት፣ ሕዝብና መንግስት በአንድ ላይ ያለው ማለት ነው። ይሁን እንጂ እነሱ (ምዕራባውያን) በ1215 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) በማግና ካርታ የሰዎችን መሰረታዊ መብት የሚጠይቁበት ጊዜ ነበር። ይህም ማንም ሰው ከሕግ ውጪ አይያዝም፣ አይታሰርም፣ አይገደለም፣ ንብረቱን አይቀማምም የሚሉትን መብቶች የዛሬ ስምንትና ዘጠኝ መቶ አመት ጠየቁ። ጥያቄውም ከትውልድ-ትውልድ አልፎ በ1215 የተጠየቀውን ጥያቄ እያነሱ እየጠየቁ፣ እየታገሉ ዛሬ ለደረሱበት የዲሞክራሲ ስርዓት ደርሰዋል። እኛ ግን የመብት ጥያቄ ማንሳት የጀመርነው መቼ ነው? ለምንድነው የዘገየነው? ጦርነት ተስማምቶን ነው? ጥቃትና ውርደት፣ ጭቆና ተስማምቶን ነው?’’ ሲሉ ጠይቀዋል። ለዚህ ጥያቄ ከእያንዳንዱ ሰው በተጨማሪ ትውልዱ እራሱን መጠየቅ አለበት ብለዋል።
በፕሮፌሰር መስፍን አገላለፅ አንድ ትውልድ በ40 አመት ክልል ውስጥ ያለ ትውልድ መሆኑን ጠቅሰው አሁንም በደርግና በወያኔ ጊዜ የተወለደው ዕድሜው ከ40 አመት በታች ያለው ትውልድ ለልጆቼ ምን አስተላልፋለሁ፣ ምን አወርሳለሁ ብሎ እራሱን መጠየቅ አለበት ብለዋል።
ይህ ትውልድ ለልጆቹ ምን አወርሳለሁ? ምን አስተላልፋለሁ ብሎ ሲያስብ አንድ ነገር ቁሞ ማሰብ እንዳለበትም ፕሮፌሰሩ ሳይጠቅሱ አላለፉም። ይኸውም የሳቸው ትውልድ የሆነው በተለምዶ ‘‘ያ ትውልድ’’ የሰራውን ስህተት እንዳይደግም መጠንቀቅ አለበት ብለዋል። ‘‘ያ ትውልድ’’ ሎሌነቱና አሽከርነቱን አልፈልግም ቢልም ‘‘ጌታ ልሁን’’ ብሎ ግን ስህተት ሰርቷል። ‘‘ጌታ ልሁን’’ ማለት በሌላ አነጋገር ‘‘ሎሌ ይኑረኝ’’ ማለት ነው። ስለዚህ ይህ ትውልድ ይህንን ስህተት መድገም የለበትም። ማለት ያለበት እኩል እንሁን፣ ዜጎች እንሁን፣ እኩዮች በመሆን ስልጣንን እንግራው ማለት አለበት። ስልጣን በስርዓት የሚገኝ እንጂ በጉልበት የሚገኝ እንዳይሆን ማድረግ አለበት። ስልጣን የጌቶች መብት እና ይዞታ ሳይሆን የሕዝብ መብት ብሎ አምኖ ማሳመን አለበት ብለዋል። ይህ ትውልድ ይህንን ካደረገ ነፃ ይወጣል ብለዋል።
ፕሮፌሰር ይህ የአሁኑ ትውልድ ብዙ የሚፈረድበት አለመሆኑን በሰፊው አብራርተዋል። መሠረት አጥቶ ገበታ ላይ እንዳለ ቅጠል የሚዋልል መሆኑን ጠቅሰዋል። ትውልዱ ዋለለ ማለት ሀገርም እንደሚዋልል ገልፀዋል። ይህ የአሁኑ ትውልድ ለራሱ ኑሮ ኃላፊነት መውሰድ አለበት ብለዋል። ይህ የዘመናችን ትውልድ ለራሱ ኃላፊነት የማይወስድ በመሆኑ እናት አባቱ ቤት የሚኖር ተጧሪ ትውልድ ነው ብለዋል። አንድ ሰው እራሱን ቻለ ማለት በደካማዎች ወላጆቹ ላይ ጥገኛ ሆኖ መኖር አይደለም ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን ቆሎ የሚሸጡ እናቶች ልጆቻቸውን ከመቀለብ አልፈው ጫት መግዣ እንደሚከጅሏቸው ነው የገለፁት። እናም ይህ ትውልድ ይህንን መቀየር ኃላፊነት አለበት ብለዋል።
የሀገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች በተመለከተ ዩኒቨርሲቲ አይደሉም ያሉት ፕሮፌሰር፤ ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ፕሮፌሰሮችና ዶክተሮች ቢኖሩም እነሱም ከጫት እና ከድራፍት (በድሮ ጠጅ ቤት አይነት) ከዚያ አይለዩም ብለዋቸዋል። ፕሮፌሰሮቹም ሆነ ዶክተሮቹ አይናገሩም አይፅፉም ሲሉ ወቅሰዋል። ድሮ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተለያዩ ጉዳዮች ውይይትና ክርክር እንደነበር አስታወሰዋል። አሁን ግን በዩኒቨርሲቲ ውስጥ አፍ፣ ጆሮ እና አይን ተከልሏል ብለዋል። በአሁኑ ጊዜ የዩኒቨርሲቲዎች ድምፅ አይሰማም ብለዋል። ይህንንም ትውልዱ መቀየር እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ሌላው የዚህ ትውልድ ችግር አያነብም ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን ጋዜጠኞችም ሳይቀሩ አያነቡም ሲሉ ወቅሰዋል።
ፕሮፌሰር መስፍን የዚህን ዘመን ትውልድ ፈተናም የሚያጠናክረው ውሸት የነገሰበት ዘመን መሆኑ፣ ወንጀል በአዋጅ የሚወጣበት ዘመን በመሆኑ ነው ብለዋል። በተለይ ሀሳብን በመግለፅ ‘‘ሽብርተኝነት’’ እየተባለ መሆኑንም አስገንዝበዋል። የዚህ ሁሉ ምንጭ የ‘‘ያ ትውልድ’’ ርዝራዥ ውጤት መሆኑንም አስረድተዋል። ደርግም ቢሆን የ‘‘ያ ትውልድ’’ ርዝራዥ፣ ወያኔም እንዲሁ ያሉት ፕሮፌሰር እስርቤትም የዚያ ትውልድ ርዝራዦች አሉ ብለዋል። የ‘‘ያ ትውልድ’’ ርዝራዥ በፈጠረው ችግር የዚህ ዘመን ትውልድ በርካታ ችግሮች ውስጥ መዘፈቁን የጠቀሱት ፕሮፌሰር መስፍን እስክንድር ነጋን በምሳሌነት አንስተዋል።
‘‘እስክንድር ነጋ ከአሜሪካ ኢትዮጵያ ከደረሰ ቀን ጀምሮ እንዲሁ ፍዳውን እንደበላ ነው። ከእስር ቤት ሲገባና ሲወጣ፣ እናቱ ፍዳዋን ስትበላ ባለቤቱ በያለበት እየዞረች ስታለቅስ ነው ያለችው። እስከዚህ ድረስ እስክንድር ምን አደረገ? በእርግጥ ይናገራል፣ የሚያምንበትን ይፅፋል፣ ይህ ትክክል አይደለም የሚል ሰው ካለ እንደሱ ንግግሩን በንግግር፣ ፅሁፉን በፅሁፍ መመከት ይችላል። ይህ ችሎታ የሌላቸው ሰዎች የሚቀናቸው ጉልበት ነው። ሀሳብን በሀሳብ መቋቋም የማይችሉ ሰዎች በጉልበት መጠቀም ይፈልጋሉ’’ ብለዋል።
ይህ ትውልድ ይበልጥ ግራ እንዲጋባ ያደረገው በሀገሩ ሰው መጥፋቱ እንደሆነም ፕሮፌሰሩ ሳይገልፁ አላለፉም።
‘‘ከ30 እና 40 አመት በፊት እኔን ‘‘ይሄ ልጅ አስቸገረ’’ እባል ነበር። ዛሬ ደግሞ ‘‘ይሄ ሽማግሌ’’ እየተባልኩ ነው። ያኔ ከ40 አመት በፊት የነበሩ ሽማግሌዎች ልጆችን አልሰማ ብለው ለእነሱም ለሀገሪቱም የማይበጅ ሁኔታ ውስጥ ጥለውን ሄዱ። አሁን ደግሞ ያሉት ጨርሶ የሚነግራቸውም የለ። ዝግ ናቸው። ውስጥ እርስ በርሳቸው ብቻ እየተነጋገሩ ከውጪ የሚገባ ኀሳብ የለ፣ ሀሳባቸውን የሚያናፍስላቸው የለም። እና አሁን ቄስ የለ፣ ንስሃ አባት የለ፣ አባት የለ፣ ሽማግሌ የለ፣ የሚቆጣ የለ፣ ማን ምን ለማን ይናገር? ዝግ ነው’’ ሲሉ አሁን ያለውን ሁኔታ ገልፀውታል።
ትውልድ ከትውልድ እየተሻሻለ አለመሄዱ ዛሬ ላለንበት ችግር መዳረጉን የጠቀሱት ፕሮፌሰር መስፍን የትውልድ ዱላ ቅብብሉ ‘‘እንዘጭ… እንቦጭ…’’ አይነት ነው ብለውታል። ለዚህም እንደማሳያ ዘመነ መሳፍንትን ጠቅሰዋል።
‘‘ዘመነ-መሳፍንት ብዙ የአውሮፓ አገሮች ጠይቀውት የነበረ፣ ከፈረንሳይ አብዮት ጋር ሊወዳደር የሚችል ፖለቲካዊ ክስተት ነው። በወቅቱ መሳፍንቶቹ ተሰብስበው ከአሁን ወዲያ ማንም በነገሰና ዘውድ በደፋ ቁጥር አይግዛን፣ በየቦታችን ወይም በየቤታችን እኛው ገዢዎች ሆነን ቁጭ እንበል አሉ። ይህ በጣም ግሩም የሆነ ሪፐብሊካኒዝም መንፈስ የነበረበት ነው። ነገር ግን ቴዎድሮስ መጣና የእነሱን መንፈስ ጉዳዩ ውስጥ ሳያስገባ እነሱን ድምጥማጣቸውን አጠፋና ያው ድሮ የነበረውን ነገር ጀመረ። ከዚያ በኋላም ደርግ አፄ ኃይለስላሴን አውርዶ መንግስቱ ኃይለማርያም ተካ። መንግስቱ ዘውድ ቢደፋ ማን ይከለክለው ነበር? አሁንም ያለው ልክ እንደዛው ነው። እና በትውልድ ሂደት ውስጥ ምን ተማርን? ሕዝቡስ ገዢዎቹ እንዲማሩ አያስገድዳቸውም’’ ሲሉ ጠይቀዋል።
ለዚህ ሁሉ ምክንያቱ የማኀበረሰባችን የጭቆና ባህል መንሰራፋቱን በአብይ ምክንያትነት ፕሮፌሰሩ አንስተዋል። ‘‘ውስጣችን ጨቋኝ የመሆን ጠንካራ ፍላጎት አለ። ሁላችንም ጨቋኝ መሆን እንፈልጋለን። ቢያጣ-ቢያጣ ባል ሚስቱን ይጨቁናል። ጨቋኝነትን ስለምንፈልግ በምትኩ ተጨቋኝ መሆንም እንችላለን። ጨቋኝ መሆን የሚቻለው በተጨቋኝነት መንገድ ላይ ነው። እሺ ብሎ፣ ሰግዶና አደግድጎ፣ ተልፈስፍሶ ይቆይና ሹመት ሲመጣ አንበሳ ነኝ ይላል። ይህ ጭቆና ተጨቋኝነት የተያያዙ ነገሮች ከመሆን አልፈው ባህላችን ሆኗል።’’ ብለዋል። ይሄንንም ተጨባጭ ባሉት ማስረጃ ሲያቀርቡ በአንድ ወቅት በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት አንድ ሚኒስትራቸውን ተናደው በጥፊ ሲሏቸው ሚኒስትሩ በበኩላቸው ወጣ ሲሉ ያገኙትን የቅርብ ረዳታቸውን በጥፊ አሉ። ይህ ጥፊ እያለ-እያለ ወጥቤት ድረስ ዘለቀ ብለዋል። እናም ኢትዮጵያውያን አንጠይቅም፣ እምቢ አንልም፣ የተማረውም ቢሆን ሲጨቆን ዝም ይላል’’ ካሉ በኋላ ሌላ አስገራሚ ተጨባጭ ምሳሌ አከሉበት።
‘‘ሀይሉ አርአያ (ዶ/ር) አንድ የደርግ ካድሬ ላይ ከኋላ ሆኖ መንገድ ልቀቅልኝ ብሎ የመኪና ጡሩምባ ነፋበት፤ ያ የደርግ ካድሬ መኪናውን እንዳቆመ መጥቶ በጥፊ ወለወለው፤ በኃላ ኃይሉ ሄዶ የነሱ ሎሌ ሆነ፤ እና የማይገባን ነገር አለ። ጨቋኝ መሆን እስከፈለግን ድረስ ጭቆናን ማስወገድ አለብን። የጭቆና አስተሳሰብ በዜግነት ባለን እኩልነት መንፈስ ላይ ማፅናት አለብን’’ ሲሉ መክረዋል።
በአጠቃላይ የዚህ ዘመን ትውልድ ያለፉ ትውልዶች የወረሳቸውን ችግሮች ላለመድገምና ቀጣይ ለሚመጣው ትውልድ በቆራጥነት መታገል ተገቢ እንደሆነ ጠቅሰዋል። በዕለቱ የተገኙ ወጣቶች በፕሮፌሰር መስፍን ገለፃ ጋር በተያያዘ በርካታ ጥያቄዎችን አንስተዋል፤ በተለይ ከማንነት መቃወስ ጋር የተያያዙ፣ ሀገሪቱ ከምትከተለው የፖለቲካ አካሄድ አንፃር ባሉ ጉዳዮች ውይይት ተደርጓል።
ይህ ትውልድ ጨለምተኛ ከመሆን ባለፈ ተስፋ ሰጪ ዕድሎች እንዳሉትም ተጠቅሷል። ፕሮፌሰር መስፍንም ይህ ትውልድ በኃላፊነትና በኢትዮጵያ ጨዋነት ከተንቀሳቀሰ ከትውልድ ትውልድ ሲንከባለሉ የመጡ መሠረታዊ ችግሮችን መፍታት እንደሚችል ገልፀዋል። ለዚህ ግን በርትቶና ጠንክሮ በቆራጥነት መታገል ተገቢ መሆኑን አስምረውበታል።

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0
Read previous post:
በሊባኖስ መሬት ለመሬት የተጎተተችው ኢትዮጵያዊት አስከሬን አዲስ አበባ ገባ

በሊባኖስ መሬት ለመሬት የተጎተተችው ኢትዮጵያዊት አስከሬን አዲስ አበባ ገባhttp://www.ethiopianreporter.com/news.html

Close