ከትናንት ጀምሮ የሚተገበር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ

images-2

የሃገሪቷን ሠላም የማይሹ ኃይሎች ከውጭ ጠላቶች ጋር በማበር በሃገሪቷ ሕዝብ ሠላም፣ ፀጥታና ደህንነት ላይ የደቀኑትን ከፍተኛ ስጋት ለመቀልበስ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከትናንት ጀምሮ የሚተገበር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀ። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፥ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሃገሪቷ እየደረሰ ባለው የህይወት መጥፋትና ከፍተኛ የንብረት መውደም ላይ በሰፊው ከመከረ በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁን ገልጸዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታወጀው የሀገሪቱ የሰላም እና መረጋጋት ሁኔታ እንዲሁም የህዝቦቿ ደህንነት ጉዳይ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ በመውደቁ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው። የስጋቱ መነሻም ፀረ ሰላም ሃይሎች የኢትዮጵያ ጠላት ከሆኑ ሀገራት ጋር በመተባበር፥ ሀገሪቱን ለማተራመስ እና ሰላሟን ለማናጋት እንዲሁም የህዝቦችን ህልውና እና ደህንነት ስጋት ውስጥ ለመጣል የሚያደርጉት የተደራጀ እንቅስቃሴ መሆኑንም ጠቅሰዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀው ምክር ቤቱ አዋጁን ለማወጅ መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን መገምገሙን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሰላም፣ የመረጋጋት እና የህዝብ ደህንነት ጉዳት አደጋ ላይ መውቀዱን አንስተዋል።

በተለያዩ ቡድኖች የሚመሩ ስጋት እና አለመረጋጋትን የጫሩ ሁከት እና ብጥብጦች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች መከሰታቸውንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት። እነዚህን ሁከቶች እና ስጋቶች በመደበኛ የሰላም ማስከበር እንቅስቃሴ መቆጣጠር የማይቻል በመሆኑ፥ በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 93 መሰረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ትናንት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ወስኗል ብለዋል። አዋጁ ከታወጀበት ትናንት ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ ላይ እየተተገበረ ይገኛል። በአዋጁ መሰረት የሀገሪቱን ህልውና ለማስጠበቅ ሲባል የተወሰኑ የዜጎች ዴሞክራሲያዊ እና ፖለቲካዊ መብቶች ላይ ገደብ መጣሉንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። በህገ መንግስቱ መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንደየ አስፈላጊነቱ የሚሻሻል ሆኖ ለስድስት ወራት ይቆያል ነው የተባለው።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አተገባበር የሚከታተል እና ሪፖርት የሚያቀርብ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ግብረ ሀይል መቋቋሙንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ አድርገዋል። በአዋጁ ትግበራ ጊዜ የዜጎች ሰብዓዊ መብት በህገ መንግስቱ መሰረት ሳይሸራረፍ እና ሳይዛነፍ እንደሚከበርም ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

የውጭ ሀገር ዲፕሎማቶች መብትም ያለ መሸራረፍ በቪየናው ድንጋጌ መሰረት እንደሚከበርም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ያረጋገጡት። ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም፥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀገሪቱን ወደ ቀደመ ሰላሟ እና መረጋጋቷ ለመመለስ እንደሚያስችልም ተናግረዋል።የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አላማ የተጀመሩ የመፍትሄ ጥረቶች ማፋጠን መሆኑን ጠቅሰው፥ ከዚህ ጋር በተያያዘ መንግስት በተከታታይ ለህዝብ መረጃ እንደሚሰጥም ነው ያነሱት።ህዝቡም ሰላምን ለማስከበር በሚደረገው ጥረት እና እርምጃ ከመንግስት ጎን እንዲቆምም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 29 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ)

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *