“…የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከሬሳ ሳጥን ወጥተው ለጸጥታ ኃይሎቻቸው «ፌስቡክ እና ትዊተር በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ እፈልጋለሁ።» የሚል ትዕዛዝ ሲያስተላልፉ አሳይቷል። የኢትዮጵያ ምርጫዎች፤ ፖለቲከኞች ስለመገናኛ ብዙኃን የሰጧቸው አስተያየቶች ጭምር ጎድፍሬይ የተሳለቀባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው…”

Meles Zenawi, Facebook and Twitter.jpg

የአፍሪቃ ፖለቲከኞች እና የእድሜ ልክ መሪዎች ስግብግብ እና በሙሥና የተጨማለቁ አድርጎ የሚስላቸው ኬንያዊው ካርቱኒስት ጎድፍሬይ ምዋምፔምብዋ የታንዜንያው ፕሬዝዳንት ማጉፉሊ የጀመሩት እርምጃ እገዛ ያሻዋል ብሎ ያምናል።

http://m.dw.com/am/kenyan-cartoonist-gado-focus-africa-12112016-mp3-stereo/av-36364087
አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:36

Godfray.jpgምስል- ካርቱኒስት ጎድፍሬይ ምዋምፔምብዋ
ሰውየው አምና ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ በሙስና እና የሕዝብ ገንዘብ በሚያሸሹ ባለስልጣኖቻቸው ላይ ጦርነት ከፍተዋል። ሹማምንቶቻቸው ወደ ውጭ የሚያደርጓቸውን ጉዞዎች ቀንሰዋል። በሙስና ነቅዘዋል አሊያም የመንግሥት ተቋማትን ለመምራት ብቁ አይደሉም ያሏቸውን አባረዋል። ደጋፊዎቻቸው እነዚህን እርምጃዎች የአንድ ዓመት የሥልጣን ዘመናቸው ስኬቶቻቸው አድርገው ይቁጥሩላቸዋል። ጋዶ በሚል መጠሪያው የሚታወቀው ካርቱኒስት ጎድፍሬይ ምዋምፔምብዋ የፕሬዝዳንቱ እርምጃዎች ሊበረታቱ ይገባል ብሎ ያምናል።
«በእርግጠኝነት ምጉፉሊ ሙስናን በመዋጋት ረገድ እየሰሩት ያለው ሥራ ጥሩ ነው። ሊበረታታ ይገባል ብዬ አምናለሁ። ነገር ግን የጀመሩትን ጦርነት ለማሸነፍ የመገናኛ ብዙኃንን ነፃነት ሊያከብሩ እና ሕጋዊውን አካሔድ ሊከተሉ እንደሚገባም ልናስታውሳቸው ይገባል። የመናገር ነኛነት ሊከበር ይገባል። ሰውየው በነበሩት መሰረታዊ መብቶች ላይ ጫና ሲያሳድሩ እና ሲያሸማቅቁ ይስተዋላል። ይህ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው ብዬ አምናለሁ። በሙስና ላይ የከፈቱትን ጦርነት ለዘላቂው ማሸነፍ ከፈለጉ በታንዛኒያ ሐሳብን የመግለፅ እና የመገናኛ ብዙኃን ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል።»

ጎድፍሬይ በጥቁር እና ነጭ የሚሰራቸው ካርቱኖች የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒሥትር መለስ ዜናዊ እና ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የአፍሪቃ አምባገነኖችን እርምጃዎች ይተቻሉ። ጋዶ ካርቱን በተሰኘ ድረ-ገጹ በጎርጎሮሳዊው ግንቦት 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ለኅትመት በበቃው ሥራው የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከሬሳ ሳጥን ወጥተው ለጸጥታ ኃይሎቻቸው «ፌስቡክ እና ትዊተር በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ እፈልጋለሁ።» የሚል ትዕዛዝ ሲያስተላልፉ አሳይቷል። የኢትዮጵያ ምርጫዎች፤ ፖለቲከኞች ስለመገናኛ ብዙኃን የሰጧቸው አስተያየቶች ጭምር ጎድፍሬይ የተሳለቀባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው። በአፍሪቃ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘው ጎድፍሬይ የካርቱን ሰዓሊያን ፈገግታ ከማጫር እና ከመሳለቅ ያለፈ ሚና አላቸው ሲል ይናገራል።

Aging Leaders Screen shot 2012-11-01 at 2.35.06 PM.png

«እንደ ካርቱን ሰዓሊ ሰዎችን ታስተምራለህ፤ መረጃ ታቀብላለህ፤ ትሞግታለህ። በተለይ በሰዎች የየዕለት ሕይወት ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድሩ ፖለቲካዊ፤ኤኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ ጉዳዮች በሚበዛበት ቀጠና ሰዎችን በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ትቆሰቁሳለህ። ስለዚህ የካርቱን ሰዓሊያንን እንደ ቀልደኛ ብቻ ማሰብ ፍትኃዊ አይደለም።»

ጎድፍሬይ ለብሪታኒያው ኒው አፍሪቃን ለፈረንሳዩ ዓለም አቀፍ ኩሪየር እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የኅትመት ውጤቶች ሥራዎቹን በመደባኛነት ያቀርባል። በዝነኛው የፈረንሳይ ጋዜጣ ለሞንዴ እና የብሪታኒያው ዘ-ጋርዲያን ላይም የቀረቡለት ሥራዎች አሉት። በተለያዩ የኬንያ ቴሌቭዥን ጣቢያዎች ተከታታይ የስላቅ ዝግጅቶች አሉት። በአፍሪቃውያኑ ላይ ለሚያሸሙረው ጎድፍሬይ ሥራው ዳፋ ይዞ መምጣቱ ግን አልቀረም።

«በአገር ውስጥ በቅርቡ ከሰው ወደ ዝንጀሮ ወደ ኋላ በዝግመተ-ለውጥ እየተለወጠ ነው በሚል ካርቱን የተቸሁት አንድ ሚኒስትር እርምጃ እወስድብሃለሁ ብሎ አስፈራርቶኝ ነበር። እስካሁን የተፈጠረ ነገር የለም። ከኃይማኖተኛ የሴቶች ማሕበር ሥራዎቼን የሚወግዝ ኢ-ሜይል ደርሶኝ ያውቃል። ይህ ለእኔ የሥራዬ አንድ አካል ነው። እንዲህ ዓይነት ምላሽ ሊመጣ እንደሚችል ትጠብቃለህ። ሁልጊዜ ምሥጋና ብቻ ልትጠብቅ አትችል። እኔ ደግሞ በመተቸቴ ደስተኛ ነኝ።

በታንዛኒያዋ ዳሬሰላም ተወልዶ ያደገው ጋዶ የጀመረውን የአርክቴክቸር ትምህርት ከአንድ ዓመት በኋላ አቋርጦታል። በምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪቃ ግዙፍ የሆነውን የኔሽን ሚዲያ ግሩፕ ከመቀላቀሉ በፊት በዕለታዊዎቹ ዴይሊ ኒውስ፤ ቢዝነስ ታይምስ እና ዘ-ኤክስፕሬስ ጋዜጦች ላይ በካርቱኒስትነት ሰርቷል። «የእኔ ኃላፊነት እውነትን መናገር ነው።» የሚለው ካርቱኒስት ጎድፍሬይ ምዋምፔምብዋ በአገሩ ኬንያ የፕሬስ ፍሬደም ይዞታ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይገኛል የሚል ሥጋት አለው። በምፅታዊ ሥራዎቹ ከፍ ያለ ዝና ያተረፈው ጎድፍሬይ የኬንያ ፖለቲከኞች የመገናኛ ብዙኃንን ለመጨፍለቅ እየሞከሩ ነው የሚል ሥጋት አለው።

july-05-13-president-morsi-and-the-military-in-egypt

«ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከታዘብንው አኳያ ለመስራት አስቸጋሪ ቦታ እየሆነ ነው። መንግሥት ነፃ ፕሬስን እየተጫነ ነው። የነፃው ፕሬስ ባለፉት ዓመታት ያገኛቸውን ጥንካሬዎች ለማፍረስ መንግስት ድንጋጌዎችን ጨምሮ ሁሉንም አማራጮች እየተጠቀመ ነው። ይህ እጅግ አሳሳቢ ይመስለኛል። ምክንያቱም የነፃ ፕሬስ እንቅስቃሴን ስንመለከት ኬንያ ሁል ጊዜም በትክክለኛው ጎዳና የምትጓዝ አርዓያ ተደርጋ ትጠቀስ ነበር። በቀጣናው የሚገኙ ሌሎች አገሮች ኬንያን እንደምሳሌ ይጠቅሳሉ። አሁን ግን ያ ነፃነት በዝግታ ተነጥቆ ሲወሰድ እየተመለከትን ነው። ይህ ጉዳይ በቀጣናው በሚገኙ እንደ ታንዛኒያ፤ ዩጋንዳ ፤ ሩዋንዳ ትልቅ ችግር ነው። ብሩንዲን ብትመለከት ቀውስ ነው። በቀጣናው ያለው ሁኔታ እንዲህ ዓይነት ነው። እኔ ሐሳብ የመግለፅ ነፃነት ሊጠበቅ ይገባል ብዬ አምናለሁ። ይህ መብት ቀጣናው እንዲያድግ፤ ቀጣናው እንዲለማ ይረዳል ብዬ አምናለሁ። ሙስናን በስኬታማነት መዋጋት የምትችለው ነፃ ፕሬስ ሲኖር ነው። ፕሬስን የመሰለ የቁጥጥር ሥርዓት ሲኖር የሕግ የበላይነት ሊከበር ይችላል። በቀጣናው የነፃ ፕሬስ መኖር እጅጉን አስፈላጊ ነው። ልንጠብቀውም ይገባል።»

እሸቴ በቀለ    አዜብ ታደሰ  http://m.dw.com/

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *