በሳይንሳዊ ሎጂክ ነው .. ህገ መንግስቱም በሎጂክ ብቻ ሊቀረፅ ይገባል” ለምትሉኝም ከመጣላት አልመለስም፡፡ ሁሉም ጥል የሀሳብ ነው፡ መንግስት ምን ማለት እንደሆነ ከምመረምር “ህሊና” ምን እንደሆነ ብመረምር ይሻለኛል፡፡ ህሊና የሚለው ቃል ምንድነው ትርጉሙ? ከማለት ይልቅ አገልግሎቱ (purpose) ምንድነው ብል በአቋራጭ ወደ ቃሉ ትርጉም እደርሳለሁ፡፡ … መንግስትን ከህሊና … ህሊናን ደግሞ ከግብሩ ጋር ማስተሳሰሬን ልብ በሉ፡፡ የመንግስትን ትርጉምና ስራ በህሊና አገልግሎት ውስጥ አገኘዋለሁ እያልኩኝ ነው፡፡

“ህሊና በግለሰብ መስተሀልይ ወይንም ነፍስ ውስጥ እኩል አድርጎ የመመዘንና ፍርድ የመስጠት ስራን ይሰራል” … ልበል እንደ መነሻ፡፡ በግለሰቡ ውስጥ በተናጠል ህሊና ከሌለ በማህበረሰቡ ወይንም ህዝብ ውስጥ ብቻውን ተነጥሎ ሊኖር አይችልም። በግለሰብ የአካልና የአእምሮ እንዲሁም የስሜት ጥምረት ውስጥ እኩል አድርጎ የሚያስተዳድር መንግስት ከሌለ ግለሰቡ የቀውስ ዳርቻ እንደሚሆነው፣ የማህበረሰብ ህሊናም ከሌለ ውጤቱ ተመሳሳይ ነው፡፡

የማህበረሰብ ህሊናን … ባህል/ሐሪሶት … ሀይማኖት … ህገ መንግስት ወዘተ ብለን እንደምንጠራው፣ የግለሰቡ ህሊና በህገ ልቦና ይገዛል። እንደኔ እምነት ህገ – ልቦና በግለሰቡ ውስጥ ከሌለ ህገ – መንግስትም በመንግስት ዘንድ ሊረቅ አይቻለውም ባይ ነኝ፡፡ ህዋስ ባይኖር የሰውነት አካል ሊኖር እንደማይችለው ማለቴ ነው፡፡ በግለሰቡ ውስጥ ያለውን (መኖር ያለበትን) ህገ – ልቦና፣ ተፈጥሮ ናት አርቅቃ የሰጠችው ብትሉኝ ባልስማማም እንኳን አያጣላንም፡፡ … ፈጣሪ ነው የሰጠው … ብትሉኝም … በድጋሚ ግማሽ ተስማምቼ፣ ግማሽ ታዝቤ አልፋችኋለሁኝ፡፡

የምጣላው … “ፈጣሪ ህገ ልቦናን ስለሰጠው … ፈጣሪ ደግሞ ክርስቲያን፣ ሙስሊም፣ ፕሮቴስታንት ወይንም ሌላ … ስለሆነ … ህገ መንግስቱ ዳግም በዛው መሰረት በሀይማኖታዊ ህግ ተቀርፆ ብቻ ህዝብ በዛ መተዳደር አለበት” ካላችሁኝ ነው፡፡ በሀሳብ ነው እንጂ የምጣላችሁ በተግባር ጫፋችሁን አልነካም፡፡ ምክንያቱም ህሊናዬ ይኼንን አይፈቅድም፡፡
እንደዚሁም በተቃራኒው “የሰውን ህገ ልቦና የሰጠችው ተፈጥሮ ናት … ተፈጥሮ ደግሞ የምትሰራው በሳይንሳዊ ሎጂክ ነው .. ህገ መንግስቱም በሎጂክ ብቻ ሊቀረፅ ይገባል” ለምትሉኝም ከመጣላት አልመለስም፡፡ ሁሉም ጥል የሀሳብ ነው፡፡

* * *

ለእኔ “ህሊና” የሚባለው ቃል … ከፍትህና ነፃነት ጋር የጠበቀ ተያያዥነት አለው፡፡ … ፍትህም ስለ እኩልነት … ነፃነትም ስለ እኩልነት ነው የሚያወሩት። እንዴት? በሉኝ፡፡ በአስራ ስድስተኛው ዘመንና በአካባቢው ለነበሩ የፖለቲካ ፈላስፎች፣ እኩልነት በሦስት መሰረታዊ ዘውጎች ስር የተተነተነ ነው፡፡ ለምሳሌ ሆብስ (Hobbs) ሰዎች እኩልነታቸው ያለው በተፈጥሯቸው ላይ ነው፡፡ በተፈጥሯቸው ደግሞ ጨካኝና መሰሪ ናቸው፡፡ እኩል የሚያደርጋቸው ይኼ ባህሪያቸው ግን ህይወታቸውን በክፋትና አደጋ የተሞላና አጭር ያደርገዋል … ባይ ነው፡፡ እና ህይወታቸው ዘለግ ያለ ጊዜ እንዲቆይና ትርጉም ያለው እንዲሆን ለአንድ የተመረጠ አንድ አድራጊ ንጉስ፣ እኩልነታቸውን ያስተዳድርላቸው ዘንድ ነፃነታቸውን አሳልፈው መስጠት ይኖርባቸዋል – ይላል፡፡

ሩሶ (Rousseau) ደግሞ፡- ሰዎች ራሳቸውን የማሻሻል አቅም ያላቸውና በራሳቸው ብቁ የሆኑ ፍጡሮች ናቸው፡፡ … ግን ይኼ ተፈጥሮአቸው … በማህበረሰብ ውስጥ ሲገባ ፍትህ ይዛባል .. እኩልነታቸው ይጠፋል፡፡ ግለሰቦች ሳይሆን ማህበረሰብ ነው እኩልነትንና ነፃነታቸውን የሚነፍገው ባይ ነው፡፡ (ነፃነትና እኩልነትን ምን አገናኘው? ለምትሉኝ በኋላ ላይ እመለስበታለሁ) ማህበረሰብ ያመጣባቸውን የእኩልነት እጦት ለመመለስ ከፍ ወዳለ ሉአላዊነት መሻገር ያስፈልጋቸዋል፡፡ በግለሰብ ሰውነት ግዛት ላይ እንዳለው ሉአላዊነት በሀገርም ደረጃ በግለሰብ አካል ላይ ያለ ስርዓትን ለመፍጠር ሲባል ትንሽ ማህበረሰቦች ስልጣናቸውን ከፍ ላለው አንድነት አሳልፈው ይሰጣሉ … እንደ ማለት ነው፡፡

ሦስተኛው እስቲዋርት ሚል የሚባለው ፈላስፋ ነው፡፡ የእሱ መንገድ ከሁለቱ ጋር በይዘት ይለያያል። ለሚል፤ መንግስትና ነፃነት … ህሊናም ጭምር ያለው በግለሰቡ የፍላጎት ምርጫ ላይ ነው፡፡ እርግጥ የማህበረሰብ ህሊና የሆነ መንግስት መኖሩን ባይቃወምም … በተቻለ መጠን የመንጋው ህሊና ወይንም መንግስት ግን የግለሰቡን ህሊና እና ነፃነት እንዳይጫነው ይፈልጋል፡፡ በግለሰቡ ላይ ጣልቃ የመግባት አቅሙም የተቀነሰ መሆን አለበት ባይ ነው፡፡

* * *

የፍትህ መጓደል ወይንም የነፃነት እጦት ከእኩልነት እጦት ይመነጫል፡፡ ይሄንን የማስተካከል ስራ የሚሰራ አካል፣ በግለሰቡ ልቦናም ሆነ በማህበረሰብ ልቦና ውስጥ አለ፡፡ ይኼንን አካል ነው መንግስት እያልኩ ለመጥራት የፈለግሁት። ተግባሩ ከታወቀ … ቃሉን መጥራት እንችላለን፡፡ ተግባር የሌለው ነገር ግን የተለየ መጠሪያ ሊኖረው አይችልም፡፡
ስለዚህ፤ የመንግስት ተግባር ህዝብ ተብሎ በሚጠራ የሰዎች ስብስብ ውስጥ እንደ በላይ ህሊና ሆኖ የሚያገለግል ማለት ነው፡፡ ህሊና ሆኖ ሲያገለግል የተዛቡ ሚዛኖችን እኩል ያደርጋል። እኩል የሚያደርገው በ“ህግ” አማካኝነት ነው። መንግስት ማለት ህሊና ማለት ነው እንዳልኩት… መንግስት ማለት ህግ ማለት ነው፡፡ … ከህግ ጋር ያልተያያዘ መንግስት … ህሊና የሌለው ተግባር እንደ ማለት ነው፡፡

ከህግ ጋር መያያዝ ስል … ህግ ማርቀቅ፣ መተርጎምና ማስፈፀምን ይጠቀልላል፡፡ ጠንካራ መንግስት ማለት ይኼንን ማድረግ የሚችል ነው። ጠንካራነቱ ግን በህግ መለኪያ እንጂ በመንግስት መለኪያ ላይሆን ይችላል፡፡ ያስፈለገውን ህግ ላስፈለገው ግብ በማርቀቅ፣ በመተርጎምና በማስፈፀም ላይ የማይታማ ሆኖ … ግን እኩልነትንና ፍትህን ማስፈፀም ላይ ስኬታማ ካልሆነ … ጠንካራ ህግ አስከባሪ እንጂ … ጠንካራ መንግስት አይሆንም፡፡

በመንግስትም ሆነ በግለሰብ ላይ ህሊና ገዢ እንዲሆን ለምን እንጠብቃለን? ለመሆኑ ህሊና የሚባለው ነገር እንደው ተንሳፋፊ ህልም (floating abstraction) ቢሆንስ? … ብትሉኝ … አልቀየማችሁም፡፡ አልቀየማችሁም ሳይሆን በአድናቆት እንዲያውም አጨበጭብላችኋለሁኝ፡፡

ተፈጥሮን በጥልቅ ስናስተውለው፣ምንም ዓይነት እኩልነት አይታይበትም፡፡ በተለይ እኩልነትም ካለ በሰው የህሊና አተረጓጎም የሚደገፍ አይደለም። …. ጠንካሮቹ ደካሞቹን አድነው ሲበሏቸው ነው የሚስተዋለው፡፡ ሰው በጉን አጋድሞ አርዶ ይበላዋል። ምንም ዓይነት እኩልነት ሊሰፍን አይችልም፤ በአንበሳና ሚዳቋዋ መሀል፡፡ አንበሳ ሚዳቋን እንዳይበላ ተብሎ ህግ ቢረቀቅ፣ አንበሳው በረሀብ ይሞታል፡፡ የተረቀቀው ህግም ከተፈጥሮ ጋር ሆድና ጀርባ መሆኑ ይኼኔ በግልፅ ይታያል፡፡

ተፈጥሮ ላይ የሚሰራው እኩልነትና በሰው ህሊና ላይ ያለው የእኩልነት አተያይ የተለያየ እንደሆነ ምንም ክርክር አያሻውም፡፡ ሰው በተፈጥሮ ህሊና ላይ የራሱን ህሊና ያበቀለ … በማብቀሉም የተራቀቀ .. የዚያኑ ያህል ያረቀቀውን ለመተግበር መከራውን የሚበላ ፍጡር ነው፡፡ ተፈጥሮ በሌላው መልከ-ገፅታዋ ላይ ብቻ ሳይሆን በራሱ በሰው ልጅ ላይ እኩልነትን አልሰራችም፡፡

የሰው ልጆች…ገና ከአፈጣጠራቸው ልዩነት ይታይባቸዋል፡፡ የአካል ብቻ ሳይሆን የአቅም ልዩነት አላቸው፡፡ በአእምሮም ሆነ በዝንባሌ እኩል አይደሉም፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ የአስተዳደግ፣ የአኗኗርና የትምህርት አሰጣጥ እጣ ፈንታ… እንደተወለዱበት ሀገርና ማህበረሰብ ሲጨመርበት… እኩል ማድረግ የማይታሰብና ተስፋ አስቆራጭ ይሆናል፡፡

ስለዚህ፤ …ስለዚህ ግለሰቡ ህሊና ቢኖረው እንኳን… ከራሱ ህሊና ጋር የተጣላ መሆኑ የማይቀር ይሆናል፡፡ ግጭቱ በሰውኛ ህሊናው (ፍትሁ) እና በተፈጥሮ ፍትሀዊነት መሀል የሚደረግ እንደሆነ ሁሉ ጠንቅቆ ሳይረዳ ይታወካል፡፡ ግለሰቡ የራሱን ህሊና ከማህበረሰቡ ጋር ለማስታረቅ ደግሞ ሌላ አበሳ ነው፡፡ ጆን እስቲዋርት ሚል፣ ይኼንን በማህበረሰብ ህሊና (ባህል/አመለካከት) የግለሰብ ህሊና ላይ የሚደርሰውን ጭቆና ‹‹the tyranny of the majority›› ሲል ይጠራዋል፡፡

እና ምናልባት የማህበረሰቡን ጭቆና በግለሰብ አቅሙ ስለማይችለው፣ የግለሰብ ህሊናውን ለማህበረሰቡ ይሸጣል፡፡ … አልያም ከማህበረሰቡ የበለጠ ሀያል ሆኖ በማህበረሰቡ ላይ ስልጣን ለመጨበጥ ይጥራል፡፡… ጥረቱን ለማሳካት የሚያደርገው ሙከራ በጥበብ ወይንም ፍልስፍና መልክም ሊገለፅ ይችላል፡፡ እንደ ፍሬድሪክ ኒቼ፣ ከማህበረሰቡ ውል ለማፈንገጥ ሲል የአራዊትን የጉልበተኝነት ህግ ለሰዎች ምርጥነት ማስረጃ አድርጎ መስበክም የዚሁ ግጭት መገለጫ ይመስለኛል፡፡

በማንኛውም ረገድ ቢሆን ግን እኩልነትን እውን ማድረግ አስቸጋሪ የፅንሰ ሀሳብም መሰረት ያለው ጥያቄ ነው፡፡ ለምሳሌ ‹‹ዴሞክራሲ›› የሚለው ፅንሰ ሀሳብ በሰዎች ዘንድ እኩልነትን ነው ወይንስ ነፃነትን ለመስጠት የሚያገለግለው? በነገራችን ላይ ነፃነት (Freedom) እና አርነት (liberty) በሚሉት ቃላት መሀል እንኳን እኩልነት የለም፡፡ አርነት… ከአንዳች የገዢ ጭቆና መውጣትን የሚያመለክት ቃል ነው። ነፃነት ግን በሁለት ዘውግ የተከፈለ ሀሳብ ነው፡፡

አዎንታዊ ነፃነት (Positive freedom)፡- ሰዎች ለህልውናቸው ምክንያት የሆነ አንዳች የሕይወት ግብን ተከትለው ወደ አለሙበት ለመድረስ ምርጫቸውን መሰረት አድርገው የሚጓዙት ጉዞ ሊባል ይችላል፡፡ ወደዚህ ግብ ከመድረስ የሚያግዳቸው ሁሉ ይኸንን አዎንታዊ ነፃነትና የህይወት ትርጉማቸውን የሚያሰናክል ጨቋኛቸው ነው፡፡

አሉታዊ ነፃነት (Negative freedom) ደግሞ ሌላ ነው፡፡ አሉታዊው ነፃነት ማንም ሰው ያሰኘውን ፍላጎቱን ያለ ምንም ቅድመ ምክኒያታዊነት ለመፈፀም የሚያስችለው የነፃነት አይነት ነው፡፡ ለምሳሌ፤አንድ ሰው የመቃም ወይንም የማጨስ ነፃነቱን ሲጠቀም ምርጫው አካሉን ወይንም የህይወት ዘመኑን ሊያሳጥር እንደሚችል አውቆ ነው፡፡ … ግን እያወቀም… ከራሱም ህሊና ወይንም ከማህበረሰቡ አሊያም ከህግ የበለጠ የፍላጎቱን ነፃነት ለመጨበጥ ሲል ምርጫውን ተግባራዊ ያደርጋል፡፡ አሉታዊ ነፃነት ይህ ነው፡፡

እነዚህ ሁለት የነፃነት አይነቶች … ራሳቸው በአንድ ግለሰብ ውስጥ ሳይስማሙ.. ወይንም እኩል ሳይሆኑ ሊቀጥሉ ይችላሉ፡፡ በመቀጠላቸው ለሁለት የተለያዩ የነፃነት አይነቶች… የተገዛ ሁለት አይነት ህሊና በግለሰቡ ስነልቦና ውስጥ ፈጥረው እኩልነትን ለማግኘት ሊሻኮቱ ይችላሉ፡፡

እና ታዲያ በአንድ ግለሰብ ላይ ሁለት ነፃነትና ሁለት ህሊና ካለ፣ማህበረሰብስ ስንት ይኖረዋል? ብለን እናስብ፡፡ ማህበረሰብ ብለን ደግሞ ሀገር …፡፡

አንድ የማውቀው ልጅ ሁልጊዜ ሲጠጣ እየደጋገመ፤ ‹‹ነፍስ ያለው አስቸጋሪ ነው!›› ይላል። ምናልባት እሱ በአንድ ዓረፍተ ነገር እኔ ከላይ የፃፍኩትን ሁሉ ቁልጭ አድርጎ ገልፆታል፡፡

…ነፍስ ህሊና ካልሆነ…ታዲያ ህሊና ምንድን ነው?

Source: ሌሊሳ ግርማ addisadmassnews.com

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *