የኢትዮጵያ ተቃውሞ በአምነስቲ እይታ
የኢትዮጵያን ተቃውሞ አንደኛ ዓመት በማስመልከት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ትናንት ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ የሚታዩ የሰብዓዊ መብት አሳሳቢ ሁኔታዎችን ለመፍታት ከይስሙላ የዘለለ ተጨባጭ እርምጃዎች አልወሰደም ሲል ተችቷል፡፡ መንግስት በበኩሉ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት የሚያስጠብቀው ማንንም ለማስደሰት ብሎ ሳይሆን ለዜጎቹ ሲል እንደሆነ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ።
የአምነስቲ ትችት
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ትናንት ባወጣው መግለጫ 800 ሰዎች የተገደሉበት ተቃውሞ ከተቀሰቀሰ በአንድ ዓመት ውስጥ የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ያሉ አሳሳቢ የሰብዓዊ መብት ሁኔታዎችን ለማሻሻል ተጨባጭ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ የይስሙላ አካሄዶችን መተግበር መርጧል ሲል ወቅሷል፡፡
ደም አፈሳሹን ተቃውሞ ያጫረው የአዲስ አበባ ከተማ እና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላን እንደነበር ያስታወሰው መግለጫው ከአንድ ዓመት በኋላ በኢትዮጵያ አሁንም ከፍተኛ ውጥረት እንዳለ እና የሰብዓዊ መብት ሁኔታውም በጣሙኑ አሳሳቢ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ባሉ ቦታዎች በጸጥታ ኃይሎች እና በአካባቢው ማህብረሰብ መካከል አልፎ አልፎ ግጭት እንደሚታይም ይጠቅሳል፡፡ የጅምላ እስር እንዳለ እና የኢንተርኔት አገልግሎት እንደተዘጋም ይገልጻል፡፡
በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪካ ቀንድ ተመራማሪ ፍስሀ ተክሌ ለዓመት ያህል በቆየው ተቃውሞ ብዙ ጉዳቶች መድረሳቸውን እና በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች የሚወሰዱ የኃይል እርምጃዎች መቆም እንዳለባቸው ያሳስባሉ፡፡
“አምነስቲ በዚህ ተቃውሞ የተነሱ ጥያቄዎች ላይ የኢትዮጵያ መንግስት እንዲወያይ ነው የሚጠይቀው፡፡ ሌላ ጥያቄ የለውም ፡፡ ተቃዋሚዎቹ ያነሱትን ጥያቄ መንግስት በትክክል ይመልከት ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ሰልፍ የወጡ፣ ኃይል የማይጠቀሙ ሰዎች ላይ የሚደረገው የኃይል እርምጃ መቆም አለበት” ሲሉ አቶ ፍስሀ የአምነስቲን አቋም ይገልጻሉ፡፡
ተቃዋሚዎች ያነሷቸውን ጥያቄያቸው ተገቢነታቸውን ተመልከቶ መመለስ እንጂ የተለያዩ ስያሜዎች እየሰጡ ማጣጣል መፍትሄ እንደማይሆን አቶ ፍስሃ ይመክራሉ፡፡ “ስለተሰለፉ ብቻ የተለያየ ስም መስጠት አሸባሪ፣ ጸረ-ሰላም ኃይል እያሉ ስም መስጠት ሳይሆን ጥያቄያቸው ተገቢነት አለው የለውም የሚለውን በተመለከተ ገምግሞ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ነው፡፡ የተለያየ ስም ብንጣቸው ጥቅም የለውም ነገሮችን አይፈታም” ይላሉ፡፡
አምነስቲ በመግለጫው አመት በዘለቀው ተቃውሞ በትንሹ 800 ሰዎች መገደላቸውን እና አብዛኞቹም ከኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች እንደሆኑ ገልጿል፡፡ ብዙዎቹ የተገደሉትም በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እጅ እንደሆነ ይከሳል፡፡ በኢትዮጵያ የሚፈጸሙ እንዲህ አይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማጣራት አስቸጋሪ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ፍስሀ ቁጥሩ ከዚህም በላይ ሊበልጥ እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ አምነስቲ ያወጣው ቁጥር በተለያዩ መንገዶች ያረጋገጣቸውን ብቻ እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡ በሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ በኋላ እንኳ ግድያው እንደቀጠለ መስማታቸውን ነገር ግን አምነስቲ ይህን ማረጋገጥ እንዳልቻለ ያስረዳሉ፡፡
በመንግስት ኮሚዩኔኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ መሀመድ ሰኢድ ግን ይህን ይቃረናሉ፡፡ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ ወዲህ ባለው አንድ ወር ውስጥ የሰላም መሻሻሎች የታዩበት ሁኔታ” እንዳለ ይከራከራሉ፡፡ የሟቾቹን ቁጥር በተመለከተ በህገ መንግስቱ ስልጣን የተሰጠው “የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አጣርቶ እስኪገልጽ ድረስ ቁጥሩ ይህ ነው ማለት ትክክል አይደለም” ይላሉ፡፡
“መንግስት በተደጋጋሚ እንደገለጸው አሁን ቁጥሮችን ከፍ የማድረግ እና ዝቅ የማድረግ ጉዳይ አይደለም፡፡ የእንድም ሰው ህይወት በእንዲህ አይነት ሁኔታ መጥፋቱ አደጋ መድረሱ በጥልቅ ያሳዘነው መሆኑን በተደጋጋሚ የገለጸበት ሁኔታ ያለው፡፡ የቁጥር ጉዳይ ሳይሆን የሰው ህይወት ጉዳይ ነው፡፡ የዜጋ ህይወት ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የምናስተላልፋቸው እና የምንገልጻቸው ቁጥሮች ትክክል መሆን አለባቸው፡፡ ከዚህ ጋር በተገናኘ በህገ መንግስቱ ስልጣን የተሰጠው እና ገለልተኛ አካል አጣርቶ በቀጣይ ለህዝቡም ለሚመለከታቸው አካላትም ጭምር ይፋ የሚያደርግበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ይህ አካል ሳያጣራ በፊት ይሄ ነው፣ ያ ነው ብሎ ማለት ትክክል እና ተገቢ አይመስለኝም”” ሲሉ የአምነስቲን የሟቾች ቁጥር ተችተዋል፡፡
መንግስት የተቃዋሚዎችን ቅሬታ ለመፍታት ተጨባጭ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ የይስሙላ አካሄድ መርጧል ሲል አምነስቲ በመግለጫው ይወቅሳል፡፡ አቶ ፍስሀ መንግስት በተለያየ ጊዜ“ እታደሳለሁ፣ ራሴን እመለከታለሁ፣ እገመግማለሁ” ማለቱን እና በቅርብ ጊዜ አዳዲስ የካቢኔ አባላትን መሰየሙን ያስታውሳሉ፡፡ እርምጃው ከተቃዋሚዎች ጥያቄ የራቀ እንደሆነ ይሟገታሉ፡፡
ተቃዋሚዎቹ የጠየቁት “መብታችን ይከበር፣ ትክክለኛ የፌደራሊዝም ስርዓት ይተገበር፣ የህግ የበላይነት ይኑር፣ የታሰሩ መሪዎች እና ተቃዋሚዎች ይለቀቁ” የሚል እንደነበርና የሚኒስትሮች ለውጥ ለእነዚህ ምላሽ እንደማይሆን ይገልጻሉ፡፡ መንግስት የተቃዋሚዎችን ቅሬታዎች በአግባቡ የማያስተናግድ ከሆነ ሌላ ዙር ተቃውሞ አይቀሬ እንደሆነም ያስጠነቅቃሉ፡፡
“ሰዎች ጥያቄ አንስተው ጥያቄያቸውን በኃይል ስትጨፈልቀው ለጊዜው ልታቆመው ትችላለህ፡፡ ግን ያ ማለት ጥያቄው ተመልሷል ማለት አይደለም፡፡ ጥያቄው በሌላ ጊዜ በሌላ መልኩ ይመጣል፡፡ አጋጣሚውን፣ ሁኔታውን ጠብቆ፣ አንዳንዴ በሚያስፈራ መልኩ ሊሆን ይችላል ጥያቄው ሊመጣ ይችላል” ሲሉ ይተብያሉ፡፡
አቶ መሀመድ ግን መንግስት ቅሬታዎችን ለመፍታት እና አስተማማኝ ሰላም ለማምጣት ከህዝቡ ጋር እየተመካከረ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ጥያቄዎቹ በአንድ ጀንበር ሳይሆን ደረጃ በደረጃ የሚፈቱ ናቸው ይላሉ፡፡
ተስፋለም ወልደየስ
አዜብ ታደሰ dw radio amharic

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *