በአማራና ኦሮሚያ፣ ከ2ሺ በላይ ተጠርጣሪዎች ታስረዋል

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መውጣቱን ተከትሎ፣ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ከተቃውሞ ጋር በተያያዘ ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉ ከ2ሺ በላይ ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ኮማንድ ፖስት፣ ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡  በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች 1600 የሚደርሱ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን በአማራ ክልል፣ ጎንደር 93 ሰዎች በገዛ ፍቃዳቸው እጃቸውን ለፖሊስ ሰጥተዋል ብሏል – ኮማንድ ፖስቱ፡፡

በሰበታ ከተማ በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ላይ ለደረሰው ቃጠሎና ውድመት እጃቸው አለበት የተባሉ 1 ሺ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ባለፈው ሳምንት ፖሊስ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል በሻሸመኔ ከተማ ብቻ 450፣ በአካባቢው ባሉ ወረዳዎች 670 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን የገለጸው ኮማንድ ፖስቱ፤ በቄለም ወለጋ ዞን 110 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል ብሏል። በኦሮሚያ ከተዘረፉት 513 የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች 384 ያህሉ መመለሳቸውን አመልክቷል፡፡ ሌሎች በግጭቱ ወቅት የተዘረፉ የመንግስትና የግለሰብ ንብረቶችም በስፋት እየተመለሱ ነው ብሏል – ኮማንድ ፖስቱ፡፡
በአማራ ክልል በጎንደር ከተማና አካባቢው “ሸፍተው” ጫካ የገቡና ከአሸባሪዎች ጋር ግንኙነት ከነበራቸው መካከል 93 ሰዎች እጃቸውን የሰጡ ሲሆን 45ቱ ከእነ ሙሉ ትጥቃቸው፣ 38ቱ ደግሞ ያለ ትጥቅ የተመለሱ ናቸው ተብሏል፡፡ በሌላ በኩል በጎንደር ከተማ የንግድ ሱቆቻቸውን በመዝጋት አገልግሎት ለማቋረጥ ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ 13 ነጋዴዎች፣ የስራ ማቆም አድማ ሲያደርጉ የነበሩ 13 ሰራተኞችና 3 መምህራን በቁጥጥር ስር ውለዋል ብሏል – ኮማንድ ፖስቱ፡፡
Written by አለማየሁ አንበሴ Addisadmas

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ፈቃድ የሌላቸው ግለሰቦችና ተቋማት በጥምቀት በዓል ድሮን መጠቀም እንደማይችሉ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *