“ግብፆች ከማንኛውም ነገር፣ ሌላው ቀርቶ ከሃይማኖታቸውም በላይ አገራቸውን ያስቀድማሉ” ይባላል፡፡ አገራቸው አገር የሆነችው ደግሞ በናይል ወንዝ አማካይነት ነው፡፡ ይህ አባባል እውነት ከሆነና ግብፆች ለናይል ሲሉ ማንኛውንም ነገር ከማድረግ የማይመለሱ ከሆነ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ጦር ከመማዘዝ የቀለለ አንድ አማራጭ በእጃቸው አለ፡፡ እርሱም እ.አ.አ. በ1978 ከእስራኤል ጋር የተፈራረሙትን የካምፕ ዴቪድ ስምምነት (Camp David Accords) አረረ መረረ ሳይሉ በማክበር ከእስራኤል ጋር ያላቸው ወዳጅነት ፀንቶ እንዲኖር ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ይህንን አያደርጉትም ማለት አይቻልም፡፡ ሲያደርጉት ደግሞ አባይን መደራደሪያ ማድረጋቸው አይቀርም፡፡ የግብፁ ፕሬዚደንት አንዋር ሳዳት የሲናይ በረሃን ከእስራኤል በማስመለስ በግብፅ ሕዝብ ተቀባይነት ለማግኘት ሲል የአረብ አገራትን በሙሉ ጥሎና የፍልስጥኤምን ጥያቄም ችላ ብሎ የካምፕ ዴቪድ ስምምነትን እንደፈረመ ስናስብ፣ ግብጻውያን ለአባይ ውሃ ሲሉ እስከምን ድረስ ሊሄዱ እንደሚችሉ መገመት አያዳግተንም፡፡ ግብጾች ይህንን ካደረጉ፣ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የማሳረፍ አቅም ያለው የአሜሪካውያን ይሁዲዎች ማኅበር (AIPAC) እና ሌሎችም የጽዮናውያን ድጋፍ አሰባሳቢ ቡድኖች (The Zionist Lobby) ኢትዮጵያ የግብጽን ጥቅም የሚጎዳ አንዳችም ነገር እንዳትሠራ ታደርግ ዘንድ በአሜሪካ መንግሥት ላይ ጫና ሊያሳድሩ ይችላሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ከተፈጠረ ኢትዮጵያ በአባይ ግድብ ላይ የምታካሂደው የኃይል ማመንጫ ግንባታ ፈተና ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡

Blue-Nile-Falls-Ethiopia

የዘመነ ደርግ እርስ በርስ ጦርነቶች እልቂትመንግሥቱ ኃይለማርያም ሰው የሚመክረውን የማያዳምጥ አምባገነን መሪ ነበር፡፡ የአገራችን ታላላቅ ጄነራሎችን በሥራ ለመጥመድ ሲል ብቻ፣ ማለትም ሰላም ከሰፈነ ጄነራሎቹ ለሥልጣኔ ያሰጉኛል ብሎ ስለሚያስብ፣ የአገሪቱ ሠራዊት ከሻዕቢያና ከወያኔ ጋር ያደርግ የነበረውን ጦርነት በሰላማዊ እና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የመፍታት አማራጭን በፍፁም አልቀበልም ብሎ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጰያውያንን ለጦርነት ገበረ፡፡ በመጨረሻ ምን አገኘን? ምንም፡፡ ያጣነው ግን ተቆጥሮ አያልቅም፡፡ የግንቦት 8፣ 1981 መፈንቅለ መንግሥት መክሸፉን ተከትሎ አገሪቱ በዘመናት ያፈራቻቸውን ብዙ የጦር ጄነራሎች አጣች፡፡ የባህር በራችንን ጨምሮ በቀ.ኃ.ሥ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ከእናት አገሯ ጋር ተዋህዳ የነበረችው ኤርትራ ተገነጠለች፡፡ ተገንጥሎ የራስን ሰንደቅ ዓላማ ማውለብለብ ብቻውን ዳቦ ባይሆናትም፣ ስንትና ስንት ሺህ ዜጋ የረገፈላት ኤርትራ ተገነጠለች፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራ ሁለት አገሮች መሆናቸው የኋላ ኋላ በአያሌ የሁለቱ አገሮች ህዝቦች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡ በ1985 የኤርትራ ሬፈረንደም ሲካሄድ፣ ኤርትራውያን ከ“ባርነት” እና ከ“ናፅነት” ምረጡ ተብለው 99.9 ከመቶዎቹ “ናፅነት”ን መረጡ፡፡ ዛሬ የኤርትራ ህዝብ የ“ናፅነት” አየር እየተነፈሰ ነውን? እኔ አይመስለኝም፡፡ … የሆነ ሆኖ መንግሥቱ ኃይለማርያም በራስ ወዳድነቱ ምክንያት የኢትዮጵያን ህዝብ ለዘረኛው ወያኔ አሳልፎ ሰጥቶ ፈረጠጠ፡፡ ወያኔ በሻዕቢያ ጫንቃ ታዝሎ አዲስ አበባን ተቆጣጠረ፡፡

የዘመነ-ህአዴግ ምንም ያላስገኘ የጦርነት እልቂት

ሻዕቢያ ከወያኔ ጋር ተቃቅፎ አዲስ አበባ እንደገባ የመጀመርያ እርምጃው የኢትዮጵያን ወታደራዊ አቅም ማሽመድመድ ነበር፡፡ በዚህም ዓላማ ግንቦት 20 ወይም 21 ቀን 1983 ሸጎሌ የሚገኘውን ለጥይት አረር መሥሪያ የሚውል የኬሚካል መጋዘንን፣ በሳምንቱ ደግሞ ጎተራ የሚገኘውን የጥይት መጋዘን አፈነዳ፡፡ በሸጎሌው ፍንዳታ በርካታ የሸጎሌ አካባቢ ነዋሪዎች ለአሰቃቂ እልቂት ተዳረጉ፡፡ ከዚህም በኋላ በመጀመርያዎቹ ሰባት ዓመታት ሻዕቢያ በኢትዮጵያ ላይ ለማመን የሚያዳግቱ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሸፍጦች ሠራ፡፡ … ያ ሁሉ አልፎ በ1991 ሻዕቢያ ባድመን እና ከፊል ሺራሮን ወረረ፡፡ ከማንም ቀድሞ ለነፃይቱ ኤርትራ የሃገርነት እውቅና የሰጠው ወያኔም “ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻችን ደም፣ እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም”ን እያስዘፈነ፣ ህዝቡ በአባቶቹ ደም ተከብሮ የኖረውን ዳር ድንበሩን እንዲያስከብር ጥሪ አደረገ፡፡ ለዚህ ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ ያልሰጠ ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም፡፡

በአገር ውስጥም ሆነ በባህር ማዶ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ተቃዋሚ ኃይሎችም በወያኔ አገዛዝ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ወደጎን በማድረግ “የአባቶቻችንን የአልደፈር ባይነት ታሪክ” ለማደስ ከመለስ ዜናዊ አምባገነን መንግሥት ጎን ተሰለፉ፡፡ ህዝቡ በአንድነት ተነሳ፡፡ ህዝቡም ሆነ ተቃዋሚ ኃይሎች “የአገራችንን ሉዓላዊነት ካስከበርን በኋላ በድል ማግሥት የመለስ ዜናዊ መንግሥት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጎልበት የሚረዱ አዎንታዊ እርምጃዎች ይወስዳል” የሚል ተስፋ ነበራቸው፡፡ ነገር ግን ይህ ዕውን አልሆነም፡፡ ከዚያ በላይ የሚያሳዝነው በወረራ የተያዙትን መሬቶች በሰላማዊ መንገድ ለማስለቀቅ የተደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተሟጥጠው ካበቁ በኋላ፣ ሻዕቢያ “ከያዝሁት መሬት አንዲት እርምጃ ወደኋላ አልሄድም፤ ከቻላችሁ በጦርነት አስለቅቁኝ፤ ጉዳዩ በደም ይፈታ፤ መሬቱን ተዋግቶ ያሸነፈ ይውስድ” አለ፡፡ እናም በጊዜው ስንል እንደነበረው “ተገድደን በገባንበት ጦርነት” በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ደማቸውን አፍስሰው ባድመንና ሺራሮን፣ በቀጣይነትም ሁሉንም በወረራ የተያዙ መሬቶች አስለቀቅን፡፡ ከዚያስ?

… ከዚያማ በሚያስገርም ሁኔታ መለስ ዜናዊ እስከ አርባ ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ደማቸውን ባፈሰሱባቸውና አጥንታቸውን በከሰከሱባቸው መሬቶች ላይ ለመዳኘት እጅግ አሳፋሪውንና አሳዛኙን የአልጀርስ ስምምነት ፈረመ፡፡ መለስ በደምና በአጥንት የተፈታውን የድንበር ውዝግብ እንደ አዲስ በዓለምአቀፍ ፍርድ ቤት እንዲዳኝ መስማማቱ ሳያንስ፣ ይባስ ብሎ ሊታመን የማይችል ታላቅ ስህተት ደገመ፡፡ ዓለምአቀፉ ፍርድ ቤት ጉዳዩን አፄ ምኒሊክ ከጣሊያን ጋር በተፈራረሙት ውል መሠረት እንዲፈታው ተስማማ፡፡ እንደሚታወቀው ጣሊያን ይህንን ውል አፍርሶ በ1928 መላ ኢትዮጵያን ወርሯል፡፡ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በዚህ የሞተ ውል ላይ ተመሥርቶ የድንበሩን ጉዳይ ሲዳኝ፣ ባድመን ለኤርትራ ፈረደላት፡፡ “ዕድሜ ለመለስ ዜናዊ” በ40 ሺህ ኢትዮጵያውያን ደም ላይ ተፈረደ፡፡ “አወዛጋቢ መሬቶቹን ያሸነፈ ይውሰድ” በሚለው የኢሳያስ መንገድ ሄደን አሸንፈን ባድመ የእኛ መሆኗን በደማችን አረጋግጠን ስናበቃ፣ በመለስ ዜናዊ የእብድ መንገድ “ባድመ የእናንተ አይደለችም” ተባልን፡፡ ጮሌው መለስ የሠራውን ታሪካዊ ስህተት አንድም ቀን ሳያምን፣ ጉዳዩን በ“ሰጥቶ መቀበል” መርኅ ስለመፍታት እንዳወራ በሰሜኑ ድንበራችን ከኤርትራ ጋር እንዳፋጠጠን ወደማይቀርበት ተጓዘ፡፡

ዴሞክራሲ ሆይ የት ነሽ? …

በጦርነቱ ማግሥት፣ አያሌ ኢትዮጵያውያን ተስፋ አድርገውበት የነበረው የአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት የመሻሻል ሁኔታ አላሳየም፡፡ በተለይ ከ1997 በኋላ፣ የኢህአዴግ አምባገነንነት እያየለ፣ የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይበልጥ እየተረገጡ፣ ፍትኅ ከዕለት ወደ ዕለት እየጠፋች ዛሬ እምንገኝበት አሳፋሪና አሰዛኝ የሥርዓቱ የዝቅጠት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ ዜጎች በህገ መንግሥት የተረጋገጡ መብቶቻቸውን ተጠቅመው መንግሥትን በተቃወሙ፣ ህገ መንግሥታዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩ በጠየቁ አሸባሪ፣ ጽንፈኛ፣ አክራሪ እየተባሉ ይብጠለጠላሉ፡፡ … መለስ ዜናዊ በድምሩ የ70 ሺህ ወንድማማቾች ደም ከፈሰሰበት የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ጋር በተያያዘ የአያሌ ኢትዮጵያውያን ደም የተከፈለባቸውን መሬቶች ለዳኝነት በማቅረብ የሠራው ታሪካዊ “ስህተት[?]” የተረሳ ይመስላል፡፡ [እውን ተረስቶ ይሆን?]

“አባይን የደፈረ መሪ!” — ጀብድ እና አምባገነንነት …

እነሆ ከኅልፈቱ ማግሥት ጀምሮ መለስ ዜናዊ “ታላቁ መሪ”፣ “አባይን የደፈረ ጀግና” ወዘተ. በሚሉ ቅፅሎች እየተሞካሸ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የኃይል ማመንጫ ግድብ ለመሥራት እንቅፋት ሁኖባት የነበረውን የግብፅና ሱዳን የ1949 (እ.አ.አ.) ስምምነት የሚገዳደር አዲስ ስምምነት በስድስት የተፋሰሱ አገራት መካከል እንዲፈረም ውጤታማ የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራቷና በዚህ ውስጥም መለስ ቁልፍ ሚና መጫወቱ አይታበልም፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ በአባይ ላይ ግድብ ለመሥራት ያኮበኮበችው እንደሚባለው የራሷን አቅም በመተማመን ብቻ አይመስለኝም፡፡ ከዚህ ጀርባ ኃያሏ አገር አሜሪካ ያለች ይመስለኛል፡፡ አሜሪካ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከኢትዮጵያም በላይ የግብፅ ወዳጅ ነበረች፡፡ የአሜሪካ እና የግብፅ ወዳጅነት ደግሞ የእስራኤልን ጥቅም ማዕከል ያደረገ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን፣ ካለፉት አሥር ዓመታት ገደማ ወዲህ አሜሪካ ለግብፅ በምትሰጠው ከፍተኛ የፋይናንስ እና ወታደራዊ ድጋፍ ዙርያ በአሜሪካ ኮንግረስ ውስጥ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ሲነሱ ቆይተዋል፡፡ የጥያቄው መንፈስ “እየረዳንና እያስታጠቅን ያለነው የነገይቱን የእስራኤል ጠላት ሊሆን ስለሚችል፣ ይህ ነገር ይታሰብበት” የሚል ነበር፡፡ ይህ ጥያቄ መነሳት የጀመረው በግብፅ “ሙስሊም ወንድማማቾች” የተሰኘው ፓርቲ በታችኛው የግብፅ ማኅበረሰብ ዘንድ ሰፊ መሠረት እየጣለ መሆኑን ከመረዳትና ውሎ አድሮ ወደ ሥልጣን ሊመጣ እንደሚችል ከመስጋት የመነጨ ነበር፡፡ ይህ ስጋት፣ ስጋት ብቻ ሁኖ አልቀረም፡፡ የእስራኤል፣ እናም የአሜሪካ ወዳጅ የነበረው ሙባረክ በሕዝባዊ አብዮት ተወግዶ፣ በአገሪቱ በተካሄደ ምርጫ የ“ሙስሊም ወንድማማቾች” ፓርቲ ሥልጣን ለመጨበጥ ችሏል፡፡ አሜሪካኖቹ ይህ ዕውን እንደሚሆን አስቀድመው አውቀው ነበር ማለት እንችላለን፡፡ ከዚህም በመነሳት ለአያሌ ዓመታት ከግብፅ ጎን ቆማ የኖረችው አሜሪካ፣ ኢትዮጵያ በአባይ ላይ ለምትሠራው ግድብ ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ የምታደርገው በነዚህ ጂኦ ፖለቲካዊ ስሌቶች ላይ በመመሥረት ይመስለኛል፡፡

ስሌቱ ቢቀየርስ? …

“ግብፆች ከማንኛውም ነገር፣ ሌላው ቀርቶ ከሃይማኖታቸውም በላይ አገራቸውን ያስቀድማሉ” ይባላል፡፡ አገራቸው አገር የሆነችው ደግሞ በናይል ወንዝ አማካይነት ነው፡፡ ይህ አባባል እውነት ከሆነና ግብፆች ለናይል ሲሉ ማንኛውንም ነገር ከማድረግ የማይመለሱ ከሆነ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ጦር ከመማዘዝ የቀለለ አንድ አማራጭ በእጃቸው አለ፡፡ እርሱም እ.አ.አ. በ1978 ከእስራኤል ጋር የተፈራረሙትን የካምፕ ዴቪድ ስምምነት (Camp David Accords) አረረ መረረ ሳይሉ በማክበር ከእስራኤል ጋር ያላቸው ወዳጅነት ፀንቶ እንዲኖር ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ይህንን አያደርጉትም ማለት አይቻልም፡፡ ሲያደርጉት ደግሞ አባይን መደራደሪያ ማድረጋቸው አይቀርም፡፡ የግብፁ ፕሬዚደንት አንዋር ሳዳት የሲናይ በረሃን ከእስራኤል በማስመለስ በግብፅ ሕዝብ ተቀባይነት ለማግኘት ሲል የአረብ አገራትን በሙሉ ጥሎና የፍልስጥኤምን ጥያቄም ችላ ብሎ የካምፕ ዴቪድ ስምምነትን እንደፈረመ ስናስብ፣ ግብጻውያን ለአባይ ውሃ ሲሉ እስከምን ድረስ ሊሄዱ እንደሚችሉ መገመት አያዳግተንም፡፡ ግብጾች ይህንን ካደረጉ፣ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የማሳረፍ አቅም ያለው የአሜሪካውያን ይሁዲዎች ማኅበር (AIPAC) እና ሌሎችም የጽዮናውያን ድጋፍ አሰባሳቢ ቡድኖች (The Zionist Lobby) ኢትዮጵያ የግብጽን ጥቅም የሚጎዳ አንዳችም ነገር እንዳትሠራ ታደርግ ዘንድ በአሜሪካ መንግሥት ላይ ጫና ሊያሳድሩ ይችላሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ከተፈጠረ ኢትዮጵያ በአባይ ግድብ ላይ የምታካሂደው የኃይል ማመንጫ ግንባታ ፈተና ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡

የግብፅ የጦርነት ነጋሪት እና የኢትዮጵያ ፉከራ

በአባይ ወንዝ ላይ የግድብ ግንባታ እየተካሄደ ባለበት በአሁኑ ሰአት ከወደ ግብፅ በኩል የግጭት አማራጭ እየተብሰለሰለ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ለዚህ ነጋሪት እየተሰጠ ያለውን ምላሽ አብዝቼ ባልከታተልም [ኢቲቪን ስለተጠየፍሁት]፣ ከኢህአዴግ መንግሥት አንዳንድ ባለሥልጣናት የተሰነዘሩ ድንፋታ አከል አስተያየቶችን አንብቤአለሁ፡፡ የግድቡ ግንባታ ከመጀመሩ በፊትና ከተጀመረም በኋላ እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ የነበረው ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ጤናማ ሁኖ ሳለ፣ ግብፆች ስለደነፉ የእኛም መንግሥት ለመደንፋት መጋበዙ በእኔ እምነት ምንም ጠቀሜታ የለውም፡፡ ከወደ ግብፅ የኃይል አማራጭ እየተብሰለሰለ መሆኑን ስለሰማን ብቻ እኛም “ዘራፍ!” እያልን ማቅራራት የትም ላያደርሰን ይችላል፡፡ ከማቅራራት በፊት የዜጎችን ስሜት ማዳመጥም መልካም ነው፡፡

… የዜጎች እንባ ይገደብ!

ከማቅራራቱ በላይ አገራችንን እጅግ በጣም የሚጎዳትና ወደፊትም ውጤቱ አስከፊ የሚሆነው ግን የኢህአዴግ ወደ አምባገነንነት ማማ የመውጣት አካሄድ ነው፡፡ በአሁኑ ሰአት ኢህአዴግ ከፍተኛ የሆነ “ማን አለብኝነት” ተጠናውቶታል፡፡ “ልማታዊ ነኝ” እያለ በመመፃደቅ እየፈፀመ ያለው የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች ገፈፋ፣ አያሌ ዜጎች “ከአባይ በፊት የዜጎች እንባ ይገደብ!” የሚል መፈክር እንዲያስተጋቡ እያስገደደ ነው፡፡ በእርግጥም የዜጎች እንባ ሌት ተቀን እየፈሰሰ፣ በዜጎች የመብትና የነፃነት ጥያቄዎች ላይ እየተላገጠ፣ ኢህአዴግ ይመስለዋል እንጂ፣ በዚህ አካሄድ ይህቺ አገር የትም አትደርስም፡፡ ከህዝብ ተነጥሎ አገር ትርጉም የለውም፡፡ የህዝቦችን ሉዓላዊነት አለማክበር ለአገር ሉዓላዊነትም ቢሆን አይበጅም፡፡ ልማት በዜጎች ላይ የሚፈፀም አፈናን፣ ጭቆናን፣ እንዲሁም የመብትና የነፃነት ገፈፋን ተገቢ አያደርግም፡፡ ኢህአዴግ ግን የዜጎችን በነፃነት የማሰብ፣ የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመደራጀት ወዘተ. መብቶች ብቻ ሳይሆን፣ የሃይማኖት እና የእምነት ነፃነትንም ጭምር እየረገጠ ነው፡፡ ይህ የዜጎችን ሰብአዊ ክብር እጅግ የሚዳፈር፣ በምንም መለኪያ ተቀባይነት የሌለው እና ሊኖረውም የማይችል አካሄድ ነው፡፡

ነገሮችን በጀብደኝነት ስሜት ብቻ ማቀንቀን የትም አያደርስም፡፡ ስለ አገራችን ሉዓላዊነት ስንጨነቅ፣ ስለ ህዝቦች ሉዓላዊነትም እንጨነቅ፡፡ መንግሥቱ ኃይለማርያም “ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻችን ደም” እያስዘፈነ ስንትና ስንት ዜጎችን በጦርነት እሳት ማገደ፡፡ ከኪሳራ በቀር ምንም የተገኘ ነገር የለም፡፡ መለስ “አፋር አሎ በሎ” እያስዘፈነ ስንትና ስንት ወጠቶችን በጦርነት እሳት ማገደ፡፡ ከኪሳራ በቀር ምንም የተገኘ ነገር የለም፡፡ … አሁንም፣ “አባይ አባይ” እያስዘፈኑ፣ በአባቶቻችን ቀረርቶ ዜጎችን በመቀስቀስ በጦርነት እሳት ስለመማገድ የሚያስብ ካለ፣ ደግሞ ቢያስብ ጥሩ ነው፡፡ ለጦርነት የሚጠራው ዜጋ፣ ስለ ዜግነት መብት እና ነፃነቱ መከበር ሲጮህም ሰሚ ቢያገኝ መልካም ነው፡፡ አባይ መገደቡ መልካም ነው፡፡ የዜጎች እንባ መገደቡ ደግሞ እጅግ በጣም መልካም ነው፡፡

=================================
ይህንን ጽሑፍ ወንድም አንዋር አንዋር ጽፎ አስተያየት እንድሰጠው በላከልኝ አንድ ጽሑፍ መነሻነት ነው የጻፍሁት፡፡ አነሳሴ አስተያየት ለመስጠት ብቻ ነበር፡፡ ሳላውቀው ግን ከአስተያየት ዘለግ ያለ ጽሑፍ ወደ መጻፉ ገባሁ፡፡ እናም፣ የጽሑፉ ሐሳብ የመነጨው፣ ወይም ጽሑፉን እንድጽፍ የጫረኝ ወንድም አንዋር አንዋር መሆኑን ታሳቢ በማድረግ አንብቡት፡፡ …
=================================

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *