ሀገሬ ሙች፣ ገንዘብ ወዳድ ሆነሻል!

ሀገሬ ገመናሽ (ክፍል ሶስት)
ሀገሬ ሙች፣ ገንዘብ ወዳድ ሆነሻል!
ሀገሬ አንዳንዴ ከሰሜን ወደ ደቡብ፣ ከምስራቅ ወደ ምእራብ የዘረጋሻቸውን ጎዳናዎች፣ ልታነጥፊያቸው ደፋ ቀና የምትይላቸውን ሀዲዶች ስመለከት ደስ ይለኛል። የአዲስ አበባን አስፋልትና በየአስፋልቱ ዳር ያቆምሻቸውን ህንፃዎች አዲስነት ስመለከት ደግሞ፣ ‹‹ቆይ ሀገሬ፣ መንገድም፣ ህንፃም አልነበራትም እንዴ?›› ብዬ እራሴን እጠይቃለሁ። እውነቴን ነው የምልሽ ሀገሬ ግንባታሽን ለተመለከተ ፈርሶ የሚሰራ ሀገር ነው እኮ የምትመስይው! ግን እኔ ልማትሽን፣ እድገትሽን፣ ትራንስፎርሜሽንሽን . . . አልነግርሽም! እንደነገርኩሽ ጉዳዬ ከገመናሽ ነው። ለልማት ለትራንስፎርሜሽንማ ራዲዮና ቲቪሽ መች አነሰሽ! ዋናው ራዲዮና ቲቪ አልበቃ ብሎ ኤፍ.ኤም፣ ኢቲቪ1፣ ኢቲቪ 2 . . . ልማትና እድገትሽ ራስምታትሽ እስኪሆን ይነግርሽ የለ! ነጋሪ ያጣው እኮ ገመናሽ ነው! እና እኔ ልጅሽ ልንገርሽ! በትልልቅ ህንፃና በተንጣለለ ጎዳና እንኳን አልሸፈን ያለውን ገመና ልንገርሽ!

በቀደም ቦሌ ሩዋንዳ አካባቢ ቀለበት መንገዱን የሙጥኝ ብላ የምትኖር አክስቴን ልጠይቅ ሄጄ ነበር። ከጠየቅኳት ብዙ ጊዜ ሆኖኝ ነበርና በቤትዋ ውስጥ ባየሁት ለውጥ ተደነቅኩ። ሀገሬ ሙች የሻይ ስኒውና የስኳር ማቅረቢያው እንኳ ልዩ ነው፤ ሶፋውም ተቀይሯል። ‹‹አጎቴ ግርማስ ደህና ነው?›› አልኩና ጎረቤትዋ ስለሆነው ታላቅ ወንድምዋ አክስቴን ጠየኳት። ‹‹ውይ! ካየሁት መንፈቅ አይሆንም ብለህ ነው!›› ስትለኝ፣ ‹‹እንዴ በሀገር የለም እንዴ!›› ብዬ መልሼ ጠየኳት። ‹‹መኖር አለ፣ ብቻ ይህ ቀለበት መንገድ መሀላችን ከገባ በኋላ … መተያየት ጠፋ›› አለችኝ። እኔም ‹‹የማታ ቡናችሁ ቀርቷላ!?›› ብዬ ደነቀኝ። ሁሉንም ዘርዝራ ነገረችኝ።

ሀገሬ ቀለበት መንገዱ ለአክስቴ ሲሳይ፣ ለአጎቴ ስቃይ መሆኑን ሳውቅ ግራ ገባኝ። ቀለበት መንገዱ የአክስቴን አካባቢ ስላለማው፣ የአጥርዋን ዙሪያ ሱቅ በሱቅ አድርጋ ጥሩ ኑሮ ትኖር ጀምራለች። የአክስቴ ልጆች ማታ ማታ የሚያስፈልገውን እየሰሩለት የሚኖረው ደካማው አጎቴ ደግሞ፣ ጠያቂ አጥቷል። ሀገሬ፣ ማዶ ለማዶ የሚተያዩት አክስቴና አጎቴ ለመጠያየቅ የሁለት ብር ከምናምን ታክሲ መያዝ ያስፈልጋቸዋል። መሸጋገሪያ ፍለጋ ታክሲ ይዘው መሄድ አለባቸው ነው እኮ የምልሽ፣ ሀገሬ! አይገርምሽም! መቼም ይህን ስልሽ በየአስር ሜትሩ መሸጋገሪያ እያበጀሽ ቀለበት መንገዱን ባለጣሪያ አስመስይው ማለቴ እንዳልሆነ ይገባሻል። ግን ምናለ በአንድና በሁለት ኪሎ ሜትር መሸጋገሪያ ድልድይ፣ ወይም ከስር መሹለኪያ ብታበጂ! አየሽ ሀገሬ! እንዲህ ብታደርጊ አክስቴም፣ አጎቴም ደስ ብሏቸው እያመሰገኑሽ ይኖሩ ነበር። አሁን ግን ሀገሬ አጎቴ ረጋሚሽ ሆነ።

ለነገሩ እኮ ሳስብሽ ሁሉንም ዜጋሽን ማስደሰት የምትፈልጊ አይመስለኝም። ሀገሬ ሙች እውነቴን ነው። ስለልማትሽ የሚያዜመውና ሙሾ የሚደረድረው እኮ መሳ ለመሳ ነው። የልማትሽ መሀንዲሶችና አስፈፃሚዎች ደግሞ በዚህ አስደሳችና አስለቃሽ በሆነው ልማትሽ የተዋጣላቸው ናቸው።

ቆይ እኔ የምልሽ! መሀንዲሶችሽ ልጆች አሏቸው ወይስ የላቸውም? ይህን መልሺ! እና ልጆች ካሏቸው ትንንሽ ከተሞችን በሲ.ኤም.ሲ. ሰሚት፣ ለቡ፣ ጀሞ… ስትቆረቁሪ የህፃናት መጫወቻ ቦታ፣ ለደስታና ሀዘናችን ዳስና ድንኳን መጣያ፣ ምነው ሳይተውልን! እኔ የምልሽ ከተማ ማለት ህንፃ ብቻ ነው እንዴ! እዚህ እኛ ሰፈር ሲኤምሲ፣ ከእኛ ህንፃ አናት ላይ ሆነሽ ዙሪያውን ብታዪው ጉድ ትያለሽ! በቃ የግንባታ ሀይቅ በይው! መጨረሻው አይታይም። ታዲያ በዚያ የግንባታ ሀይቅ ውስጥ በመቶና ሁለት መቶ ቤቶች መካከል አንድ ህንፃ የሚያሰራ ቦታ ትተሻል?! እሱም ቆጭቶሻል መሰለኝ ሰሞኑን የእኛን ሰፈር ለአንድ ቱጃር ሰጥተሽው ይሁን ሸጠሸው፣ ይገነባበት ጀምሯል። መናፈሻ… ዛፍ… ምናምኑንማ ተይው!

የሰሞኑ የአዲስ አበባ ሙቀት ያስጨነቀው ወዳጄ፣ ‹‹በዚሁ ከቀጠለ እኮ በቃ! አዲስ አበባም በረሀ መሆንዋ ነው! መንግስት ልክ እንደ ኮንዶሚኒየም ግንባታ ዛፍ ተከላው ላይም መዝመት አለበት›› ሲል ሰማሁት። እኔ የምልሽ ሀገሬ፣ እሺ እሱ እንዳለው በዘመቻ ዛፍ እንትከል ብንልስ የት ነው የምንተክለው! ህንፃ እያፈረስን?! አንዳንዴ ምን እንደማስብ ታውቂያለሽ?! ዛሬ በየሰፈሩ ደሳሳ ጎጆዎችሽን እያፈረስን ትልልቅ ቪላ እና ህንፃ እንደገነባነው፤ ወደፊት እንደቻይና ሀብታም ስንሆን ደግሞ ዛሬ የሰራናቸውን ቪላዎችና ህንፃዎች እያፈረስን ዛፍ ስንተክል ይታየኝና መጀመሪያ ፈገግ፣ ከዚያ ብስጭት እላለሁ።

ሀገሬ እንዲያው እውነቴን ነው የምልሽ ኦሎምፒክ ላይ አድሏዊነት በውድድር አይነት ቢኖር እንዳንቺ ወርቅ በወርቅ የሚሆን የት ይገኛል? በእውነት አድሏዊ እኮ ነሽ!! አሌ ካልሽ ደግሞ ሩቅ ሳልሄድ እዚህ ሰፈራችን ስላደረግሽው አድሎ ልንገርሽ። መቼም እኛ ይህንን አሁን የምንኖርበትን ህንፃ እንዴት እንደሰራነው ታውቂያለሽ! መጀመሪያ አስራ ስድስት ሆነን ተደራጀን። ባንክ ስምንት ስምንት ሺህ ብር አስቀምጠን፣ መሬት ስጭን፣ ስንልሽ ዝም አልሽ። አንድ አመት አለፈ፤ ሁለት አመት አለፈ። የግንቦት 97 ምርጫን ጠብቀሽ ሚያዝያ ላይ መሬት ሰጠሽን። ታዲያ ይኽው ከሰባት አመት በኋላ ሰርተን ገባን። አንዱ የማህበራችን አባል ግን ማህበሩን የተቀላቀለው የህንፃው መሰረት ከወጣ በኋላ ነበርና እስከዛሬ ቤቱን በስሙ ማዞር አልቻለም። ሀገሬ ሙች! ክፍለ ከተማና ቤቶች አስተዳደር ሲመላለስ ሰባት አመት ሞላው። የሚገርምሽ ግን ይህ አይደለም። እዚህ ከእኛ ህንፃ ቀጥሎ ያለውን፣ ለአስራ ስድስት ሰው የተሰጠ ቦታ፣ አንዱ ዜጋሽ ጠቅልሎ በስሙ አድርጎ ውብ ባለ ሁለት ፎቅ ቪላ ሰራበት። አየሽው ያልሸፈንሽውን፣ አድሏዊነትሽን!

ሀገሬ የአንቺን ልማት ሳስብ፣ በአንደኝነት የሚጠቀስ ባህሪው አድሏዊነት ይመስለኛል። የምታደይው ደግሞ ለቱጃሩ ነው። የምር ነው የምልሽ! ቆይ ሀገሬ ለባለዝቅተኛ ገቢው እያልሽ የምትገነቢውን ኮንዶሚኒየም እንኳን የሚኖርበት ማነው! ‹‹ድሀው›› እንደማትይኝ እርግጠኛ ነኝ። እንዴ! እኛም እኮ ዜጎችሽ ነን። ድሃ ስለሆንን ድህነት ምን ማለት፣ እንዴት መኖር እንደሆነ እናውቃለን። ለነገሩ ባንቺ ማን ይፈርዳል፤ ውሎሽ ከቱጃርና ከባለስልጣን ጋር እየሆነ ድህነት ምን ማለት እንደሆነ ጠፍቶሻል። እውነቴን ነው የምልሽ፣ ከፈለግሽ ልንገርሽ! ድሀ ማለት ለከተሜው፣ ማታ የማዳበሪያ ሽንቁሩን በመርፌ ሲጠቅም አምሽቶ፣ ጠዋት ከፍራሹ የተራገፈበትን ጭድ አራግፎ፣ አሮጌ ማዳበሪያውን አንጠልጥሎ ከቤቱ የሚወጣ፤ ቀኑን ሙሉ በአምስት ብር የገዛውን በሰባትና ስምንት ብር ለመሸጥ የሚናውዝ ሰው ማለት ነው። እና ከየት አምጥቶ ነው ኮንዶሚኒየም የሚገዛው? በቃ ልንገርሽ ድሀው ኮንዶሚኒየም ውስጥ የሚኖረው አይደለም። ለኮንዶሚኒየሙ መሰረት ጉድጓዱን የሚቆፍረው፣ ድንጋዩን የሚከሰክሰው፣ ብሎኬቱን የሚደረድረው ነው ድሀው! በርግጥ አንዳንድ ጊዜ ሀገሬ፣ የተጋ ድሀ በስሙ የተሰራለትን ቤት ከገዛው ሀብታም ዜጋሽ ላይ ተከራይቶ ሊኖር ይችላል።

ሀገሬ ሙች፣ ገንዘብ ወዳድ ሆነሻል! እና ገንዘብ ባትወጂ በየሀብታሙና ባለስልጣኑ ስር የምታውደለድይው ለምን ነው? ግን የሚገርምሽ እነሱ ከቁብ አይቆጥሩሽም። ሳት ብሏቸው እንኳን በቋንቋዎችሽ የተሰየሙ ሆቴሎችሽ ውስጥ ሻይ አይጠጡም። ውሏቸው ሸራተን፣ ሂልተን፣ ጁፒተር፣ ኮንቲነንታል… ምናምን ነው፤ ሀገሬ ሙች ንቀውሻል።

ሀገሬ አዋዋልሽ ነው መሰል፣ አንቺም ድሃ ዜጎችሽን መናቅ ጀምረሻል። በማናለብኝነት በዚህ በመዲናሽ በየሰፈሩ አድሏዊነትሽን የሚዘክሩ ሀውልቶች አቁመሻል። ለዛሬ እዚህ እኛ ሰፈር ስለአድሏዊነትሽ ያቆምሽውን መዘከሪያ ላስታውስሽ።

ዛሬ የአዲስ አበባ አንድ ሰፈር መጠሪያ፣ ለአንቺ የአድሏዊነት መዘከሪያ የሆነውን የሲ.ኤም.ሲን የመኖሪያ ሰፈር የሰራው የደርግ ወታደራዊ መንግስት ነው። እንደሰማሁት በመዲናሽ በተለያዩ ቦታዎች ፈረስ የሚያስጋልብ ግቢ የያዙትን ኤምባሲዎችና ቆንጽላዎች፣ በአንድ ግቢ ለመሰብሰብ አስቦ ነበር አሉ፣ ደርግ ሰፈሩን የመሰረተው። ታዲያ ይህ በተመረጠ ድንጋይ፣ በላቀ የምህንድስና እውቀትና ክሂል፣ የተሰሩ ህንፃዎችና የተሟላ የልጆች መጫወቻ፣ የመናፈሻና የመኪና ማቆሚያ ያለው ግቢ፣ አሁን በኪራይ ቤቶች አስተዳደር ስር ሆኖ ሀብታሞችሽ ይኖሩበታል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሰፈሩ አጥር አልባ፣ እንዲያውም በመሀሉ ሰፈሩን ሰንጥቆ የሚያልፍ የአስፋልት መንገድ ያለው ነበር። እዚህ ግቢሽ አካባቢ እስከ ቅርብ አመታት ድረስ ነዋሪዎች አልነበሩም፤ በሜዳና ጫካ (ቁጥቋጦ) የተከበበ ነበር። እና ሀብታሞችሽ አይሰጉም፤ አንቺም ስለሀብታሞችሽ ስጋት ያለ እንቅልፍ አታድሪም ነበር።

የነዋሪዎቹም የአንቺም ስጋት የጀመረው በአካባቢው ሰዎች መኖሪያ ቤት መገንባት ሲጀምሩ ነው። ያኔ ስለነዚህ ዜጎችሽ አብዝተሽ ተጨነቅሽ፤ ከሁለት ተኩል ኪሎሜትር በላይ የሚረዝመውን ግቢ ዙሪያውን በግንብና በብሎኬት አጠርሽላቸው። በግቢው የሚያልፈውን አቋራጭ ዘግተሽ ሌላውን ዜጋ ለአምስት ኪሎሜትር ተጨማሪ መንገድ ስትዳርጊው ቅንጣት ፀፀት አላደረብሽም። ሀገሬ ሙች ትገርሚያለሽ! ይባስ ብለሽ በገነባሽላቸው የግንብ አጥር ላይ አደገኛ ሽቦ አስቀመጥሽ። በቡድን በቡድን ሆነው በግቢው ዙሪያ ቤት የሚሰሩ ዜጎችሽ፣ የአምስት ኪሎ ሜትሩ ተጨማሪ መንገድ እምብዛም አላናደዳቸውም። በግንብና በአደገኛ ሽቦ የታጠረውን በተመለከቱ ጊዜ ግን ዜግነታቸውን ተጠራጠሩ፤ አዘኑብሽ። እውነቴን ነው የምልሽ፣ በግቢው ያስቀመጥሻቸውን ዜጎች ሲያስቡ፣ ምን ያህል አድሏዊ እንደሆንሽ መግለጽ ያቅታቸዋል። አንቺ ግን ሀገሬ፣ ድሀ መች ትፈሪያለሽ! የእግር ማቋረጫቸውን ሁሉ ከግቢው በሚወጣ ቆሻሻና ፍሳሽ አጥለቀለቅሽው። ኧረ ሙች ጉደኛ ነሽ!

እኔም ይህንን የአድሏዊነትሽን ዘካሪ ግቢ ስመለከት፣ ለመሆኑ ማን ነው የሚኖርበት? ብዬ መጠየቄ አልቀረም። ሀብታም፣ አነስ አነስ ያሉ ባለስልጣናት (ለትልልቆቹማ የየራሳቸውን ግቢ ሰርተሽላቸዋል)፣ የአፍሪካ ህብረትና የሌሎች የውጭ ድርጅቶች ሰራተኞች ናቸው፣ አምስት ሺህ ብር በወር እየከፈሉ ነው የሚኖሩት ሲሉኝ ማመን አቃተኝ። ሀገሬ ሙች ገረመኝ! እኛ ህንፃ ላይ አምስት ሺህ ብር ከፍለው የተከራዩ ስድስት ቤተሰቦች አሉ አይደል እንዴ?! አድሏዊ ነሽና እነሱን አትንከባከቢያቸውም። የነዛኞቹን ቆሻሻ ታፈሺባቸዋለሽ። የሚገርም ነው!

ሀገሬ እኔ የምልሽ አምስት ሺህ ብር እየተከፈለ የሚኖርበት ምድረ-ገነት ግቢ፣ አምስት ሺህ ብር እየከፈሉ በሚኖሩ ሌሎች እንዳይደፈር በዘመናዊ አጥርና በታጠቀ ዘበኛ ተጠብቆ፣ በሌሎች መተላለፊያ ላይ ቆሻሻውን ሲከምር ከማየት የበለጠ፣ ለአንድ ሀገር አድሏዊነት ሊቆም የሚችል ሀውልት ከየት ይመጣል! አየሽ ሀገሬ! ለዚህ ነው በኦሎምፒክ ላይ የአድሏዊነት ውድድር ቢኖር ወርቅ በወርቅ ትሆኚ ነበር ማለቴ። ሀገሬ! ሁልጊዜ በዚህ የአድሏዊነት ሀውልትሽ ዙሪያ ስሄድ፣ በህፃንነቴ ያነበብኩት፣ ‹‹በድሉና ውሻው›› የሚለው ተረት ትዝ ይለኛል። ታውቂው የለ፤ ያ በድሉ የሚባለው ህፃን፣ እናቱ ሞታ በእንጀራ እናት ያየውን ፍዳ! ፍዳው አልበቃ ብሎ እንጀራ እናቱ መርዝ በምግቡ ውስጥ አድርጋ ልትገድለው ነበር። ውሻው አዳነው! እና እኛ በግቢው ዙሪያ የምንኖረው ምስኪኖች በድሉን የሆንን ይመስለኛል። ወንዙ ውስጥ የሚገባውን ቆሻሻ ስመለከት ደግሞ እኛን ለማጥፋት የተጣለ መርዝ ይመስለኛል። እኛ ግን ውሻ የለንም! ምን ዋጋ አለው! ሀገሬ አንቺ ነበርሽ እኮ ውሻውን ሆነሽ በመርዙ እንዳንሞት ልትታደጊን የሚገባው!

ተረቱ የሚጭርብኝ ሀሳብ በዚህ ብቻ አያበቃም። ‹‹ለመሆኑ እናት፣ እንጀራ እናት እንደሚባለው፣ ሀገር-እንጀራ ሀገር የሚባል ነገር አለ?›› እያልኩ እጠይቃለሁ። እንደዚህ አይነቱ ተጠየቃዊ ተብሰልስሎት ሁለት ጥቅም አለው። ትልቁና ዋናው ግማቱን በሀሳብ አሸንፌ፣ ልብ ሳልል አልፈዋለሁ። ሁለተኛውና ምንም ያልጠቀመኝ ጥቅም ደግሞ ጉዳዩን አስመልክቶ አንድ መደምደሚያ ላይ መድረሴ ነው። ምነው ሳቅሽ ሀገሬ!? የደረስኩበትን መደምደሚያ መስማት ከፈለግሽ ልንገርሽ።

በተጠየቃዊ ተብሰልስሎት እንደደረስኩበት በሰው ልጅ ህይወት ውስጥ እንዳለው አይነት እንጀራ እናት፣ የሚባል ነገር በአገር ላይ የለም። በአገር ህይወት ውስጥ ያለው እንጀራ አባት ብቻ ነው። በአገር ህይወት ውስጥ እንጀራ ሀገር የሚባል ጉዳይ የለም። ለምን ብትዩ ሀገሬ! አገር ሞታ፣ በሌላ የምትተካ አይደለችም። ሁሉንም ዜጋ ይዛ በእናትነት ታኖራለች። እስዋ ብትሞት ሌላ አገር ማምጣት አይቻልምና የእንጀራ ሀገር ይሉት ነገር የለም። በአገር ህይወት ውስጥ ያለው የእንጀራ አባት ብቻ ነው። የአገር አባት መንግስት ነው። ሰው እንደሚሞተው፣ መንግስት ይለወጣል። በመሆኑም እንደአፍሪካና መሰል በዲሞክራሲ ያልሰለጠኑ መንግስታት አዲስ በሚመጡ ጊዜ በቀደመው መንግስት አፍቃሪዎች ላይ የእንጀራ አባትን ይሆናሉ። አገሬ ካልገባሽ ገመናሽን ጠቅሼ ልንገርሽ!? የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት በወታደራዊው መንግስት ሲተካ፣ በንጉሱ አፍቃሪዎች ላይ ደርግ የእንጀራ አባት ሆነ። የወታደራዊው መንግስት በኢህአዴግ መንግስት ሲተካ፣ በወታደራዊው መንግስት ዘመን ተጠቅመዋል፣ ያፈቅሩታል ባላቸው ላይ ኢህአዴግ የእንጀራ አባት ሆነ። ይህ ብቻ አይደለም ሀገሬ! የጣሉት መንግስት አፍቃሪ ባይሆን እንኳን፣ እነሱን ካልወደደ አዳዲሶቹ መንግስታት የእንጀራ አባት ይሆኑታል። እና ይኸውልሽ ‹‹የእንጀራ ሀገር፣ ሳይሆን የእንጀራ መንግስት ይሉት ነው ያለው›› ይላል፤ የደረስኩበት የማይጠቅም መደምደሚያ።

የሚገርመው ግን ሀገሬ አንቺም ያለተፈጥሮሽ አቅል ነሳሽ። የመንግስትን ዘይቤ አድምቀሽ፣ ለእሱ የእንጀራ መንግስት ሆነሽው፣ አንቺም የእንጀራ ሀገር በመሆን ያለተፈጥሮሽ፣ አቅልሽን ስተሽ ታስነውሪያለሽ! እውነቴን ነው እኮ! መንግስት ሀቅን ቢስትና ቢያዳላ፣ ተፈጥሮው ከሰው ነውና አይፈረድበትም። ያንቺ ግን ሀገሬ … ያንቺ ግን… መጥኔ!

ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *