- Tuesday, 25 June 2013 16:32
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት በእነ መላኩ ፋንታ የተጠርጣሪ መዝገብ ላይ ለ4ኛ ጊዜ የተጠየቀውን የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ፈቀደ፡፡
በዚህ መዝገብ ከነበሩ የተጠርጣሪዎች አቶ ማርክነህ አለማየሁ አሽሽተውት የነበረውን 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ገንዘብ በማሸሽ ሂደት ተሳትፈዋል በሚል የተያዙት ሁለት ተጠርጣሪዎች ምርመራቸው በመጠናቀቁ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በዋስ እንዲለቀቁ አመልክቷል፡፡
ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ አቃቤ ህግ የጠየቀውን ተጨማሪ የ14 ቀን ቀጠሮ መፈቀዱ በደንበኞቻቸው ላይ የዋስትና መብት እያሳጣቸው መሆናቸውን ጠበቆች አስረድተዋል፡፡ይህም አቃቤ ህግ በተሰጠው የጊዜ ቀጠሮ በአግባቡ ባለመጠቀሙ እንደሆነ ነው የገለፁት ፡፡
መርማሪው ክፍል በተሰጠው የጊዜ ቀጠሮ ከአራጣ ማበደር ጋር የተያያዙ በቂ ማስረጃዎችንና ጥቆማዎችን መመርመሩን አስታውቋል፡፡ በሁሉም መዝገቦች ላይ 96 የቃል ምስክሮችን መቀበሉንና ነገር ግን 74 የቃል ምስክሮች እንዲሁም 60 ሙያዊ ትንታኔ የሚሰጡ ምስክሮችን ቃል መቀበል እንደሚቀረው አስረድቷል፡፡
ክርክሩን ያዳመጠው ከፍተኛው ፍርድ ቤት የምርመራ ቡድኑ ቀደም ብሎ በተሰጠው የጊዜ ቀጠሮ መሰረት መስራት የሚገባውን ያህል እንደሰራ አረጋግጧል፡፡ይሁን እንጂ ወደፊትም የሚቀሩ ስራዎች በመኖራቸው የተጠየቀው የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ መፍቀዱን ገልጿል፡፡
ፍርድቤቱም የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ባለመቀበል ተለዋጭ ቀጠሮውን ለሀምሌ 2/2005 ዓም ሰጥቷል፡፡
ሪፖርተር ሀብታሙ ጣሂር http://www.ertagov.com