አወራራጆች!! – የምትቅለሰለሱ ተገረዙ

… ብልት አውጪዎች፣ የመኪና የሆድ እቃ አውላቂዎች፣ የሚያስፈሩ፣ ደረታቸው ሰፋፊ፣ ጡንቻቸው ትልልቅ፣ ቁመታቸው ረጃጅም የመኪና ቀዶ ጥገና አድራጊዎች፡፡ በላቾች!!
የመኪናን የሆድ እቃ፣ የመኪናን ማጋጌጫ፣ የመኪናን ዓይኖች በደቂቃዎች ውስጥ ከቆርቆሮ የመለያየት አቅም ያላቸው፣ መኪናን እርቃን የሚያስቀሩ፣ ሞተር ለሁለት አንጠልጥለው የሚያወርዱ በስፖርት ዳብረው፣ የበላችነት ኮርስ ወስደው፣ በቅርጫ የሚተዳደሩ የለሊት ጭልፊቶች፣ የቀን ድብርታሞች …    

ደላላው አምበርብር ስለበላቾች የሰማው ከባልንጀራው ጋር ሶማሌ ተራ፣ አብነት አካባቢና አንድ ትልቅ የተዘጋ ግቢ ውስጥ ተዛውሮ ስላለው የመኪና እቃ ገበያ ግብይት በተመለከተበት ወቅት ነው፡፡የብለታ ድራማና የበላቾች መደራደሪያ አስገረመው።“አሁን እኔም ደላላ እባላለሁ?”ሲል ጠየቀ።ደላላው አምበርብር የድለላ አቅሙን ማሳደግ ቢገባውም በብለታ ደረጃ እንዳልሆነ ግን ወዲያው አምኗል።የመኪና አወራራጆች የስራ ክፍፍልና መለያ አላቸው።
“ጉዳተኛ ” የሚባሉት መኪናቸውን በቆሙበት ተዘርፈው የራሳቸውን እቃ ለመግዛት እቃው ያለበት ሰፈር ለድርድር፣ ለልመናና ለምልጃ የሚሄዱ ናቸው፡፡ “ጋቡ “ ዎች የመኪናውን ጋቢና የሚከፍቱ”የሚበረግዱ ” ሰርሳሪዎች ናቸው፡፡ “ቂማ ” ስትራቴጂ የሚነደፍበት ጊዜ ሲሆን፣ ለሊት ለሥራ የሰው አጥር የሚዘሉ፣ ጎዳና የሚያስሱ በላቾች ተኝተው ውለው አመሻሽ ላይ የሥራ እቅድ ለማውጣት የሚመርጡት ጊዜ ነው፡፡ ደላላው አምበርብር በደረሰው መረጃ መሠረት መኪና “ከነገባው ” ከተሰራ (እንዳለ ከተወሰደ ) “ዝግ ተዘጋ ” ይባልና በላቾቹ እንደ አራስ በዝግ ለሳምንታት ይቀለባሉ፡፡ በዝግ ይዝናናሉ፣ይጠጣሉ፣ ሁሉንም ነገር ያደርጋሉ፡፡ ይጨሳሉ፣ ይጫጫሳሉ . . .
መኪና “የሚያጫውቱ ” ዋና በላቾች ቃፊር አላቸው፡፡ ቃፊሮች “ገበያ ተኮር” አሰሳ ያካሂዳሉ፡፡ በግቢ ውስጥ የቆሙ መኪኖችን የዓይን ራጂ (X-Ray) ያነሳሉ፡፡ ቃፊሮቹ መረጃቸውን አጠናክረው ለበላቾች ይሰጣሉ፡፡ አምበርብር ምንተስኖት ያሰባሰበው መረጃ በርካታ ነው፡፡ የብለታ ሥራ በትዕዛዝ እንደሚሰራም አውቋል፡፡
የመኪና ስርቆት በትዕዛዝ ይሰራል፡፡ ትዕዛዝ በተዋረድ መጥቶ እንዲህ ያለ መኪና፣ እንዲህ ያለ ዕቃ፣ ይምጣ ይባላል፡፡ ዋጋውና የመኪናው ሞዴል አስቀድሞ ይነገራል፡፡ የሚፈለገው የተሽከርካሪ ዓይነትና እቃ በሞባይል ፎቶ ተነስቶ ይቀርባል፡፡ ቃፊሮች በተሰጣቸው የስዕል መረጃ መሰረት ተፈላጊውን እቃ የያዘ ወይም ተፈላጊው እቃ ያለበትን ተሽከርካሪ ያድናሉ፡፡ አግኝተው ሪፖርት ያቀርባሉ፡፡ በሪፖርቱ መሠረት በላቾች እቅድ ይነድፋሉ፡፡ትዕዛዙን አሳክተው በድል ይመለሳሉ፡፡ ባይመለሱም በመንገድ በድንገት ለሚገጥማቸው ችግር ራስን የመከላከል አካላዊ ድርጅታቸውን በቁሳዊ አቅማቸው አስደግፈው እንዳመጣጡ ይመልሱታል።
በሰላም እንዳያድሩ የተፈረደባቸው “ተጎጂዎች”የለፉበትን በሰዓት ልዩነት ተነጥቀው ባዶ ይቀራሉ።በሰላም ተመስገን ብለው ከተኙበት ሲነሱ መኪናቸውን ያጡ፣አገር አማን ብለው መኪናቸውን ዘንድ ሲደርሱ አይናቸውን ማመን አቅቷቸው አሁን ድረስ ህልሙ ያልለቀቃቸው፣የጠፋባቸውን መኪና ፍለጋ በእግር መንገድ ጀምረው አሁን ድረስ ጉዞ ያላቋረጡ እግረኞች፣…..ቤት ይቁጠራቸው።የቀናቸውም ወደ ማገገሚያ ይወርዳሉ።
“ማገገሚያ”የመኪና እቃ የተሰረቀባቸው እቃቸውን የሚያገኙበት ሰፈር ነው፡፡ ተሰራቂ (ጉዳተኛ ) ከራሱ መኪና የተሰረቀውን እቃ ለመግዛት ሶማሌ ተራ ወደ አሜሪካን ግቢ መግቢያ ጎራ ሲል እንደ ሌባ የሚሸማቀቀው ራሱ ነው፡፡ ደላላው አምበርብር ያስገረመው ጉዳይ ይህ ነበር፡፡
አንድ ወዳጄ በሰላም መኪናቸውን ግቢያቸው አስገብተው አቁመው ይተኛሉ፡፡ እሳቸው ሲተኙ የነጋላቸው መኪናዋን ሲበልቷት አድረው ባዶ ያስቀሯታል፡፡ የተሰረቀው እቃ አንድ ብሎን ሳይጎድለው የሚገኝበት ሰፈር ስለሚታወቅ አብረን አቀናን፡፡ እቃው ሙሉ በሙሉ ተገኘ፡፡ እቃው እንዳለ የተናገሩት አንድም መደናገጥ አይታይባቸውም፡፡
የበላቾቹና የተበለተው እቃ፣ አንዳንዴም ሙሉ መኪና ተሰርቆ የሚገባበት ሰፈር ይታወቃል፡፡ሰፈሩ ፈረሰ ሲባል ተጠናክሮ የሚገነባ ነው፡፡ ተዘጋ ሲባል ቅርንጫፍ ቢሮዎችን አጠናክሮ በመክፈት የአገልግሎት ሥራውን ያሰፋል፡፡ ባለሟሎቹ በቁጥጥር ስር ዋሉ ሲባል እንደ አሸን ይፈላሉ፡፡ በግልጽ በአደባባይ ለሰረቁት እቃ የባለንብረቱን ኪስ እንደገና ያራቁታል፡፡ ደላላው አምበርብር ተገረመ፡፡ “እንዲህ ዓይነት አዲስ አበባ “ሲል ተነፈሰ፡፡ “አይናውጣዎች ” ሲል ተራገመ፡፡ የወጣትነት፣ የጉርምስና ጊዜውን ናፈቀ፡፡ በሽመል ቀልጥሞ ሊጥላቸው፡፡
ነገሩ ይገርማል፡፡ በየጊዜው የሚሰረቅ የመኪና ሆድ እቃ በአደባባይ ይሸጣል፡፡ ክሪክ፣ ባትሪ፣ ጌጅ፣ ሰዓት፣ ዳሽቦርድ፣ ጎማ፣ መብራት፣ መስተዋት፣ ስፖኪዮ፣ ቴፕ፣ ዲናሞ፣ ሞተሪኖ፣ የቴስታታ መዝጊያ፣የዝናብ መጥረጊያ፣ የተለያዩ ጎሚኒዎች . . . ተሰቅለው ይሸጣሉ፡፡ እቃዎቹ ላይ ያልተለጠፈው የተሰረቁበት ቦታና የመኪናዋ ታርጋ ብቻ ነው፡፡ ህጋዊ ሱቅ ከፍተው ህገወጥ እቃ ይሸጣሉ . . . “ደላላውአምበርብር እንቅልፍም የለኝ ከሰው አልጣላ ” ሲል የጉዳዩን አሳሳቢነት ተረድቶ ተናገረ፡፡
አምበርብር ከማንጠግቦሽ ጋር እየሄደ ያጋጠመውን አስታወሰ፡፡ የጋራዥ ሰራተኛ ቱታ ለብሰው መንገድ ላይ የሚቆሙ አሉ፡፡“ ሁጳዎች ”ይባላሉ፡፡ በሰላም የሚሄደውን መኪና እግር ስር ችግር እንዳለው አድርገው ምልክት ይሰጣሉ፡፡ ምልክት ያየው አሽከርካሪ ያቆማል፡፡ በተለይ ሴት አሽከርካሪዎች ለዚህኛው ሥራ ይመረጣሉ፡፡ መኪናው ከቆመ በኋላ “መኪናው እግር ተገንጥሎ ሊሄድ ነው ” በማለት የመኪናውን መሪ ወደ አንድ በኩል ይጨርሱና በጡንቸኛው ክንዳቸው ጎማውን እያወዛወዙ ያሳያሉ፡፡ ባለመኪናዋ ደንግጣ ይሰራልኝ ትላለች፡፡ ያልተበላሸው መኪና ይሰራ ይባላል፡፡ ክሪክ፣ የጎማ መፍቻ፣የመተኛ ምንጣፍ እያሉ መኪናውን ይበረብራሉ፡፡ በመጨረሻም ለሙከራ ብለው እየነዱ የአሽከርካሪዋን ቦርሳ ይበረብሩና ባዶ ያስቀራሉ፡፡ አንዷ አሽከርካሪ በእንዲህ መልኩ ተዘርፋ፣ መዘረፏን ካወቀች በኋላ ደንግጣ ለከበቡዋት ሰዎች የሆነችውን ስትተርክ ነበር፡፡
ያዲሳባ ሌብነት አድጓል።መኪና እየሄደም አስቁመው የወስዳሉ።ሲቆምም ይሰርቃሉ።የቀናው አላርም “የደህንነት ደወል” ነጋዴ ነው።አስመጪዎቹ ደግሞ እነ እንትና ናቸው።ህጉም፣ጥበቃውም እንዲላላ የተደረገው ላስመጪዎቹ ሲባል ስለመሆኑ አምበርብር መረጃ የለውም።
ሰርቆና ተሰርቆ መለያየት ያለ ነው፡፡ ከተሰረቁ በኋላ የራስን እቃ እንደገና ለመግዛት መለመን ሞት ነው፡፡ ሰው የራሱን እቃ እንዴት በሺህ የሚቆጠር ብር አውጥቶ ይገዛል ? ደላላው አምበርብር ጠየቀ፡፡ ሰው የራሱን ንብረት ለመግዛት ከተስማማ በኋላ እቃው ሲመጣለት እንኳን እንዴት ወንድነቱ አይመጣም ? ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ ወንድ ጠፋ፣ ሲዘረፍ የሚናገር የለም፡፡ የዘረፈውን አይቶ ዝም ማለት ተለመደ፡፡ ለዘራፊዎች በተዘዋዋሪ ፈቃድ የሰጡት “ጉዳተኞች ” ናቸው፡፡ ተጎድተውም ዝም የሚሉ ዜጎች እየበዙ ናቸው፡፡ ሰው ንብረቱን የዘረፈውን ሰው አይቶ እንዴት ዝም ይላል ? የሰው ልጅ ወኔ ከዳው፡፡ ወኔ የሌላቸው እየበዙ ናቸው፡፡ “ወኔ የሌላቸው ነዋሪም አኗኗሪም አይሆኑም፡፡ ለመኖር ሞራል ያስፈልጋል፡፡ አኗኗሪ ለመሆን ደግሞ ልብ ይጠይቃል፡፡ ልብ ስልህ ይገባሃል ?” በማለት ማንጠግቦሽ ደጋግማ ትጠይቃለች፡፡ ልብ የለም፡፡ ልብ ያላቸው ጠፉ፡፡ ለንብረታቸው የሚቆረቆሩ ታጡ፡፡ ንብረታቸው ለራሳቸው ሲሸጥ እልል ብለው፣ ለምነው፣ ተቅለስልሰው፣ አሸርግደው፣ ተዋርደው፣ አልቅሰው የሚገበያዩትን ደላላው ረገመ፡፡ ወዳጁንም ረገማቸው፡፡ “አሁን የእኔ አሟሟት አሟሟት ነው ወይ . . . ” የሚለው ዘፈን ትዝ አለውና መረጠላቸው፡፡
ቀበኞች በዝተዋል፡፡ የቀበኞቹ መብዛት ሳይሆን ለቀበኞቹ ባሪያ ሆኖ መኖር አንበርብር ምንተስኖትን አስደንግጦታል፡፡ ቀበኞች ህግ አይፈሩም፡፡ ቀበኞች ፖሊስ አይፈሩም፡፡ ቀበኞች የጎዱትን ሰውአይፈሩም፡፡ ቀበኞች ጨለማ አይፈሩም፡፡ ቀበኞች የሚፈሩት ፀሐይ ብቻ ነው፡፡ ቀን ይተኛሉ፡፡ አመሻሽ ላይ እቅድ ይነድፋሉ፡፡ በደንብ ሲመሽ አፈፃፀማቸውን ያቀላጥፋሉ፡፡ በሌላኛው ቀን የእቅዳቸውን አፈፃፀም ይገመግማሉ፡፡
አምበርብር ምንተስኖት በላቾችም ግምገማ እንደሚያደርጉ ሰምቷል፡፡ ግምገማ የሌለበት የለም፡፡ በግምገማ መታደስ አለ፡፡ የቀማኞች መታደስ ምን ይሆን ? ደላላው ጠየቀ፡፡ የሰው ንብረት ለመዝረፍ፣የሰው አጥር ግቢ ለመዝለል፣ የሰው እቃ በፍጥነት ስለመስረቅ፣ የሰው እቃ ሰርቆ ስለመሮጥ፣ ድንገት ችግር ቢፈጠር ስለሚወሰድ እርምጃ ቀበኞች ግምገማ ያካሂዳሉ፡፡ የስርቆት ሪከርድ ለማሻሻል ስልት ይቀየራል፡፡ በዚህ መልክ የተጎዳችሁ ቤት ይቁጠራችሁ፡፡ ደላላው አምበርብር ከጉዳዩ ነፃ ነው፡፡ ችግሩ አይመለከተውም፡፡ ችግሩ ባይመለከተውም በሰማው ግን አዝኗል፡፡ በተመለከተው ተገርሟል፡፡የሰማውንና ያየውን ለማንጠግቦሽ ማጫወት አለበት፡፡ የራሳችሁን እቃ በልመና የምትገዙ ከፍርሃታችሁ ንቁ፡፡ንብረታችሁን በልመና ለማስመለስ የምትቅለሰለሱ ተገረዙ። ሰላም ሁኑ፡፡ ሰላም !

ማስታወሻ – ሪፖርተር ጋዜጣ ስሰራ በነበርኩበት ወቅት ደላላው አምድም ላይ እጽፍ ነበር።አምዱ ላይ ስም መጻፍ ክልክል በመሆኑ ጽሁፌም እኔም በነጻነት አውሮፓ ተገናኘን።በሪፖርተር ጋዜጣ የታተመ መሆኑን እየገለጽኩ መጠነኛ ማዳበሪያ አክዬ በማስታወሻዬ ላይ አኖርኩት

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *