ከጎሣ ልዩነት ወደሃይማኖት ልዩነት? ያዋጣል?

ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያም የካቲት 2004 ፍትሕ ጋዜጣ

ከዓመታት በፊት አንድ ጊዜ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ከፍተኛ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገው ነበር፤ አብዛኛዎቹ ተሳታፊዎች ይዘውት የነበረው መፈክር፡ ‹‹እስልምና በቋንቋ ወይም በጎሣ አይከፋፈልም!›› የሚል ነበር፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በአንዋር መስጊድ ውስጥ ብዙ ሰዎች ተገደሉ፣ ያንን አልፈን ወደሌላ ምዕራፍ የተሸጋገርን መስሎኝ ነበር፤ ነገር ግን አዲስ ክስተት እይተፈጠረ ይመስላል፤n ሰሞኑን በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች መሀል ወይም በእነሱ ላይ አዲስና አንዳንዶቹ የማይቀበሉት  ጥቃት የተፈጸመባቸው ይመስላል፤ በጋዜጦች ላይ አንዳንድ ስሞታዎችን በተደጋጋሚ አንብቤአለሁ፤ በሚወጡትና እኔ ባየኋቸው ጽሑፎች የተጣራና  ግልጽ የሆነ ነገር ባለማግኘቴ ወደኢንተርኔት ገብቼ ‹‹አህባሽ›› ስለተባለው የእስልምና ዓይነት ለማወቅ ሞክሬ ያገኘሁት፡–

•  ምንጩ አንድ አብዱላ አልሀራዊ የሚባል ኢትዮጵያዊ ሙስሊም መሆኑን፣

•  የተጀመረውም በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን   መሆኑን፣

•  በሊባኖስ ውስጥ መስፋፋቱን፣

•  በጣም ሰላማዊና ከሁሉም ጋር የመቀራረብ  ዝንባሌ ያለው መሆኑን፤  ለመረዳት ቻልሁ፤

ሃይማኖት ጥሩ ነው፤ መጥፎ ነው ባይባልም አህባሽ የተሰኘው የእስልምና ዓይነት የሚቃወሙትን ሰዎች ያስጠላቸው ምን እንደሆነ በትክክል አልገባኝም፤ ‹‹የእኛ አይደለም፤ አናውቀውም፤›› በማለት ብቻ ከሆነ አንድ ነገር  ነው፤ ‹‹ከተለመደው እምነታችን ያፈነገጠና ስሕተት ያለበት ነው፤›› ማለት ሌላ ነገር ነው፤ በተቃዋሚዎቹም ሆነ በደጋፊዎቹ በኩል ያለውን መሠረታዊ ጉዳይ ለማወቅ አልተቻለም፤ ግራም  ነፈሰ ቀኝ አንድ እምነትን በጉልበት በሌላው ላይ  መጫን ሕጋዊም አይደለም፤ ልክም አይደለም፡፡ በጋዜጦች ላይ የሚነበበው ደግሞ–

• አውልያ በሚባሉ የእስልምና የግል ትምህርት  ቤቶች ውስጥ የሚያስተምሩትን መምህራን  አስወጥተው በሌሎች መተካታቸውን፤

• የትምህርት ቤቱ ቤተ መጽሐፍት መዘጋቱን፣

• በዚያ አካባቢ ያሉት የመስጊድ አለቃ  መሻራቸውን፣

• የአስተማሪዎቹም ሆነ የአለቃው መነሳት  በደብዳቤ የተገለጸ መሆኑን ነው፡፡

ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ባለሥልጣኖቹ ስሕተታቸውን ተገንዝበውም ይሁን፣ ተቆጪ መጥቶባቸው፣ ለጊዜው ለማፈግፈግ ይሁን ለዘለቄታው በሃይማኖት ትምህርት ቤቱ አመራር  ውስጥ እጃቸውን ላለማስገባት ወስነው እንደሆነ የታወቀ ነገር ባይኖርም፣ የወጡት አስተማሪዎቹ ተመልሰው የማስተማር ተግባራቸውን እንዲጀምሩና  የመስጊዱ አለቃም እንዲሁ የቀድሞ ሥራቸውን  እንዲቀጥሉ ተፈቅዶአል ይባላል፤ ሆኖም  አስተማሪዎቹ እና አለቃው በደብዳቤ ተሰናብተው  በቃል እንዲመለሱ መታሰቡ ተቀባይነትን አላገኘም። እዚህ ላይ ቆም ብለን ሁለት ጥያቄዎችን  እናንሣ፡- የትምህርት ቤቱ ባለቤት ማን ነው?  ለሠራተኞቹ ሁሉ ደመወዝ የሚከፍል ማን ነው?

የእነዚህ ጥያቄዎች መልሶች የትምህርት ቤቱን  ሕጋዊ ባለመብት ለማወቅ ያስችሉናል፤ ይህንን

እንያዝ፡፡

የትምህርት ቤቱ ባለቤት ተማሪዎቹ  የተወሰነ የእስልምና ዓይነት ብቻ እንዲማሩ የሚያስገድድ ውለታ አለበት ወይ? ለምሳሌ  በክርስትና ቢሆን የካቶሊክ ሚስዮን ትምህርት

ቤት የካቶሊክ ክርስትናን ብቻ የማስተማር ግዴታ እንዳለበት፤ ሌሎችም እንደዚሁ፤ ይህንንም እንያዝ።

ተማሪዎቹ የሚማሩትን የእስልምና  (ወይም የማናቸውንም ሃይማኖት) ዓይነት የሚወስነው ማነው? ወላጆች ናቸው? ተማሪዎች  ናቸው? አስተማሪዎች ናቸው? የትምህርት ቤቱ ባለቤት ነው? ለትምህርት ቤቱ ገንዘብ ያዋጣ ሁሉ ነው? መንግሥት ነው? ወይስ ሁሉም ናቸው? ወደፍሬ ነገሩ ስንገባ መጽሐፍት ቤቱን  የዘጋው፣ አስተማሪዎቹን ያስወጣው፣ የመስጊዱን

አለቃ ያስወጣው፣ ማን ነው? የየትኛው መሥሪያ ቤት ነው? ምን ሕጋዊ ሥልጣን አለው?

ለአስተማሪዎቹ የተጸፈላቸው ደብዳቤ ምን ይላል?   የሕገ መንግስቱ አንቀጽ ፳፯ የሚከተለውን ይላል፡-

‹‹ማንኛውም ሰው የማሰብ፣ የሕሊናና  የሃይማኖት ነፃነት አለው፡፡ ይህ መብት ማንኛውም

ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም የመቀበል፣ ሃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም  በግል የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣  የማስተማር ወይም የመግለጽ መብትን ያካትታል።›› በሕገ አራዊት የሚመካ ወይም በመሃይምነት  የተጋረደ ሳይሆን በሕገ መንግሥቱ መሰረት የሚሰራ ባለሥልጣንም ሆነ መሳሪያ ቤት ከሆነ  በጋዜጦች ላይ የሚሰማው ሮሮ ለምን ይከሰታል?

ከላይ የተጠቀሰው አንቀጽ 27 (1)፣ አንቀጽ 27 (5) በተከታታይ የሃይማኖትንና የእምነትን ነፃነት ያረጋግጣሉ፤ ስለዚህም በአውልያ ትምህርት ቤት ላይ የተፈጸመው ጣልቃ-ገብነት በቀጥታ ሕገ መንግስቱን የሚቃረን የሕገ አራዊት ሥራ ነው፡፡

ይህ ሕገ-ወጥ እርምጃ ሲወሰድ ፖሊስና ዓቃቤ-ሕግ የት ገብተዋል?

በተማሪ ቤቱም ላይ የሚነሡ ጥያቄዎች ይኖራሉ አህባሽ የሚባለውን የእስልምና ዓይነት በፈቃዳቸው የሚከተሉ ሰዎች ከሌሎች  የእስልምና ተከታዮች ጋር በሃይማቱም ሕግ፣  በሕገ መንግስቱም እኩል መብቶች እንዳላቸው  የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪዎች አምነው ይቀበላሉ  ወይ? ለራሱ መብቶች ሽንጡን ገትሮ የሚከራከር  ሰው የሌሎችንም ሰዎች መብቶች ተቃዋሚዎችም  ቢሆኑም እንኳን እንዳያጓድሉ የበለጠ ጥንቃቄ  መውሰድ ያስፈልገዋል፤ ይህንን የሚያሰኘኝ የአህባሺ  አማኞች ጭራሽ ድምጻቸው የማይሰማ መሆኑ  ነው፤ ባለመኖራቸው ነው ወይስ በኃይል ተዳፍነው  ነው? መብት ሁልጊዜም የሚመጣው ግዴታን አዝሎ ነው፤ በሌሎች ሙስሊሞች እና በአህባሽ መሀከል ያለው ልዩነት ትልቅ ከሆነ ለአህባሺዎቹ ሌላ ትምህርት ቤት የሚሰራበትን ዘዴ ማፈላለጉ  ከጠቡ ሳይሻል አይቀርም፤ የበለጠ በማውቀው በክርስትና ሃይማኖት ውስጥ በልዩነት ለየብቻቸው የቆሙትን የካቶሊክ፣ የፕሮቴስታንትና የኦርቶዶክስ  ቤተ ክርስቲያኖችን ብንወስድ የአንዱ መምህር  በሌላው ቤተ ክርስቲያን ገብቶ እንዲያስተምር አይፈቀድለትም፤ ወይም የኦርቶዶክሱን መምህር በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ እንዲያስተምር አይፈቀድለትም፤ ወይም የኦርቶዶክሱ መምህር በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እንዲያስተምር ማስገደድ ከሕገ አራዊት በቀር ከሁሉም ዓይነት ሕጎች የወጣ አሠራር ነው፤ በእስልምናም ውስጥ በካቶሊክና በኦርቶዶክስ መሀከል አለ የሚባለውን ያህል ልዩነት ከአለ ለየብቻ ማስተማሩ የሚመረጥ ነው፡፡ ዋናው ጥያቄ ግን በእስልምና አማኞች መሀል ጠብ ቢፈጠር በተለያየ መልኩ መንግስት ገብቶ ጠቡን ለማብረድ መሞከር ሥራው ነው፤ ነገር ግን ከዚያ አልፎ አንዱን በመደገፍ ሌላውን ለማጥቃት መሞከር ተገቢ ሊሆን አይችልም፤ ሕገ መንግሥቱ በሁሉም ሲከበር ስምምነትና ሰላም ይሰፍናል፡፡ 

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *