ፎቶ ፋይል፡ በቢሾፍቱ በእሬቻ በዓል ላይ የሞተ ወጣት የቀብር ሥነ ስርዓት(መስከረም 3/2009)voa

“እንደዚህ አይነት ችግር የለም” አስተዳደር

የለቅሶ ሳግ በያዘው አንደበት የመረረ ሃዘን ይሰማል። ተናጋሪዋ የሚሰሩት ድራማ ወይንም ዘጋቢ ፊልም ሳይሆን በትክክል የደረሰባቸውን ነው። የልጃቸው አስከሬን እንደምናምንቴ በማዳበሪያ ተደርጎ ነው የተሰጣቸው። ልብ ይነካል። ያማል። ጉዳዩ ከሃዘንም በላይ ይሆናል። አንድ ልጃቸው ” መመኪያዬ” የሚሉት ተገደለባቸው፤ ሌላኛው ክፉኛ ተደብድቦ ታሟል፤ ሁለቱ ታስረዋል። እኚህ የ65 ዓመት አዛውንት ሲያልቅ አያምር ሆነና ባዶ ሆኑ።

” ልጄን ገለው በማዳበሪያ አመጡልኝ” አሉ። አስከትለው አስከሬኑ መበላሸቱንና ደም ይፈሰው እንደነበር ገለጹ። ወግ አይቀር ተቀበረ። አሁን አሁን ” ወዴት እየሄድን ነው” ከማለትም ያለፈ ይመስላል። ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት የወረዳው አስተዳዳሪ ” በአሁኑ ሰዓት እንዲህ ያለ ችግር የለም” ማለታቸው፣ ዋና አስተዳዳሪውና የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ምላሽ ለመስጠት አለመፈለጋቸው ሌላው አስዛኝ ጉዳይ ነው።
በምስራቅ ሸዋ ዞን፣ ቦሰት ወረዳ ቆምቤ ጉግሳ መንደር ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ሎሚ ዋቀዮ የ65 ዓመት፣ ባለቤታቸው የ74 ዓመት አዛውንት ናቸው። እኒህ ሁለት አዛውንቶች የደረሰባቸው ሃዘንና ግፍ ኢህአዴግን ለሚደግፉም ሆነ ለሚቃወሙ ለሁሉም ልብ የሚሰብር ነው።የወ/ሮ ሎሚ ዋቀዮን ቤት መበተን ጀግንነትም አይሆንም። እሳቸው ላይ የደረሰው ሃዘን በፖለቲካ ሚዛንና ትርፍ ማየትም አግባብ አይሆንም።
” የሞተ አይመለስም” የሚሉት እናት ” የተበታተኑትን ልጆቼን መልሱልኝ” በሚል ጠይቀዋል። እናም የገዢዎች ምላሽ ምን ይሆን?የሃላፊዎች ምላሽ ምን ይሆን?
ቀደም ሲል በወለጋ አንድ እናት የልጇ አስከሬን ላይ እንድትቀመጥ ተደርጎ የተፈጸመውን ያስታወሰው ይህ ዜና፣ አፋጣኝ ምላሽ የሚያሻው ሆኖ ተገኝቷል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀና ከመታወጁ በፊት በአገሪቱ ታሪክ ክፉ የተባሉ ተገባራት ተፈጽመዋል። ይህ የሚቆምበትና ሁሉም ነገር በህግ የሚታይበት አግባብ እያለ እንዲህ አይነት የከፋ ድርጊት መፈጸም በየትኛም ጊዜ ዋጋ የሚያስከፍል፣ ለማንኛውም ወገን ገድል ሆኖ የማይቀመጥ፣ ነውና ሁሉንም ባግባቡ ማስተናገድ፣ አግባብ እንደሆነ አዛውንቶችና ነገሮችን በሰከነ መንፈስ የሚመለከቱ ይመክራሉ።  የቪኦኤ ዘገባ ከዚህ የሚከተለው ነው።

Related stories   ብርሃኑ ነጋ አቋማቸውን ቀየሩ፤ ኢዜማ ደርግ በግፍ የዘረፈውን የግል ሃብት ለተከራይ እንደሚሸጥ ይፋ አደረገ፤ የኢዜማ የ ” ፍትህ” ሩጫ

http://amharic.voanews.com/a/boset-area-mother-received-the-body-of-her-son/3579672.html
“የሞተው ልጄ ሞቷል፤ ያሉትን መልሱልኝ” ወ/ሮ ሎሚ ዋቀዮ
ፎቶ ፋይል፡ በቢሾፍቱ በእሬቻ በዓል ላይ የሞተ ወጣት የቀብር ሥነ ስርዓት(መስከረም 3/2009)
የአሜሪካ ድምጽ ያነጋገራቸው በምስራቅ ሸዋ ዘን ቦሰት ወረዳ የሚገኙ ወ/ሮ ሎሚ ዋቀዮ የተባሉ እናት አንድ ልጃቸው እንደተገደለ ሁለቱ እንደታሰሩና አንዱ በእጅጉ መደብደቡን ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ለስድስት ወር አስቸኳይ ጊዜ ከታወጀ አንድ ወር ሊሞላው ጥቂት ቀናት ይቀሩታል። ይህ ዐዋጅ ይፋ ከተደረገ በኋላ ሰዎች ከየቦታው እየተለቀሙ እንደሚታሰሩ በተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችና በሰባዊ መብት ተሟጋቾች ጭምር ሲነገር ቆይቷል።
ወ/ሮ ሎሚ ዋቀዮ በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ ቆምቤ ጉግሳ በተባለ መንደር ነዋሪ እንደሆኑ ይናገራሉ። የ65 ዓመት አዛውንት ናቸው። ባለቤታቸው ደግሞ የ74 ዓመት አዛውንት መሆናቸውን ገልጸውልናል። እንደ ወ/ሮ ሎሚ ገለጻ አራት ልጆች ነበራቸው። አቢቲ ደጃሳ የተባለ የ30 ዓመት አርሶ አደር ልጅ ነበራቸው። ደምሴ ደቻሳ ወይም ደሜ እያሉ በቁልምጫ የሚጠሩት የ22 ዓመት ልጃቸው ደግሞ “አዳማ ሄዶ ሥራ ፍለጋ ሲንከራተት ተይዞ ታስሯል” ይላሉ። የት እንደታሰረ ግን አያውቁም።
ንጉሴ ደቻሳ የተባለው ልጃቸው ደግሞ ከቤት ውስጥ ተደብድቦ ተወስዶ ወለንጪቲ ተወስዶ መታሰሩን ይናገራሉ። ወ/ሮ ሎሚ በለቅሶ በታጀበ ድምጽ ረዳታቸው የ30 ዓመቱ ወጣት አቢቲ ደቻሳ ለስብሰባ ይፈለጋል ተብሎ ከቤታቸው ከተወሰደ በኋላ ጥቅምት 12 ቀን 2009 ዓ.ም አስክሬን እንደመጣላቸው ይናገራሉ።
የልጃቸው ለቅሶ ባይመጣና ቤታቸው ሐዘን ባይገባ ኖሮ ወለንጪቲ ታስሯል የተባለውን ልጃቸውን ንጉሴን ሄደው ይጠይቁት እንደነበር ገልጸዋል። “አንዱን በሞት አጣሁ። አሁን አንድ ሰው አብሮኝ የለም። ቤቴ ባዶውን ቀርቷል። ደካማ ነኝ” የሚሉት ወ/ሮ ሎሚ ዋቀዮ “የሞተው ልጄ ሞቷል፤ ያሉትን መልሱልኝ” ሲሉ ይጠይቃሉ። የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ይህን በተመለከተ የደረሰን ሪፖርት የለም ብለዋል።
ህዳር 03, 2016 የኦሮመኛ ቋንቋ ዝግጅት ባልደረባ ጃለኔ ገመዳ ያጠናቀረችውን ዘገባ በጽዮን ግርማ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *