·        የ544 ሰዎች ሀብት እንዳይንቀሳቀስ ታግዷል

 የፌዴራሉ የሥነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በሕገወጥ መንገድ ሀብት አከማችተዋል፣ ስልጣናቸውን ያለአግባብ ተጠቅመዋል፣ የታክስና የቀረጥ ማጭበርበር ፈፅመዋል፣ የጉምሩክን ስርዓት ባልተከተለ መንገድ ከትራንዚት ድርጅቶች ባለቤቶችና ደላሎች ጋር በመመሳጠር የተለያዩ ዕቃዎች ፍተሻ ሳይደረግባቸው ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ አድርገዋል ሲል በሙስና ወንጀል ጠርጥሮ ክስ ከመሰረተባቸው 60 ግለሰቦች መካከል በ1ኛው መዝገብ ስር የተጠቀሱት ሰባት ባለስልጣናትና ነጋዴዎች በትንሹ ከ230 ሚሊዮን ብር በላይ መንግስትን አሳጥተውታል አለ።
577735_3392435245065_1095175962_32588391_619919939_n
በዚህም መሠረት ከባለስልጣናቱ እና ከባለሃብቶቹ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሎ የታመነባቸውን 544 የሚደርሱ ቤተሰቦች ሀብት እንዳይንቀሳቀስ በፍርድ ቤት በኩል የዕግድ ትዕዛዝ አስተላልፎባቸዋል። በሕገወጥ መንገድ የማይገባቸውን ጥቅም አግኝተዋል፤ በዚህም ከባለስልጣናቱና ባለሀብቱ ጋር ግለሰቦቹ በእጅጉ ትስስር አላቸው ሲል በማመኑ በተፈፀመው የሙስና ወንጀል በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ጉዳት አድርሷል ያለው የመርማሪ ቡድኑ፤ በተጠርጣሪዎቹና በቤተሰቦቻቸው ላይ ባስፈፀመው የዕግድ ትዕዛዝ መሠረት በባንክ የሚገኝ ጥሬ ገንዘብ፣ የአክሲዮን ባለቤትነት ድርሻና የከበሩ ማዕድናት እንዳይንቀሳቀሱና ለሦስተኛ ወገን እንዳይተላለፉ እንዲታገድ አድርጓል።
ከዚህም በተጨማሪ ኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን 92 የተለያዩ ተሽከርካሪዎችን እግድንም ተፈፃሚ አድርጓል። ከነዚህም ተሽከርካሪዎች መካከል ከተጠርጣሪዎቹ አንዱ በሆኑት በአቶ ነጋ ገ/እግዚአብሔር ስም የተመዘገቡ ናቸው። ቀሪዎቹ ሁለቱ ተሽከርካሪዎች በኮሎኔል ሃይማኖት ተስፋዬ ማለትም የአቶ ገብረዋህድ ወ/ጊዮርጊስ ባለቤት ስም፤ 4ቱ ተሽከርካሪዎች ደግሞ የአዳማ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ሠራተኛ በነበሩት በአቶ አሞኘ ታገለ ስም የተመዘገቡ መሆናቸው ታውቋል። የተቀሩት 4ቱ ደግሞ ከውጪ ሀገር የሚመጡ ባለሃብቶች ያለቀረጥ ዕቃዎቻቸውን እንዲያስገቡ ለጉምሩክ ሰራተኞች ጉቦ አቀባብለዋል ተብለው በተጠረጠሩት አቶ ዳዊት መኮንን ስም የተመዘገቡ ናቸው። ሌሎች 7 ተሽከርካሪዎች በአልቲሜት ፕላን ኃላ/የተ/የግ/ማኅበር ስም እና 6 የሚሆኑት በይትባ ኮንስትራክሽን ማሽነሪ፣ አከለ ኃላ/የተ/የግ/ማኅበር ስም ነው ተመዝግበው የሚገኙት ይላል የመርማሪ ቡድኑ ሐተታ።
የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን የባንክ ገንዘብ፣ የአክሲዮን ድርሻና የከበሩ ማዕድናትን በተመለከተ ያቀረባቸው ዕገዳዎች ተፈፃሚ ያደረገውን ትዕዛዝ ተፈፃሚነት ግልባጭ ለፍትህ ሚኒስትር በሰነዶችና ማረጋገጭ ጽ/ቤት እና ለአስሩም ክፍለ ከተሞች ማሳወቁን አትቷል። ይህ ጉዳይ የአቶ መላኩ ፈንታን መዝገብ እንጂ ሌሎችን የተመለከተ እንዳልሆነም ታውቋል። በዚህም የተጠርጣሪዎች ጉዳይ በፍርድ ቤት ዕልባት ሲያገኝ ማንኛውንም ሀብት ሊያንቀሳቅሱና ለ3ኛ ወገን ሊያስተላልፉ እንደሚችሉም ጠቁሟል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ትናንት እና ከትናንት በስቲያ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት በነበረው ቆይታ በእነ አምባው ሰገድ አብርሃ እና በእነ ዳዊት ኢትዮጵያ መዝገብ የተጠየቀውን የተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ፍ/ቤቱ ተቀብሎ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
መርማሪ ቡድኑ በባለስልጣኑ የከፍተኛ ግብር ከፋዮች የህግ ማስከበር ሃላፊ በሆኑት በአቶ አምባውሰገድ አብርሃም ስር 11 ተጠርጣሪዎች የሚገኙ ሲሆን፤ 1ኛው ተጠርጣሪ ከባለስልጣኑ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በመመሳጠር በከፍተኛ ደረጃ የተመሰረቱ ክሶችን አቋርጠዋል፤ እንዲሁም ስልጣናቸውን በመጠቀም ዕቃዎች ሳይፈተሸ ወደሀገር ውስጥ አስገብተዋል። እንዲሁም ለጠቋሚዎች የተፈቀደን አበል ለግል ጥቅም ማዋል የሚሉት ተጠቅሶባቸዋል። በችሎቱ የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን ያከናወናቸውን እና የሚቀሩትን ጉዳዮች በዝርዝር ካስረዳ በኋላ ፍርድ ቤቱን የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜን ጠይቋል።
የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች በበኩላቸው መርማሪ ቡድኑ ሰነዶችን ከቤትና ከመስሪያ ቤት የሰበሰበ በመሆኑ፣ የምስክሮችንም ቃል የወሰደና ኦዲት የሚደረጉ ሰነዶችን በማስተንተን ማስረዳቱን አትቶ እነዚህን ተግበራት ለማከናወን የደንበኞቻቸውን በእስር መቆየት ግድ አይልም ሲሉ በመከራከር ፍርድ ቤቱ በደንበኞቻቸው የዋስትና መብት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድኑም የወንጀሉን ውስብስብነትና በመመሳጠር የተሰራ መሆኑን በማስረዳት ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢለቀቁ ማስረጃዎችን ከማጥፋትም በላይ ምስክሮቻችንን ሊያባብሉና ሊያሸማቅቁ ይችላሉ በሚል የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎትም የመርማሪ ቡድኑን የ14 ቀናት ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ በመቀበል በሰኔ 24 ቀን 2005 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል።
በሌላም በኩል በትናንትናው ዕለት ጉዳያቸው በፍርድ ቤቱ የታየው በእነ ዳዊት ኢትዮጵያ መዝገብ ስር ከተጠቀሱት 7 ተሽከርካሪዎች መካከል አቶ ኮነ ምህረቱ በነፃ መሰናበታቸውን ተከትሎ የስድስቱን ተጠርጣሪዎች ጉዳይ ተመልክቷል።
በዚህም መዝገብ ስር መርማሪ ቡድኑ ያከናወናቸውን ተግባራት ሲገልፅ፤ በሁሉም ተጠርጣሪዎች ላይ በከፊል የምስክሮችን ቃል መስማቱን እና በከፊልም የሰነድ ማስረጃዎችን ማሰባሰቡን አስታውቋል። ከ1ኛ እስከ 6ኛ ያሉ ተጠርጣሪዎች ከትራንዚት ድርጅቶች ጋር በመመሳጠር ዕቃዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ አመቻችተዋል ያስባሉ ሰነዶችም ተሰብስበዋል ብሏል። ከዚህም በተጨማሪ ወደ አዳማ ሰዎችን በመላክ ስራዎች በመሰራት ላይ መሆናቸውን ገልጿል። በ4ኛ፣ በ5ኛ እና በ6ኛ ተጠርጣሪዎች ላይ ያገኛቸውን መረጃዎች በሚመለከት የቴክኒካል ባለሙያዎችን ምስጢርነት እየጠበቀ መሆኑንም አስታውቋል።
በሌላ በኩል መርማሪ ቡድኑ 10 የሚጠጉ የኦዲት ሪፖርቶችን መመርመር፣ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ያሉ ተጠርጣሪዎች በሕገወጥ መንገድ ቀረጥ ሳይከፈልባቸው የገቡ ዕቃዎችን በተመለከተ ያለውን የኦዲት ማስረጃ ማሰባሰብና የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ከአዳማ በማስመጣት የባለሙያዎችን ምስክርነት መስማት እንደሚቀረው አስታውሷል። በዚህም ፍ/ቤቱ ተጨማሪ የ14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ እንዲፈቅዱለት ጠይቋል።
ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው የተጠየቀው የ14 ቀን ቀጠሮ ተገቢ አለመሆኑን፤ ደንበኞቻቸው በዋስ ወጥተው ሊፈፀሙ የሚችሉ ተግባራት መሆናቸውን በመጥቀስ ተከራክረዋል።
የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎትም መርማሪ ቡድኑ ያቀረበው ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ በመቀበል ለሰኔ 24 ቀን 2005 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።  በአሸናፊ ደምሴ 

የሰንደቅ ዜናዎች (ሰኔ 12/2005)

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *