የአቶ ማርክነህ ወንድም አቶ ብርሃኑ አለማየሁ የተጠረጠርኩበት ወንጀል እውነት ነው ሲሉ ለፍርድ ቤቱ አረጋገጡ።

በእነ አቶ መላኩ ፈንታ የክስ መዝገብ በ8ኛ ተራ ቁጥር ተጠቅሰው በትናትናው የችሎት ውሎ ከወላይትኛ ቋንቋ ውጭ አማርኛ እንደማይናገሩ በመግለጻቸው ነው ዛሬ ችሎቱ ጉዳያቸውን በአስተርጓሚ ለማየት አሳድሮ የነበረው።

የፌዴራሉ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የምርመራ ቡድን በእርሳቸው ላይ እነ አቶ መለካ ፈንታን ጨምሮ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆባቸው ፥ በቋንቋ ምክንያት የቃል ክርክር ሳያካሂዱ ቀርተው ዛሬ በአስተርጓሚ ሃሳባቸውን ገልጸዋል።

እኔ አርሶ አደር ነኝ ፤ ወንድሜ ማርክነህ ቤት የምሰራበት ገንዘብ ነው አስቀምጥልኝ በማለት በማላውቀው መንገድ ጉድ ሰርቶኛል ሲሉ ለችሎቱ አስረድተዋል።

በመሆኑም ጥፋቴን ያመንኩ በመሆኑ የዋስትና መብቴ ይከበርልኝ ሲሉም ጠይቀዋል።

የኮሚሽኑ የምርመራ ቡድን በበኩሉ ምንም እንኳን ጥፋታቸውን ቢያምኑም ተቀብሮ የነበረው ገንዘብ ከአዲስ አበባ በምን አይነት ሁኔታ ወደ ወላይታ እንደደረሰ ለማጥናት ምርመራ የተጀመረ ስለሆነ የዋስትና ጥያቄውን ፍርድ ቤቱ ውድቅ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ የወንጀል ችሎትም ከምርመራው አዲስነት ጋር ተያይዞ በቡድኑ የቀረበውን የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ በመፍቀድ ለሰኔ 18 ቀን 2005 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

በሌላ በኩል ችሎቱ 12 ተጠርጣሪዎች በሚገኙበት መዝገብ ላይ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

በዚህ መዝገብ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የናዝሬት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የስራ ሃላፊዎች ፣ ደላሎች ፣ ትራንዚተሮች እና የትራንዚተር ባለቤቶች ናቸው።ተጠርጣሪዎቹ አቶ መሃመድ ኢሳ ፣ አቶ ሰመረ ንጉሴ ፣ አቶ ዳኜ ስንሻው ፣ አቶ ዘሪሁን ዘውዴ ፣ አቶ ማርሸት ተስፋዬ ፣ አቶ ሙሉቀን ተስፋዬ እና ወይዘሮ ህይወት ጌታቸው ናቸው።በእነዚህ ላይ የምርመራ ቡድኑ ባለፈው በተሰጠው የ12 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ላይ ዛሬም ለሁለተኛ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

ቡድኑ የተከናወኑ እና ያልተከናወኑ የምርመራ ስራዎችን በመጥቀስ በተጠየቀባቸው የጊዜ ቀጠሮ ላይ የተጠርጣሪ ጠበቆች ተቃውሞን  አሰምተዋል  ። ችሎቱም ግራ ቀኙን ተመልክቶ የ14 ቀናት ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል።

 ሌላኛው መዝገብ የብስራትና ናትራን ኩባንያ ባለቤት እንደሆኑ የሚነገርላቸው አቶ ባሃሩ አብርሃ እና ሌሎች 4 ግለሰቦች ያሉበት መዝገብ ነው።በተመሳሳይ የምርመራ ቡድኑ ጅምር የምርመራ ስራዎችንና የቀሩትን በመጥቀስ ተጨማሪ የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል።ፍርድ ቤቱ በተጠርጣሪ ጠበቆች የቀረበውን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የተጠየቀውን የጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል።የምርመራ ውጤቱን ለመጠበቅም ለሰኔ 19 ቀን 2005 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 4 ፣ 2005 (ኤፍ ቢ ሲ)

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *