ሀገሬ ገመናሽ (ክፍል አንድ)
ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ
የጥበብ ማዕዶችሽን የደፈረ አቀረሸባቸው፡፡
የጎጆዎቻንን ገመናስ እንሸፍንበት ገዶን አያውቅም፤ ድሮ በደህናው ጊዜ፣ ኑሮ ርካሽ በነበረበት ዘመን፣ ኑሮ ከሀገራችን እድገት ጋር እንዲህ አብሮ ሳያድግ፣ የጋገርነውን የዘንጋዳ ቅይጥ፣ ባሰጣነው ማኛ፣ እርቃናችንን በሰልባጅ እንሸፍነው ነበር፡፡ ዛሬም ቢሆን እንደየአቅማችን ገመናችንን እንሸፍንበት አልገደደንም፡፡ ሌላው ቀርቶ መሶባችን ባዶ ሆኖ የሚበላ ቢጠፋ፣ ጦም መዋላችንን እንሸፍንበት የከራረመ ስቴኪኒ ከጥርሳችን አይጠፋም፡፡ እንደርበው ጃኬት ባይኖረን፣ ቆዳ በሚያሻክር ብርድ ሙቀቱን እናማርራለን፡፡ አቦ የራስን ገመና ይሸፍኑበት መች ይገዳል!
ሀገሬ የገደደው ያንቺ ገመና ይሸፈንበት መንገድ ነው፡፡ ሁሉም የጎጆውን ገመና ለመሸፈን ደፋ ቀና ሲል፣ የአንቺ ገመና እንደአዳል በግ ላት ተገልብጦ አረፈው፡፡ ለነገሩማ፤ አዎ ያስተማርሻቸው ልጆች አሉሽ፤ ህገ-መንግስትም አቁመሻል፤ ህግ የሚያሰከብርልሽ መንግስትም ሰይመሻል፣ ግን አንዳቸውም ያገጠጠ ገመናሽ ላይ እራፊ ጨርቅ አልጣሉልሽም፡፡
እንዲህ እንደዛሬው ብቻዬን ቁጭ ስል፣ እንዲህ እንደዛሬው ከልጆች ትምህርት ቤት፣ ከቤት ኪራይ፣ ከታክሲ፣ ከአስቤዛ ክፍያ አብሰልስሎት የተረፈ ማሰቢያ አእምሮና ጊዜ ሲኖረኝ፣ ‹‹እውነት ሀገሬ ማፈሪያ ገመናሽን ከአደባባይ ኩራትሽ ለይተሽ ታውቂያለሽ?›› እያልኩ አሰላስላለሁ፡፡
አንዳንዶች እንደሚሉኝ ግትር ተሟጋች ሆኜ እንዳይመስልሽ፡፡ ነቅሼ እሟገትበት ማስረጃ ሞልቶኛል፡፡ እኔ የምልሽ እስቲ ስለቀጣይነትሽ ንገሪኝ! ‹‹ሀገር የሚቆመው በምን ነው? የሚፈርስስ በምን ነው?››፡፡ ንጉሰ ነገስታት ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ከሚጠቀሱላቸው ንግግሮቻቸው አንዱ ይህን አስመልክተው የተናገሩት ነው፤ ሀገርና ታሪክ የሚቀመው በዜጋው መሆኑን የተናገሩበት፡፡ ታዲያ ሀገር የሚቆምም የሚፈርስም በዜጋው ከሆነ፣ ዜጋንስ በምን ያንፁታል? መቼም በእህል ውሃ እንዳልሆነ ታውቂያለሽ፡፡ ያማ ቢሆን ወቅቱን ጠብቆ በእሳት የሚያጠምቀን ረሃብ፣ ሰውነታችንን አዋርዶ፣ አንቺም ሀገሬ በፈራረስሽ ነበር፡፡ ግን ስለረሀብ አልፈረሽም፡፡
አዎ ልክ ነሽ ሀገሬ፣ ዜጋ ሀገሩን የሚያፀናው በእውቀትና በስነ ምግባሩ ነው፡፡ ይህን ካወቅሽ ታዲያ ምነው እንዲህ ከሀገር ተራ ስትወጪ ገመናሽን ታስተካክይበት ይቅር፣ ትሸፍኚበት ማጣትሽ! ምነው? እዚህ ላይ ሀገሬ ዘመን ካቋደሰሽ ስልጣኔ ተኳርፌ፣ ስልጣኔ ከሸረሸረው ቀርነት ጋር ተቃቅፌ እንዳይመስልሽ፡፡ የስልጣኔ ግቡስ የሰዎችን ኑሮ ማቅለል አይደል? ስልጣኔን ማን ይጠላል! ሀገሬ ችግሩ ስልጣኔው አይደለም፡፡ ችግሩ ያልሰለጠነውን እኛን በሰለጠነ ሌላ ለመተካት መሞከርሽ ነው፡፡ ማለቴ ያልሰለጠነውን ኢትዮጵያዊ በሰለጠነ ፈረንጅ ለመተካት መሞከርሽ መጀመሪያ ያሳፍራል፤ ቀጥሎ ያበሽቃል፡፡
እኔ የምልሽ ሀገሬ የሰለጠነ ኢትዮጵያዊ የማትፈልጊው ለምንድነው? ‹‹ለምን አትፈልጊም?›› ማለቴ ወጌን ላተጋ እንዳይመስልሽ፤ የዛሬ ስልጣኔሽ ውስጥ የአንቺ አሻራ ቢደበዝዝብኝ ነው፡፡ ራዲዮና ቲቪሽን ከየፈረንጅ ሀገሩ በተቃረሙ ፕሮግራሞች ልትሞዪ ደፋ ቀናሽ በዛ፡፡ ሀገሬ ‹ዲል ኖ ዲልን› እስማማለሁ አልስማማም አልሽ ዝም አልን፡፡ ‹አይዶልን› ከየፈረንጅ ሀገሩ ሳትተረጉሚ አመጣሽ፤ ይሁን ብለን ዘፈንን፡፡ ‹ፕራንክ›ን የካሜራ አይን ምናምን እያልሽ በፈረንጅ ቀልድ በየጎዳናውና በየመዝናኛው ቀልባችንን የምትገፊው ምን ሆነሽ ነው? መሰልጠን መተርጎም ነው እንዴ? እውነት በዛ! አንባሰልን፣ ትዝታን፣ አንቺ ሆዬን . . . የመሳሰሉ የሙዚቃ ምቶችሽን ጥለሽ ሂፖፕን፣ ሮክን ትተረጉሚያለሽ! የወጣቶችሽም አለባበስ ከፈረንጅ የተተረጎመ ነው፡፡ የየብሄረሰቦችሽን ጭፈራ በፈረንጅ ዳንስ አዳቅለሽ ስታሰቃዪው ማየት ያሳዝናል፡፡ . . . መቼም ሀገሬ እድሜ ከሰጠኝ ኢትዮጵያዊ ማለት የአንድ ፈረንጅ ትርጉም ሆኖ ማየቴ አይቀርም፡፡
ሀገሬ ወጣቶችሽን እኮ የአንድ ዋልጌ ፈረንጅ ትርጉም እንዲሆኑ እየወተወትሻቸው ነው፡፡ አሁን ማን ይሙት ሀገሬ፣ እነዚያ በአመት አንድ ቀን ጥምቀተ – ባህር ሲወጡ የተወረወረላቸውን ሎሚ ለማንሳት የሚሽኮረመሙት ልጃገረዶች መሀል አዲሳባ፣ በጠራራ ፀሐይ ሳይቀር እርቃናቸውን ይደንሳሉ ብለሽ ታምኛለሽ! ይከብዳል፡፡ ግን ይደንሳሉ፡፡ ወንዱም ያስደንሳል፡፡ ለምን? ለምን እንደሆነ ልንገርሽ! አብዛኞቹ ሴቶች ካንቺ ከሀገራቸውና ከሰየምሽላቸው መንግስት እጅ ያጡትን የእለት እንጀራ ፈጣሪ ከሰጣቸው ውበት ለማግኘት ይደንሳሉ፡፡ ጥቂት ወንዶች ደግሞ አንቺና መንግስት የለገሳችኋቸውን ንዋይ ያፈሱበት አጥተው፣ የልጃገረዶችሽ ሰውነት ላይ እያፈሰሱ ውበታቸውን ያረክሱታል፡፡
እረ ስንቱ ሀገሬ! ገመናሽ ይናገሩት ያፀይፋል፡፡ የራስሽንና የህዝቦችሽን ገመና ይሸፍንልሽ ዘንድ የሰየምሽው መንግስትም ጉድፍሽን እንደብራ መብረቅ አገነነው፡፡ አስተማርኩት ያልሽው ዜጋም ደጁን ቆልፎ ሌላ ገመና ሆነሽ፡፡ ለነገሩ ምን ያድርግ! አንቺ ያስታጠቅሽውን እንጂ መቼ ያስተማርሽውን ታዳምጫለሽ! በምትሰይሚው መንግስትና በተማሩ ልጆችሽ መካከል የአዳምና – የእባብን እጣ አኑረሻል፡፡ አዳም የእባቡን አናት ይጨፈልቅበት ቆመጥ ቢኖረውም፣ እባቡም አዳምን ይገድል መርዝ አለው፡፡ ያንቺ ግን ሀገሬ ግፍ ነው! ለመንግስት ያስተማርሽውን የሚገልበት ነፍጥ፣ የሚያጉርበት እስር ቤት ሰጥተሸ፣ ለተማረው ብዕር ሰጠሽ፡፡ በእውነት ግፍ ነው! እና የተማረው ልጅሽ በየዘመኑ ለምትሰይሚው መንግስት የሰጠሽው ነፍጥና ማጎሪያ ቢሰለቸው በአካሉ ላይ ቤቱን፣ በእውቀቱ ላይ አእምሮውን ቆልፎ ከአደባባይሽ ራቀ፡፡
ይኽው ታዲያ ዛሬ ሀገሬ አደባባይሽን ደፋር ሸለለበት፡፡ ማሳዎችሽ የተማሩ የሚቀጭጩባቸው፣ የደፈሩ የሚያፈሩባቸው ሆኑ፡፡ ራዲዮና ቲቪሽ ዜጎችሽን ለሚያንጹ አስተዋዮች ሳይሆን፣ ኢትዮጵያውያንን ወደ ፈረንጅነት ለመተርጎም ታጥቀው ለተነሱና ጊዜም ለሰገደላቸው ደፋሮች ተሰጡ፡፡ ቆይ እኔ የምልሽ እነ ዮሐንስ፣ ደበበ፣ ፀጋዬ፣ . . . ስንቱ በተጠበበበት መድረክ የስነ ጥበብን ዋጋ የማያውቁ ደፋሮች ሲያቀረሹበት ትንሽ አይሰቀጥጥሽም! እንዴት አድርገሽ ነው ለዚህ ትውልድ ስብራት እነዚህን የስነ ጥበብን ምንነት ከቁብ ያልከተቱ ነጋዴዎች በወጌሻነት የመረጥሽው? እሺ ይሁን እንዳልሽው ባለሙያው ዝም ሲል እነሱ ደፈሩ! ነገዱ! ይነግዱ፡፡ ሲራራ ሆኖ የተጫነ ወይ የተጫነውን መጋዣ ማልዶ የጎተተ ሁሉ ሸቅጦ በሚያተርፍበት በዚህ ዘመን . . . ደግሞ ለመነገድ! በዚህ አልወቅስሽም፡፡ ማዘኔ እነዚህን ደፋር ነጋዴዎች ለዜጎችሽም መስፈሪያ ባደረግሻቸው ጊዜ ነው፡፡
እንዴት ነው የስነ ጥበብን ዋጋ ዘነጋሽ እንዴ! ዛሬ እኮ ደፍረን ለጓደኞቻችን የማንነግረው የዘቀጠ ጉዳይ ነው ፊልም እየተባለ በየሲኒማ ቤቱ የሚታየው! የውልሽ ሀገሬ ያገጠጠ፣ አፀያፊ ገመናሽን ከለላ ሆኖ እንዲሸፍን፣ ቢችል ደግሞ ወጌሻ ሆኖ እንዲጠግን፣ አደራ ያልሽው መንግስት ራዲዮና ቲቪውን በጥበብ ስም ለሚተፋ የደፋር ቅርሻት ሸለመው፡፡ እና ገመናሽ ራዲዮና ቲቪ ገባ፡፡
ከዘነጋሽ እስቲ የበቀደሙን የገናን በዓል የኢቲቪ ውሎ ልንገርሽ! የውልሽ፤ ጥበብ የጠራችው የጥበብ ሰውና ሌላው ሲጠራ ተከትሎ ሄዶ ጥበብን አስገድዶ የደፈረ ዋልጌ ተሰብስቦ አጫዋችና ተጫዋች ሆኖ ውሎውን አዋለን፡፡ አየሽ ሀገሬ! አንቺ የፖለቲካ አዋቂ፣ የታሪክ ተመራማሪ፣ አንጋፋ የባህልና ወግ አዋቂ፣ ሳይንቲስት እንደሌለሽ ቲቪሽን ደፋር አርቲስት ነኝ ባይ ሞላው፡፡ ልጆቻችን ከዘፋኝ፣ ከዳንሰኛና ከተዋናይ ውጪ ‹‹እሱን እሆናለሁ›› የሚሉት ዜጋ ናፈቃቸው፡፡
በአንድ ቅዳሜና እሁድ ባላገሩ አይዶል (ዳንስና ዘፈን)፣ ኢትዮ ታለንት ሾው (አሁንም ዳንስና ዘፈን)፣ ኮካኮላ ‹ታለንት› ሾው (አሁንም ዳንስና ዘፈን) እያቀረቡ፣ የእረፍት ቀኖቻችንን በፈንጠዝያ ሞሉት፡፡ ልጆቻችን ከዘፈንና ከዳንስ የዘለለ ‹ታለንት› አለመኖሩን አምነው እንዲቀበሉ የመንግስት ቲቪ ፍዳቸውን ያሳያቸዋል፡፡ አየሽ ሀገሬ፣ ገመናሽን እሸፍን ብለሽ የበለጠ አሰጣሽው፡፡ አንዳንዴ በውስጥሽ የሚደረገውን ስመለከት ብርርር ብለህ ጥፋ ጥፋ የሚል ስሜት ይሰፍርብኛል፡፡ ድንቄም ሀገር! እስቲ አሁን እንዲያው የሀገር ወግ ያለው ሀገር ‹‹ከተወለድኩ አንድም መጽሐፍ አንብቤ አላውቅም›› የሚል ደፋር አርአያ ብሎ ለዜጋው በቲቪ ያቀርባል! ትንንሾቹ ልጆች ምን ሲሉ እንደሰማሁ ልንገርሽ? ‹‹ለካስ ሳይነበብም ትልቅ ሰው ይኮናል፤ ለካስ ማንበብ ጊዜ ማጥፋት ነው›› አሉና አረፉት፡፡
እነ ከበደ ሚካኤል፣ የንባብና የእውቀትን ጥቅም በሰበኩበት መቅደስ፣ ንባብና እውቀት ያልሞረዳቸው ደፋሮች ንባብ ለምኔን አዜሙበት፡፡ እውነት እልሻለሁ ያሁኑ ግን በዛ! ሀገሬ ሙች በዛ! ፊልሙንና ዘፈኑንስ እሺ ‹‹የሚመረጥ ከተገኘ መርጠን እንመለከታለን፤ እናዳምጣለን፣ ካልተገኘም ይቅር›› ብለን በራችንን ቆልፈን ተቀመጥን፡፡ አንቺ ግን ሀገሬ፣ በእለተ እሁድ ከልጆቻችን ጋር በተቀመጥንበት ግራና ቀኙን አዙሮ የማያይ ደፋር ላክሽብን፡፡ እኔ ምልሽ እነሱን፣ ጃስ! ብሎ ፈትቶ የለቀቀብንን መንግስትንስ ተይው አንቺ ግን አይሰማሽም!
እኔ የማውቀው ምድር በፀሀይ ዙሪያ ስትሽከረከር ነው፡፡ አንቺን ማነው ከምድር ተለይተሸ በደፋር ነጋዴ አርቲስቶች ዙሪያ እንድትሽከረከሪ የፈረደብሽ? ቆይ ሰማንያ ሚሊየን ህዝብ አለኝ ትዪ የለ እንዴ! ፊልሙን ከድርሰቱ እስከ ዝግጅቱ፣ ማስታወቂያውን፤ ይባስ ብለሽ ደግሞ ስንት ትምህርትና ንባብ የሚጠይቁ ማህበረ-ባህላዊ ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ ትምህርታዊ ውይይቶችን ሳይቀር ገንዘብና ድፍረት ለታጠቀ ደፋር አርቲስት መሸለምሽ የጤና ነው? ሀገሬ ሙች የጤና አይመስለኝም፡፡ አስሮ ጸበል የሚወስድ ጎረቤት አጥተሸ እንጂ ሀገሬ ሙች ወፍፈሻል፡፡ ደፋሮችሽን የጥበብ ብቻ ሳይሆን የእውቀትም መስፈሪያ አደረግሻቸው እኮ!
መቼም አንድ ሰው ያቅሙን ነው፤ ‹አንብቤ አላውቅም› ያለ ደፋር የአራተኛ ክፍል ትምህርቱን አስታውሶ፣ ስላለው ገንዘብና ስለማያውቀው እውቀት፣ ጠዋት ጠዋት ስለሚጠጣው ቡና፣ አልያም ፈርምልን ስለሚሉት የዋህ የድፍረቱ አድናቂዎች ልፈላሰፍባችሁ ቢል ላይገርም ይችላል፡፡ ሀገሬ ይህን ገመናሽን ግን በሳምንት አንዴ የሚመጣ ሰንበታችንን ማርከሻ ማድረግሽ እውነት ግፍ ነው፡፡ ቆይ ቲቪው ያንቺ ቢሆንስ! ልጆቻችንስ የአንቺ አይደሉም እንዴ! ጦም አድረን የምናስተምራቸው እኮ ለእራሳቸውም ለአንቺም የሚጠቅሙ ዜጎች ይሆኑ ዘንድ ነው፡፡ እና ራዲዮና ቲቪሽን ሰብስቢልና! የሌለንን ገንዘብ ሆጭ አድርገን እያስተማርን የምናንጻቸውን ልጆቻችንን ስነምግባር ናድሽው እኮ!
ቆይ እኔ የምልሽ አንቺ ሀገር አይደለሽም እንዴ! ቆይ እነ ህሩይ ወ/ሥላሴ፣ ገብረህይወት ባይከዳኝ፣ ዮፍታሔ፣ ዮሐንስ፣ ፀጋዬ… እረ ስንቶች ታውቂያቸው የለም እንዴ! በእነሱ አልነበረም እንዴ እውቀትን የምትለኪው! አይጣል ምፀትሽ! ዛሬ በማያነቡ አርቲስቶች ድፍረት እውቀትን ትለኪ ገባሽ፡፡ መጥኔ መዝቀጥ!
አንድ በቲቪሽ የምናየውን ‹‹ሰው ለሰው›› የተባለውን፣ ዘወትር እረቡ ማታ የሚታየውን ተከታታይ ድራማ ታውቂው የለ! በቀደም እለት በምሳ ሰአት ድንገት ቲቪሽን ስከፍት፣ ድራማው ላይ ያሉ አንድ የቤተሰብ አባላት ተመለከትኩ፡፡ ‹‹የድራማው ሰአት ተቀየረ እንዴ›› ብዬ ባተኩር፣ ጉዳዩ የቢራ ማስታወቂያ ሆኖ አገኘሁት፡፡ አየሽው አይደል ሀገሬ ጥበብን እንዴት እንዳረከሽው! አውርደሽ መሸቀጫ እንዳደረግሽው! ድራማው ላይ ጠላት ያልናቸው ማስታወቂያው ላይ ወዳጅ ሆነው ጽዋቸውን ሲያነሱ ተመልክተን እኛ በመጀመርያ አፈርን፤ ቀጠልንና ‹‹ደፋሮች የጥበብን ቤተ-መቅደስ አርክሰው፣ የጽላትዋን በልተው፣ ትእዛዛትዋን ለገንዘብ ቸረቸሩት›› አልን፡፡ ልጆቻችን በመጀመሪያ ግራ ተጋቡ፤ ቀጥለው በማስታወቂያና በድራማ መካከል ያለውን ግንብ አፈረሱ፡፡
ሀገሬ ነውር እኮ ገመና የሚሆነው ተሸፋፍኖ፣ ተደብቆ ሲቀመጥ ነው፡፡ ያንቺ ግን ቅጥ አጣ! ገመናሽ ነው ብለን በየጎጇችን የምናንሾካሹከውን ነውርሽን እንዲህ ዝቀሽ ቲቪ ላይ ታሰጪው!

ልዕልና ጋዜጣ
Posted on March 27, 2013 by መስፍን ወልደ-ማርያም (Mesfin Wolde-Mariam)

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *