አንተ ማነህ?

(ኢትዮጵያዊነት በእውነት ሚዛን ሲመዘን)

who are u

June 27, 2013 07:12 am By  Leave a Comment

“… እንዲያውም ይህ በሽታ አልበቃ ብሎን ከዚህ በባሰ መልኩ መቀሌ ከተማ ላይ አደዋና መቀሌዎች፣ ባሕርዳር ከተማ ላይ ጎንደሬ፣ ጎጃሜ፣ ወሎዬና ሸዌ፣ናዝሬት ከተማ ላይ የወለጋ፣ የባሌ፣ የአሩሲና የሸዋ ኦሮሞዎች፣ አዋሳ ከተማ ላይ ሀዲያ፣ ከንባታ፣ ወላይታ ሶዶ ወዘተ በማለት የሚታየው የሹመትና የጥቅም ሽኩቻ ዘመነ መሳፍንትን ምስጋና ይግባው የሚያሰኝ ሆኗል (ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል እንዲሉ)፡፡ …

“በተቃዋሚው ጎራ የተሰለፉት ፖለቲከኞቻችንም ቢሆኑ የስልጣን እድሉ ቢገጥማቸው ምን ሁኔታ እንደሚፈጠር ለመገመት ነቢይ መሆን አያስፈልግም፡፡ (አብዛኛዎቻችን ከቂም በቀል አዙሪት ገና ያልወጣን በመሆኑ) ይህን ያልኩትም ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ያሳዩት አሳፋሪ ንትርክና የትዕቢት ባሕሪ በቂ የማንነት መገለጫ ስለሆነ ነው፡፡ …

“… (ስለዚህ) ሰው ሆኖ ሰው ያለመሆን ማንነት” አለ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ከውጭ አንተ ማነህ? ወይም በተሻለ መልኩ ከውስጥ እኔ ማነኝ? ለሚለው ጥያቄ ለራሳችን ተገቢ የሆነ መልስ ካላገኘን በሕይወት መንገዳችን ላይ ቀይ መብራት በርቶብናል ማለት ስለሆነ እንደ አስተዋይ ሰው ቆም ብለን ብናስብ ጥቅሙ ለራሳችን ብሎም ለምድራችን ሊተርፍ ይችላል፡፡ ሰውነቱ በትክክል ያልገባው ሰው ደግሞ ከራሱ ውጪ ለሌላው ሰው አያስብም፡፡ አስባለሁ ቢልም በምክንያት እንጂ ዘላቂነት ባለው ምክንያት የለሽ ፍቅር አይደለም፡፡ የግል ዓላማ ሲሳካ የሚረሳው ስለሆነ፡፡ …

“ከዚህ ጠቅላላ የመንደርደሪያ ሃሳብና ዛሬ በእኛ በኢትጵያዊያን መካከል እየሆነ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ትክክለኛ የኢትዮጵያዊነትን የሕይወት ወይም የኑሮን ትርጉም በሚከተሉት አራት ርዕሶች ማለትም፡-

1.    ከፖለቲካው፣

2.    ከኢኮኖሚው፣

3.    ከማህበራዊ ሕይወት እና

4.    ከሐይማኖታዊ ልምምዳችን አንፃር አብረን ለማየት እንሞክር፡-

ይህ ከጽሁፉ ተቀንጭቦ የተወሰደ ሲሆን ሙሉውን ጽሁፍ ከዚህ በታች ይመልከቱ፡፡


አንተ ማነህ?

(ኢትዮጵያዊነት በእውነት ሚዛን ሲመዘን)

ይህ ጥያቄ “ክርስቲያኖች” የሕይወታቸው መመሪያ አድርገው ከሚጠቀሙበት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተወሰደ ጥያቄ ነው፡፡ በተጠያቂው ለየት ያለ በጎ የማንነት ሕይወት ላይ ግራ በተጋቡና በተጠራጠሩ የልማድ ሃይማኖተኞች አማካኝነት በ27ዓም አካባቢ የተሰነዘረ ጥያቄ ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን ትክክለኛውን የሰው ትርጉም እንደሚገባ ተረድተውና ይህንኑ ማንነታችውን ጠብቀው በእውነት ለእውነት ለራሳቸውና ለሌላው የሚኖሩ ሰዎች ሕይወት  በመምሰልና በማመቻመች ለሚኖሩ “ሥጋውያን ሰዎች” እንቆቅልሽና ግራ የሚያጋባ  ጥያቄ  ይሆንባቸዋል፡፡

የፈጣሪው የተስፋ ቃል የገባው ሰው ነገን ዛሬ ላይ ቆሞ አሻግሮ ያያል፤ የዛሪ ለቅሶና እንባም ነገ በደስታና በፍቅር እንደሚተካ ስለሚያምን ውብ ተደርጎ በተሰራው ፊቱ ላይ የሃዘንና የጭንቀት ምልክት አይታይበትም፤ በዚህ ፋንታ ይልቅ እንደ መልካም ሸክላ የሠሪውን ጥበብና ውበት በአካባቢው ለሚገኙ የፍጥረት አድናቂዎች በማንጸባረቅ አንተ ማነህ? የሚል ጥያቄ የኑሮ ትርጉም በጠፋባቸው አእምሮ ውስጥ እንዲፈጠርባቸው ምክንያት ይሆናል፡፡ ለመጥምቁ ዮሐንስም ከእኛ በላይ ማን አለ በሚሉ የሃይማኖት ሰዎች በኩል የቀረበለት  የ“አንተ ማነህ?“ጥያቄ (ዮሐ 1፡9) የሚያሳየን ይህንኑ ነው፡፡

የሚሰማው ሁሉ ጆሮን ጭው የሚያደርግ፣ የሚታየው ደግሞ የሚዘገንን በሆነበት በዚህ ዘመን ግን ጥያቄው ከውጭ ሳይሆን ከራሳችን (ከውስጥ) በመነሳት፡- እኔ ማነኝ? ከየት ተገኘሁ? የመኖር ዓላማዬ ትርጉሙ ምንድነው? መጨረሻዬስ ምን ይሆን? ወዘተ የመሳሰሉትን ጠይቀን ተገቢ መልስ ማግኘት ብንችል በሌሎች የሚነበብና ትርጉም የሚሰጥ ኑሮ መኖር እንችላለን፡፡

ማንኛውም ሰው ለሕይወቱ ወይም ለኑሮው የሚያስፈልጉት መሰረታዊ ነገሮች ተሟልተውለት በሰላምና በደስታ መኖርን አጥብቆ ይሻል፡፡ የእነዚህ ለሕይወት የሚያስፈልጉ ነገሮች ወይም ሃብት አመጣጥ ደገሞ በተገቢው መንገድ ካልሆነ የተፈለገውን ደስታና ሰላም ሳይሆን በምትኩ ጭንቀትንና የጤና ጉድለትን በማስከተል እርካታ የለሽ ኑሮን እንድንገፋ ያደርጉናል፡፡ ለዚህ ነው አብዛኛዎቹ ሃብታሞች ባላቸው መርካት አቅቶአቸው ለበሽታና ለማጉረምረም ተዳርገው የሚገኙት (ጎመን በጤና ለጤና ይሏል ለዚህ ነው)፡፡

ሕይወት ለአንዳንዶች ቀላል፣ ለብዙዎች ደግሞ ከባድ ነው፡፡ ቀላል የሚሆነው ማንነታቸውንና ምንጫቸውን ጠንቅቀው በመረዳት ያለኝ ይበቃኛል ለሚሉ ሲሆን ከባድ የሚሆነው ደግሞ የተፈጠሩበት ዓላማ ጠፈቶባቸው በመሆን ሳይሆን በመምሰል ለሚኖሩና ሁሉን ነገር ለሚያግበሰብሱ ሰዎች ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ሳይሆን አይቀርም አጉር የሚባለው ሰው (በመጽሐፈ ምሳሌ 30፡8) ላይ “ድህነትንና ባለጠግነትን አትስጠኝ፤ ነገር ግን የሚያስፈልገኝን እንጀራ ስጠኝ” በማለት የጠየቀው፡፡ ይህ አባባል እንደሚገባ ሠርቶ ማግኘትን ለመቃወም ሳይሆን ያላግባብ ተሰብስቦ ጭንቀትንና ብሎም ሞትን የሚያመጣውን የሀብት ዓይነት ባለመፈለግ የተጸለየ ጸሎት እንደሆነ ይታመናል፡፡

ከሃዲዎች በድፍረት እንደሚሉት ሰው በኢቮሉሽን ሂደት የተገኘ ሳይሆን ሠሪው/ፈጣሪው በዓላማ ለዓላማ ካለመኖር ወደ መኖር እንደምሳሌው አድርጎ ከልዩ ብቃት ጋር ያመጣውና ሃላፊነት የተሰጠው ፍጡር ነው፡፡ ያለመታደል ሆኖ የመጀመሪያው ሰው የተሰጠውን አደራ ረስቶ ወይም ዘንግቶ ስፍራውን ለቆ በመውጣት ለመከራና ለስቃይ ኑሮ ራሱን ዳረገ፡፡ በሌላ አባባል በሌባው ተሰርቆ ዘሩ ወይም ትውልዱ ሁሉ በአራጁ ለእርድ ተዘጋጀ፡፡ የመጀመሪው ሰው በሰው ግድያም በሁለቱ ወንዶች ልጆቹ በይፋ ተጀመረ፡፡ የሕይወት ምንጭ ከሆነው ከእግዚአብሔር የተለዬ ሰው፤ እድል ፋንታው ሞት እንደሆነ በተግባር ተረጋገጠ፡፡ የምህረት አምላክ ግን በሰው ድካም የተዘጋውን የሕይወት በር ቃሉን (ጌታ ኢየሱስን) ልኮ በመስቀሉ ሥራ በመክፈት የወደደ ሁሉ ገብቶ እንዲያርፍ የፍቅር ጥሪ ቢያደርግም ከጥቂቶች በስተቀር አብዛኛው ሕዝብ በእምቢተኝነቱ ቀጥሎበታል፡፡ ትእግስቱ የበዛው አምላክም “ጆሮ ያለው ይስማ” በማለት እስከ አሁን ድረስ እጁን ዘርግቶ ይጣራል፡፡

ከፈጣሪው ሳይርቅ ለተፈጠረበት ዓላማ በመኖር ሕይወትን እንዲያጣጥማት በመሻቱ ዳዊት ከመሞቱ በፊት ልጁን ሰሎሞንን “በርታ ሰውም ሁን”(1ኛ ነገሥት 2፡3) በማለት አባታዊ የሆነውን መንፈሳዊ ምክሩን ለገሰው፡፡ ከዚህ ጥልቅ ምክርም እንደምንረዳውና ማስተዋላችንን እንደሚገባ ብንጠቀምበት “ሰው ሆኖ ሰው ያለመሆን ማንነት” አለ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ከውጭ አንተ ማነህ? ወይም በተሻለ መልኩ ከውስጥ እኔ ማነኝ? ለሚለው ጥያቄ ለራሳችን ተገቢ የሆነ መልስ ካላገኘን በሕይወት መንገዳችን ላይ ቀይ መብራት በርቶብናል ማለት ስለሆነ እንደ አስተዋይ ሰው ቆም ብለን ብናስብ ጥቅሙ ለራሳችን ብሎም ለምድራችን ሊተርፍ ይችላል፡፡ ሰውነቱ በትክክል ያልገባው ሰው ደግሞ ከራሱ ውጪ ለሌላው ሰው አያስብም፡፡ አስባለሁ ቢልም በምክናያት እንጂ ዘላቂነት ባለው ምክናያት የለሽ ፍቅር አይደለም፡፡ የግል ዓላማ ሲሳካ የሚረሳው ስለሆነ፡፡

ከዚህ ጠቅላላ የመንደርደሪያ ሃሳብና ዛሬ በእኛ በኢትጵያዊያን መካከል እየሆነ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ትክክለኛ የኢትዮጵያዊነትን የሕይወት ወይም የኑሮን ትርጉም በሚከተሉት አራት ርዕሶች ማለትም፡-

  1. ከፖለቲካው፣
  2. ከኢኮኖሚው፣
  3. ከማህበራዊ ሕይወት እና
  4. ከሐይማኖታዊ ልምምዳችን አንፃር አብረን ለማየት እንሞክር፡-

1) ኢትዮጵያዊነት ከፖለቲካዊው ታሪካችን አንጻር፡

ደካማና ጠንካራ ጎናችንን በሚገባ ተገንዝበን የሆነውን (“ነ” ትጥበቅ) ነን ያልሆነውን ደግሞ አይደለንም ማለት መቻል በራሱ ብስለት ነው፡፡ በዚህ ከተስማማን ከዚህ ጽሑፍ ትንሽም ብትሆን ቁምነገር ማግኘት ይቻላል፡፡ በተጨማሪም ለዘመናት የተቸገርንበትን የጋራ ጉዳይ ጠንቅቀን በመረዳት የማያዳግም መፍትሔ ለወገናችን ማምጣት እንችላለን፡፡ በዚህ መሰረት ይህ ጽሑፍ ማንንም ቢሆን ተጠያቂ ወይም ጠያቂ አድርጎ ለመፈረጅ ሳይሆን ከትናንት ተከትሎን በመጣ ድካምና የዛሬ ተረኞች በፈጠርነው ችግር የከሸፈውን ታሪክ (ፕ/ር መስፍን እንደነገሩን) ማቃናት እንድንችል ለማሳሰብ ነው፡፡

በቀድሞው የዘመነ መሳፍንት የአገዛዝ ስርአት ወቅት አብዛኛው ክፍለ ሀገር የራሱ የሆነ ገዢ ወይም ንጉሥ  እንደነበረው ታሪክ ይነግረናል፡፡ የትግሬው ጎጃሜውን፣ ጎንደሬው ደግሞ የሸዋውን፣ (የሸዋን መኳንንት እጅ ነስተው ሄዱ ተብሎ እንደተቀኘው ባለቅኔ) በአጠቃላይ አንዱ ሌላውን በቁጥጥሩ ስር አድርጎ  ለመግዛትና ለማሰገበር ጦርነት ያደረጉ ሲሆን የጉልበት አቅማቸውንም እግረ መንገዳቸውን ደህና አድርገው በመፈተን አልፈውታል፡፡

በእነዚሀ ገዢዎች መካከል የነበረው ቅራኔ ጥላቻ ቂም በቀልና መቆራቆዝ ከራሳቸው አልፎ ወደ ተገዢው ሕዝብ በመውረድ መርዙ የተስፋፋ ሲሆን በረካታ ትውልድን ገድሎና ቀብሮ በመሻገር አሁን እስከ አለንበት ዘመን ድረስ ጠባሳው አልጠፋ ብሎን እየተቸገርንበት እንገኛለን፡፡ አለቀን ያለ ከዘር የተላለፈ የትቢትና የቂም በቀል መንፈስም ተጋብቶብናል፡፡

በእነዚህ መሳፍንት መካከል በተደረገ የእርስ በርስ ጦርነት ምክናያት የሰው ሕይወትና የአገር ሀብት እንደጠፋ የታመነ እውነት ነው፡፡ (ወለጋ ላይ በሚኒልክና በተክለሐይማኖት መካከል እንደሆነው) አሁን ግን በጦር ብዛቱ ለማስደንገጥ ለተፎካካሪው ባላንጣ በስልቻ የተላከ ጤፍን በምጣድ ቆልቶ በመመለስ ሳይሆን ጥይት በማያስጮህና በረቀቀ የዘረኝነት የስነ ልቦና በሽታ/ጦርነት ምክንያት ያልታመመና ያልተለከፈ ኢትዮጵያዊ የለም፡፡

መሳፍንቱ በዘመናቸው ይህን የመሰለ ሽኩቻ ማድረጋቸው ከራሳቸው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር አብሮ የሚሄድ የአስተሳሰብ ውጤት በመሆኑ ያንኑ ተከትለው ግዛታቸውን በጉልበት ለማስፋፋት መሞከራቸውና እርስ በርስ መናቆራቸው ስርአቱ በራሱ ግድ ስለሚላቸው ነበረ፡፡

እጅግ የሚደንቀውና የሚያሳዝነው ግን በግምት ከ120 ዓመታት በፊት ይኖሩ የነበሩ አባቶቻችን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ለአንድነት ብለው የሠሩትን አንዳንድ መልካም ሥራ ከማንሳት ይልቅ እንደማንኛውም ሥጋ ለባሽ የታየባቸውን ድካም ወደእኛ ዘመን ጎትተን በማምጣት ዘመናዊ መሳፍንቶችን በየክልሉ ለራሳችን መፍጠራችን ነው፡፡ ለዚህ ነው የዛሬ መቀራረብና መለያየት መለኪያ መስፈርታችን ሸዌ ነው፣ ትግሬ ነው፣ ጎንደሬ ነው፣ ወለጌ ነው ጎጃሜ ነው፣ወሎዬ ነው፣ከምባቴ ነው፣ሀረሬ፣ ወዘተ የሚለው የሆነው፡፡ 120 ዓመት የኋልዮሽ ጉዞ ወይም  ከፕ/ር መስፍን መጽሃፍ አባባል ልበደርና “የታሪክ መንሸራተት” ማለት ይህ አይደልምን?

እንዲያውም ይህ በሽታ አልበቃ ብሎን ከዚህ በባሰ መልኩ መቀሌ ከተማ ላይ አደዋና መቀሌዎች፣ ባሕርዳር ከተማ ላይ ጎንደሬ፣ ጎጃሜ፣ ወሎዬና ሸዌ፣ናዝሬት ከተማ ላይ የወለጋ፣ የባሌ፣ የአሩሲና የሸዋ ኦሮሞዎች፣ አዋሳ ከተማ ላይ ሀዲያ፣ ከንባታ፣ ወላይታ ሶዶ ወዘተ  በማለት የሚታየው የሹመትና የጥቅም ሽኩቻ ዘመነ መሳፍንትን ምስጋና ይግባው የሚያሰኝ ሆኗል (ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል እንዲሉ)፡፡ethio political

በተቃዋሚው ጎራ የተሰለፉት ፖለቲከኞቻችንም ቢሆኑ የስልጣን እድሉ ቢገጥማቸው ምን ሁኔታ እንደሚፈጠር ለመገመት ነቢይ መሆን አያስፈልግም፡፡ (አብዛኛዎችቻችን ከቂም በቀል አዙሪት ገና ያልወጣን በመሆኑ) ይህን ያልኩትም ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ያሳዩት አሳፋሪ ንትርክና የትዕቢት ባሕሪ በቂ የማንነት መገለጫ ስለሆነ ነው፡፡ (ለበለጠ መረጃ የፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያምን አገቱኒ መጽሐፍ ያንብቡ)

ይህን ስል በሕዝቡ ላይ እየወረደ ያለውን ዘርፈ ብዙ የመከራ በረዶ በእውነትና በፍቅር በመሆን ለማስወገድ መደራጀትን ለመቃወም ሳይሆን በጥላቻና በጉልበት በተገኘ ድል ላይ ሌላ በድል አድራጊው ቡድን ተጠልቶ የተወገደ ቡድን በፈንታው ጊዜ ጠብቆና ተደራጀቶ  በጥላቻ መንፈስ መነሳቱ ስለማይቀርና ከጥላቻ አዙሪት ውስጥ መልሶ ስለሚዘፍቀን ብቻ ነው፡፡

“ተቃዋሚ” ከሚለው ስም ከራሱ ብንነሳ በሰለጠነው ዓለም እንደሚሆነው ደካማና ለአገር የማይጠቅም ሃሳብን በሌላ በተሻለ ሃሳብ ለመተካት መሞከር የሚደገፍ ሆኖ ሳለ የእኛዎቹ ፖለቲከኞች ግን ጉዳያቸው የሚያተኩረው ሃሳቡ ላያ ሳይሆን ሃሳቡን ባቀረበው ግለሰብ ላይ ጥላቻን በመፍጠር በገባበት ገብቶ ማሳደድ ስለሆነ “ተቃዋሚ” የሚለው ትርጉም ፈጽሞ አልገባ ብሎኛል፡፡ በውስጡ ያረገዘው ክፉና ጎጂ ነገር አለ ብዬ ስለማምን፡፡ ስለዚህ በስልጣን ላይ ያለውም ሆነ የሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ማንነት ለአገሪቱ የተሻለ ነው ብለው በነደፉት ፕሮግራማቸው ተለይተው ለሕዝቡ ቢታወቁና በዚህ ማንነታቸው ቢጠሩ መልካም ነው እላለሁ፡፡

ያለመታደል ሆኖ እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ በድፍረት ክርስቲያን ነን እያልን “እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትህትና ይቁጠር”(ፊልጵ2፡3) የሚለውን የእግዚአብሔር ቃል መተግበር ይቅርና ቃሉ መኖሩንም ስለማናውቅ “እኔ ያልኩት ካልሆነ ሙቼ እገኛለሁ” ሆኖአል መፈክራችን፡፡ በሌላ አባባል በእኔ/በእኛ ከቀረበው ሃሳብ ይልቅ በእሱ/በእነሱ የመጣው ሃሳብ ለሁላችንም የሚጠቅምና የተሻለ መሆኑን ጠንቅቀን ብንረዳም ተቀብሎ የማስተናገድ ባሕሪ ፈጽሞ የለንም፡፡

ሌላው “የተቃዋሚዎች” ድካም በእኔ እይታ ደግሞ አንዳቸው ከአንዳቸው ጋር በየጊዜው እየፈጠሩት ያለው አንድነት ለአገር ዘለቄታ ውጤት ሊያመጣ በሚያስችል መልኩ ሳይሆን በስልጣን ላይ ያለውን ቡድን ለማስወገድ የሚያስችል ጊዜያዊ የአቅም ማሳደግ ስምምነት ይመስላል፡፡  ይህ ደግሞ “የጠላትህ ጠላት ወዳጅህ ነው” እንደሚባለው በመሆኑ ለዋናው ችግራችን ዘላቂ የሆነ መፍትሄ አያመጣም፡፡

እጅግ የሚገርመው ደግሞ ሕዝቡ ነገ የእሱ ቀን መሆን አለመሆኑን ሳይረዳ ወይም ሳያውቅ “ጊዜ እስከሚያልፍ የአባትህ አገልጋይ ይግዛህ” ወይም “የወንጭፍን ድንጋይ ዝቅ ብሎ ማሳለፍ ነው” በሚሉ ተረቶች ውርደቱን በመሸፈን እራሱን ከማታለሉም በላይ በየጊዜው የሚነሱ ገዢዎች ሁሉ የልብ ልብ ተሰምቷቸው እንደ ፈለጉ መሆን እንዲችሉ አድርጎአቸዋል (“የኢትዮጵያ ሕዝብና አንድ ጠንካራ ግዙፍ ፈረስ እስከ ሚወጡባቸው ድረስ ያስቸግራሉ ከወጡባቸው ደግሞ ለመጋለብ ምቹ ናቸው” ሲባል እንደሰማሁት መሆኑ ነው)፡፡

በሌላ አንጻር ደግሞ እንደባለ አእምሮ ሰው ማሰብ ብንችል ለሕዝቡ ነጻነት ብለው ለ17 ዓመታት በርሃ ለበርሃ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ እንግልትን በተግባር ያዩና የቀመሱ፣ እንዲሁም ከደርግ የበለጠ ጨካኝ ይመጣብኛል ብሎ ሳይገምት በቤቱ ሸሸጎ እያበላና እያጠጣ ለዚህ ያበቃቸውን የትግራይና የአካባቢው ሕዝብ በተግባር የሚያውቁ እነዚህ ሕዝባዊ ወያኔ ትግሬዎች በችግራቸው የደረሰላቸውን ይህን ምስኪን ሕዝብ አላሰቡለትም፡፡ ምክናያቱም በሕዝቡ ስም እየተደረገ ያለው ማንኛውም እንቅስቃሴ ይህን ሕዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር አብሮ ሊያኖረው የሚያስችለውን የወደፊት ሕይወት ዕጣ ፋንታ ፈጽሞ የሚያሻክርና አደገኛ ሁኔታ ላይ የሚጥል በመሆኑ ነው፡፡

ተስፋ የሚያስቆርጥ ኢትዮ- ፖለቲክስ ይሏል እንግዲህ ይህ ነው፡፡ “ሰው ሰውን ለመጉዳት ገዢ የሚሆንበት ጊዜ አለ” ተብሎ (በመክብብ 8፡9) የተጻፈው ትንቢት አሁን በኢትዮጵያ ፖለቲከኞች (ባለስልጣኖች) በኩል እየተፈጸመ ይመስላል፡፡ በሌላ አገላለጽ የኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታን አሳዛኝ ያደረገው ለአብዛኛው ምስኪን ሕዝብ ሕይወት መሻሻልና የስልጣን ባለቤትነት በራሱ በባለቤቱ ሕዝብ በኩል የሚደረግ እንቅስቃሴ ሳይሆን በራሱ ጫንቃ ላይ ቁጢጥ ብለው በተማሩ ጨካኝና እራስ ወዳድ ገዢ ልጆቹ በኩል መሆኑ ነው፡፡

በመሆኑም ከዚህ ተጨባጭና ነባራዊ የፓለቲካ ሁኔታ ተነስተን ኢትዮ – ፖለቲክስን ስንተረጉመው “ባለውለታን የሚያስረሳ ስልጣን” ወይም “ከድህነት ማስመለጫ ስልጣን” ወይም  “ሳይለፉ ባቋራጭ ሀብትን የሚያስገኝ ስልጣን”  ወይም “ቂም በቀልን መወጣት የሚያስችል ትልቅ የስልጣን በትር” (በዳይ ተበዳይ ማን ማንን እንደሆነ በግልጽ ሳይታወቅ)  ወይም ጥቂቶች በብዙው ሕዝብ ለቅሶ ላይ የሚስቁበት ወይም ጥቂት ጮሌ ልጆች ለፍተው ባሳደጉ አባቶች ላይ የሚያፌዙበት ወይም ጊዜን ጠብቆ የሚፈነዳ የዘርኛነት ቦንብን በየቦታው የመቅበር ዝግጅት ሥራ ማለት እንደሆነ በተግባር እያየነው ነው፡፡ መጪው ተረኛ ተገራፊ ወይም ገራፊ ማንና የመግረፊያው ጅራፍ ዓይነት ምን ይሆን በማለት ሁላችንም በስጋትና በፍርሃት በመጠባበቅ ላይ ነን፡፡

መፈትሔው፡- ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ወገኔና እንዲሁም በተለይ በስልጣን ላይ ለምትገኙ ወገኖቼ!! ቀን ያልፋልና አሳድጎ ላስተማራችሁ ምስኪን ሕዝብ ስትሉና እንዲሁም በየቤታችሁ በማደግ ላይ ለሚገኙትና መጪውን ትውልድ ለሚረከቡት ልጆቻችሁ ስትሉ እስከ አሁን ድረስ የሆነው ይብቃና በይቅርታ መንፈስ ሕዝብን በሙሉ ወደሚጠቅም ሥራ እንመልስ? የጥፋት ደመናው ምናልባት ካልታያችሁ መንፈሳችሁን ነፍሳችሁንና ሥጋችሁን በአንድነት ሰብሰብ አድርጋችሁ ነገሩን አሻግራችሁ እንድትመለከቱት በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም እጠይቃችኋለሁ?? የሰላሙን በር ለሁሉም ለመክፈት ሰፊ የሆነው እድል በእናንተ እጅ ውስጥ ሰለሆነ ነው፡፡ማለትም ፖለቲካውን በመልካም አስተዳደርና በዜጎች ሙሉ ነጻነትና ተሳትፎ እንዲሆን በማድረግ ለጠላት ቀዳዳውን ድፍኑበት ለማለት እወዳለሁ፡፡

2)ኢትዮጵያዊነት ከኢኮኖሚው አንጻር፡

የምጣኔ ሀብት ሳይንስ ማለት ቀለል ባለ ትርጉም አልመጣጠን ያለን የአንድ አገር ሃብት ምንጭንና የምርት ፍላጎትን ሚዛን በማስጠበቅ የሃብት እድገትን በዜጎቿ ሙሉ ተሳትፎ ለማምጣትና ምርቱንም  ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለሁሉም እንደ የሥራው ማከፋፈል የሚያስችል የጥናት መስክ  ማለት ነው፡፡

የመስኩ ቀጥተኛና አጭር ትረጉም ይህ ቢሆንም ሥራ ላይ እንዲውል የሚያደርገው ሰው በመሆኑና ሰው ደግሞ በአብዛኛው ራስ ወዳድ ስለሆነ የምጣኔ ሀብት ሳይንሱ በተገቢው መልክ ሥራ ላይ ሲውል አይታይም፡፡

ከዚህ ጠቅላላ እውነት ተነስተን ኢትዮጵያዊነትን በምጣኔ ሃብት እድገትና በምርት ክፍፍሉ አንጻር ለማየት ስንሞክር ታዲያ “እድሜ” ለግብፅ ኮብቲክ ቤተ ክርስቲያን እና ትዕዛዝ አስፈጻሚ ለነበረችውና አሁንም የታሪክ ተወቃሽ  ለሆነችው ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ “ቤተ ክርስቲያን” (አንዳንድ ጠንካራ ጎኖች ቢኖሯትም) የፍጥረት ሁሉ ፈጣሪ፣ የአባቶቻችን (የአብርሃም፣ የይስሃቅ፣ የያዕቆብ ) አምላክና ዛሬም የእኛ አምላክ የሆነው እግዚአብሔር  በህያው ቃሉ ከሳምንቱ 7 ቀናት ውስጥ  “ስድስት ቀን ሥራ” (ዘጸአት 20፡9) በማለት የደነገገውን በመሻር በአንድ መባቻ፣ በሁለት ልደታ፣ በሶስት ባታ፣………. በሰላሳ ማርቆስ የሚባል ባእል ስለሆነ ገዝቸሃለሁ መሥራት አትችልም እየተባለ ሕዝቡ (በተለይ ገጠሬው)  አብዛኛውን ጊዜ ሥራ እንዲፈታና ለድህነት ኑሮ መዳረጉን ታሪክ መዝግቦ ያስቀመጠው ገሀድ እውነት ነው፡፡

ethሌላው ሕዝቡ በአብዛኛው የመማር እድል ስላልገጠመውና የኋላ ቀር አስተሳሰብና ጎጂ ባህል ተጠቂ ስለሆነ አዲስ የተሻለ ዓይነት የአሠራር ግኝትን በቀላሉ ተቀብሎ የማስተናገድ አቅም ፈጽሞ የሌለው መሆኑ ለድህነታችን ሌላው ምክናያት ነው፡፡

ከጠቅላላ ሕዝቡ ቁጥር አነጻር ጥቂቶች ቢሆኑም እንኳ የከበርቴዎቻችን የሐብት ማግኘት ተሞክሮ  ደግሞ ሠርቶ በማግኘት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በአቁዋራጭ (በስልጣን/በጉቦ) በተለያዬ ስልትና ዘዴ በመጠቀም በአጭር ጊዜ ውስጥ በመሆኑ ሠርቶ የማግኘት ባሕል ጨርሶ እንዳይለመድና ሁሉም ሰው ይህንኑ ስልት ተጠቀሞ ባለሃብት ለመሆን አድፍጦ አጋጣሚውን የሚጠባበቅ ሕዝብ አድርጎታል፡፡

እንደ “ክርስቲያንነታችን” እግዚብሔር አምላክ በቃሉ “ሊሠራ የማይወድ አይብላ”(2ተሰ3፡10) በማለት መለኮታዊ ትዕዛዙን ሰጥቶ ሳለ በምድራችን ውስጥ ሌት ከቀን የሚለፋው በርካታ ሕዝብ ፍጹም ድሀ ሲሆን  የአገሪቱ ጠቅላላ ሃብት ግን እጃቸው ሥራ ነክቶ በማያውቁ ጥቂት ብልጥ አሠሪ ሰዎች ቁጥጥር ስር መሆኑ ዜግነትን 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ያለው አስመስሎታል፡፡

የንግዱን ሥራ እንቅስቃሴ የሚቆጣጠረውም ገበያው ሳይሆን የዘመድ አዝማድ ጉባዔ እና ጉቦ እንደሆነ በየንግድ ዘርፉ የተሰለፉትን ወገኖች ማየትና ነገዴዎች ጉዳይ ለማስፈጸም ወደ ባለስልጣናት ቢሮ ጎራ ሲሉ ምን ይዘው እንደሚቀርቡ በማየት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

በተጨማሪ አብዛኛውን የየክልሉ ንግድ እንቅስቃሴ ብንመለከት ደግሞ የተያዘው በአካባቢው ተወላጆች እንጂ ከደቡብ ወደ ሰሚን ወይም ከምስራቅ ወደ ምዕራብ በመጡ ሰዎች አይደልም፡፡ ወይም በሌላ አባባል ፍጹም የኢትየጵያዊነት ድፍረት ወይም ስሜት ኖሮት በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ኢንቨስት የሚያደርግ ሰው አይታይም፡፡

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ሳይቀሩ ባላቸው አቅም በመንቀሳቀስ ላይ ያሉት በተወለዱበት አካባቢ ወይም በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ መሆኑ ጥያቄ ያጭራል፡፡ ከዚህ ተጨባጭ መረጃ በመነሳት የሕዝቡ አስተሳሰብ ከአገር ይልቅ ወደ ክልል ደረጃ ዝቅ በማለቱ ክልሎችን ውድድር ውስጥ የገቡ አስመስሏቸዋል፡፡

ሌላው የንግዱን ሥራ አስቸጋሪ ያደረገው ጉዳይ  በገበያው መስክ ላይ ለውድድር የተሰለፉት ተጫዋቾች አቅም ሚዛኑ አለመመጣጠኑ ነው፡፡ በሌላ አባባል የአንድ ምርት የገበያ አቅርቦትና ፍላጎት ሕግ በሰው ሠረሽ ሕግ እንደሁኔታው ስለሚቀያየር ነጋዴው በገበያ ሥራ ጥናት ላይ ተመሰረቶ ያደርግ የነበረውን እንቅስቃሴ በማቆም ከጨዋታው መስክ ውጭ እንዲሆን ይገደዳል፡፡

በገበሬው አካባቢ ያለውን የሥራ እንቅስቃሴም ለማየት ብንሞክር የመሬት ድልድሉ የፖለቲካ ወገናዊነትን ተከትሎ የሚታደል በመሆኑ የነፃ ሕሊናው ባለቤት የሆነው አርሶ አደር እድል ፋንታ መሬት አልባ መሆንና ከቤተሰቡ ጋር በሙሉ በጠኔ መመታት ሆኗል፡፡

በአጠቃላይ ሲታይ በምድሪቱ የሚኖረው የአብዛኛው ሕዝብ ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ በመሆኑ ለማኝና የበይ ተመልካች የሆነበት፤ በአንጻሩ ደግሞ ጥቂቶች እጅግ ባለፀጋ የሆኑበት ሁኔታ በገሃድ ይታያል፡፡ ከዚህ የተነሳም አገሪቱ ለብዞዎች “የእንጀራ እናት” እንጂ “ወላጅ እናት” በመሆን ሁሉንም በእኩልነት መንገድ ማስተናገድ አልቻለችም፡፡

ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት ከኢኮኖሚው አንጻር ሲተረጎም በአብዛኛው “የሥራ ባህል የሌለው፣ ወይም “ሳይሠራ መብላትና መክበር የሚሻ”፣ ወይም በአብዛኛው ልመናን ባህሉ ያደረገ (ላሊበላንና አዲስን የሚጎበኙ ቱሪስቶች የተመረሩበት ጉዳይ) ወይም “ኩራት ራቱ የሆነ ሕዝብ”ማለት ሲሆን በሌላ ጎኑ ደግሞ “የትም ፍጪው ዶቄቱን አምጪው በማለት ለሚሳለቁ “ለጥቂቶች በአቋራጭ ሃብታም መሆን” ማለት ነው፡፡

መፍትሔ፡ ብዙዎች በሚራቡባት፣ ጥቂቶች ደግሞ በሚንደላቀቁባት አገር ውስጥ እውነተኛ ሰላም ጨርሶ የለም፡፡ ስለዚህ ዛሬ ሁኔታው ያልተመቻቸለት የበይ ተመልካች የተደረገ ረሀብተኛ በዚህ ሁኔታ ይቀጥላል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ወይም እውርነት ነውና ያገሪቱ ባላሀብት እንዲሁም ባለስልጣናት ለሆናችሁ መፍትሔው በእናንተ እጅ ነውና ለጋራ የአገር ጥቅም ስትሉ ዛሬውኑ ቆም ብላችሁ እንድታስቡበት በእግዚአብሔር ፍቅርና በችግረኛው ወገኔ ስም እጠይቃችኋለሁ???

3)  ኢትዮጵያዊነት ከማሕበራዊ ሕይወት አንጻር፡-       

የማሕበራዊ ሳይንስ ጠበብቶች ሰው ለኑሮ የሚያስፈልጉትን ነገሮች በራሱ አሟልቶ ብቻውን መኖር እንደማይችል ያስተምራሉ፡፡ በሌላ አገላለጽ ሰው የተሟላ ኑሮ ለመኖር የሌላው ሰው ድጋፍ የግድ ያስፈልገዋል ማለት ነው፡፡ ይህን ጉዳይ በእኛ በኢትዮጵያውያን ተጨባጭ የኑሮ ሁኔታ ለማየት ብንሞክር የማምረቱ፣ የንግዱ፣ የቢሮው፣ ሕግ የማውጣቱና የማስፈጸሙ ሥራ ወዘተ ይቅርና ሀዘንና ደስታችን እንኳን ሳይቀር ማህበራዊ ነው፡፡

የማሕበራዊ ሕይወት አስፈላጊነት ሰው ፈልጎ የሚያመጣው ብቻ ሳይሆን የመኖር ግዴታም ጭምር በመሆኑ ማነኛውም የሰው እንቅስቃሴ ለጋራ ኑሮ በጋራ የሚደረግ ተግባር ሆኗል፤ ሆኖም ግን ይህ ማሕበራዊ የሕይወት እንቅስቃሴ ለማሕበራዊ ጥቅምና እድገት ሳይሆን ቀርቶ በምትኩ ለግል ጥቅም ወይም ለሌላው ጉዳት የሚውል ከሆነ ውጤቱ ሰላምና እውነተኛ ፍቅር ሳይሆን ማሕበራዊ ቀውስንና አለመረጋጋትን በማስከተል ሕይወትን ትርጉም የለሽ ያደርገዋል፡፡

በሰው ልጅ የታሪክ ሂደት ውስጥ ትልቁ የሕይወት ችግር በሕብረተሰቡ መካከል ያለው ሁለንተናዊ የግንኙነቱ መስመር ሚዛኑ ተጠብቆ ሥርዓት ባለው መንገድ መመራት ካለመቻሉ የተነሳ ወይም ከመልካም አስተዳደር እጦትና ከሰባዊ መብት አለመከበር ምክንያት የሚመጣ ያለተስተካከለ የኑሮ ቀውስ ነው፡፡

ማሕበረሰባችን በፆታ፣ በእድሜ፣ በዘርና በጎሳ፣ በእውቀት ደረጃ፣በሃብታምና በድሃ፣ በሠራተኛና በአሰሪ፣ ወዘተ የተከፋፈለ ነው፡፡ ከነዚህ ክፍፍሎች መካከል የመጀመሪያዎች ሦስቱ በሰው ፈቃድ የመጡ ሳይሆኑ በተፈጥሮ ያገኘናቸው ውብ የፈጣሪ ስጦታዎች ናቸው፡፡ በሌላ አባባል ማንኛችንም ብንሆን ሴት ወይም ወንድ፣ ኦሮሞ ወይም ትግሬ፣ ጉራጌ ወይም አማራ፣ ከምባታ ወይም ሀድያ ወዘተ ሆነን ለመወለድ ያደረግነው አስተዋጽኦ የለም፡፡ ስለዚህ ሰውን በፆታው ወይም በዘሩ መጥላትና መበደል ተፈጥሮን እንደ መጥላትና መቃወም ይቆጠራል ማለት ነው፡፡

በነዚህ መስፈርቶች ሚዛንነት ሕብረተሰባችንን ለማየት ስንሞክር የወንድና የሴት፣ የሺማግሌና የወጣት የአንዱ ዘርና የሌላው ዘር፣ የተማረውና ያልተማረው፣ የሃብታሙና የድሃው፣ የገዢውና የተገዢው አጠቃላይ ግንኙነት እራስን ከፍና ዝቅ አድርጎ ከማየት በመጣ ሰው ሠራሺ ችግር ሚዛኑ እንዲበላሽ ተደርጓል፡፡ በሌላ አገላለጥ ሕብረተሰቡ በሙሉ በጋራ በመኖር እንዲጠቀምበት ከተፈጥሮ የተቸረው ወይም ያገኘው “ክቡር ሰውነቱ”  ትዕቢት፣ ስግብግብነት፣ ኩራት፣ ራስ ወዳድነት፣ ጨካኝነትና እኔነት በሚባሉ የሕይወት መርዞች በመበከሉ በሕዝባችን መካከል ያለው የእርስበርስ ግንኙነት ኑሮአችን ትርጉም አጥቷል፡፡

ከዚህ ጠቅላላ እውነታ ተነስተን  ኢትዮጵያዊነትን  ከማሕበራዊ ሕይወታችን አንጻር ስናየው ወንዱ ከእናቱ ውጪ የተገኘ ይመስል ለሴቷ (ለሚስቱ) የሚገባትን ክብር ከመስጠት ይልቅ በአፈጣጠር አንድ ነገር እንደጎደላት ለመቁጠር ሲሞክርናethio poor እንዲሁም ድሀው ከሃብታሙ ፊት በሃዘን ቆሞ ራበኝ የምበላው ስጠኝ ብሎ ሲለምን ሂድ ከፊቴ ጥፋ! በማለት ሲያባርረው ማየቱ (ልመና መብት ባይሆንም) ግንኙነቱን ሰብአዊ እውቀትና ርህራሄ የጎደለው አስመስሎታል፡፡

ሌላው የፍርሃት ቆፈን ሆኖ ያስቸገረንና መድሃኒት ያልተገኘለት በሽታ ደግሞ ማሕበረ ሰባችን ለባለስልጣናት የሚሰጠው ግምት ነው፡፡ ድሮ ንጉሡ እራሳቸውን ለሕዝቡ ያስተዋወቁበት መንገድ ዘራቸው ከሰው የተለየ መልአክ እስከሚመስሉ ድረስ ስለነበረ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በወላጅ አባቱ ስም ምትክ “ኃይለ ስላሴ ይሙት” በማለት ሲምልባቸው እንደነበረና በተጨማሪም ከእሳቸው ጀምሮ እስከ ታች ድረስ ያሉትን ባለስልጣናት ሲፈራና ሲንቀጠቀጥላቸው እንደነበረ የሚታወስ ነው፡፡

በደርግና አሁን ባለው መንግሥት ቢሆንም በተከታታይነት ሶሻሊዝም” እና “ዲሞክራሲ” ከሚሉ ስሞች ጋር ጉልበትና ኃይል ስለተጨመረበት የፍርሃቱና አንገት የመድፋቱ መጠን ከፍተኛ ነበር አሁንም ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ የገዢና የተገዢ ወይም የመፈራትና የመፍራት ግንኙነቱ ታዲያ ይዋል ይደር እንጂ አንድ ቀን ሓይለኛ አቧራ በማስነሳት እንደልቡ ተንሰራፍቶ የነበረውን ዛፍ ሁሉ ከነስሩ እየገነደሰ እንዳልነበረ እንደሚያደርገው የቅርብና የሩቅ ታሪኮች አሳይተውናል፡፡ (ጆሮ ያለው ይስማ!!!)

ከሆነውና እየሆነ ካለው ነባራዊ ሁኔታ መማር የሚችል ብልህ ሰው ካለ ግን ከሚመጣው መከራ እንደ ሎጥ ሸሽቶ ማመለጥ ይችላል (ዘፍ19፡22)፡፡ ወይም በአመራር ጥበቡ የታወቀው ንጉሥ ሰሎሞን በምሳሌ 2፡11 ላይ በእግዚአብሔር መንፈስ ውስጥ ሆኖ “ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፤ ማስተዋልም ይጋርድሃል”  በማለት የጻፈውን መልእክት እንደሚገባ ያሰተዋለ ሰው ከሕዝቡ ጋር በመሆን ከወዲሁ ዝግጅት በማድረግ የሚፈራው(ፈራ ይጥበቁ) ነገር እንዳይከሰት ወይም ድንገት ቢከሰት  እራሱ ከመከራው አምልጦ ሕዝቡን የሚያስመልጥበት ስልት ከወዲሁ ይቀይሳል፡፡ (ኮሎኔል መንግሥቱ በራሳቸው ሰዎች የግልበጣ ሙከራ በተደረገባቸው ማግስት ቆም ብለው በማስተዋል ስልጣኑን ለሕዝብ ለማስረከብ ቢሞክሩ ኑሮ በራሳቸውና በአገሪቱ ላይ ምን ዓይነት ታሪክ ይፈጠር እንደነበረ እንገምት)

ሌላው ደግሞ ሕዝቡ ምንም ሳይኖረው በይሉኝታ ተበድሮ በየምክንያቱ ድግስ መደገስና ማብላት የሚወድ መሆኑ ነው፡፡  በዚህ ምክንያት እንደ ባሕል ወይም ሐይማኖት ተቆጥሮ በክርስትና፣ በልደት፣ በጽዋ፣ በሰርግ፣ በባዕላትና በሞት፣ (ሳልስት፣ ዐርባ፣ ተዝካርና አመታት) በሚደረገው ድግስ ላይ በሌለ አቅም ከሚባክነው ሃብት ባሻገር ማሕበራዊ ግንኙነቱን በስካር መንፈስ የመጠላላትና የቆየ ቂም መወጣጫ መድረክ አድረጎታል (በየዓመቱ ጃንሜዳ በሚከበረው ጥምቀት ላይ የኦሮሞዎችንና የትግሬዎችን ድብድብ ያስታውሷል-የዛሬን አያድርገውና አማራ ገላጋይ ነበረ ይባላል)፡፡  እጅግ የሚገርመው ነገር ቢኖር ደግሞ ይኸው ተበድሮ ሳይቀር የሚደግስ ሕዝብ “ትለብሰው የላት ትከናነበው አማራት” ከሚለው የአባቶች አባባል አለመማሩና ተረቱን ዛሬም በማለት/በመናገር ላይ መሆኑ ነው፡፡

ethio richከሌላው ወገናችን ጋር የምናደርገውን ግንኙነት ካለእውቀትና ካለአቅም ሰው ምን ይለኛል በሚል ብቻ በይሉኝታ ማድረጉ የእውነተኛ ማሕበራዊ ሕይወትን ትርጉም ማበላሸት ነው የሚሆነው፡፡ ምክናያቱም እውነተኛው የማሕበራዊ ሕይወት ትርጉም በግል ዝናና ጥቅም ወይም ውርደትና ውድቀት ላይ ያነጣጠረ ሳይሆን ጠቅላላ ማህበረ ሰቡ እንደ ችሎታው በመደጋገፍ የሚኖረው የጋራ ኑሮ ማለት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ሌላው ስላደረገው እኔ ምን ይጎድለኛል በማለት በሌለ አቅም ለማድረግ መሞከር ሳይሆን ሁሉም በአቅሙ ተደጋግፎ ግብዝነት በሌለው ፍቅር በመኖር ለበለጠ የጋራ ውጤት በመጣር ሕይወትን ወይም ኑሮን በመተሳሰብና በሰላም መምራት ማለት ነው፡፡

የእውነተኛው ማሕበራዊ ሕይወት ትርጉም የሚያጠነጥነው “እኛ ለእኛ” በሚለው የጋራ ጉዳይ ላይ እንጂ “እኔም አንተም – ለእኔ” በሚለው የስግብግቦች ብሒል/ብልጠት ላይ አይደለም፡፡ ጠቅላላው እውነታ ይህ ሆኖ ሳለ ግን በሕዝባችን መካከል እየሆነ ያለው “ለእኔ ካልሆነ እበትነዋለሁ”  ወይም “ባሌ ከባልሽ ይበልጣልና……”ወይም በሌላ አገላለጽ ዘመዴ፣ አበልጄ፣ የወንዜ ልጅ ስለሆነ ችሎታው ባይኖረውም ይቀጠር ወይም ጉዳዩ ይደረግለት/ይፈጸምለት በማለት ቀጭን ትዕዛዝ በማስተላለፍ ጉዳይን ያላግባቡ የማስፈጸምና የመፈጸም ልምምድ የሕዝቡ የለት ተለት ተግባር ሆኖ ይታያል፡፡

የሚደንቀው ደግሞ ሕዝባችን “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” በማለት ተረቱን እየተረተ በተግባራዊ ሕይወቱ ግን አባባሉን  ለግል ፍላጎቱ ብቻ በመቆም እራሱ መለሶ ሲያፈርሰው መታየቱ ሕዝባችን ተረት ተራች እንጂ የሚናገረውን ተግባራዊ ማድረግ የማይችል ነው አስብሎታል፡፡ እንዲያውም አሁን አሁንማ አዳዲስ አባባሎች ተፈብርከው “ ኢትዮጵያውያን አብሮ መብላት እንጂ (ይህም ቢሆን በይሉኝታና በሌለ አቅም ከማን አንሼ በሚል ፈሊጥ ) አብሮ መሥራት አያውቁም” እየተባለ ነው፡፡

ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት ከማሕበራዊ ሕይወት አንፃር ሲተረጎም “በሁሉ ነገር እኔ፣ በእኔ – ለእኔ” ወይም “አንተም፣ አንችም፣ እናንተም – ለእኔ” ማለት እንጂ በእውነት ከልብ “ለወንድሜ”፣ ወይም “ለእህቴ” ወይም “ለወገኔ” ወይም “ሁላችንም ለጋራችን” ወይም ለአገራችን የሚለው አባባል ከአማርኛ ዲክሽነሪ ጨርሶ የጠፋ እስከሚመስል ድረስ ተረስቶአል፡፡ የሚገርመው ደግሞ አንድ በውጭ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ከአንድ ቦዘኔ ነጭ ጋር ወደ መዲናችን ጎራ ቢል መስተንግዶውንና አክብሮቱን ለነጩ ብቻ በማድረግ ወገናችንን የምንረሳ ወይም የምንንቅ አጉል እንግዳ ተቀባዮችና ጥሩ ወረተኞች መሆናችንን በተግባር ማየት ይቻላል፡፡

በአጠቃላይ ማሕበራዊ ግንኙነታችንን በተመለከተ ኢትዮጵያዊ ማለት ለራሱ ወገን ክብር የሌለው፣ ትቢተኛ፣ ከወንድሙ ከሚማር ይልቅ ሞትን የሚመርጥ፣ እርስበርሱ የማይተማመን፣ መተባበርን የማይወድ፣ የወንድሙ መሻሻል የሚያስከፋው፣ በመምሰል እንጂ በመሆን የማይኖር፣ ተባበሮ መልካም ነገር ከመሥራት ይልቅ ለክፉ ሥራ መተባበር የሚቀናው ወዘተ እንጂ በሕብረት ሆኖ መልካም ሥራ መሥራትን የማይፈልግና እርስ በርሱ የሚናናቅ ማለት እንደሆነ በማሕበራዊ ኑሮአችን ላይ የሚታየው ሁኔታ በቂ ምስክርና ልንክደው የማንችለው እውነት ሆኖአል፡፡

መፍትሔ፡ እያንዳንዱ በግሉ ቆም ብሎ በማሰብ በመጀመሪያ በራሱ ላይ ፍጹምና ቅን የሆነ የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት እርምጃ ይውሰድ፤ ከዚያም በአጠገቡ ካለው ወንድሙ ጋር በጎ የሆነውን ለማድረግ ይመካከር እንዲዚህ እያለ የግንኙነቱን አድማስ በማስፋት ሕብረተሰቡ በጋራ ሆኖ ለአገር ሰላምና እድገት በእውነተኛ ፍቅር እንዲነሳ ማድረግ ይቻላል፡፡

4)  ኢትዮጵያዊነት ከሃይማኖት አንፃር ሲታይ፡-

በአገሪቱ ውስጥ ጎልተው የሚታዩት ሃይማኖቶች የክርስትና (ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክና የፕሮቲስታንት – በተለምዶ ጴንቴኮስታል) እና የእስልምና ሃይማኖቶች ናቸው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያዊነትን ከሃይማኖት አኳያ በትክክል መተርጎም እንችል ዘንድ ትንታኔያችንን ከነዚህና በስራቸው ካሉ የሃይማኖት ተከታዮች አስተሳሰብና ተግባራዊ የሕይወት ተሞክሮ አንጻር በተናጠል ማየቱ ማን ምን? እንደሆነ በግልጽ እንድናይ ስለሚረዳን በዚሁ መሰረት እያንዳንዳቸውን እንደሚከተለው እንመልከት፡-

ማሳሰቢያ፡ የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ድካምን በማስተዋል አውቆ በማስወገድ ለጋራ ሕይወት ሁሉም በያለበት ድርሻውን እንዲወጣ በፍቅር ለፍቅር ሥራ ለማነሳሳት እንጂ ሐይማኖቶችን ለመንቀፍ አለመሆኑ በቅድሚያ ይታወቅ፡፡   

4.1 ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፡-

ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ በትክክል ገባ የሚባለው ፍሬምናጦስ ተብለው በሚጠሩ የግብጽ አገር ተወላጅ በሆኑ የመጀመሪያው ጳጳስ በኩል እንደሆነ የቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ ያረጋግጣል፡፡ እዚህ ላይ ክርስትናውን ማንም ይጀምረው ማን ዋናው ቁምነገር የኢትዮጵያ ክርስትና (በኋላ ኦርቶዶክስ በመባል የታወቀው) አጀማመር እንደ ስሙ በክርስቶሰ ወንጌል ላይ ያተኮረ በመሆኑ የጀማሪው ጳጳስ ስም ሳይቀር በወንጌል ትምህርታቸው ብርሃን ፈንጣቂነት ምክናያት አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን እንደተባሉ አሁንም የቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ በግልጽ ይመሰክራል፡፡

ክርስትናን በቀደምትነት ከተቀበሉት ሌሎች አገሮች ጋር አብራ የተፈረጀች ይች ጥንታዊት አገር እውነተኛውን ክርስትና በወንጌል ጀምራ የተወሰነ ርቀት ብትጓዝም ከጊዜ በኋላ በተፈራረቁባት የጠላት ወረራዎች ምክናያት መሰረቷ የሆነውን የመስቀሉን ቃል ጥላ ልዩ ወንጌል መስበክ መጀመሯን አሁን ያለችበት ሁኔታ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ ይህን የልዩ ወንጌል መሰበክም ውጤት (ገላ1፡6-9) በወቅቱ ተረድተው የተቃወሙ “መነኮሳት” በሚዘገንን ሁኔታ በወቅቱ በነበሩት ንጉሥ መጨፍጨፋቸውን ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ “ደቂቀ እስጢፋኖስ” በተባለ መጽሐፋቸው ላይ በሚገባ ገልጠውታል፡፡ethio ortho

አሳዛኙና ሌላው የታሪካችን ገጽታ ደግሞ ከመጀመሪያው ጳጳስ ጀምሮ ለ1600 ዓመታት ከወንጌል ይልቅ የሌላ ሐይማኖትና የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው 111 ግብጻውያን ጳጳሳት ከግብጽ መሪዎች ተሹመው ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ቤተ ክርስቲያኒቷን በሚፈልጉት መንገድ (በመንፈሳዊ ባርነት) ማስተዳደራቸው ነው፡፡ እነዚህ ጳጳሳት የተላኩበትን መንፈሳዊ ሥራ ከመሥራት ይልቅ በአብዛኛው ስውር የፖለቲካ ሥራ ለራሳቸው ሕዝብ ይሠሩ እንደነበረ የአባይን ወንዝ ፖለቲክስ ማጥናቱና ማየቱ በቂ ማስረጃ ነው፡፡

በተጨማሪም እነዚህ “ጳጳሳት” ከአመጡብን በረካታ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች አንዱ  የኢትዮጵያ ሕዝብ ሠርቶ እንዳያድግ ከእግዚአብሔር ቃል ውጪ የሆነ ቀንበር በመጫን ከ 1 እስከ 30 ያሉትን የየወሩን ቀናት በሞቱ “ቅዱሳን” እና “በመላእክት” ስም ሰይመው መንፈሳዊ ባዕል በማድረግ ሥራ እንዳይሠራና በድህነት እየማቀቀ ለማኝና የእነሱ ጥገኛ ሆኖ እንዲቀር ማድረጋቸው ሌላው ተነኮላቸው ነበር ነውም!!!(አሁንም ስላልተወገደ)፡፡

እጅግ የሚያሳዝነው ጉዳይ ደገሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የራሷን ጳጳስ መሾም ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ እነዚህ ክርስቲያን ለመምሰል ሥራቸውን መስቀል በማሳለም ብቻ የወሰኑ “የፖለቲካ መልዕክተኞች” ለራሳቸው ጥቅም፣ ለሕዝባችን ሕይወት ግን መቀጨጭ ብለው የጫኑብንን ቀንበር ኢትዮጵያውያኑ አባቶች መስበርና ሕዝቡን ነጻ ማውጣት ጨርሶ አለመፈለጋቸው ነው፡፡ እንዲያውም እስከ ዛሬ ድረስ እዚያው ላይ ቆመው “ማርቆስ አባታችን እስክንድርያ እናታችን በሚል ቅዳሴ” ሙገሳውን መቀጠላቸው ምን ዓይነት “መንፈሳዊ ድንዛዜ” ላይ መሆናችንን ያመላክታል፡፡

ሌላው የሚገርመውና እጃችንን በአፋችን ላይ እንድንጭን የሚያደርገን ነገር ቢኖር ደግሞ ከግብጽ የወረስነውና አሁንም እየኖርነው ያለውን (የታቦቱ፣ የቤተ መቅደሱና የባዕላቱ ጋጋታ ወዘተ) የክርስትና ዓይነት በአሁኑ ሰዓት ወላጃችን በተባለችው በግብጽ ቤተክርስቲያን ውስጥ ፈጽሞ አለመገኘቱ ነው፡፡ እዚህ ላይ የሚያስተውል ሰው ከተገኘ ወላጇን መምሰል ያልቻለች ይች ልጅ ነኝ ባይዋ የእኛዋ ቤተ ክርስቲያን ለምን ብላ ነው “ማርቆስ አባቴ እስክንድርያ እናቴ” በማለት በሌለ ማንነት እስከ አሁን ድረስ የምትቀድሰው? የሚል ጥያቄ ማንሳት ይችላል (መልሱ አለማስተዋል ነው)፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ከሌሎች ኦርቶዶክስም ሆነ ፕሮቴስታንት ክርስቲያኖች ልዩ የሚያደርጋት የክርስትና መሰረት ከሆነው ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ይልቅ ለመላእክት እና በሕይወት ለሌሉ ቅዱሳን ሰዎች ቅድሚያ ስፍራውን መስጠቷ ነው፡፡ ለምሳሌ መስቀለ ኢየሱስ  (ለቤተ ክርስቲያን የሞተላት ጌታ) ይውልበታል የተባለበትን ዕለት በሥራ  ተጠምዳ ስታሳልፈው፤ ግብጻዊ ሰው የምትላቸውን አቦእና የሸዋው ተወላጅ ተክለሃይማኖትና ሌሎች በሕይወት የሌሉ ሙታን የሚውሉበትን ቀናት ግን ያለ ሥራ አክብራ የምትውል ሲሆን በእነዚህ እለት የሚሰበከውም ቃል በወንጌል ፋንታ የእነዚሁ ሰዎች ገድል ብቻ  መሆኑ ብዙ አስተዋይ ልጆቿ እየተዋት እንዲኮበልሉ አድርጓታል እያደረጋትም ነው፡፡(ቤተ ክርስቲያኒቱን የወላድ መካን ያደረጋት ጉዳይ!!!)

ሌላው የሚያስለቅሰው ጉዳይ ደገሞ ነፃ የሆነ የሰላምና የፍቅር ሕይወት እንዲኖር በመስቀል መከራ የሐጢአቱን ዋጋ በከፈለለትና ጽድቁ በሆነለት በክርስቶስ ስም “ክርስቲያን” የተባለ ሕዝብ ጽድቅን ፍለጋ ከደብር ወደ ደብርና ከአገር ወደ አገር በሌለ አቅም እንዲንከራተት መደረጉ ነው፡፡ ይህም በቦታና በጊዜ የማይወሰነውን እግዚአብሔር አምላከን በቃሉ መሰረት ካለማወቅ የመጣ ችግር ሲሆን በዚህ ዓይነት መንከራተት ሰላምና እረፍት እንደማይገኝ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ከእስራኤል ጉዞው ሲመለስ በመንገድ ላይ ያገኘውን እውነተኛ የደስታ ምንጭ (እስራኤል ደርሶ በመሳለሙ ያላገኘውን ሰላምና ደስታ) ቆም ብለን ብናስተውል ሕዝባችንን በከንቱ ከመድከም አርፈን ባሳረፍነው ነበር፡፡

ለማጠቃለል ያህል የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቋንቋን ከነፊደሉ አዘጋጅታ ያበረከተች፣ የአገርን ዳር ድንበር ያሰጠበቀችና ለአገሪቱ በርካታ ውለታ ያስቆጠረች ብትሆንም በአንጻሩ ወንጌልን ለበርካታ ተከታይ ሕዝቧ እንደሚገባ ባለማስተማሯ የድግምት፣ የአስማት፣ የመተት፣ የክፋት፣ የተንኮልና በአጠቃላይ የአጋንንት መንጋ መጫዎቻ እንዲሆንና ከገዢዎች ጋር በመወገን ሦስተኛ ፈላጭ ቆራጭ ገዢ በመሆን “እሱ ያመጣውን እሱ እስኪመልሰው ድረስ” በሚል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባልሆነ አባባል አንገት የሚደፋና የሚፈራ ምዕመን  ለገዢዎች በማዘጋጀት ሥራ ላይ የተጠመደች ቤተክርስቲያን ነች፡፡

ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት ከኦርቶዶክስ ሃይማኖት አኳያ ሲተረጎም የስም ክርስቲያን ወይም ያለወንጌል ክርስቲን መሆን፣ ወይም በአገሪቱ ውስጥ የክፋት፣ የተንኮል፣ የጥንቆላ፣ የአስማት፣የምቀኝነትና የጥላቻ ወዘተ ዋና መፈልፈያ ምንጭ መሆን ማለት ነው፡፡

በሌላ መልኩ ኢትዮጵያዊነት ከኦርቶዶክስ አነፃር እውነተኛ ፍቅር ሳይኖር በጥላቻ አገሬ፣ ባንዲራዬ፣ ሃይማኖቴ እያሉ እርር፣ ድብን፣ ቅጥል ማለት፣ ወይም በሰላቢ ምክናያት ሃብታም መሆን፣ ወይም በአስማትና በድግምት ወንድምንና እህትን ማሳበድ፣ ወይም ልብን ጥቁር አድርጎ ውጪውን አካል በነጭ ልብስ ማሽሞንሞን፣ ወይም ማስመሰል እንጂ መሆን ፈጽሞ አለመፈለግ ማለት ነው፡፡

መጨመር ካስፈለገም ኢትዮጵያዊነት ከኦርቶዶክስ ተከታይ አንፃር በጠንቋዮች ትዕዛዝ የማርያምን ወይም የቁልቢውን መለአክ (የእግዝአብሔርን ቅዱስ መለአክ ሳይሆን) ወይም የተክልዬን ወዘተ ጸበል ጠጣ ወይም ጠጪ ለሚሉ አታላዮች የተጋለጠ፤ ወይም ሳይማሩ በጠመጠሙ  ሰዎች በኩል ጽድቅን አገኛለሁ የሚል፣   የሕይወት ትክክለኛ ትርጉም ያልገባው ነገር ግን እንደሌላው ሁሉ ለሃይማኖቱ የሚሞትና የሚገድል ዜጋ የተሰባሰበበት የጽዋ ማኅበር ማለት ነው፡፡

መፈትሄ፡- ክርስትና እውነትን በፍቅር በመናገር ተግባራዊ የሆነ ሕይወት ከሌላው ወገኑ ጋር በሰላም፣ በጤናና በመቻቻል መኖር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የቤ/ክኗ መሪዎች የሰላምን ወንጌል ለሕዝቡ በማሰተማር በፍቅር የሚኖር እውነተኛ አማኝና ለአገሩ በተገቢ መልኩ የሚቆርቆር ሕዝብ ማፍራት ይኖርባቸዋል፡፡ ሌላው ከእኔ ሌላ አዋቂና እውነተኛ ክርስቲያን የለም በማለት እንደ ጎረቢት አገሮች ጦር ሰብቆ ከመነሳትና ወንድምን ጥላሸት እየቀቡ ከማሳደድ ይልቅ የክርስትና ታሪካችን እንደሚገባ ተጠንቶ አሁን እየሆነ ካለው ክርስትናችን ጋር ተመሳክሮ መታረም የሚገባው ጉዳይ ቢስተካከል ብልህነት ከመሆኑም በላይ እየመጣ ካለው መከራም መትረፍና ማትረፍ ስለሆነ ሁላችንም ቆም ብለን በማሰብ የጋራ እርምጃ እንድንወስድ በእግዚአብሔርና በየዋሁ ሕዝባችን ስም እጠይቃለሁ!!!!

4.2 ኢትዮጵያዊነት ከፕሮቴስታንት አማኞች አንፃር፡-

ኢትዮጵያውያን ፕሮቴስታንቶች መጤ ሃይማኖት ወይም ጴንጤ በመባል የሚታወቁ መመሪያቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ያደረጉና አብዛኛዎቹ ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲን የፈለሱና ይችው ቤ/ክ ስማቸውን ፀረ-ማርያም ብላ የምትጠራቸው የወንጌል አማኞች ናቸው፡፡ አባላትም ወደነዚህ አብያተ ክርስቲያናት በብዛት በመጉረፋቸው በኦርቶዶክስ ቤተ ከርስቲያን ዘንድ እጅግ ይጠላሉ፡፡

ለነገሩ  ከእውቀት ጉድለት የተነሳ ሆኖ ነው እንጂ  “መጤ”  የሚለው አባባል ለሁለቱም  መጠሪያቸው መሆን የሚገባው ስም ነው፤ ምክናያቱም የቅደም ተከተል ጉዳይ ካልሆን በቀር ኦርቶዶክስም ፕሮቴስታንትም ከውጭ የመጡ ስለሆኑ፡፡ ከዚህ በተረፈ አንዱ ሌላውን መጤ በማለት መወንጀሉ ክርስትና ከኢየሩሳሌም ተነስቶ ዓለምን ሁሉ ማዳረሱን ካለመረዳትና ከክርስትና ታሪክ እውቀት ጉድለት የተነሳ የመጣ አባባል ስለሚሆን ከዚህ ይልቅ ኦርቶዶክስን ከፕሮቴስታንቱ እድሜ አንፃር ቀደምት “ቤተክርስቲን” ብሎ መጥራቱ የሚያዋጣ እውነት ይሆናል፡፡

እኔ እንደ ገባኝ የእነዚህ ሁለት ኢትዮጵያን ሃይማኖቶች ቅራኔ ዋና ምንጭ ወንጌልን በመስበክና ባለመስበክ ወይም የተራበን መንጋ ተገቢ የሆነ ምግብ በመመገብና ባለመመገብ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ ችግሩ ይህ ለመሆኑ መረጃ ከተፈለገ ደግሞ ጴንጤ ተብለው በተፈረጁ በእነዚህ ፕሮቴስታንቶች መካከልም እንደዚህ ያለው የአባላት መፍለስ መታየቱ ነው፡፡ ከዚህ እውነት ላይ ተነስተን ማጠቃለል የምንችለው ታዲያ የተራበንና የተጠማን መንጋ በአንድ በረት አጉሮ ማቆም ፈጽሞ የማይቻል መሆኑን ነው፡፡

ነባር አባላትን መጠበቅም ሆነ በጎውን ማን ያሳየናል? በማለት በውጪ የሚቅበዘበዘውን ሰው ሁሉ ወደ እውነተኛው ክርስትና ለመሳብ ከተፈለገ ተበልቶ የሚያጠግብና የሚያረካ ማለፊያ መንፈሳዊ ምግብ በመንፈስ ቅዱስ ምሪትና አስተማሪነት ማዘጋጀት ይገባል፡፡ እንኳን በመንፈስ ቅዱስ የተቀመመ የነፍስ ምግብ ይቅርና በጥሩ ሙያተኛ ለሥጋ ተብሎ የሚዘጋጅ ምግብ እንኳ ሳይቀር ያልተጋበዘ መንገደኛ በላተኛን ሁሉ በጠረኑ ከሩቅ ይጣራል፡፡

ethio protestለመንደርደሪያ ያህል ይህን ካልኩ ዋና ርዕሴ ወደ ሆነው ”ፕሮቴስታንታዊ ኢትዮጵያዊነት” ላይ ልመለስ፤ እነዚህ ወገኖች ቁጥራቸው በየጊዜው እየጨመረ የሚሄድ ሲሆን ለዚህም ምክናያት የሆናቸው የሚሰጡት ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በማተኮሩና እንዲሁም ባህላዊ ከሆነው ከኦርቶዶክሱ ዓይነት አሰጣጥ ለየት ያለ በመሆኑ እንደሆነ ብዙዎቹ ያሰምሩበታል፡፡

አዎ! አድማጭን መማረክ የሚችል አቀራረብ ተቀባይነት ይኖረዋል፤ ሆኖም ግን የእነዚህ ወገኖች ትኩረት እና ጥረት የሰው ሁለንተና በሆነው መንፈስ፣ ነፍስና ሥጋ ላይ ሳይሆን መንፈስና ነፍስ ላይ ብቻ በመሆኑ ሥራቸውን ሙሉ አላደረገላቸውም፡፡ ለዚህ አባባል ምስክር የሚሆኑ ሁለቱ መረጃዎች፡-

በሚያገለግሉት ሕዝብ መካከል ብዙ ሥራ መሥራት የማይወድ ጸሎተኛና በላተኛ ድሃ አባላት መኖሩ እንዲሁም

በኑሮ ችግር ምክናያት በተቀበሉት ፀጋ መጠን ስፍራቸውን ጠብቀው በቀጣይነት በኃይልና በስልጣን የሚያገለግሉ ሠራተኛች አለመበርከታቸው የሚሉት ናቸው፡፡

እንደ እኔ መረዳት እውነተኛ የሆነውን ክርስትና ድህነት የሚያሸንፈው አይመስለኝም፡፡ እንዲያውም “ሊሠራ የማይወድ አይብላ”(2ተሰ 3፡10) በሚለው የመጽሐፍ ቅዱሰ መሪ ጥቅስ ላይ በመመስረት የሥራ ትጋትን በግልም ሆነ በኅብረት በማሳየትና በመባረክ (ባ-ትጥበቅ) ለሌላው ሕዝብ መልካም አርአያ መሆን ያለበት “እውነተኛ ክርስቲያን” ነው፡፡

አዎ! ድህነትን በጸሎት ብቻ ማስወገድ ፈጽሞ አይቻልም፤ የእግዚአብሔር ቃልም አይደግፈንም፡፡ እያንዳንዱ ሰው ግን በአለው አቅምና ችሎታ ከሌላው ወገኑ ጋር በመቀናጀትም ሆነ በግል እየጸለየ ሥራውን በንጽኅናና በትጋት ቢሠራ  እንደ ቃሉ ሰጪ እንጂ ተቀባይ አይሆንም፡፡

እዚህ ላይ ኢትዮጵያውያን ፕሮቴስታንቶች መጽሕፍ ቅዱስ ከሕይወት ሰጪነቱ በተጨማሪ የእውነተኛ ሥራ መመሪያ መጽሐፍ መሆኑን የረሱት ይመስላሉ፡፡ በዚህ መሰረት በመካከላቸው እየሆነ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ተመስርተው በዘመናቸው የሥራን ጥቅም በመረዳት “አንድ ቄስ ለአንድ መቅደስ” ያሉት አፄ ቴወድሮስ  ምነው በዚህ ዘመንም በነበሩ ያሰኛል፡፡ ሐዋርያ፣ ፓስተር፣ ወንጌላዊ ወዘተ በመባል በየቤተ ክርስቲያኑ ያለጥሪና ያለሥራ የተቀመጠውን ሁሉ ልኩን ያሳዩት ነበርና፡፡

ሌላው የኢትዮጵያውያን ፕሮቴስታንቶች ትልቁ ድክመት በአገሪቱ ውስጥ እየሆነ ባለው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ውስጥ በመግባት መሳተፍ አለመቻላቸውና ቸልተኛ መሆናቸው ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንዶችማ “እኛ አገራችን በሰማይ ነው” የሚለውን ጥቅስ በድፍረት ያለቦታው በመጥቀስ ምክንያት ሲሰጡ ሃፍረት በፊታቸው ላይ ፈጽሞ አይታይባቸውም፡፡

በእነዚህ ሰዎች ላይ የሚነሳው ጥያቄ ታዲያ እንደ እውነተኛ ክርስቲያን በሌላው ሕዝብ መካከል እንዴት አድርገው ነው የጽድቅ ተጽዕኖ ማምጣት የሚችሉት? ወይም በምን መልኩ ነው የዓለም ብርሃንና ጨው በመሆን ቃሉን በመታዘዝ ተግባራዊ የሚያደረጉት? የሚለው ይሆናል፡፡ ክርስትና ደግሞ ተግባራዊ በሆነ መልኩ ለሕዝብ ጥቅም በሥራና በፍሬ የሚገለጥ በመሆኑ “የአገራችን በሰማይ ነው፤ ጥቅስ ጠቃሾች ጥቅሱ መቼ፣ ለማንና ለምን እንደተጠቀሰ በመንፈስ ሁነው ሊረዱትና ተጸጽተው በንስሃ አምላካቸው ፊት ሊወድቁበት ይገባል ያሰኛል፡፡ ደግሞም ክርስትና ለሰማያዊ የዘላለም ሕይወት አሁን በምንኖርባት በዚች ምድር ላይ ሁነን በጎ የሆነውን ሁሉ በማድረግ የምንዘጋጀውና በኃጢአት ምክንያት የመረረውን የሰው ኑሮ የምናጣፍጥበት ተግባራዊ እርምጃ እንጂ ስንፍና አይደለም፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ፕሮቴስታንቶችን በአገር ጉዳይ ላይ ተጠያቂ የሚያደርጋቸው ነገር አምልኮአቸውን ከሕዝቡ ልማድና የመረዳት አቅም በላይ ልዩ በማድረጋቸው (ምሳሌ የአዲስ ልሳን አጠቃቀምንና ጾምን በተመለከት) ባህላዊ የሆነው ብዙው ሕዝብ (በተለይ ኦርቶዶክሱ ወገናችን) በመናፍቅነትና በጥላቻ መልኩ እንዲፈርጃቸውና እንዲርቃቸው ከማድረጋቸውም ባሻገር በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ ስም አንድ የሆነው ቁጥረ ብዙው የአገራችን (የኦርቶዶክስ፣የካቶሊክና የፕሮቴስታንት ተከታይ) ሕዝብ ለጋራ የሃገር ጥቅም በጋራ ተሰልፎ መልካም ውጤት እንዳያመጣ ተደርጓል፡፡

እንግዲህ ኢትዮ-ፕሮቴስታንትነት ማለት “የቃሉ እውነት ከገባኝ ለሌላው ምን አገባኝ” ወይም “ትክክለኛ ክርስትና ከእኔ ሌላ ለአሳር ነው” ወይም “ለሌላው ወገን ሕይወት አለመጠንቀቅ” ወይም “በአገር ጉዳይ እኔን ምን አገባኝ” ወይም “ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም ….” እና “አገራችን በሰማይ ነው” የሚሉትንና የመሳሰሉትን ጥቅሶች ያላግባብ በመጥቀስና ለድካማቸው ምክናያት በመስጠት አባላቱ በአብዛኛው በአገሪቱ ላይ መልካም አስተዳደር ሰፍኖ እድገት እንዲመጣ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ በተግባር በመሳተፍ  የዜግነት ድርሻቸውን በአግባቡ መወጣት የማይችሉ ዜጎች ማለት ሊሆን ይችላል ተግባራዊ ትርጉሙ፡፡

መፍትሄው፡ ክርስትና ለሌላው ወገን ጥቅም ጭምር መኖር ማለት ነውና በአገሪቱ ውስጥ እየሆነ ባለው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ላይ ተግባራዊ በሆነ መልኩ በትጋት በመሳተፍ ሌላው ኢትዮጵያዊ ዐይቶ ሊማርና ሊማረክ በሚችልበት መልኩ  ወይም የጽድቅ ተጽዕኖ ሊያመጣ በሚያስችል ሁኔታ ለመገለጥ ሁሉም አማኝ እንደ ዜጋ ጨክኖ ቢነሳ (በተለይ መሪዎች) መልካም ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል፡፡

4.3 ኢትዮጵያዊነት – ከእስልምና አንጻር፡-

ከቅርብ ጊዜ ወዲሕ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ወገኖቻችንን በተመለከተ የሚባለውና እየሆነ ያለው ጉዳይ ዋና የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል፡፡ መቼም ትክክለኛ አዕምሮ ያለው ሰው በደልን፣ ጭቆናን፣ መገፋትን፣ መታሰርንና መሰቃየትን፣ በወገኑ ላይ ይቅርና በጠላቱ ላይ እንኳ ሲደርስ ማየት የሚፈልግ አይመስለኝም፡፡

ከልጅነት እስከ ጎልማሳነት እየሰማን ብቻ ሳይሆን በዐይናችን እያየን ያደገነው ከእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ወገኖች ጋር በጉርብትና ቡና በማጣጣት፣ በጓደኝነት አንድ ክፍል ውስጥ በመማር፣ የየራሳችን ምግብ ተዘጋጅቶልን አብረን በመብላት ሃዘኑንም ሆነ ደስታውን በጋራ በመካፈል የኖርን የአንድ አገር ዜጎች እንጂ ባይተዋርነት ተሰምቶት የሚያውቅ ሰው ፈጽሞ አልነበረም፡፡ ታዲያ በዚህ መልኩ በሰላም ይኖሩ የነበሩ ዜጎች ዛሬ ምን ነገር ተፈጥሮ ነው ይህ ሁሉ መተራመስ የመጣው? የሚል ጥያቄ ማንሳት ይኖርብናል፡፡ አዎ! ጥያቄ ማንሳት ቀላለ ነው፤ ሆኖም ግን ለጥያቄው ተገቢና የሚያረካ መልስ በጥንቃቄ ፈልጎ ትክክለኛና ለሁላችንም የሚበጀውን አቋም ለመያዝ መቻል ደግሞ ብልህነት ነው፡፡

እንደሚታወቀው በዓለም ዙሪያ እየሆነ ላለው የሰላም መደፍረስ ዋናና ግንባር ቀደም ተጠያቂው ማን እንደሆነ ለማንኛችንም የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ሁከትና ብጥብጥ ደግሞ ጤነኛ አእምሮ ያለው ሰው ሁሉ የሚደግፈው አይመስለኝም፤ ነገር ግን ይህን እንቅስቃሴ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚመራው ቡድን በየዋሕነት እንግዳን እየተቀበለች የማስተናገድ ባሕሪ ያላትን ኢትዮጵያ አገራችንን (እንደ ሙሐመድ ተሰዳጆች) ሊጠቀምባት አይችልም ወይም አይፈልግም ብሎ ማሰብ ሞኝነት ይመስለኛል፡፡

ይህ ሲባል በሙስሊም ኢትዮጵያውያን ወገኖች ላይ መጥፎ የጥርጣሬ ዘር ለመበተን ሳይሆን በኑሮ ችግር ምክንያትና በሕዝባችን ድካም በመግባት እንደዚህ ያለ የክፉ ሥራ ሃሳብ ለማራመድ አጥብቀው የሚሹ የጎረቢት ጠላቶች ስለማይጠፉና ሁላችንም ለጉዳዩ ትኩረት ከመስጠት እንዳንዘናጋ ለማሳሰብ ጭምር ነው፡፡ethio muslim

መቼም አንዳንድ መልስ የሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች ቢቀርቡ ሙስሊም  ወገኖች ቅር እንደማትሰኙ እገምታለሁ፡- በአለፈው ጊዜ በጅማ አካባቢ በርካታ ቤተ ክርስቲያንን የማቃጠሉ መጥፎ ተግባር ከየት የመጣ ነው? የውጭ አገር ዜጎችስ ባልተገመተ ሁኔታ በሕዝቡ መካከል መገኘታቸው ለምንድነው? ወዘተ የሚሉትን ጥያቄዎች በማንሳት እነዚህን የመሳሰሉት አሳዛኝ ጉዳዮች በአሁኑ ወቅት በምድራችን መታየታቸው ምክንያቱ ምን ይሆን?በማለት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ እራሱን ደህና አድርጎ እንዲጠይቅና ተገቢ የሆነ መልስ እንዲያገኝ ይፈልጋል፡፡

እውነቱን ከልብ በመነጨ ፍቅር ለመናገር ማንም በራሱ ላይ ሊደረግበት የማይወደውን ነገር በሌላው ወገን ላይ ሲደረግ ሲያይ ዝም ማለት ተገቢ አይደለም፤ ሆኖም ግን ተደረገ የተባለውና እየሆነ ያለውን ጉዳይ በትክክል መረዳትና ተገቢ የሆነ አቅዋም መውሰድ የሁላችንም ግዴታ መሆን ይኖርበታል፡፡

በተረፈ በአጽንዖት ለማሳሰብ ያህል! እንኳን ሰው ሰውን የእኔን ሃይማኖት እመን በማለት ማስገደድ ይቅርና እግዚአብሔር አምላክም ቢሆን “እሺ ብትሉ ብትወዱ ወደ እኔ ኑ” ይላል እንጂ ጉልበት ተጠቅሞ አምልኩኝ አይልም፡፡ ጦር የሚመዝና ነፍስን የሚያጠፋ በጥባጭ ሰይጣን ብቻ ነውና  አገራችንን በጦርነት ባሕር ሊያሰምጧት የሚሹ ገዢዎችም ሆኑ አክራሪ ሃይማኖተኞች ታዲያ ከዚህ የክፋት ሥራቸውና ተንኮላቸው እንዲታቀቡ ለማድረግ ሁላችንም ባለንበት ዘብ እንቁም!!!

ስለዚህ የኢትዮ-ሙስሊም ትርጉም አንደኛው የጥንቱና አሁንም በአብዛኛዎቹ እየተገለጸ ያለው ዓይነት በሰላም አብሮ መኖር፣ መከባበር፣ ለጋራ አገር የጋራ ኣላማ ይዞ መንቀሳቀስ፣ በሃዘንና በደስታ ውስጥ አብሮ መሳተፍ፣ መልካም ጉርብትና ማለት ሲሆን፤ ሌላው ዓይነት “ኢትዮ-ሙስሊም” ማለት ደግሞ በሰሜን የአፍሪካ ክርስቲያን አገሮች (ሞሮኮ፣ ቱኒዢያና አልጀሪያ ወዘተ) ላይ እንደተደረገው በሕዝባችን ላይ ለማድረግ የሚፈልገውን የውጪ ኃይል ትዕዛዝ አድፍጦ የሚጠባበቅና አጋጣሚውን ሁሉ ለመጠቀም የሚቋምጥ ማለት እንደሆነ መዘንጋት የለብንም፡፡ ስለዚህ አገር ወዳድ የሆኑትንና ያልሆኑትን ወይም የተደበቀ ሌላ ስውር ዓላማ ያላቸውን ወገኖች ለይቶ ተገቢ የሆነ እርምጃ ለመውሰድ መሞከር እንጂ ያለውን መንግሥት የተቃወመ ሁሉ ትክክል ነው ብሎ እንቅስቃሴውን በጭፍን መደገፉ ትልቅ ስህተትና ጸጸት ነው የሚሆነውና ጠንቀቅ ማለቱ አይከፋም፡፡

መፍትሔው፡ በጉልበትና በኃይል የሚደረግ ነገር ሁሉ ልብን የሚማርክ ሳይሆን የሚሰብር በመሆኑ ይህን ስልት በመከተል ላይ ያላችሁ ያገሪቱ ዜጎች በሙሉ ይህን አሳሳቢ የሆነ የወቅቱ ጉዳይ  ቸል ባለማለትና በማስተዋል በመከታተል የየግላቸንን ድርሻ በመወጣት ይህን ለዘመናት በሰላም አብሮ የኖረ ሕዝብ ከአንዣበበት የጥፋት ደመና አምልጠን እንድናስመልጠው በጋራ እንነሳ፡፡ እየሆነ ያለውን ሁኔታም በጭፍን አንደግፍ!!! እንዲሁም አንቃወም!!! የጠራ አቋም በመረጃና በእውቀት ላይ ተመስርተን እንያዝ፣ ተግባራዊ እርምጃም በጋራ በመውሰድ እንጂ፡፡

አጭር ማጠቃለያ!!!

ይህ ከዚህ በላይ የቀረበው አስተያየት ኢትዮጵያዊ ነን የምንል ሁላችንን የሚመለከት ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም በምድሪቱ ላይ እየሆነ ያለውን አጠቃላይ የሕዝብ ችግር ማስወገድ የምንችለው እኛው እራሳችን በእውነትና በፍቅር ተቀራርበን በመወያየት መልካም የሆነውን ስናደርግ እንጂ በመነቃቀፍ ስላልሆነ በዚሕ ጽሑፍ ላይ ለማስቀመጥ እንደተሞከረው ድካማችንን በማስወገድና የሆነውን ማንነታችንን አምነን በመቀበል በጋራ በመመካከር እንነሳ በማለት ለማሳሰብ ነውና ስህተት ካለ ለመታረም ዝግጁ ነኝ፡፡ ደግሞም ስንደግፍና ስንቃወም ጉዳዩን በሚገባ ተረድተን ቢሆንና እንዲሁም የዛሬን ጊዜያዊ ድል ሳይሆን መጪውን የአገር አጠቃላይ ዘላቂ ጥቅምን አሻግሮ በማየት ቢሆን መልካም ይሆናል፡፡ አስተዋይ ልቦና ይስጠን!!!

አገራችንን እግዚአብሔር ይጠብቃት!!!

ተናገር  ነኝ

lemisgana2012@gmail.com

http://www.goolgule.com/who-are-you/

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *