“ዳጎማ ” ከሞት ጋር ግብግብ

ሊቢያን መሸጋገሪያ ለማድረግ ወስነው ያልተሳካላቸው በኮንቴነር በረሃ ውስጥ መታሰራቸው የተለመደ ነው። የዚሁ ክፉ ጽዋ ገፈት ቀማሽ ስለ ኮንቴነር አስርና በውስጡ ስላለው የሚያነፍር ሙቀት ሲተርክ እውነት አይመስልም። ከታች የተቃጠለው ምድር፣ ከላይ እንደ እሳት የሚፋጀው ነበልባል ፣ እንደ ረመጥ የሚለበልበውና እንደጅራፍ በሚጋረፈው አጥበርባሪው ወላፈን ከያቅጣጫው የሚለበልበው ኮንቴነር በውስጡ ከታጎሩት ሰዎች ትንፋሽ ጋር ተዳምሮ የነብስ ውጪ ግቢ ግብ ግብ፤ ለሚሰማው የሚጨንቀው የላሜራ ቤት ወበቅ ስንቶችን ለዘላለሙ እንደወሰዳቸው ቤት በረሃው ይቁጠረው።…… ታሪኩ ብዙ ነው።

የተለመደው ትንፋሽ እየተመናመነ፣ ሃይል እየከዳ፣ ነብስ መወጠር ስትጀምር የነበሩበትን ኮንቴነር በመቀጥቀጥ የርዳታ ድምጽ ለማሰማት ታገሉ። በቻሉት ሁሉ የጣር ድምጽ አሰሙ። በተቆለፈባቸው ኮንቴነር ውስጥ ዓለም ቁና ሆነችባቸው። ህይወትን ለማለምለም፣ ከጉስቁልና ሽሽት የጀመሩትን የሲኦል ጉዞ  ታግለው፣ ታግለው… ጸጥ አሉ። ድምጽ ቆመ። የተበጠሱ፣ ሊበተሱ ደረሱ፣ የሰለሉ፣ የቀዘቀዙ ወገኖቻችን!!

ይህ አሳዛኝ፣ አንገብጋቢና ልብ የሚያስደቃ ዜና በወገኖቻችን ላይ የደረሰ አሰቃቂ ሃዘን ነው። በተለምዶ ኢቲቪ የምንለው “ልማታዊው” የ “ውድ” አገራችን ብቸኛው የስዕል የመረጃ መስኮት ሰኔ 26 ቀን 2002 ዓ.ም ባሰማው ዜና የወገኖቻችንን ህልፈት ሲናገር ሃዘኑ መሪር ነበር።

ኢቲቪ ለስራ ፈጠራ ከተመደበው አንድ ቢሊዮን ብር 680 ሚሊዮን ብር ብቻ ስራ ላይ መዋሉን በመጥቀስ ዜናውን “ ስደቱ የጥጋብ አይነት” ነው ወደሚል ንጽጽር መግባቱ ባይወደድም የስደቱ ምክንያት ለተሻለ ኑሮ፣ ስራ ፍለጋ፣ ስርቶ ለመቀየር መሆኑን አልሸሸገም። እንደውም ቢቢሲ በወቅቱ የታንዛንያን ምክትል የኢሚግሬሽን ሚኒስትር ጠቅሶ በወቅቱ ከዘገበው በላይ ዜናውን ደንቁሎ አስለቅሶናል።

ኬኒያ ናሮቢ ከደረሱ በሁዋላ ወደ ታንዛንያ አቅንተው በማላዊ በመሻገር የማንዴላን አገር መዳረሳ ለማድረግ ወስነው በከባድ  የጭነት ተሽከርካሪ ኮንቴነር ውስጥ የተሳፈሩት ወገኖች 127 ነበሩ። ወደ ማላዊ ለማቅናት ከታንዛንያ ተነስተው ሲከንፉ አየር አተራቸው። እንደተቆለፈባቸው ንዳዱ በርክቶ የራሳቸው ላብ እንደ ዝናብ ውሃ ያርሳቸው ገባ። ኮንቴነሩ አየር አነሰው። ቀስበቀስ ጣር ተከተለ። ላሜራውን እየደበደቡ አሽከርካሪው እንዲያቆም ቢማጸኑም ሰሚ አጡ። ቀስ በቀስ እየተዳከሙ ዛሉ። ያልቻሉም ነብሳቸው እየተበተሰች አረፉ። የተቀሩትም ጣር ጣላቸው። ሁሉም ነገር እርጭ አለ። ሾፌር ይህን ጊዜ መኪናውን አቁሞ ሁሉንም ጫካ ውስጥ በመዘርገፍ ተሰወረ። አስከፊው ስደት ዳጎማ ላይ ተደመደመ። ተስፋና ምኞት እዛው ተቀበሩ።

እንደመረጃው ከሃድያና ጠንባሮ እድሜያቸው ከ17- 32 የሚደርሱ ወጣቶችና ታዳጊዎች ከሰላሳ እስከ 35 ሺህ ብር በመክፈል ለተሻለ አማራጭና ራሳቸው ጠንቅቀው ለሚያውቁት ምክንያት ለመሰደድ የወጡት 127 ነበሩ። ከነዚሁ የከፋቸው ወገኖቻችን ሙቀት አንፍሯቸው ጫካ የተገኙት በሚያሳዝን መልኩ 43 ህይወታቸው አልፎ፣ 84 ደግሞ በጣር ውስጥ ሆነው ነበር።

ከሳምንት በፊት ማላዊ ሃይቅ የሰመጡትን ወገኖቻችንን ሳንረሳ በታንዛኒያ ምድር የቀሩትን የ “ ድህነትና የራሳቸው ” አመለካከት ሰለባዎች ዜና ተከተለልን። አኒህ ወገኖቻችን ከደቡብ ክልል ሃድያና ጥንባሮ ብቻ መሆናቸው፣ የአካባቢው አብዛኛ ተወላጆች በተለይ ለስደት የሚደረጉበት ጉዳይ አነጋጋሪ ቢሆንም አሟሟታቸው መክፋቱ ከሁሉም በላይ ልብ የሚሰብር ሆኗል።

መተዛዘን የራቀው ያገራችን ፖለቲካና፣ የባለስልጣናት ከወገኖቻቸው ችግርና ጉዳት  ይልቅ ለንዋይ ቅድሚያ መስጠታቸው ስደቱንና ድህነቱን እያባባሰው፣ ከተለያዩ አገራት የስደት ምድር የሚሰሙት የሀዝን ዓይነቶች  ተስፋ የሚያመነምኑ ሆነዋል።

በታናዛንያ ቆንስላና ኮንስቲወንስ ጉዳይ ሃላፊ አቶ መለስ ዓለም “ አካባቢው በረሃ በመሆኑ አስከሬናቸው ወዲያውኑ ጠረኑን በመቀየሩ የሰለባዎቹን አስከሬን ወደ አገር ቤት ማምጣት አልተቻለም ’’ ሲሉ በስፍራው ለተገኘችው የኢቲቪ ዘጋቢ ተናግረዋል። 22 ሞንጎ፣ 21 ዳጎማ መቀበራቸውን ያመለከቱት ሃላፊው “ ተግባሩ የኢትዮጵያንና የታንዛንያን ግንኙነት የሚያጠናክር ” ሲሉ አወድሰውታል። ፊታቸውን በሃዘን ከስክሰው የወገኖቻችንን ታንዛንያ መቀበር የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ማዋደጃ እንደሚሆን መናገራቸው ፖለቲካውን እንደቀድሞ ኮሚኒስቶች “ ሁሉንም ጉዳይ ከምትከተለው ርዕዮተ ዓለም ጋር አገናኘው” ዓይነት አስመስሎባቸዋል። አንድ ዜናውን የሰማ ስደተኛ በስደተኞች ሞት ብዛት ወዳጅነት የሚመሰረት ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያዊያን በሳዑዲ፣ በየመን፣ በኤርትራ…. ከወዳጅነት አልፎ የፓርላማና ወንበር ለማግኘት በተወዳደሩ ነበር በማለት አሽሟጧል።

ዜናው በስተመጨረሻ መንግስት ለስራ ፈጣሪዎች በብድር የሚሰት አንድ ቢሊዮን መድቦ እንደነበር አውስቶ፣ ከተመደበው ገንዘብ ውስጥ 680 ሚሊዮን ብር ብቻ ጥቅም ላይ ሲውል የተቀረው ተመላሽ እንደሆነ አስታውቋል። ዜናው እነዚህ ወገኖች ህይወታቸው ያለፈው ይህንን ስራ ላይ ያልዋለ ገንዘብ መጠቀም ይችሉ ነበር ለማለት አስቦ መሆኑ አስገራሚ ሆኗል። በህይወት የተረፉት አገር ቤት እንደሚመለሱም አመልክቷል።

ከሃድያ ዞን ደቡብ አፍሪካ ዋንጫ ትመለከታላችሁ ተብለው በህጋዊ ባንክና በህጋዊ ቢሮ ገንዘባቸውን የተዘረፉት በርካታ ወጣቶች ሰርተን እንከፍላለን በሚል በአራጣ ብድርና ከብቶቻቸውን በመሸጥ ገንዘብባቸውን በወጋገን ባንክ በኩል አስገብተው መበላታቸው ይታወሳል። የቀስቀሳ ስራው ሲሰራ ኢቲቪ የተሳተፈ ሲሆን ከፍተኛ ባለስልታናትም ለድርጊቱ ሽፋን በመስጠት ተሳታፊ እንደነበሩበት ተደርጎ ዝርፊያው መከናወኑ በወቅቱ መዘገቡ አይዘነጋም። ቀደም ሲልም መርከብ ላይ ስራ እናስቀጥራለን በሚል በተሰራ ድራማ ለምርመራ፣ ለፎቶ ግራፍና ለመመዝገቢያ በሚል በጠራራ ጸሃይ ዝርፊያ መፈጸሙ አይዘነጋም። ዝርፊያው ሲከናወን ዋና ተዋናይ የነበሩት ዶክተር መታሰርና መጠየቅ ሲገባቸው ይባስ ተብሎ አምባሳደር ተደርገው መሾማቸው አይዘነጋም። በዚህ ሁሉ ዝርፊያ ዋንኛ ሰለባ ሚሆኑት የአንድ አካባቢ ሰዎች መሆናቸው ጥያቄ ያስነሳል። ምላሽም ይፈልጋል። ለማንኛውም ነብስ ይማር!!

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *