አርበኞች ግንቦት ሰባት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ጥቃት እያካሄደ መሆኑንን በኢሳት በኩል ገልጿል። በሌላ በኩል ጠ/ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በአገሪቱ አንጻራዊ ሰላም በመስፈኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሊነሳ እንደሚችል ተናገሩ።

ዜናው የግንባሩን የሰሜን ጎንደር አስተባባሪን ጠቅሶ እንደዘገበው አባሎቻቸው በሰሜን ጎንደር በተለያዩ አካባቢዎች ለወራት ሲደራጁና ሲያደራጁ ከቆዩ በሁዋላ፣ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ወታደራዊ ጥቃት በመፈጸም ላይ ናቸው። በተለይ ከትናንት ጀምሮ በቃፍታ ሁመራ እና በአከር አካባቢ ከፍተኛ ውጊያ እያካሄደ ነው። ሙሉ ዘገባው የሚከተለው ነው።
አደንድን በሚባል አካባቢ ባለፈው ሳምንት በተደረገው ጦርነት 48 የአገዛዙ ወታደሮች መገደላቸውን የገለጹት አስተባባሪው፣ ከትናንት ጀምሮ በመካሄድ ላይ ያለው ጦርነት በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑንና አንድ የጸረ ሽምቅ ሃላፊ መገደሉን ገልጸዋል። ሃይላቸው ወደ መሃል አገር ለመግባት እየታገለ መሆኑንም ተናግረዋል።
ራሳቸውን በጎበዝ አለቆች አደራጅተው በረሃ ወርደው ሲታገሉ የነበሩትን በማሰባሰብ እና ድጋፍ በማድረግ ወደ አንድነት እንዲመጡ ማድረጋቸውን የገለጹት አስተባባሪው፣ አገሩን ነጻ ለማውጣት የሚፈልግ ሃይል ሁሉ በማንኛውም ጊዜ መጥቶ ሊቀላቀላቸው እንደሚችል ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር ከምሽቱ 1 ሰአት ላይ በደረሰን መረጃ ደግሞ በሁለቱ ሃይሎች መካከል ከፍተኛ ጦርነት ሲካሄድ ከዋለ በሁዋላ፣ አርበኞቹ ከርሰሌት በሚባለው ቦታ ላይ የሚገኘውን አደባይ ተራራን መቆጣጠራቸውን ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል። የመጀመሪያው ጥቃት በአዲ ጎሹና ሁመራ መካከል በምትገኘው እንድሪስ አካባቢ መፈጸሙ የታወቀ ሲሆን፣ በእዚሁ አካባቢ በነበሩ የገዢው ፓርቲ ወታደሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል። ከአርበኞች ግንቦት 7 በኩል 3 ሰዎች መስዋት መሆናቸውንም ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ከሰአት በሁዋላ በ52 መኪኖች የተጫኑ ወታደሮች በሽሬ ፣አድርቃይ፣ ማይጸብሪ፣ ጸለምት አድርገው ታጋዮችን ለመግጠም የተንቀሳቀሱ ሲሆን፣ በዳንሻ አካባቢም በ8 መኪኖች የተጫኑ ወታደሮቸ ሰፍረዋል። ታጋዮቹ ወደ ጠገዴ፣ አርማጭሆ ፣ ቆላ ወገራና ሌሎችም አካባቢዎች ሰንጥቀው ከገቡ ከህዝብ ጋር በመቀላቀል ወደ መሃል ይገሰግሳሉ የሚል ስጋት የገባው አገዛዙ፣ ለትግራይ አካባቢ ህዝብና ሚሊሺዎች “ አርበኞች ግንቦት7 መጥቷልና ራሳችሁን አድኑ “ በማለት ሲቀሰቅስ፣ ለአማራ ተወላጆች ደግሞ “ሽፍቶች ገብተዋል”ና ተነሱ እያለ ነው። በገዢው ፓርቲ በኩል እስካሁን የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ የለም።

Related stories   የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ህወሓት” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ ወሰነ

በተመሳሳይ ቀን ጠቅላይ ሚንስትሩ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ አምባሳደሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ስለወቅታዊው የሀገሪቱ ሁኔታ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሊነሳ እንደሚችል መጠቆማቸውን የዘገበው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኤጀንሲ ነው። ኢቢስ አቶ ሃይለማርያምን ጠቅሶ የሚከተለውን ዘግቧል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሊነሳ ይችላል፡- ጠ/ሚ/ር ኃይለማርያም
ህዳር 8፣ 2009

አሁን በሀገሪቱ የተፈጠረው ሠላምና ጸጥታ በዚሁ ከቀጠለ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሊነሳ እንደሚችል ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ አስታወቁ፡፡

Related stories   እንግሊዝ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እቅዷን ይፋ አደረገች፤ ዶክተር ዳንኤል የማይካድራን ጂኖሳይድ ዝም ማለቱ ክህደት ነው

በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሁከት ተሳትፈው ከነበሩ ግለሰቦች መካከል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት ትምህርት ተሰጥቷቸው ምህረት እንደተደረገላቸው ጠቅላይ ሚንስትሩ አስታውቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ አምባሳደሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ስለወቅታዊው የሀገሪቱ ሁኔታ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካበቢዎች ተከስቶ የነበረውን አለመረጋጋት በመደበኛ የህግ ማስከበር ሥርዓት ለማስተካከል ባለመቻሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፡፡ አዋጁም በተወሰኑ የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ፖለቲካዊ መብቶች ላይ ገደብ መጣሉ ይታወሳል፡፡ አዋጁ ከታወጀ ከመጀመሪያ ቀን ጀምሮ ሀገሪቱ እየተረጋጋች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

Related stories   አፍሪካ ህብረት ቁርጠኛነቱን አሳይቷል፤ አውሮፓ ህብረት ምርጫ አልታዘብም አለ

በሁከትና ብጥብጥ ተግባር በቁጥጥ ስር ውለው ከነበሩት ግለሰቦች መካከል አብዛኛዎቹን የማስተማርና ወደ ህብረተሰቡ የመቀላቀል ስራ መሰራቱንም ተናግረዋል፡፡ በህግ የሚጠየቁ ግለሰቦች ጉዳይ ተለይቶ ወደ ፍርድ ቤት መላኩን ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ አስታውቀዋል፡፡ የጠቅላይ ሚንስትሩን ማብራሪያ ተከትሎ ከዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ጥያቄና አስተያየቶች ቀርበው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ሞገስ መኮንን EBC

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *