ከተወለደች አንድ ሳምንት የሞላትን ጨቅላ ህጻንን መድሃኒት ለመስጠት ከሁለት ቀን በላይ ክንዷን በማሰርና መርፌ በመውጋት በቸልተኝነት ለእጇ መቆረጥ ምክንያት የሆኑ አራት የጳውሎስ ሆስፒታል ነርሶች በእስራት ተቀጡ። ነርሶቹ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት በቸልተኝነት የሚፈጸም ከባድ የአካል ጉዳት ማድረስ ወንጀል ነው ክስ የተመሰረተባቸው። ተከሳሾቹ 1ኛ ሩት ሃይሉ፣ 2ኛ ህብረወርቅ ሃይማኖት፣ 3ኛ ሩቂያ መሃመድ እንዲሁም 4ኛ አባይነሽ ተስፋዬ ሲሆኑ፥ የጳውሎሰ ሆስፒታል ነርሶች ናቸው።
ተከሳሾቹ የሌላን ሰው አካል ወይም ጤንነት የመጠበቅ የሙያ ግዴታ እዳለባቸው እያወቁ በጳውሎስ ሆስፒታል፥ ከጥር 27 ቀን 2008 እስከ የካቲት 4 ቀን 2008 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ከተወለደች አንድ ሳምንት የሆናትን ህጻን በተፈጠረባት ማመርቀዝ (ኢንፌክሽን) ህክምና ለመስጠት በሚል ከሁለት ቀን በላይ ክንዷን በማሰርና መርፌ በመውጋት በቸልተኝነት ለእጇ መቆረጥ ምክንያት ሆነዋል ሲል ጠቅላይ አቃቢ ህግ በክሱ አመልክቷል።
ተከሳሽ ነርሶች ችሎት ፊት ቀርበው ድርጊቱን አልፈጸምንም ብለው ተከራክረዋል፤ አቃቢ ህግም የሰውና የህክምና የሰነድ ማስረጃዎችን ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል። የግራ ቀኙን ክርክር የተከታተለው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መናገሻ ወንጀል ችሎት ተከሳሾች የቀረበባቸውን ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻላቸው ጥፋተኛ ብሏቸዋል። በተከሰሱበት የወንጀል ክስም በዛሬው ውሎው 1ኛ ተከሳሽ በሁለት አመት ከስድስት ወር እስራትና በ2 ሺህ ብር ስትቀጣ፥ ከ2ኛ እስከ 4ኛ ያሉ ተከሳሾች ደግሞ በሁለት አመት ከሶስት ወር እስራትና በ1 ሺህ 800 ብር የገንዘብ ቅጣት ተወስኖባቸዋል።
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ)

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *