የኢህአዴግ አዲሱ አሰላለፍ ፪ – ከተመስገን ደሳለኝ (ጋዜጠኛ)
ሰላም የራቀው-ኢህአዴግ
በግንባሩ አባል ድርጅቶች መካከል ዛሬም ድረስ ሙሉ በሙሉ የተረጋጋ ፖለቲካ አልሰፈነም፤ የዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ፣ ቁልፍ የሥልጣን ቦታዎችን ጠቅልሎ ይዞ በነበረው በቀድሞ ሊቀ-መንበሩ ህልፈት ሳቢያ የተፈጠረው የአመራር ክፍተት እና እርሱን ሊተካ የሚችል መሪ ማግኘት ባለመቻሉ ይመስለኛል፡፡ እንዲህ አይነት አጋጣሚዎችም በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባለ ከሕግ ይልቅ የጠመንጃ ኃይልና የግለሰብ አምባገነናዊነት በገነነበት ሀገር ‹የማይገመቱ ክስተቶች› (Unpredictable Event) ማምጣታቸው የሚጠበቅ ነው፡፡
‹‹ሙስና ሠራዊቱን ሊያበላሸው ይችላል፡፡ ሙስና ፀረ-ልማት ነው፤ ሠራዊቱን ሊበትነው እና ሕዝባዊ ባህሪውን እንዲያጠፋ ሊያደርገው ይችላል፤ አንድ ሠራዊት ሠራዊት ነው የሚባለው እንደ ወታደር እንደ አንድ አካል ሲያስብ እንጂ ለግሉ ሲያስብ አይደለም፡፡ …በአጠቃላይ (ሠራዊቱ) በዚህ ነው የሚፈርሰው፡፡››
መቼም ጄነራሉ ይህንን የተናገረው እራሱን ጨምሮ በርካታ ከፍተኛ መኮንኖች እንደ እንግሊዝ ንጉሳውያን ቤተሰቦች በተንጣለለ ቪላ ቤት ውስጥ፣ የተቀማጠለ ኑሮ መኖራቸውን ረስቶት አይመስለኝም፤ ‹ይህ የተንዛዛ ወጪያቸውም የሚሸፈነው ከደሞዛቸው በሚያገኙት ገቢ ነው› ብሎ ቧልት መሳይ ክርክር ሊያመጣ አይችልም፡፡ ይሁንና እታች ያለው ጭቁን የኢትዮጵያ ሠራዊት ምንም እንኳ በአለቆቹ ‹ቴክሳስ›ነት ላይ ለመቆጣት ባይደፍርም፣ እንደማንኛውም ዜጋ ለኑሮ ውድነትና አስከፊ ድህነት የተጋለጠ መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡
የፖለቲካውን መዘውር የጨበጠው ኃይል
በሌላ በኩል ደግሞ በፓርቲውም ሆነ በመንግስት አስተዳደር ከህወሓት ሰዎች ትልቁን ስልጣን የያዘው ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ከምዕራባውያን ጋር የቆየ ቀረቤታ እንዳለው ሰምቻለሁ፤ እንደሚታወሰው ደብረፅዮን ከክፍፍሉ በፊት (የደህንነት መስሪያ ቤቱ እንዲህ እንደ ዛሬው እጅግ ዘመናዊ በሆነው የቻይና ቴክኖሎጂ ሳይጥለቀለቅ) ከነበረው ከፍተኛ የሥልጣን ቦታ ላይ ተነስቶ፣ ቁልቁል ወርዶ በሁመራ በአንድ ዞን እንዲሰራ የተመደበው (ሁላችንም ስንገምት እንደነበረው) የአንጃው አባል ወይም ደጋፊ ሆኖ አይደለም፤ ይልቁንም የእነስዬ-ተወልደ ቡድን በመባል የሚታወቀው (‹አፈንጋጩ› ኃይል) ደብረፅዮንን በሲ.አይ.ኤ እና ሞሳድ ወኪልነት የመክሰሱ ጉዳይ የድርጅቱን በርካታ አባላት ቀልብ በመሳቡ፣ መለስ ይህንን ተከትሎ ከሚመጣበት አደጋ ራሱን ለመከላከል የወሰደው እርምጃ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት እስከ 1998 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ በሁመራና ራያ አካባቢዎች በዞን ደረጃ ለማገልገል ተገዷል፡፡ እናም እርሱን የምዕራቡ ዓለም ፊት-አውራሪ አሜሪካና ሸሪኮቿ ወዳጅ ነው የሚያስብለው በቀድሞ መስሪያ ቤቱ በኩል በነበረው ግንኙነት ይመስለኛል።