መግቢያ

ኢትዮጵያ ከሌሎች የዓለም ሀገራት በተለየ የምስጢራት እና የጥበባት መገኛ ነች ፡፡ ለዚህም ዋንኛው መንስኤ በምድራዊ ሰማያትና በሰማያተ ሰማያት በሚገኙት መላእክት ቅዱሳን አባቶች ብሎም የአዳም ልጆች መካከል ግንኙነት ከሚፈጠርባቸው በምድር ላይ ከሚገኙት ሰባቱ የክብር ቦታዎች መካከል አራቱን ይዛ መገኘቷ ነው፡፡ ከነዚህ የክብር ቦታዎች አንዱ የየረር ተራራ ሲሆን ወደዚህ ምስጢራዊ የክብር ቦታ ጉዞ ያዘጋጀሁበት ዋነኛ ዓላማም በራፋቶኤል ዙሪያ ያሉና የጥንቷን ኢትዮጵያ ናፋቂ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ምድራችን ኢትዮጵያ የያዘችውን መንፈሳዊ ጸጋ እና ጥበብ በመረዳት እንዲሁም የምስጢራቱን መገኛ እንዲመለከቱ በማድረግ ከአባቶች በረከት እና እውቀት እንዲቋደሱ ለማስቻል ነው፡፡ ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት በርካታ ቅዱሳን አባቶች ከብሔረ ህያዋያን በመምጣት ምድራችን ኢትዮጵያን የሚጎበኟት ሲሆን በቆይታቸው የሚያርፉባቸው ሰባት የክብር ቦታዎች አሉ፡፡

እነዚህ የክብር ቦታዎች በተጨማሪም ቅዱሳነ መላእክት ወደዚህ ምድር ለመልእክት ሲወርዱ ሲወጡ የሚያርፉባቸው ቦታዎችም ናቸው፡፡ ከነዚህ ቦታዎች አራቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ቀሪዎችም ቢሆን ከሰባት መቶ ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ግዛት በነበሩት የመን ሲና በርሃ እና ኢየሩሳሌም ግዛቶች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በዚህም የተነሳ አባቶቻችን ሰማያዊና ምድራዊ የሆነውን ጥበብ እና ምስጢራት ከቅዱሳኑ ማግኘት ችለዋል፡፡ ይህም ዛሬም ድረስ ለዓለም እንቆቅልሽ የሆኑ የጥበብ ስራዎችን ሰርተውልን እንዲያልፉ አስችሏቸዋል፡፡ ለአብነትም በሶስት የተለያዩ ቀለማት የተገነቡትንና በራሳቸው በአባቶቻችን የተሰወሩትን ከግብጽ ፒራሚዶች በመጠናቸው የሚበልጡትን ፒራሚዶች በርካታ ከቋጥኝ ድንጋይ የተፈለፈሉ አብያተ ክርስትያናትን በርካታ የተሰወሩ ከተሞች እንዲሁም በርካታ የኣለማችንን ምድራዊ እና ሰማያዊ ጥበቦችን ያስቀመጡበትን ጥንታዊ መጻህፍትን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ቅዱሳን መላእክት አባታችን አዳምን የምድራዊ ሰማያትን እና የሰማያተ ሰማያትን ምስጢራት እና ጥበባትን አስተምረውታል፡፡ ታዲያ አባታችን አዳም ርስት ተደርጋ በተሰጠችው ኢትዮጵያ እና የምድር ማእከላዊ ስፍራ በሆነው የረር በሚገኘው ተራራ ላይ ለኢትዮጵያውያን ልጆቹ ያገኘውን የረቀቀ የሰማያተ ሰማያትና የምድራዊ ሰማያትን ጥበቦች ስላስተማራቸው በዘመናቸው ሃያል እና ገናና ህዝቦች ሆነው አልፈዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን እስከ ሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ድረስ ሀያላን ሆነው የዘለቁበት ምክንያት ለዚህ ትውልድ እና ለተቀረው ዓለም የተሰወሩትን ስድስቱን ምስጢራትን ተረድተው በመጠበቃቸው ነው፡፡ እነዚህ ስድስቱ ምስጢራተ ጥበባት ሰማያዊ የሆነው ምስጢር በመያዛቸው የዓለማችን የሃይል ሚዛን የመቀየር አቅም አላቸው ቢሆንም ግን ከሶስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኃላ ከስድስቱ ምስጢረ ጥበባት ወጥተን እንደራሳችን ሀሳብ መራመድ ስንጀምር ነገሮች ሁሉ ተሸፈኑብን ወደ ስድስቱ ምሲጢረ ጥበባት የሚያደርሰን መንገድም ተዘጋብን፡፡
ይህ ቢሆንም ግን ሃገራችን ኢትዮጵያን ከሌላው ሀገራት ለየት የሚያደርጋት ሌሎች ነገሮች አሉ ይህም ደግሞ የሃገራችንን ታሪክ ብቻ ሳይሆን የዓለማችን ታሪኮች መዝግባ ይዛ ለዚህ ዘመን ማድረስ መቻሏ ነው፡፡ ለዚህም ትልቁን የአንበሳ ድርሻ የምትይዘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትን ናት፡፡ ኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ሲሆኑ አብዛኛውን የዓለማችንን የተነገሩም ያልተነገሩ ታሪኮችን ይዛ ያቆየቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ናት፡፡
ኢትዮጵያ በአንድም በሌላው መልኩ ስልጣኔን በዓለማችን ላይ ያስፋፋች ቀዳሚ ሃገር ስትሆን ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ሰዎች ወደሃገራችን በመምጣት ፍልሰፍናን የአስተዳደር ስርአተን ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን የጊዜ አቆጣጠርን እና ሌሎች በርካታ ጥበቦችን ከአባቶቻችን በመማር ወደተቀረው የዓለማችን ክፍሎች አስፋፍተዋል፡፡
ቅድስት ሃገራችን ኢትዮጵያ ፈጣሪዋን አውቃ በሶስቱም ህግጋት እግዚአብሔርን ስታመልክም ማንም ቀዳሚ አልነበራትም ዓለም ሁሉ በአምልኮ ጣኦት ባህር ውስጥ ሲዋኝ በሞራል ስብራትና ስነልቦናዊ ውዥንብር ውስጥ ተዘፍቆ አምላኩን ሲያሳዝን በነበረት ዘመን ሁሉ እንደ ርእሰ አበው እንደ አብርሃም በተፈጥሮ ባገኘችው እውቀት የእግዚአብሔርን ሀልዎትን አውቃ ከኔ በቀር ሌላ አምላክ አታምልክ የሚለውን አምላካዊ ቃልና ሌሎችን ትእዛዛት ተቀብላ የኖረችበት በእግዚአብሔር ፈቃድም በቀዳማዊ ምንሊክ አማካኝነት ታቦተ ጽዮንን አምጥታ ለመስዋእተ ኦሪት የኖረች የክርስቶስን የባህርይ አምላክነት በፍጹምነት አምና በመቀበል በእግዚአብሔር ትእዛዝ በሐዋርያው በፊሊጶስ እጅ የተጠመቀች ሀገረ እግዚአብሔር መሆኗም በቅዱሰ መጽሀፍ በብዙ ስፍራ የተረጋገጠላት የቅዱሳን ማረፊያ የምስጢራት ምድር ጥናታዊት ሃገር ናት፡፡
ከላይ እንደገለጽኩት የሁለት ሺህ ዓመታት የሀዲስ ኪዳን አገልግሎት የእድሜ ባለጸጋ የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ለሀገራችን ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለማችን የታሪክ የስልጣኔ የባህል የፍልስፍና የነጻነት የአንድነት የጥበብ የምስጢራት ማእከል ሆና መቆየቷ መኖሯ የማይታበል ሀቅ ነው ፡፡
እንደዛሬው ዘመን ዘመናዊ የህትመት መሳሪያዎች ባልነበሩበት በዚያ ዘመን ብራና ፍቃ ቀለም በጥብጣ መቃ ቀርጻ ቅዱሳት መጻህፍትን ሰማያዊ ጥበቦችን እና ምስጢራትን ባህልን ስነምግባርን ፍልስፍናን ለልጆቿ በማስተማር አንቱ የተባሉ ታላላቅ የጥበብ ሰዎችን ያፈራች ከማንም ሀገር ያልተዳቀለና የራሳችን የሆነ ለዓለም ፊደላት መሰረት እና መነሻ የሆነ ፊደል አኃዝና የቀን መቁጠርያ ያዘጋጀች ህዝቡ በመንፈሳዊ ህይወት በስነምግባር ታንጾና ተጠብቆ ስነአእምሮዋዎ ደህንነቱም የተጠበቀ እንዲሆን ለእያንዳንዱ ቤተሰብ የንስሃ አባት በማዘጋጀት የምክር አገልግሎት ከሳይንሱ አስቀድማ እየሰጠች ስታገለግል የቆየችው ሀገርን የሚወር የውጭ ጠላትም በመጣ ጊዜ ከጀግኖች አባቶቻችን ጋር ታቦት ይዛ በየጦር ግንባሩ በመዝመት በጸሎት ከፈጣሪዋ ዘንድ እየጠማጸነች በሰማያዊ ሃይል ድል እና ነጻነት ያስገኘችልን በህዝቡ ዘንድም ፍቅር ሰላም አንድነት መተሳሰብ መረዳዳት እንዲጎለብት የጽዋ መንፈሳዊ ማህበራትንና ሰንበቴ በማቋቋም በማስፋፋትና በማጠናከር የእንግዳ ተቀባይነት አብሮ የመብላትና የመጠጣት የመከባበርና የመደጋገፍ ባህላዊ እሴቶች እንዲዳብሩ ያደረገች በመኳንንቱ በመሳፍንቱ መካከል አለመግባበትና ጸብ በተፈጠረባቸው ወቅቶች የእርቅና የሰላም ምልክታችን የሆነውን መስቀል ይዛ አቀራርባ በማወያየት በማስማማት በማስታረቅ የዲፕሎማሲ ስራ በመስራት የሀገር አንድነትን እያስጠበቀች የኖረችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ናት !!!
ታዲያ የኢትዮጵያ ገናናነት እና ሃያልነት ከቅርብ መቶ ዓመታት ወዲህ እየተዳከመ ጥበቦቿ እና ምጢራቶቿ እንዲሁም ስልጣኔዋ እየደበዘዘ መጥቷል ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ከቅዱሳን መላእክት ያገኘነውን የምድራዊ እና የሰማያዊ ሰማያትን ጥበባት በአንድነት ጠቅልለው የያዙትን ስድስቱን ምስጢረ ጥበባት ችላ ከማለታችን በተጨማሪ በእግዚአብሔርና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የማያቋርጥ ፍቅር እና ትስስር ችላ በማለት በምእራባውያን ባህል እና የፖለቲካ ፍልስፍና በመተካታችን ነው፡፡ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች(መዝ 68፡3) የሚለውን መጽሀፍ ቅዱሳዊ ቃል ዘንግተን እጃችንን ለልመና ወደ ምእራባውያን ሀገራት መዘርጋት የጀመርን ጊዜ ባለፈው ሃያል እና ገናና በነበረው እና በዚህ ትውልድ መካከል የነበረው አሻጋሪ ድልድይ ተሰበረ ሰፊ የትውልድ ልዩነትም ተፈጠረ፡፡ እግዚአብሔርን ሳይሆን ገንዘብን ማምለክ ጀመርን በምእራባውያን ላይ አድሮ የሚሰራው የሉሲፈር መንፈስ በኛም ላይ እንዲሰራ ራሳችንን አስገዛንለት በዚህም የተነሳ ከሰማይ ከሰማያዊ ሃይላት ያገኘነው እውቀት ጥበባት ሃብታት ሁሉ እየተሰወሩብን እና እየደበዘዙብን ሄዱ ዓምላክም በዚህ በማዘኑ አሳልፎ ሰጠን፡፡
ዓለም ገና ጨለማ ውስጥ በነበረበት ወቅት የእውቀት ብርሃን ፈነጥቆባት የነበረችው ኢትዮጵያ ዛሬ ዛሬ በልጆቿ ጨልሞባት የራሳችን ትተን እውቀት ፍለጋ የምእራባውያንን ጭራ እየተከተልን እንገኛለን፡፡
ራፋቶኤል ይህ ያላዋቂነት ጊዜ መብቃት አለበት ብሎ ያምናል፡፡ ለዚህም የመጀመርያው እርምጃ ይህን ትውልድ ስድስቱን ምስጢረ ጥበባትን ብሎም ያለፈውን የአባቶቻችንን ትሩፋትን ማሳወቅ ነው፡፡ ለውጥ የሚጀመርው ከራስ ነውና የአባቶቻችን የምስጢራዊነታቸው እና የሃይላቸው መሰረት የሆኑትን ስድስቱን ምስጢረ ጥበባት እና በአባታችን አዳም የተሰጠንን የህይወት መጽሀፍ(መጽሀፈ ራዚኤል) አውቀን በማሳወቅ ብሎም ወደ ተግባራዊ ለውጥ በመሻገር የተከናነብነውን የነጮች ካባ አውልቀን በመጣል እውነተኛውን የኢትዮጲያዊነት ካባችን ተጎናጽፈን የተሰበረውን የትውልድ ክፍተት ጠግነን ከአባቶቻችን የተቀበልነውን የእውቀት እና የጥበባት ጮራ አቀጣጥለን የደበዘዘውን ሃያልነታችን ዳግም እንመልሰው ዘንድ ፈቃደ እግዚአብሔርን አንግበን በጋራ እንድንሰራ ራፋቶኤል ከጥልቅ ኢትዮጵያዊነት ፍቅር የመነጨ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

ምስጢረ ኢትዮጵያ ወሰማያት
ለጥንቷ የምስጢራት ምድር ኢትዮጵያ ካለኝ ጥልቅ ፍቅር ይህን ጽሁፍ ለመጻፍ ምንም እንኳ የብእሬን ቀለም ማለብ ብጀምርም ይህ ጥልቅ የምድር ምስጢር በኔ በደካማው አንደበት የሚነገር እና የሚተነተን ሆኖ አይደለም፡፡ ቢሆንም ግን ይህ በምእራባውያን ማንነቱን የተሰለበ ትውልዳችንን ከሞራል ስብራትና ዝቅጠት ውስጥ ለማውጣት ብሎም ብቁ መንፈሳዊ ዜጋ በማድረግ ኢትዮጵያን ሀገረ እግዚአብሔር ለማሰኘት ብሎም የጥንቷን ኢትዮጵያ ዳግም ለመመልከት የአባቶቻችን እውቀቶች እና ጥበቦች ማጋራት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነገር እንደሆነ አምናለሁ፡፡ በመሆኑም የአባቶቻችን የሃይል ሚዛን ስለነበሩት ስድስቱ ምስጢረ ጥበባት ብሎም ስለሰባቱ የምድራችን የክብር ቦታዎች ከማንሳታችን አስቀድመን የአባቶቻችን አስተምህሮት የሆነውን አምሳላዊ ንድፈ ሀሳብ መሰረት በማድረግ ስለ አስራ ሁለቱ ሰማየ ሰማያት እና ምድራዊ ሰማያት እና ከየረር ተራራና ከሌሎቹ ስድስት የክብር ቦታዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንመለከታለን፡፡
በተምሳሌታዊ እውቀት ትንታኔ መሰረት ማንኛውም ፍጥረት የተፈጠረበት በፍጻሜ ላይ የሚገኝ አሳብ አለው በዚህ መሰረትም ምድራዊ ሰማያት የሰማያተ ሰማያት አምሳል ናት፡፡ በመሆኑም በሰማያተ ሰማያት የሚገኙ ስፍራዎች የፈጣሪያችን መገኛ የሆነውን ማእከላዊ ስፍራ በአራት አቅጣጫ ከበውት እንደሚገኙ እንዲሁ የምድራዊ ሰማያት ክፍል የሆኑት አስራሁለት ስፍራዎች በአራት አቅጣጫ የፈጣሪ ማደሪያ አምሳል በሆነችው ጸሀይ ዙሪያ ይገኛሉ፡፡ ይህን በተምሳሌታዊ ንድፈ ሃሳብ መሰረት ድርሳነ ዑራኤልን ጨምሮ በተለያዩ በተለያዩ ቅዱሳን አዋልድ መጻህፍት እና አባቶች የምድር እምብርት ተብሎ የተጠቀሰው በየረር ተራሮች መሃከል የሚገኘውን ምስጢራዊ ተራራ መሀከል አድርገን ስናጠና ቦታውን በአራት አቅጣጫ የሚከቡትን የምድራዊ ሰማያት አቀማመጥ እንረዳለን ፡፡

ስዕል ፩፡ በዚህ ስእል መሀል ላይ የምንመለከተው ንስር ብዙ አምሳያ ቢኖረውም ከመሀል በመሆኑ በምድራዊ ሰማያት በአራት ክፍሎች በተከበበችው ጸሀይ እንወስደዋለን በሰሜን በወደምስራቁ ያዘነበሉትን ሰባቱ ምድራዊ ሰማያትን የምናገኝ ሲሆን በምስራቅ ሶስት ስፋራዎች ይገኛሉ ከነርሱ አንዷ እኛ የምንኖርባት ምድር ናት በስተደቡብ የስማስያዝ ወገን የሆኑ የሚኖሩበት ሲሆን በስተምእራብ ሲኦል ይገኛል፡፡
በመሬት ላይ ሆነን የምንመለከታት ጸሀይ በአራቱ አቅጣጫ ተከባ የምትገኘውን ሲሆን እኛ የምንኖርባት ምድር ከጸሀይ በስተምእራብ በሚገኘው የመጀመርያው ምድብ ውስጥ ትገኛለች፡፡ በዚህ ምድብ ውስጥ ሌሎች ሁለት ስፍራዎች የሚገኙ ሲሆን ምንም አይነት ፍጡር አይገኝባቸውም፡፡ ይህ ምድብ በቢጫ ቀለም ይወከላል፡፡
በሁለተኛው ምድብ በሰሜን አቅጣጫ በተወሰነ ወደምስራቅ የተጠጉ ሰባት ሰማያት ይገኛሉ፡፡ እኛ በምንኖርበት ምድር ላይ ሆነን ልናያቸው አንችልም፡፡ በዚህ በሁለተኛው ምድብ ውስጥ የሚገኙት ሰባት ሰማያት የቅዱሳን መኖሪያ በመሆናቸው በአረንጓዴ ቀለም ተወክለዋል፡፡ እነዚህ ሰማያት በጥቅሉ ሶስት ጨረቃዎች ይገኙበታል በተጨማሪም የበርካታ አእዋፋት መኖሪያ ነው ገነትና ብሐየረ ህያዋንም በዚህ ስፍራ ውስጥ ይገኛሉ፡፡
በሶስተኛው ምድብ ውስጥ በስተምእራብ በቀይ ቀለም የተወከለ አንድ ስፍራ ብቻ የሚገኝ ሲሆን ይህም ሲዖል ነው፡፡ በአራተኛው ምድብ በሰማያዊ ቀለም የተወከለ ሲሆን የስማዝያ ወገኖች ይኖሩበታል፡፡ እኛ የምንኖርበት መሬት እና በፀሀይ መውጫ አቅጣጫ የሚገኘው ስፍራ በሰማያተ ሰማያት በጥበብ ማደርያ በሚገኘው አራት ፊት ባለው የሰው አምሳል ጠልሰም ይጠበቃል፡፡ እኛ ከምንኖርበት በስተሰሜን አቅጣጫ የሚገኙት ሠባት ስፍራዎች በሰማያተ ሰማያት አራት ፊት ባለው የንስር ጠልሰም ይጠበቃሉ፡፡ እኛ ከምንኖርበት መሬት በስተምእራብ የሚገኘው ስፍራ በሰማያተ ሰማያት በሚገኝ አራት ፊት ባለው የአንበሳ ጠልሰም ይጠበቃል፡፡ እኛ ከምንኖርበት መሬት በስተደቡብ አቅጣጫ የሚገኘው ስፍራ በሰማየ ሰማያት አራት ፊት ባለው የላም አምሳል ይጠበቃል፡፡ በዚህ መሰረት ለበርካታ ሺህ ዘመናት ኢትዮጵያንና ኢትዮጲያዊነትን በንስር አሞራ ይመስል ነበር የኃላ ኃላ ግን አይሁዶች በኛ ላይ በፈጠሩት የታሪክ ሽሚያ አማካይነት በፈጠሩት ታሪክ ንስራችንን አሳጥተውናል፡፡ በዚህም የተነሳ ግብጾች ጀርመኖች እና አሜሪካውያን የሰባቱ ሰማያት መለያ የሆነውን ንስር መለያቸው አድርገውታል፡፡
ልክ እንደ ምድራዊ ሰማያት ሁላ ሰማያተ ሰማያትም የጥበብን ማደርያ ማዕከል በማድረግ በአስራ ሁለት ሥፋራዎችና በአራት ምድቦች ተከፍላ ትገኛለች፡፡ በመሀከል የሚገኘው የጥበብ ማደርያ የፍጥረታት ጌታ የሆነው የአምላካችን እግዚአብሔር መገኛ ነው፡፡ በመጀመርያው ምድብ ሶስት ስፍራዎች ይገኛሉ ከእነዚህም ሁለቱ የአምላካችንን ዙፋን የሚሸከሙት ኪሩብኤል እና ሱራፋኤል የሚገኙበት ስፍራ ነው፡፡ በዚሁ ምድብ የሚገኘው አንድ ስፍራ ባዶ ሲሆን ለአዳም የተዘጋጀለት የክብር መኖርያውና ተስፋ የምናደርጋት መንግስተ ሰማያት ናት፡፡
በሁለተኛው ምድብ እንደምድራዊ ሰማያት ሰባት ሰማያት የሚገኙ ሲሆን ቅዱሳን መላእክት ተከፋፍለው ይኖሩበታል፡፡በሶስተኛው ምድብ አንድ ስፍራ ብቻ የሚገኝ ሲሆን ሳጥናኤል የሚኖርበት ስፍራ ነው፡፡ በመጨረሻው አራተኛ ምድብ ደግሞ ሳጥናኤል አምላክ ነኝ ባለ ጊዜ በመጠራጠራቸው የአየር ላይ ጋኔን ሆነው የቀሩት እና ስማዝያ በሚባለው መልእክ የሚመሩት ነገዶች የሚኖርበት ስፍራ ነው፡፡
በሶስተኛው እና በአራተኛው ምድብ የሚገኙት የሳጥናኤል እና የስማዝያ ነገዶች በመጀመርያው ነገድ ባዶ ሆና የተቀመጠችውን የአዳም ተስፋ የሆነችውን መንግሰተ ሰማያት ለመውረስ ብዙ የጣሩ ሲሆን ይኀውም ሳጥናኤል የአዳም ተስፋው እንደሆነች አስቀድሞ በመረዳቱ በተንኮል ተነሳስቶ በእባብ ተመስሎ አዳምን አስቶ ከገነት አስወጥቶታል፡፡ ከሁሉ የሚከፋው ግን የስማዝያ ተንኮል ሲሆን አሁንም ድረስ የአዳም ተስፋ የሆነችውን መንግስተ ሰማያትን ከሰው ልጆች ጋር ተቀላቅሎ ለመውረስ በርካታ ስውር ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ አሁን ዓለማችንን ከጀርባ ሆነው እየገዝዋት የሚገኙት የምስጢር ሰዎች ወይም Illuminati’s በመባል የሚጠሩት ቡድኖች የስማዝያ ዘሮች ናቸው፡፡
የሰማየ ሰማያት አምሳያ የሆነችው ምድራዊ ሰማያት በመሆኗ አቀማመጣቸውም ተመሳሳይ ነው ይህ በተመሳሳይ ሁኔታ ለየረር ብቻ ሳይሆን ለዓለማችን እምብርት በሆነው በየረር ለሚገኘው ተራራም ይሰራል፡፡ በሰማያተ ሰማያት እና በምድራዊ ሰማያት መካከል የሚገኘው ስፍራ ጠፈር የሚባል ሲሆን በሰማያተ ሰማያት አንድ ቀን በምድራዊ ሰማያት አንድ ሳምንት በገነት አንድ አመት በመሬት አንድ ሺህ ዓመት በሲዖል ሰባት ሺህ ዓመታት ሲሆን በስማዝያ መኖርያ ደግሞ በአንድ ዓመት እና ሰባት ሺህ ዓመታት መካከል ይዋልላል፡፡ ምድራዊ ዓለም ከተፈጠረበት ቀን አንስቶ ፀንቶ እስከሚቆይበት የምንቆጥረው ከሆነ በሰማየ ሰማያት አንድ ዓመት በምድራዊ ሰማያት አንድ ሺህ ዓመታት በገነት ሰባት ሺህ ዓመት በመሬት አንድ ሚሊየን ዓመታት በሲኦል ሰባት ሚሊየን ዓመታት ሲሆን በስማዝያ መኖርያ ደግሞ በሰባት ሺህ ዓመታት እና በሰባት ሚሊየን ዓመታት መካከል ይዋልላል፡፡ ስለዚህ በዚህ መሰረት በምድራዊ ሠማያት የሚገኙት ፍጥረታት በምድራዊ ሰማይ ላይ መኖር ከጀመሩ በሰማየ ሰማያት አቆጣጠር ስድስተኛ ዓመታቸው ላይ ይገኛ ማለት ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን የቀን አቆጣጠራችንም መሰረቱም ይህ የጊዜ አቆጣጠር ሲሆን አባታችን አዳም ወደ እዚህ ምድር ከገነት ተመልሶ ከመጣበት ጊዜ አንስቶ የተቆጠረ ነው፡፡ ይህም በእኛ ስሌት ስድስት ሺ ዓመታትን ሰባት ሺ ዓመታት ውስጥ ይገኛል፡፡ ይህ በሰማየ ሰማያት ስድስተኛው ቀን አልቆ ሰባተኛው ቀን ላይ መሆኑ ነው፡፡ አዳም ወደዚህ ምድር ተመልሶ ከመምጣቱ በፊት በርካታ ጊዜያትን ይህች ምድራዊ ሰማያት አሳልፋለች፡፡ ለዚህም ማስረጃችን አቡሻህር የተሰኘው መጽሃፋችን ነው፡፡
አባታችን አዳም አትብላ የተባለውን እጽ በልቶ ከገነት በተባረረበት ወቅት ቅዱሳን መላእክት በምድራዊ ሰማያት በሁለተኛው ምድብ ከሚገኘው ስፋራ ወደአንደኛው ምድብ ወደምትገኘው ወደዚች ምድር በመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል አማካይነት ሲመጣ መጀመርያ ያረፈውና መጽናኛ ትሆነው ዘንድ ርስት ተደርጋ የተሰጠችው ስፍራ በየረር ተራሮች መካከል በምትገኘው እና የምድር እምብርት በሆነችው ተራራ ላይ ነው፡፡ ይህን ተራራ መሀከል አድርገን በስተሰሜን ስንመለከት የበርካታ ቅዱሳን አባቶች መገኛ የሆነው ደን እና ዋሻዎች እናገኛለን እነዚህ የበቁ የተሰወሩ አባቶች የሚገኙበት ስፍራ በሁለተኛው የምድራዊ ሰማያት ምድብ በሆነው ክፍል ብሄረህያውን የሚገኝበት ቦታ እንደሆነ ልብ ይበሉ በተጨማሪ ሰባቱ ምድራዊ ሰማያት የበርካታ አእዋፋት መኖርያ ሲሆን በዚሁ አቅጣጫ በርካታ አሞሮችና አእዋፋት ወደየረር ማእከላዊ ቦታ ይመጣሉ ይህም አዳም ገነት በነበረበት ወቅት ከሌሎቹ ሰማያት ሊጠይቁት እንደሚመጡት ማለት ነው፡፡ ይህን አንድምታ ስንፈታው በዚህ ተራራ ስር ከሚገኙት ዋሻዎች በአንዱ የሚገኘውን የበቃ ባለትንቢቱን አባት ለመጠየቅ እና ለመመልክት ከቅዱሳን ስፍራ አእዋፋት እና ቅዱሳን ይመጣሉ፡፡
የምድር እምብርት(የረር) እና የኢትዮጵያ ትንሳኤ
የተለያዩ ከብሔረ ህያዋን የሚመጡ ቅዱሳን አባቶችን ጨምሮ ቅዱሳን መላእክት ለመልእክት ወደምድር ሲመጡ የሚያርፉባቸው ሰባት የተመረጡ ቦታዎች አሉ፡፡ እነዚህ የክብር ቦታዎች በሰማያተ ሰማያት እና በምድራዊ ሰማያት መካከል ግንኙነት የሚፈጠርባቸው ታላቅ መንፈሳዊ ቦታዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ሰባት የክብር ቦታዎች መካከል አራቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን አንደኛው የመን ውስጥ ሌላው በሲና በርሃ የተቀረው ደግሞ በእስራኤል ምድር ውስጥ ይገኛል፡፡ እነዚህ የተቀሩት ቦታዎች ቀድሞ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት የክብር ቦታዎች ዋንኛውና አንደኛው በየረር ተራሮች መካከል የሚገኘውና በበርካታ ቅዱሳን መጽሃፍት የምድር እምብርት በተጨማሪም የአዳም ርስት ሃገር ብለን የምንጠራው ስፋራ ነው፡፡ ይህ የምድር እምብርትና ከሰባቱ የክብር ቦታዎች አንዱ የሆነው የአዳም ርስት ቦታ ሶስት ስፍራዎችን በአንድነት ይዟል፡፡
የመጀመርያው የዋሻዎቹ መገኛ ስፍራ ሲሆን ሁለተኛው ከዚህ ተራራ ባሻገር የሚገኘው የረር ብለን በምንጠራው ተራራ መካከል ላይ የሚገኝ ስፍራ ነው ይህም ስፍራ በስተደቡብ የሚገኘውና እመቤታችን ልጇን ይዛ በተሰደደችበት ወቅት ከዚህ ስፍራ ተገኝታ ነበር፡፡ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሀገራችን ኢትዮጵያን አስራት ሀገር አድርጎ የሰጣት በዚህ ስፍራ ላይ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ለስም አጠራሯ ምስጋና ይድረሳትና አሁንም ድረስ የእመቤታችን በረከት ከቦታው ላይ አልተለየም፡፡
ሶስተኛው ክፍል በዋሻዎች መገኛ በምድር ውስጥ የሚገኘው ስፍራ ነው፡፡ የዚህን ተራራ ምስጢር ለመረዳት የቤተክርስትያናችንን አሰራርን ምሳሌ በማድረግ እንመልከት፡፡ በዚህ አካባቢ የሚገኘው ይህ ቤተክርስትያን ሁለት ክፍል ያለው ሲሆን ከመሬት በታችችና በላይ የሚገኘው ክፍል ነው፡፡ ይህ ቤተክርስትያን በሁለት አስተዳዳሪዎች ይመራል የመጀመርዎቹ በአካል የምናገኛቸው አስተዳዳሪዎች ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ በምስጢር ቤተክርስትያኗን እያስተዳደሩ የሚገኙት የተሰወሩ አባቶች ናቸው በዚህ መሰረት የአዳምን ርስት ቦታ የሆነውን ክፍል ስንመለከት ከውጭ በሚገኘው የተራራው ስፍራ በሰሜን በደቡብ እና በምስራቅ በኩል የሚገኙ ዋሻዎች የሚገኙ ሲሆን የታራራው ሌላኛው ክፍል ደግሞ ከተራራው የውስጠኛ ክፍል እና ምድር ውስጥ የሚገኘው የተሰወሩት ከተሞች ናቸው፡፡ በዚህ የውስጠኛው የተሰወረው የከተማው ክፍል ውስጥ አባታችን አዳም ከገነት በተመለሰ ወቅት ለኛ ለህዝቦቹ ቅዱሳን መላእክት ያስተማሩትን የሰማያተ ሰማያት እና የምድራዊ ሰማያት ምስጢራትና ጥበባት እንዲሁም የምድራችንን የሃይል ሚዛን ጠቅልለው የሚይዙት ስድስቱን የክብር እቃዎች ያስቀመጠበት ቦታ ነው፡፡ እነዚህ ሶስት ስፍራዎች በአጠቃላይ የአዳም ርስት ሃገር እንብርት ተብለው ይጠራሉ፡፡
ታዲያ ወደዚህኛው የተራራው ውስጠኛው ስውር ከተማ ለመግባት ሶስት በሮች የሚገኙ ሲሆን የመጀመርያው በምስራቅ በኩል በቴዎድሮስ ቤተክርስትያን ይገኛል፡፡ በዚህኛው መግቢያ በር መጠቀም የሚችሉት ከብሔረህያዋን የሚመጡት ብሎም በዚህ ምድር የሚገኙ ግን የበቁ ስዉራን አባቶች የሚጠቀሙበት በር ነው፡፡ ሁለተኛው መግቢያ በር በምድራዊ ሰማያት ሁለተኛው ምድብ የሚገኙበት እና ጠባቂያቸው ንስር አሞራ በሚገኝበት ስፍራ የሰሜን አቅጣጫ ይገኛል፡፡ በዚህ ስፍራ ሲጠቀሙበት የነበሩት ከሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አስቀድሞ የነበሩት የኢትዮጵያውያን ነገስታት ሲሆኑ ከዚህ በኃላ የገዥነት ክብሩን ይዞ የሚመጣው ንጉሳችን ቶዎድሮስ የሚጠቀምበት መግቢያ በር ነው፡፡ ሶስተኛው መግቢያ በር በስተደቡብ በኩል በእመቤታችን ቤተክርስትያን በኩል ይገኛል፡፡ በዚህ መግቢያ በር የሚጠቀሙት ሴት ነገስታት ናቸው፡፡
ሁለተኛው መግቢያ በር በሚገኝበት እና በርካታ አእዋፋት በሚገኙበት ስፍራ በርካታ የተሰወሩ ቅዱሳን አባቶች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ አባቶች መካከል በስጋዊ ህይወታቸው ስኬታማ የነበሩና በዓለማዊ ትምህርታቸው እስከ ሶስተኛ ድግሪ የዘለቁ ቢሆንም ግን ይህን የምእራባውያንን ጥበብ በመናቅ ስድስቱን ምስጢረ ጥበባት ለማጥናት ራሳቸውን ያስገዙ ናቸው፡፡ እነዚህ አባቶች መካከልም የኢትዮጵያን ትንሳኤ ሳያዩ እንዳይሞቱ ቃልኪዳን ተገብቶላቸው ከሁለት መቶ ሀምሳ አመት በላይ እድሜ ያስቆጠሩ አባቶችም ይገኛሉ፡፡ ሌላው የሚስደንቀው የኢትዮጵያ ትንሳኤ ቅርብ እንደመሆኑ የዓለማችንን የሃይል ሚዛን ዳግም ለመቀልበስ ስድስቱ ምስጢረ ጥበባት

ላይ ሰፊ የሆነ መንፈሳዊ ስራን የሚሰሩና ከስማዝያ ወይም ከምስጢር ሰዎች ገዥ ከሆነው ክፉ መንፈስ ጋር ጦርነት ገጥመው እያሸነፉ ያሉ የቅዱሳን አባቶች ህብረት የሚገኝበትም ስፍራ ነው፡፡ ይህን የሚያውቁ አንዳንድ ዓለምዓቀፍ ተቋማትም ሆኑ የውስጥ አካላቶች ቦታው ላይ እና የአባቶቻችን ህብረት ላይ ጥቃት በመሰንዘር የአካባቢውን ምስጢር ለመቆጣጠር ቢሞክሩም የረር ግን ራሱን ይጠብቃል ምንም ማድረግ አልቻሉም፡፡
አባታችን አዳም ይህችን ቦታ ርስት አድርጎ ካገኘበት ጊዜ ጀምሮ በምድራችን ላይ የነበሩት አባቶቻችን በየረር በሚገኘው የምድር ማእከል ስር የተቀመጠላቸውን ስድስቱን ምስጢረ ጥበባት እና ስድስቱን የክብር እቃዎች አንድ ላይ ባዋሃዱበት ምስጢራት በመመራት እና በጥበቦቹ ጸንተው በመኖር ታላቅ ህዝቦች ሆነው አልፈዋል፡፡ እነዚህ ስድስቱ ምስጢረ ጥበባት ከሰው አእምሮ የሚረቁ ጥበቦች የያዙ ሲሆን ከሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ በኃላ በተለያዩ ምክንያች ስድስቱን ምስጢራተ ጥበባቶች ችላ በማለታችን ከፍ ካልንበት የሃያልነታችንን ዘውድ አሽቀንጥረን ጥለን የውርደት ካባን ተከናንበናል፡፡ለዚህም ታላቁን ሚና የተጫወቱት የስማዝያ ወገን የሆኑት አይሁዶችና የምስጢር ቡድኖች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ጠላቶቻችንም ዳግም ወደነበርንበት የገዥነት ዙፋን እንዳንመለስ እነዚህን ስድስቱ ምስጢራተ ጥበባትን ከአእምሮዋችን ለመስለብ ብዙ ሴራዎች የሰሩ ሲሆን ወደመጨረሻ በሰፊው እንመለከተዋለን፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያን ትንሳኤ ስናልም ስድስቱ ምስጢራተ ጥበባት አያይዘን ማሰባችን ብሎም ትውልዱን ስለነዚህ ጥበባት ግንዛቤ መፍጠር የመንገዱ ግማሽ መንገድ ነው፡፡ ልብ ይበሉ ጊዜው ደርሷል ኢትዮጵያ ትንሳኤ ቀርቧል ስድስቱ ምስጢራተ ጥበባትና ስድስቱ የክብር እቃዎች መገለጫ ምልክቱም ይህ ነው እኔ እና እናንተ ይህን መነጋገር መጀመራችን . . . .
ስድስቱ ምስጢረ ጥበባት እና የዓለማችን የሃይል ሚዛን
አባታችን አዳም አትብላ የተባለውን እጽ በልቶ ከገነት በወጣ ወቅት የአዳም የቅርብ ወዳጅ የሆነው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልና ሌሎች መላእክት ከገነት ይዘውት እንደተመለሱ ሀዘኑን እና ትካዜውን ያስረሳለታል ብለው ያሰቡት ቦታ ማለትም አዳም ርስት ብለው የጠቀስነውን በየረር በሚገኘው እምብርት ቦታ አስቀምጠውታል፡፡ ታዲያ የአዳምን የአላዋቂነት እና የየዋህነት ባህሪውን ተረድቶ ሳጥናኤል በቀላሉ እንደረታው ቅዱሳን መላእክት ስለተረዱ ድል የሚነሳበትን የምድራዊ ሰማያና የሰማያተ ሰማያትን ጥበቦች አስተምረውታል፡፡ አዳምም ይህን ከቅዱሳን መላእክት የተማረውን ትምህርት በድንጋይ ላይ ጽፎ በርስት ቦታው ላይ አስቀምጦታል፡፡ የአዳም ልጆች የሆኑት ኢትዮጵያውያንም መንግስታቸውን እንዴት ስድስቱን ምስጢረ ጥበባትን ተጠቅመው መግዛት እንዳለባቸው ከአዳም አባታቸው የተማሩትን ምስጢራቶች ጠብቀው በመኖራቸው በዘመናቸው ሃያላን ሆነው አልፈዋል፡፡ የኃላ ኃላ ግን እንደራሳችን ሃሳብ እና እንደምእራባውያን ጠባብ ፍልስፍና መመራት ጀምረን እነዚህ ምስጢራት ችላ ስንል የገዥነት ክብራችን አጣን፡፡
ስድስቱ ምስጢረ ጥበባት እኛ በምንኖርባት ምድርም ሆነ በሌሎች ምድራዊ ሰማያት ላይ የገዥነት ክብራችንን የምናገኝበት ሰማያዊ ጥበብ ነው፡፡ ስደስቱ ምስጢረ ጥበባት ብለን የምንጠራቸውም ፡ 1. ስም
2. በረከት
3. ሃይል
4. ስልጣን
5. ህብረት
6. ጥበብ ናቸው፡፡
እነዚህ ምስጢራት ለማብራራት የኔ እውቀት ቢገድብኝም ያለችንኝም አረዳድ ለመተንተንብዙ ወረቀቶችን ማብዛት ይኖርብናል ምክንያቱም ሰፊ የሆኑ ምስጢር አዘል እውቀት በመሆኑ ነው፡፡፡ ቢሆንም ግን በአጭሩ ለእርስዎ ግልጽ ለማድግ ልሞክር፡፡
1. ስም
በመጀመርያ ደረጃ የተቀመጠው ምስጥራዊ ጥበብ ስም ነው፡፡ የዚህን እውቀት በቀላሉ ለማስረዳት ራፋቶኤል የተሰኘው የኔ ስም ለመክበሬም ይሁን ለውርደቴ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል፡፡ እኔን ሳታውቁኝ በፊት ስለእኔ መልካምነት ሰምተው ከሆነ እኔን ሲያገኙኝ ለሀሳቤ ተገዥ ይሆናሉ ድርጊቶቼንም በመልካም ጎኑ ይረዱታል በተቃራኒው ግን እኔን ከማግኘትው አስቀድሞ ስለራፋቶኤል ምግባረ ብሉሽነት ቢሰሙ ሲያገኙኝ ለሃሰቤ ተገዥ መሆን ይከብደዎታል ራስዎንም ለኔ ከማስገዛት ይቆጠባሉ፡፡
ሰው በስሙ እጅግ የከበረ ቢሆን በእዚሁ በከበረው ስሙ የሚፈልገውን ማከናወን ይችላል ምክንያቱመ አስቀድሞ የከበረው ስሙ ከእሱ በፊት እየተገኘ ሁሉን ያድርግለታል፡፡ ስምን መልአክ ያወጣዋል እንዲሉ እኛ ከመክበራችን በፊት ቀድሞ የሚከብረው ስማችን ነው፡፡ እኛ ሄደን ድል ከማድረጋችን አስቀድሞ ድል የሚያደርገው ስማችን ነው፡፡ በተጨማሪም ተፈጥሯዊ የሆነውን ባህሪያችንን እና ከየትኞቹ መላእክት ጋር አስተሳሰባችን ህበረት እንዳለው መረዳት የምንችለውም በስማችን ነው፡፡ይህ እኛ ስም የምንለው ጥበብ አሁን ፖለቲካ ብለን የምንጠራው ፍልስፍና ነው፡፡

2. በረከት
ሁለተኛው በረከት ተብሎ የተሰየመው ምስጢረ ጥበብ ነው፡፡ እኛ የሰው ልጆች በስጋችን ብቻ ሳይሆን በነፍሳችንም በረከትን እናገኛለን፡፡ በስጋችን የምናገኛቸው በረከቶች ቁሳዊ የሆኑት ሃብትን ንብረቶቻችን ሲሆን በነፍሳችን የምናገኘው በረከት ደግሞ በምድራዊ ሰማያት በገነት በሰማያተ ሰማያት ደግሞ በመንግስተ ሰማያት ገብቶ የሚያገኘው የደስታ ሕይወት ሲሆን በዚች ምድር ደግሞ እያለ የሚኖርው ውስጣዊ የሆኑ ሃብቶቹ ናቸው እነዚህም ጤና ትህትና ፍቅር ሰላም ተስፋ እና እርጋታ የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ይህን ቀለል ባለ አንደበት ለመረዳት ሰው ከእሱ በላይ በስጋም በነፍስም ለከበረ ፍጥረት ራሱን ያስገዛል፡፡ ሀሳቡን ከመቀበል ባለፈም ይገዙለታል ይህም ያለው ማማሩ ወደሚለው ጥግ ያደርሰናል፡፡ ከአዳም በኃላ የነበሩት ኢትዮጵያውያን ነገስታት ህዝቡ እንደ ችሎታውና እንደስራ መስኩ ቁሳዊውን ሀብትና ንብረት በጥረታቸው እንዲያፈሩ ሲያድርጉ ቅዱሳን አባቶች በበኩላቸው መንፈሳዊውን በረከት በህዝቡ ላይ ያመጡ ነበር፡፡ ህዝቡም እነዚህን ስጋዊና መንፈሳዊ በረከቶቹን አንድ ላይ በማጣመር በኢኮኖሚ ወይም በበረከት የበለጸገች ሃገርን ገንብተዋል፡፡ ታዲያ ቁሳዊ ሃብታችን ዘሌቄታዊ እድገት እንዲኖረው ብሎም ባለን ሃብትም ደስትኛ ለመሆን መንፈሳዊ በረከት ያስፈልገናል ይህ የሚሆነው ደግሞ ቁሳዊ ሃብታችን ከመንፈሳዊ ሃብታችን ጋር ግንኙነት ሲኖረው ነው፡፡ ይህ የበረከት ጥበብ አሁን ኢኮኖሚ ብለን የምንጠራው ነው፡፡

3. ሃይል
አባታችን አዳም በድሎ ወደዚች ምድር ዳግም ከመመለሱ አስቀድሞ በአራት ምድብ የተከፈሉት አስራሁለቱ ምድራዊ ሰማያት ገዢ እና አስተዳዳሪ ስለነበር የገዥነት ሃይል አብሮ ተሰጥቶት ነበር ቢሆንም የኃላ እግዚአብሐየርን አሳዝኖ የገዥነት ክብሩን አጥቶ ወደምድር ሲመለስ ቅዱሳን መላእክት በምድር ላይ ለሚኖሮ ልጆቹ ይጠቅመው ዘንድ ለምድር ፍጥረታት የሚያገለገል የሃይልን ጥበብ አስተምረውታል፡፡ ይህ ጥበብ በምድር ላይ የሚገኙ ማንኛውንም አይነት ፍጡራን ክፉ መናፍስትን ጨምሮ ለማንበርከክ የሚያስችል ሃይል ነው፡፡ ሰው ከእርሱ በላይ ለሆነ ሃይል እንደሚገዛ እንዲሁም ሃገራትም የላቀ ሃይል ላለው መንግስት ይንበረከካሉ፡፡ የጥንቷ ኢትዮጵያ የገዥነት ሃይልም ከዚህ የመነጨ ነው፡፡ ይህ የሃይል ጥበብ በዚህ በኛ ጊዜ መከላከያ ወይም ሚሊተሪ የምንለው ነው፡፡ በዚህ ዘመን የሚኖረው ትውልድ በኃይል የበላይነቱን ለመያዝ እጅግ የረቀቀ የጦር መሳሪያዎችን የሚጠቀም ሲሆን ጥንት የነበሩት አባቶቻችን ደግሞ በዘመናቸው የበላይነትን መያዝ የቻሉት በምድራዊ ሰማይትና በሰማየ ሰማያት ከሚገኙ ቅዱሳን መላእክት ጋር ህብረት በመፍጠራቸው ነው፡፡ ከጠላት ጋር ውጊያ በገጠሙ ወቅት ቅዱሳን መላእክት በግልጽም ሆነ በስውር አብረዋቸው በመሰለፍ ጠላትን ድል ይነሱላቸው ነበር፡፡

4. ስልጣን
አባታችን አዳም የገዥነት ክብሩን ይዞ የተወለደ ሲሆን በምድራዊ ሰማያት የሚገኙትን አስራሁለቱን ሰማያት እና በውስጣቸው የሚገኙትን ፍጥረታት ይገዛና ያስተዳድር ነበር፡፡ ታዲያ በነዚህ ሰማያት የሚገኙ ፍጥረታት ተገዥነታቸውን ለማሳየት አዳም በነበረበት ገነት በመመላለስ ይሰግዱለት ነበር፡፡ ኃላ ግን አዳም የገዥነት ክብሩን ከምድራዊ ሰማያት ላይ ቢነፈግም ቅዱሳን መላእክት የገዥነት ክብሩን የሚያገኝበትን ምስጢር አስተምረውታል፡፡ አዳምም ይህን ጥበብ ርስት ተደርጋ ለተሰጠችው ምድር ህዝቦች አስተምሮዋቸዋል፡፡ እነዚህ ህዝቦች የቀደሙት ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውን በነዚህ ምስጢራተ ጥበባት ጸንተው በመቆየታቸው የገዥነት ክብራቸውን እስከሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ አስጠብቀው ቢቆዩም ከዛ በኃላ የመጣው ትውልድ ግን እነዚህን ጥበባት ንቀው ምእራባውያን የስማዝያ ወገኖች ባሳዯቸው መንገድ በመጓዛቸው የውርደትን ካባ ተከናንበን የድህነት ጭራ ስር ተገኝተናል፡፡

5. ህብረት
አዳም ከተፈጠረ ጊዜ አንስቶ ከቅዱሳን መላእክት ጋር መልካም የሆነ የወንድማማችነት ህብረት ነበረው በዚህም የተነሳ የቅርብ ወዳጁ በሆነው በመልአኩ በቅዱሳ ገብርኤል አማካይነት ወደገነት ተሸጋግሮ ምድራዊ ሰማያትን ይገዛ ነበር በኃላም አምላክን በድሎ ወደምድር በመጣ ጊዜ ቅዱሳን መላእክት አልተለዬቱም ይልቁንስ የምድራዊና የሰማያ ሰማይትን ጥበባት አስተምረው የኢትዮጵያን ምድር መጽናኛ እንድትሆነው ሰጥተውታል፡፡ ከዚህም በኃላ ቢሆን ስድስቱን ምስጢረ ጥበባትና ስድስቱን የክብር እቃዎች ሰጥተውት የገዥነት ክብሩን መልሰውለታል፡፡ ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው ታዲያ አዳም ከቅዱሳኑ ጋር በፈጠረው ህብረት መሆኑን የተረዱት ጥንታውያን አባቶቻችን ከተለያዩ ሰማያዊ መላእክት ሰማእታት ቅዱሳን ሐዋርያት አባቶች ጋር በፈጠሩት ህብረት አማካይነት የገዥነት ክብራቸውን ጠብቀው የኢትዮጵያን ግዛት አስፋፍተዋል፡፡ ይህ የህብረት ምስጢረ ጥበብ አሁን በዚህ ዘመን ዲፕሎማሲ የምንለው ነው፡፡

6. ጥበብ
ይህ የመጨረሻው ጥበብ ከላይ የዘረዘርናቸውን ምስጢረ ጥበባት በግለሰባዊ ህይወታችን በንግድ ድርጅታችን ብሎም በሀገር ደረጃ እንዴት ተጠቅመን የገዥነት ሃይላችንን እንደምናገኝ የምንረዳበት ዋንኛው ምሰሶ ነው፡፡ይህ ጥበብ ተብሎ የተጠቀሰው በዚህ ዘመን ቴክኖሎጂ የምንለው ነው፡፡ እነዚህን ስድስት ምስጢረ ጥበባት የምንጠቀምባቸው ሌሎች ስድስት የአዳም የክብር እቃዎች ይገኛሉ፡፡ ስድስቱ ምስጢረ ጥበባትና ስድስቱ የክብር እቃዎች በአንድ ሲዋሃዱ ዳግም የዚች ምድር ትንሳኤ ይሆናል የገዥነት ክብሯም ይመለሳል፡፡

ስድስቱ የክብር እቃዎች እና ባለትንቢቱ ንጉስ ቶዎድሮስ
አባታችን አዳም ከገነት በተባረረበት ወቅት በመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እና በሌሎችም ቅዱሳን መልአክት አማካይነት የገዥነት ክብሩን የሚመልስበትን ስድስቱን ምስጢረ ጥበባትን የተማረ ሲሆን እነዚህን ጥበባት የሚያዋህድበት ወይም የሚያሰራበት ስድስት የክብር እቃዎችን ይዞ መጥቷል፡፡ እነዚህ ስድስት የክብር እቃዎች የአዳም ርስት ቦታ ብለን ከላይ በገለጽነው እና የምድር እምብርት በሆነው የየረር ተራራ ውስጥ ተሰውሮ ይገኛል፡፡ እነዚህ ስድስት የክብር እቃዎች በዚህ ጽሁፍ ላይ ለማብራራት ባልፈቅድም በአጭሩ ግን ግንዛቤ ለመስጠት እሞክራለሁ፡፡
1. እጽ
ይህ እጽ የተባለ የክብር እቃ አባታችን አዳም ከገነት ይዞት የመጣው የመጀመርያው የክብር እቃ ሲሆን ባለትንቢቱ ንጉስ ቶዎድሮስ የሚይዠው እጽ ( በትረ ሙሴ) የተሰራበት ነው፡፡ ይህ የንጉሱ በትረ ሙሴ አንደኛው የሃይሉ ምንጭ ይሆናል፡፡ ይህ እጽ በቀጥታ ስም ካልነው ምስጢረ ጥበባት ጋር ይያያዛል ይኀውም ፖለቲካ ያልነው ነው፡፡
2. ጽላት
በታሪክ የምናውቀው ለምድራችን የመጀመርያዋ እና ታላቅ መንፈሳዊ ሃይል ያላት ጽላት ታበተ ጽን እንደሆነች ነው ይሁን እንጂ ለምድራችን የመጀመርያዋ ጽላት አዳም ከገነት ይዞት የመጣው ጽላተ አዳም ነው፡፡ ይህ ጽላት ለሰው ልጆች የእለት ተእለት ኑሮ ብሎም ለሃገር ስጋዊና መንፈሳዊ በረከትን ያመጣል፡፡ ባለትንቢቱ ንጉስ የምድራችን ኢኮኖሚ ወይም በረከት የተሰኘውም ምስጢረ ጥበብ የሚገነባው ይህን ጽላት ተጠቅሞ ይሆናል፡፡
3. ገረረ ሰረገላ
ሶስተኛው የክብር እቃ ገረረ ሰረገላ የሚባል ሲሆን ይኀውም እንደሌሎቹ አዳም ከገነት ያመጣው የክብር እቃ ነው፡፡ ይህ ሰረገላ ለዘመናት ለኢትዮጵያውያን የሃይላቸው ምንጭ ነበር፡፡ በተጨማሪም አሁን ድረስ አንዳንድ ምስጢራዊ መረጃዎች የሚያመለክቱት ሮም ገናና በነበረችበት ወቅት የኃይላ ምንጭ ይህ ገረረ ሰረገላ ነበር ኃላ ግን ከባቢሎዋውያን ጋር ውጊያ ላይ በነበሩበት ወቅት ይህ ገረረ ሰረገላ ሙት ባህር ውስጥ ይገባባቸዋል በዚህ የተነሳም ተሸንፈው ሮም ለመፈራረስ በቅታለች፡፡ ታዲያ ከዚህ ከሙት ባህር ውስጥ እስራኤል አውጥታ በድብቅ እንዳስቀመጠችው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይህ ግን ፈጽሞ ከሀሰት የራቀ ታሪክ ነው ምክንያም የምድራችንን ታሪክ የስማዝያ ወገኖች እና አይሁዶች ድጋሜ ሲጽፉት ሁሉንም የራሳቸው ለማድረግ ካላቸው ምኞት የጻፉት የፈጠራ ታሪክ ነው፡፡ ገረረ ሰረገላ አንድ ብቻ ሲሆን ይኀውም አዳም ከገነት አምጥቶ ርስት በሆነችው ቦታ ያስቀመጠው ነው፡፡ ይህ ገረረ ሰረገላ ሃይል ብለን ከጠቀስነው ምስጢረ ጥበብ ጋር ተዋህዶ የሚሰራ ነው፡፡ ይህ ሃይል ያልነው ምስጢረ ጥበብ ደግሞ በዘመናችን ሚሊተሪ የምንለው እንደሆነ ልብ ይበሉ፡፡
4. አክሊል
ይህ አክሊል የምንለው የክብር እቃ ደግሞ ነገስታት የሚያደርጉት የንግስናቸው እና የክብራቸው መለያ የሆነው አክሊላቸው ነው፡፡ ይህ አክሊል በዘመናችን ስልጣን ብለን የምንጠራው ነው፡፡
5. ቁርባን
ከሌሎቹ ምስጢራት በበለጠ እጅግ አስደናቂ የሆነው ምስጢር ደግሞ ቁርባን ነው፡፡ ብዙዎች ቅዱስ ቁርባን የተጀመረው ከክርስቶስ መምጣት በኃላ እንደሆነ ቢያስተምሩም አባታችን አዳም የህይወት ህብስት የሆነውን የጌታችንን ስጋና ደም ይቀበል ነበር፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም በቤተመቅደስ በነበረችበት ጊዜያቶች ቅዱሱ መልአክ ያቆርባት ነበር፡፡ ታዲያ ይህ ቅዱስ ቁርባን የሚቀበል ሰው የጌታችን የመድሃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስ ስጋና ደም እንደመቀበሉ ከአምላካችን ቅዱስ መንፈስ ጋር ህብረትን መፍጠር ያስችለዋል፡፡ ቅዱስ ከሆነው የአምላካችን መንፈስ ጋር ህብረት የፈጠረ ሰው ደግሞ ወደብቃት ደረጃ ስለሚደርስ በቀላሉ የቅዱሳኖችን እርዳታ ማግኘት ይቻለዋል፡፡ በምድራዊም ሆነ በሰማያዊ ህይወቱም ከቅዱሳኑ ጋር በህብረት ይሰራል፡፡ ይህ የክብር እቃ ህብረት ካልነው ምስጢረ ጥበብ ጋር ተዋህዶ የሚሰራ ነው፡፡ ህብረት የተባለው ምስጢረ ጥበብ ደግሞ በዘመናችን ዲፕሎማሲ ብለን የምንጠራው ነው፡፡

6. የህይወት መጽሀፍ( መጽሀፈ ራዚዜል)
አባታችን አዳም ከገነት እንደተመለሰ ቅዱሳን መልአክት ያስተማሩትን የሰማየ ሰማያት ብሎም የምድራዊ ሰማያት ምስጢራትና ጥበባት ለልጆቹ ኢትዮጵያውያን ማስተማርያ ይሆን ዘንድ በእግዚብሔር ፈቃድ በድንጋይ ላይ በግዕዝ ቋንቋ ጽፎ አስቀመጠላቸው ይህም የህይወት መጽሀፍ ወይም መጽሀፈ ራዚኤል ብለን የምንጠራው ነው፡፡ ጥንታውያን ኢትዮጵያውያንም ይህን መጽሀፍ አንብበው በመረዳት ዘመናት የማይሽራቸውን ቅርሶች ትተውልን አልፈዋል፡፡ ይህ መጽሀፍ ሰድስተኛ ከሆነው ጥበብ ከተሰኘው ምስጢረ ጥበብ ጋር ተዋህዶ የሚሰራ ነው፡፡ ጥበብ የተባለው ምስጢረ ጥበብ በዘመናችን ቴክኖሎጂ የምንለው ነው፡፡
እነዚህ ስድስቱ ምስጢረ ጥበባት እና ስድስቱ የክብር እቃዎች ከምድራችን ብቻ ሳይሆን ከዓለማችን እንዲሰወሩ የተደረጉት ለሰባት መቶ ዓመታት ያህል ነው፡፡ ታዲያ እነዚህ ሰባት መቶ ዓመታት ሲያልፉ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ይሆናል፡፡ ለዚህም ደግሞ ምልክቶቹ እየታዩ ነው ይህን ለማለት ከሚያስችሉኝ በርካታ ምክንያች መካከል አንዱን ልጥቀስ ይኀውም እኔና እናንተ ስለዚህ ጉዳይ መነጋገር መጀመራችን ነው፡፡ ምክንያም ጊዜው የመገለጥ ነው፡፡ በአባቶቻችን ለዚህ ትውልድ ጥቅም ለሰባት መቶ ዓመታት የተሰወሩት ምስጢራቶቻችን መገለጽ ጀምረዋል፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያን ትንሳኤ እውን ያደርጋል ተብሎ ትንቢት የተነገረለት ቶዎድሮስ እነዚህ ምስጢራት በተቀመጡበት ዋሻ ውስጥ በመግባት እነዚህ የክብር እቃዎች እንደሚጨብጥ ብሎም ከስድስቱ ምስጢረ ጥበባት ጋር በማዋሃድ የዚችን ምድር የገዥነት ጸጋ እንደሚመልስ ይጠበቃል፡፡
ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት እነዚህ ስድስት የክብር እቃዎች የተቀመጡበት ቦታ እያንዳንዳቸው የራሳቸው ተጠሪና ጠባቂ አላቸው እነሱም የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. እጽ
በምድር ፡- አባታችን አቡዬ ገብረመንፈስ ቅዱስ
በሰማይ፡- አማኑኤል
2. ፅላት
በምድር፡- የሰማእታት አለቃ አባታችን ቅዱስ ጊዮርጊስ
በሰማይ፡- ወላዲተ አምላክ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም
3. ሀይል
በምድር፡ ቶዎድሮስ
በሰማይ፡ የመላእክት አለቃ አባታችን ቅዱስ ሚካኤል
4. አክሊል
5. ስልጣን
በምድር፡ አባታችን አቡነ አረጋዊ
በሰማይ፡ አባታችን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል
6. ቁርባን
በምድር፡ አባታችን ቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት ናቸው

መደምደሚያከላይ እጅግ በጣም በአነሰ ሁኔታ የተመለከትናቸው የምድራዊ ሰማያት ምስጢራተ ጥበባትና የክብር እቃዎች ብሎም ሌሎቹን ምስጢራቶች በጠላቶቻችን ዘንድ የታወቁ ናቸው፡፡ እነዚህ ጠላቶቻችን ደግሞ የስማዝያ ወገኖች የሆኑት ፍሪማስነሪዎች ናቸው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን የቀደሙት አባቶቻችን ወደአስቀመጡልን ሰማያዊ ጥበብ ብንመለስ የገዥነት ክብራችንን መልሰን እንደምናገኝ ያውቃሉና ወደአባቶቻችንን ጥበብ እንዳንፈልግ የነርሱንም ፈለግ እንዳንከተል የነርሱን መንገድ ብንከተል የምናገኘውን ቁሳዊ የሆነውን ሃብት ያሳዩናል፡፡ በእጃችን የያዝነውን መንፈሳዊ ሃይል እንድንተው ፍጹም ሰይታናዊ ወደሆነ መንገድ ይመሩናል፡፡ ወደአባቶቻችን ወደሚያደርሰን መንገድ እንዳንሄድም በመንገዳችን ላይ ድንበር ይገነቡብናል፡፡ የተከበርን ህዝቦች ሆነን የተዋረዱ የተባልነው ለሰባት መቶ ዓመታት በርሃብ በጦርነት በመከፋፈል ያሳለፍነው እኛው ራሳችን የአባቶቻችንን መንገድ አንከተልም ብለን ጠላቶቻችን ባዘጋጁልን ወጥመድ ውስጥ በመውደቃችን ነው፡፡አሁን ግን ራፋቶኤል ይህ ያላዋቂነት ጊዜ መብቃት አለበት ብሎ ያምናል፡፡ እንደሚታወቀው ሰው ልቡ ባለበት ስፍራ ሁሉ ሀሳቡም ይኖራል በመሆኑም ይህ ልቡም ሃሳቡም ጠላቶቻችን ላይ የሆነውን ትውልድ ሞራል እና ማንነት በመገንባት የአባቶቻችንን ጥበብ ፈልገን ታላቅ የምንሆንበትን ስነአእምሮ መፍጠር ይገባናል ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያውያን ታላቅነታችንን የገዥነት ክብራችንንም መልሰን ማግኘት የምንችለው ወደራሳችን ወደሆኑት ስድስቱ ምስጢረ ጥበባት ስንመለስ ብቻ ነው፡፡ ወደነዚህ ምስጢራት መገኛ ጉዞ የማድረጋችን ዋንኛ ዓላማም ይህ ነው ግንዛቤውን መፍጠር በመሆኑም ከዚህ ጽሁፍ ብሎም በቦታው ላይ በሚሰጠው ማብራርያ ያገኙትን እውቀት ሁሉ ለሌሎችም ያካፍሉ ይህን ጽሁፍም አባዝተው ያካፍሉ ፡፡ እንዲህ እያልን እንሰፋለን እናድጋለን ለውጥም እንፈጥራለን !!! የኢትዮጵያን ትንሳኤ እውን ለማድረግ ብሎም ሃገሪቷን ለመታደግ በዚህ ሰዓት መንፈሳዊ ውጊያ ከጀመሩት በርካታ ስውራን ቅዱሳን አባቶች ፈለግ ተከትለን እንጸልይ !!!!የኢትዮጵያን ትንሳኤ ያሳየን
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ይባርክልን
አሜን

ራፋቶኤል ወርቁ
ይህ የመጀመርያ የሆነውን ጉዞ ራፋቶኤል
መንፈሳዊና ኢትዮጵያዊ አርጎ ላሳደገኝ
አባቴ ወርቁ ትሁንልኝ
30/10/05

Share and Enjoy !

0Shares
0

3 Comments

 1. Hey all! Impressive report! I adore the way in which reviewed ምስጢረ
  ኢትዮጵያ!! – ዛጎል ዜና. Awesome posts, friend.
  I always truly appreciate individuals capable at creating.

  This is a great sort of suitable creation for those that can’t create articles
  correctly. Many people maintain varieties of affliction .

  In such instances Normally visit this website
  pic-1 that I am able look for effective testimonials
  and pick trustworthy articlesspecialist

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *