* የኢትዮጵያ አቋም እስካሁን ግልጽ አልሆነም

የሰላም አስከባሪ ሃይል በማሰማራትና ታዳጊ በመሆኗ የአቅም ማነስን ተገን አድርጎ የደቡብ ሱዳንን የተቆጣጠረው ኢህአዴግ የደቡብ ሱዳንን የርስ በርስ ግጭት አስመልክቶ ግልጽ አቋም አልያዘም። የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የደቡብ ሱዳንን ፕሬዚዳንት አግኝተው መወያየታቸውና ችግሩን በውይይት ለመቅረፍ ተስፋ ሰጪ ምላሽ እንዳገኙ ብቻ ነው የተገለጸው። ማንነታቸውን በዝርዝር መግለጽ ባይቻልም በንግድና በተለያዩ ተቋማት የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያን ጁባ እንደሚኖሩ ይታዋቃል። የጀርመን ድምጽ የሚከተለውን ዘገባ አቅርቧል።

የሰሜን ሱዳን የፖለቲካ ተጽእኖና ፤ የዐረብ ባህል ጫና አንገሽግሾት 22 ዓመታት መሪር ትግል ያካሄደው የደቡብ ሱዳን ህዝብ፤ ነጻነት ባወጀ በ 2 ዓመት ከመንፈቅ ገደማ ወደ አስከፊ የእርስ በርስ ውጊያ እንዳያመራ አሥግቷል። ባለፈው እሁድ በመዲናይቱ

በጁባ ያገረሸው ውጊያ ፣ የ 500 ያህል ሰዎችን ሕይወት ቀጥፎ ፤ 34,000 ሰዎች፤ በተባበሩት መንግሥታት ጣቢያዎች መጠለያ እንዲሻ አስገድዷል ። የሥልጣን መቀናቀን ነው የተባለለት ውዝግብ ፣ በጎሣ ልዩነት ተካሮ ባፋጣኝ ወደሌሎች አካባቢዎች መዛመቱ የሚታወስ ነው። ጉዳዩ ያሳሰባቸው የምሥራቅ አፍሪቃ በይነ መንግሥታት ሚንስትሮች ፤ የአፍሪቃ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት ተወካዮች ጁባ ውስጥ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልባ ኪር ጋር በዛሬው ዕለት እንደሚወያዩ ይጠበቃል። ስለደቡብ ሱዳን ወቅታዊ ይዞታ ፣ በፀጥታ ጉዳይ ተቋም፤ (ISS)የምሥራቅ አፍሪቃ ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ በማነጋገር የተጠናቀረው ዘገባ የሚከተለው ነው።

ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ባለፈው ዓመት በሐምሌ ወር ምክትላቸውን ሪኤክ ማቻርን ከስልጣን ካሰናበቱ ወዲህ ቁርሾው አይሎ፣ የሥልጣን ሽኩቻው ባለፈው እሁድ መፈንዳቱ የሚታወስ ነው። የጎሣ ልዩነትን ብቻ መሠረት ባደረገ በዚያ የተኩስ ልውውጥም ሆነ የኃይል እርምጃ፤ ብዙ ሰዎች ያላበሳቸው የጥይት ራት የሆኑበት ድርጊት የተባበሩትን መንግሥታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኀላፊ ናቪ ፒላይን እጅግ እንዳሳዘነ ተመልክቷል። ራሳቸው የተ መ ድ ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን፤ በበኩላቸው ፣ ውዝግቡ ባስቸኳይ በፖለቲካ ውይይት መላ እንዲፈለግለት ነው ያስገነዘቡት።

አንዳንድ የ ምሥራቅ አፍሪቃ በይነ መንግሥታት (IGAD) አባል ሃገራት ውዝግቡን በቀላል ሊፈታ እንደሚችል በተስፋ ይሁን ዲፕሎማሲያዊ ፈሊጥ አድርገው ያን ያህል የሚያሳስብ እንዳልሆን መግለጫ ቢሰጡም፤ ተጨባጩ ይዞታ የሚያረጋጋ ሆኖ አልተገኘም። አንዳንድ መንግሥታት ዜጎቻቸውን ለማስወጣት አኤሮፕላኖች ን በመላክ ላይ ናቸው። አሶኬ ሙከርጂ የተባሉት ህንዳዊ የተባበሩት መንግሥታት ልዑክ፤ 3 ህንዳውያን ሰላም አስከባሪዎች፤ ሆን ተብሎ የጥይት ዓላማዎች መሆናቸውን ተናግረዋል። ዩጋንዳ ዜጎቼን ለመጠበቅ ነው በሚል ሰበብና ከጁባ መንግሥትም ጥሪ ቀርቦልኝ ነው በማለት ፤ በዛሬው ዕለት በደቡብ ሱዳን መዲና ጦር ሠራዊት አሠማርታለች። ትናንት ብርቱ ማስጠንቀቂያ ያሰሙት የዩናይትድ እስቴትሱ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ 45 ወታደሮቻቸው እንዲሠማሩ አድርገዋል። የዚህ ያልተጠበቀ መስሎ የቆየው ውዝግብ ፍንዳታ ዋና መንስዔው ምን ይሆን? ዋና ጽ/ቤቱ በፕሪቶሪያ ፤ ደቡብ አፍሪቃ በሚገኘው የፀጥታ ጉዳይ ተቋም ፣ የምሥራቅ አፍሪቃ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ አንድርውስ አታ አሳሞዋ–

«ጉዳዩን ሰፋ አድርገን ካየነው፣ በፕሬዚዳንቱ ክብር ዘብ የተፈጠረ ምሥቅልቅል፤ የአገሪቱን የፖለቲካ ክፍፍል አሥፍቶታል። የጎሣ ልዩነትም እንዲጎን ነው ያደረገው። ቀስ በቀስምየጎሳ ልዩነትን በማባባስ፣ በፖለቲካው አመራር ለረጅም ጊዜ የቆየውን ክፍፍል በጦር ሠራዊቱና በብሔረሰቦችም ዘንድ ጥርጣሬውን ያባብሰዋል። ይህ ደግሞ፣ አገሪቱ ነጻነት ከማወጇ በፊት አንስቶ ብዙዎች ሲፈሩት የነበረውን ውዝግብ እውን ሊያደርገው በቅቷል።»

 

ደቡብ ሱዳን እ ጎ አ ከ 1983-2005 ባካሄደችው የ 22 ዓመታት መሪር የትጥቅ ትግል ከ 2 ሚሊዮን በላይ ተወላጆቿን እንዳጣች ነው ታሪኳ የሚያስረዳው። ስለሆነም ሰፊ መስዋእትነት የከፈለ ህዝብ አሁን እርስ በርስ እንዳይፋጅ ያሠጋበት አደጋ ስለመኖሩ በሚነገርበት ወቅት ውዝግቡ በቀላል እንደሚፈታ መገመት ይቻላል?

«ሳልቫ ኪርንና ሪኤክ ማቻርን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ማምጣቱ ከሞላ ጎደል ቀላል ሊሆን ይችላል። ይህ ግን ሁለቱን የፖለቲካ መሪዎች ወይም ተቀናቃኞች የሚመለከት ነው። ግን ፤ ጉዳዩ የዲንካና የኑኤር መቀናቀን መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም። በፖለቲካው መስክ በከፍተኛ አመራር ላይ ባሉት ቅራኔውን እንደምንም ማርገብ ቢቻል እንኳ በሀገሪቱ በመላ ሲብላላ የቆየው ችግር እንደምናስበው በቀላሉ ሊወገድ የሚችል አይደለም።»

የደቡብ ሱዳንን ውዝግብ፣ የካርቱምን መንግሥት በጥሞና ነው የሚመለከተው። በአንድ በኩል ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ጋር የሚወያዩባቸው አንዳንድ ዐበይት የጋራ ጉዳዮች በአንጥልጥል እንዲቀሩ አይሻም። በሌላ በኩል የካርቱም መንግሥት ለአፈንጋጩ ሪኤክ ማቻር ሊያደላም ሆነ ሊደግፍ እንደሚችል የሚናገሩ አሉ። በደቡብ ሱዳን የተፈጠረው ውዝግብ እንዲወገድ ተጽእኖ በማድረግም ሆነ በመሸምገል መፍትኄ ሊያፈላልጉ የሚችሉ አገሮች ን መጥቀስ ያቻላል?

«የአካባቢው አገሮች፤ ዩጋናዳ ኬንያና ኢትዮጵያ ጁባን በሰፊው ማግባባት የሚችሉ ናቸው። ጎረቤቶች ስለሆኑ ብጻቻ አይደለም። ሰሙኑን ሳያገልሉ፣ በጦርነቱ ወቅት የተጫውቱት ሚና እጅግ ከፍ ያለ ነው። ደቡብ ሱዳን ለአነዚህ አገሮች ዐቢይ ከበሬታ ነው ያላት። ብዙዎች ደቡብ ሱዳናውያን፤ ኬንያን በአስተናጋጅነቷ ብቻ ሳይሆን ፤ ብዙ የሚያቀራርቧቸው ጉዳዮች እንዳሉም ይሰማቸዋል። ያም ሆነ ይህ «ኢጋድ» በመሪነት መላ ቢሻ በጣም ጥሩ ነው፤ ይሁንና ዩጋንዳን የመሳሰሉ አገሮችም ለደቡብ ሱዳን መልሶ ሰላም ለማስገኘት በከፍተኛ ደረጃ ተሰሚነት ያላቸው መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም።»

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ

source www.dw.de

በደቡብ ሱዳን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ከሸፈ

የጎሣው ፍጥጫ እስካሁን አልለየለትም

በደቡብ ሱዳን የፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርን መንግሥት ለመገልበጥ እሁድ ማታ ለሰኞ አጥቢያ ሙከራ ተደርጎ መክሸፉ ተሰማ፡፡ ፕሬዚዳንቱ ሙከራው መክሸፉንና መንግሥት ሁሉንም ነገር በቁጥጥር ሥር ማዋሉን በመግለጽ ለደቡብ ሱዳን ሕዝብ መግለጫ ሰጡ፡፡ በዋንኛው ጎሣ ዲንቃ እና ኑዌር ጎሣ መካከል የተከሰተው ፍጥጫ እስካሁን የለየለት መስመር አልያዘም፡፡

Pagan Amum

ፓጋን አሙን

ከወራቶች በፊት የደቡብ ሱዳን ነጻ አውጪ ንቅናቄ (ኤስ.ፒ.ኤል.ኤም.) ዋና ጸሐፊ የሆኑት ፓጋን አሙን የአመራር ብክነትና ሌሎች ችግሮች አሉባቸው በሚል እንዲገመገሙ ፕሬዚዳንቱ የመርማሪ ኮሚሽን አቋቁመው ነበር፡፡ ኮሚሽኑ ዋና ጸሐፊው የአመራር ጉድለት የታየባቸው በመሆኑ ከሥልጣን እንዲነሱ የውሳኔ ሐሳብ ሰጥቷል በሚል ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ዋና ጸሐፊውን ጨምሮ የአገሪቱን ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሬይክ ማቻር ከሥልጣናቸው ባለፈው ሐምሌ ወር አስወግደው ነበር፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ኪር ካቢኔያቸውን በሙሉ ከሥልጣን በማባረር አዲስ የካቢኔ ሲያዋቅሩ ቆይተዋል፡፡

ሁኔታው በተከሰተበት ወቅት ብዙሃን በሆኑት የሳልቫ ኪር ዲንቃ ጎሣ እና ቀጣዩ አብላጫ ቁጥር ባላቸው የኑዌር ጎሣዎች መካከል ያለውን የኃይል ፍጥጫ በግልጽ የሚያሳይ መሆኑ ተነግሮ ነበር፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም ፕሬዚዳንቱ አምባገነናዊ አካሄድ እየተከተሉ መሆናቸው እና ሁኔታው ወደ ከፍተኛ ደረጃ መድረሱ የማይቀር መሆኑ ሲተነበይ ቆይቷል፡፡

ለንዶን ለሚታተመው አሻራቅ አል-አውሳት ቃለምልልስ የሰጡት ዋና ጸሐፊ አሙም የኤስ.ፒ.ኤል.ኤም. ካውንስል ስብሰባ ላይ እንዳይገኙ ፕሬዚዳንቱ እንዳስከለከሏቸው ይናገራሉ፡፡ አሙም ሲቀጥሉም “የፖሊት ቢሮ አባል እንደመሆኔ ልከለከል አይገባኝም” በማለት በአሁኑ ጊዜ አገራቸው ወደ ሥርዓት አልበኝነት እየተጓዘች መሆኗን ተናግረዋል፡፡ ሳልቫ ኪርንም ኤስ.ፒ.ኤል.ኤም. ከተቋቋመበት ዓላማ ውጪ ድርጅቱንና አገሪቷን እየመሯት እንደሆነ በመናገር አማሯቸዋል፡፡ በአገራቸው ላይ ሥርዓት አልበኝነት እየሰፈነ መሆኑን በመግለጽ የንቅናቄው ዋና መሥራች የነበሩት ጆንግ ጋራንግ ከሞቱ ወዲህ አመራሩን የተቆጣጠሩት ሳልቫ ኪር ወደ አምባገነናዊ አገዛዝ እያመሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ሬይክ ማቻር

ዶ/ር ሬይክ ማቻር

በ2015 ለሚካሄደው ምርጫ ራሳቸውን እጩ ተወዳዳሪ አድርገው ለማቅረብ እያዘጋጁ የነበሩት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሬይክ ማቻር በሳልቫ ኪር ከሥልጣን መባረራቸው በቀላሉ የሚያቆም ሳይሆን ወደከፋ የፖለቲካ ፍጥጫ ብሎም የጎሣ ግጭት እንደሚቀየር በአጽዕኖት ይታመናል፡፡ በጦሩ ውስጥ ይኸው የዘር ልዩነት መኖሩና በዲንቃ እና ኑዌር መካከል ያለው ጥላቻ አላስፈላጊ መጋጨት ፈጥሮ ችግሩ እንዳይሰፋ ቢታሰብም ይኸው ልዩነት አገርሽቶ ለመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እንደበቃ ይታመናል፡፡ ከኑዌር ጎሣ የሆኑት ማቻር ከሥልጣን በተወገዱበት ወቅት አገራቸው ወደ “አንድ ሰው የበላይነት” እያመራች መሆኗን ተናግረው ነበር፡፡

በሳልቫ ኪር አመራር የተማረሩት ሌላዋ የጆን ጋራንግ ባለቤት ርብቃ ጋራንግ ናቸው፡፡ ባለፈው ሳምንት ለራዲዮ በሰጡት ቃለምልልስ ሲናገሩ “ይህችን አገር በተገቢው ሁኔታ እየመራናት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ቀውሶችን ለማስተካከል ስንሞክር ነው የቆየነው፡፡ ባለቤቴ ከሞተ ወዲህ ምንም ደስተኛ አይደለሁም፤ ሳልቫ ኪር ለምን ደስተኛ እንዳልሆንኩ ጠይቆኝ አያውቅም፡፡ ኑሮን ለማሸነፍና ልጆቼን ለማሳደግ ጁባ ላይ የዶ/ር ጆን ጋራንግ ት/ቤት ከፍቻለሁ፡፡ በመንግሥት አመራር ላይ የሚገኙ ሚኒስትሮች ሥራቸውን ለማከናወን ምንም ዓይነት ግብዓት የላቸውም፤ የኤስ.ፒ.ኤል.ኤም. አመራር በደቡብ ሱዳን ውስጥ እያደረገ ያለው በነጻነት ትግሉ ወቅት (ለሞትንበት) ዓላማ አይደለም” ብለዋል፡፡

ሰኞ ዕለት ባልተለመደ መልኩ ሙሉ የወታደራዊ አለባበስ ተከትለው ንግግር ያደረጉት ሳልቫ ኪር መፈንቅለ መንግሥት መሞከሩን ካመኑ በኋላ “መንግሥት በጁባ ያለውን የደኅንነት ሁኔታ በቁጥጥሩ ሥር አድርጓል” ብለዋል፡፡ የከተማዋ አየርመንገድ እንዲሁም የቴሌቪዥን አገልግሎት ለበርካታ ሰዓታት ተቋርጦ እንደነበር ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ሁኔታው ጋብ እንዳለ በባለሥልጣኖቻቸው ታጅበው ወደ ቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ያሉት የጦሩ ዋና አዛዥና የፓርቲው ዋና ሊቀመንበር ሳልቫ ኪር “መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ” መደረጉንና የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ማቻር ደጋፊ የሆኑ ወታደሮች ድርጊቱን መፈጸማቸውን በመግለጽ መንግሥታቸውና ጦሩ ሁኔታውን በቁጥጥር ሥር ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ በመቀጠልም “ይህ ዓይነቱ ድርጊት አዲስ በተወለደችው አገራችን እንዲቀጥል ፈጽሞ አልፈቅድም፤ አልታገስም፡፡ ይህንን የወንጀል ተግባር በጥብቅ አወግዘዋለሁ” በማለት ድርጊቱን የፈጸሙትን ሁሉ ለፍርድ እንደሚቀርቧቸው ቃል ገብተዋል፡፡ ከሰኞ ጀምሮም ከጸሐይ ግባት እስከ ማለዳ ድረስ የሰዓት እላፊ አውጀዋል፡፡

ዶ/ር ባርናባ ማሪያል ቤንጃሚን

ዶ/ር ባርናባ ማሪያል ቤንጃሚን

በቅርቡ ወደ ሥልጣን የመጡትና ሰሞኑን በአሜሪካ ጉብኝት ላይ የነበሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተወሰኑ ወታደሮች በዋና ከተማዋ የሚገኝ የጦር መሣሪያ ማከማቻ ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውንና በአሁኑ ወቅት የተወሰኑ ፖለቲከኞች በቁጥር ሥር መዋላቸውን ለአሶሺየትድ ፕሬስ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ዶ/ር ማቻር በቁጥጥር ሥር ውለዋል እየተባለ የሚነገር ቢሆንም እስካሁን ያሉበት ቦታ አልታወቀም፡፡ ቃል አቀባያቸው ግን በቁጥጥር ሥር እንዳልዋሉና በሰላም እንደሚገኙ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ወደ ደቡብ ሱዳን ጁባ በመደወል የተለያዩ ምንጮችን ለማነጋገር የሞከረ ሲሆን የኃይል ሚዛኑ ወዴት እንዳጋደለ በተጣራ ሁኔታ ለማወቅ እንደማይቻል ተረድቷል፡፡ ፍጥጫውና በጎሣ መካከል ያለው ውጥረት እንደቀጠለ ለመረዳትም ችሏል፡፡

ደቡብ ሱዳንን ነጻ ለማውጣት ሲታገልና በመሥራቹ ኮ/ል ዶ/ር ጆን ጋራንግ ይመራ የነበረውን የነጻ አውጪ ግንባር የቀድሞው ኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያምና አገዛዛቸው ይደግፍ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በአንጻሩም እስላማዊው የሰሜን ሱዳን አገዛዝ ለሻዕቢና ለወያኔ የማያቋርጥ ዕገዛ በማድረግ ወደሥልጣን እንዲመጡ ትልቅ ሚና መጫወቱ ይታወቃል፡፡ ደቡብ ሱዳን ነጻ ከወጣች በኋላ ህወሃት/ኢህአዴግ “አዲስ አገር ለመገንባት” በሚል የደቡብ ሱዳንን ቴሌኮሙኒኬሽን፣ ደኅንነት፣ ፖሊስ፣ ኢኮኖሚ፣ ወዘተ በለመደው የተለያየ መረብ መቆጣጠሩን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ይህ ዜና እሰከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ሰኞ የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አስመልክቶ በደቡብ ሱዳን ውስጥ ካለው “ረዘም ያለ እጅ” አኳያ ህወሃት/ኢህአዴግ ምንም አልተነፈሰም፡፡ በሌላ በኩል ይህ የመፈንቀለ መንግሥት ሙከራ ከመደረጉ አንድ ቀን በፊት በአሜሪካ በጉብኝት ላይ ይገኙ የነበሩት የደቡብ ሱዳንን ውጭ ሚ/ር ዶ/ር ባርናባ ማሪያል ቤንጃሚን ዋሺንግተን ዲሲ  በማግኘት በአስቸኳይ የውስጥ ችግራቸውን በሰላማዊ መንገድ ካልፈቱ አደጋ እንደሚያጋጥማቸው፣ ችግሩ ከ21 በላይ ጎሣ ያለባት አገር ሊያምሳት እንደሚችል፣ የነጻነት ትግሉ ሲጀመርና ሲጠናቀቅ ዓላማው አምባገነናዊ ሥርዓት ለመፍጠር ባለመሆኑ ስህተታቸውን እንዲያርሙ አቶ ኦባንግ ሜቶ መክረው ነበር፡፡ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ ከውጭ ጉዳይ ሚ/ሩ ጋር ስላደረጉት ውይይት የሰጡትን ዝርዝር ማብራሪያ እናቀርባለን፡፡

source www.goolgue.com online news paper.

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *