የሰንበት ወግ

…አድማ፣ ባድመ፣ አኬልዳማ፣ ውሃ ማቆር፣ ወደፊት ፣ ወደ ሁዋላ፣ ግብርና መር፣ ውጤት ተኮር፣ ግምገማ፣ ውስወሳ፣ ጥርነፋ፣ ጎጥ፣ ማተራመስ፣ ማደናበር፣ ቆረጣ፣ አርበኛ፣ ማዕበል፣ ታሪክ ሰሪ፣ ታሪክ አዳሽ፣ አሸባሪ፣ ተሸባሪ፣ አቀነባባሪ፣ ያለምንም ደም..፣ተነሳ ተራ.መድ፣ ቦንድ፣ ግንድ፣ ህዳሴ፣ ውዳሴ፣መታደስ፣ ጥልቅ ተሃድሶ… ……….ተጋድሎ፣ ስድብ፣ አብዮት፣ አክቲቪስት፣ ነፍጠኛ፣ ጠባብ፣ … .ያበደው መፈክር ጠሩ ነው…

ያበደው መናገር የሚፈልገው የህይወቱን ስንጣሪ ነው። ያበደው ለምን እንዳበደ ለሚጠይቁት ምንም መልስ የለውም። ያበደበትን ምክንያትም አያውቀውም። ግን አብዷል። በማበዱ አያዝንም። ደስተኛ ነው። ስለማበዱ ከንፈር የሚመጡለትን አጥብቆ ይጠላል። ጤነኞች ስለማይመስሉት!! እብድ አሰዳቢዎችን ይረግማል። አማኑኤል ሆስፒታል እየኖሩ “ከሚቀለቡት” እብዶች መካከል አብዛኞቹ የብሄር ፖለቲካ መጋኛ የመታቸው ናቸው ብሎ ስለሚያምን አያከብራቸውም። ሩቅ ሆነው በብሄር ቫይረስ የተነደፉት ይጸየፋቸዋል። ደም ዘሪዎች፣ የአገርና የትውልድ ውርጃዎች ይላቸዋል።

ያበደው አኗኗሪና አጋር የሚላት የትዳር ጓደኛ አለችው። ትዳር በመፈቃቀድ እየተካፈሉ መኖር እንጂ ውስብስብ ግንኙነት ስላልሆነ ማካበድ አይወድም። ፍቅርም ቢሆን ሰዎች ሲፈጠሩ የተሰጣቸው ነጻ ስጦታ እንጂ የራሳቸው ግኝት አይደለም ብሎ ያምናል። “ሰው”እነሱ አልጠቀምበት ሲሉ ተኖ የሚያልቅ በረከት እንጂ ታግለው የሚጎናጸፉት ባለመሆኑ ለማፍቀር ታምኖ መኖር በቂ ነው ባይ ነው። ብዙ ውዝግብ አይወድም። ሰው የፈለገውን ለመሆን ፈቃድ ሊጠይቅ አይገባውም ከሚሉት ወገን ነው። እንደውም የሰው ልጆችን ፍላጎት የሚገቱ ህጎች “እንዲወድሙ”ይመኛል። የአኗኗሪው ስም ቦሰና ይባላል። ቦሰናን ሲያስተዋውቅ “አኗኗሪዋ ነኝ” በማለት ነው። በቃ!!ቦሰና ጠባብ፣ አክራሪ፣ ዘር፣ ጎሳ፣… አታውቅም። ጽድት ያለች የፍቅር ምሶሶ ናት። ፍቅር ስትሰጥም ሃይለኛ ናት። ነገር አለሙን ታስረሳለች።

Related stories   ብርሃኑ ነጋ አቋማቸውን ቀየሩ፤ ኢዜማ ደርግ በግፍ የዘረፈውን የግል ሃብት ለተከራይ እንደሚሸጥ ይፋ አደረገ፤ የኢዜማ የ ” ፍትህ” ሩጫ

ደጎል ውሻው ነው። ያበደውና ደጎል ከፍቅራቸው የተነሳ በጥቅሻ ይግባባሉ። ደጎል ህልሙን ሳይቀር ልክ እንደሰው ይተርክለታል።ለፍቺው ቦሰና ትቀርባለች። ደጎል አሜሪካን ኤምባሲን ተቆጣጥሮ ስለሰራው ጀብድ ያጫወተውን ያበደው አይረሳውም። ለሊቱን ሙሉ ውሾች ስሪያ ሲያድሩ እሱ አሜሪካን ኤንባሲን ተቆጣጠሮ ነበር። ጊዜውን ጠብቆ ይተርካዋል። በነገራችን ላይ ስሪያ በየቦታው ነው። በውድቅት ለሊት መንገድ ላይ መገበያየት እዚህም አለ። እዚህ የሰለጠኑት አገር ውስጥ ወገን ወገኑን ይገበያያል። ያበደው መስመር ሳተ። ቸኮለ።

ያበደው በህይወት ዘመኑ ሊመለከታት የማይወዳት እንስሳ ድመት ነች። ያበደው ድመት አይወድም። ድመት ሲመለከት ቆዳው ይቆማል። ሰውነቱን ይወረዋል። አፉን ምራቅ ይሞላውና ሽቅብ፣ ሽቅብ ይለዋል። እድሜ ለጊዜ አሁን ግን ድመትን መሸሸ የማይችልበት ቦታ ነው። በጀት የሚመደብላቸው ድመቶች ከነሙሉ መብታቸው ይቀልዱበታል። ሊተሻሹት የሞክርሉ። ጉድ ነው !!ኑሮን እንደ ወረደ ሲቀበሉት የሚጠሉትን ባይወዱም መወደድ ግድ ነው። ለነገሩ የእኛ አገር ፓለቲከኞችም እንዲሁ ናቸው። ያልሆኑትን፣ ያላደረጉትን፣ እየቀባጠሩ ” ውደዱን” ይላሉ። በተቃዋሚ ” አውራ ፓርቲ” አመራሮች ዘንድ ያለው ይብሳል መሰለኝ። ለጊዜው ያበደው ዳታ ስላልሰበሰበ በዚህ ጉዳይ አይከራከርም። ግን ሕዝብ በውስጥና በውጭ አምባገነኖች መወጠሩን ያለጥርጥር ያምናል። ሞጋች ካለ አይፈራም።

ድሬደዋ 1985 ዓ ም ከጠዋቱ 5 ሰአት ግድም የአንድ ሰው መኖሪያ ቤት በሰዎች ተከቦ ይታያል። ያበደው ስለሁኔታው ለማወቅ ተጠጋ። ቤቱ ተሰብሮ ሲገባ የቤቱ ባለቤት ህይወቱ በራ ወደ መጣችበት ተመልሳ ኖሮ በድን ሆኗል። ወ/ሮ ስርጉት እያለቀሱ ይራገሙ ጀመር።ያበደው ርግማኑን ካየው ጉድ ጋር አዋህዶ ድመት ጠላ። ነገሩ እንዲህ ነው።

Related stories   አስከሬን እንዲለቀም ታዘዘ - ትህነግ የአጽም ፖለትካ ድራማ ይፋ ሆነ

ሟች በመጠጥ የተለከፈ ነበር። ዘወትር ይጋታል፤ ይሰክራል። ሰክሮ እየተንገዳገደም ለድመቱ ስጋ ሳይዝ ቤቱ ገብቶ አያውቅም። አራት ልጆች ያፈራቸው ድመት እንደወትሮው ስጋ ተገዝቶላት ማታ ራቷን ከልጆቿ ጋር በልታለች። ምስክርም አለ። በቅምጥል ስለመኖሯ ጎረቤቶች ሲያሙ “አይጦቹ የሚደበቁት እሱ ቤት ነው። የሱ ድመት እንደሆነ ያለ ስጋ አትነካም። አይጥ ትጠየፋለች። ይሄ ሰካራም ሚስቱ ያደረጋት ይመስላል..”እያሉ ነው። እኛ እኮ ለማማት የተፈጠርን እኮ ነው የምንመስለው። “ሚስቱ ያደረጋት ይመስል”እያሉ በድመትም ያሙታል።……..እንደዚህ በንክብካቤ የተያዘች ድመት ማታ ቤቱ የደንቡን ይዞ ገብቶ እንደተኛ ያሸለበውን አሳዳሪዋን አጅሪት ከግልገሎቿ ጋር በመሆን ነግቶ በሩ እስኪከፈት ድረስ ሰፈረችበት። ከጆሮው ጀምረው ይከረክሙት ጀመር……

ያበደው ሌላም ታሪክ ያውቃል። ድመት ወልዳ ትበላለች። ወልደው የሚበሉ ሰዎችም አሉ። ወልዶ መጣል፣ ሳይወልድ ማስገደል፣ በሌሎች ቤተሰቦች ላይ ፈርደው ልጆችን የሚያሰቃዩ… ያበደው አመመው። በሆዱ ተራገመ። ፍርድን ጠየቀባቸው። ወደ ድመቲቱ / የወለደችውን አምጣ እንዳበቃች ትሰለቅጣለች። ለመብላት እየጎመጀች ታምጣለች። ያበላት ላይ ተንጠልጥላ ቆዳ ትገፋለች። ያበደው ድመት የሚጠየፈው ወዶ አይደለም። ሰው እንዴት ከድመት ጋር ህብረት ይኖረዋል? ብሎ ይጠይቃል። ለዓመታት ድመት ሲሸሽ ኖሮ ቤቱ ገባች፤ ሳይወድ በግዱ “ፒስ” ሲል ሰየማት። አወሮፓ!! ዶሮ ማነቂያ አቶ ኩማ ድሪባ ቢሮ ፊት ለፊት በሚኖርበት ወዶ ገብ ቤቱ አይጥ ተጨማሪ የኑሮ ሁከት ሆነበት ሰላሙን በድመት ያገኘውን ጓደኛውን አሰበና የድመትን ውለታ የሚቆጥሩ ታወሱት። የሚበላው ያጣ ድመት እንኳን አይጥ የራሱን ልጅ ይበላ የለ!!

Related stories   መከላከያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ “ጁንታውን” ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን አስታወቀ! በርካታ በቁጥጥር ስር ውለዋል

ያበደው ወዶ ገብ ስለሆነበት ቤቱ ብዙ ታሪክ ለማውጋት ቃል ይገባል። በድመት አምሳያ የተፈጠሩ አውሬዎች እንዳሉ ያውቃል።ያበላቸውን የሚቧጥጡ፣ ያሳደገቻቸውን አገር የሚቆራርሱ፣ እናታቸውን መልሰው የሚበሉ፣ የሚገፉ፣ የሚያዋርዱ፣ የልጅ ልጆቻቸውን አልመው የሚቀነድቡ፣ የሚዘርፉ….”የናት አገራቸው የእንግዴ ልጆች…”

ሳትማር የተማረችው ቦሰና ማብራሪያዋ መሬት ጠብ አይልም። አዕምሮዋ ይመትራል። “በመሃይም አንደበቴ” እያለች ፖለቲካውን ትበልታለች። ፖለቲከኞችን ” ጅቦች” ትላቸዋልች። አዎ ትውልድን ከሚበሉ የዘመኑ ጅቦች ጋር እየተኖረ ነው። ያበደው ፍልስፍና ጀመረ። አዎ ጅቦች አለ። ጅብ እንኳን … ያበደው ሊያውዳድር አስቦ ተወው። “ተንስ፣ ተነስ፣…” ቀረርቶ፣ ባዶ.… ባዶ ተስፋ። ቻርተር፣ የሽግግር ጊዜ፣ የሽግግር መንግስት፣ አገርህን አድን፣ ውህደት፣ ፍቺ፣ ቀለበት፣ ምህላ፣ የርስ በርስ ትርምስ… ያበደው ቆሽቱ ሸተተው… በሌለ ነገር መባላት!!

ያበደው ግሩፕና የቡድን ፍረጃ አጥብቆ ይጠላል። አድማ፣ ባድመ፣ አኬልዳማ፣ ውሃ ማቆር፣ ወደፊት ፣ ወደ ሁዋላ፣ ግብርና መር፣ ውጤት ተኮር፣ ግምገማ፣ ውስወሳ፣ ጥርነፋ፣ ጎጥ፣ ማተራመስ፣ ማደናበር፣ ቆረጣ፣ አርበኛ፣ ማዕበል፣ ታሪክ ሰሪ፣ ታሪክ አዳሽ፣ አሸባሪ፣ ተሸባሪ፣ አቀነባባሪ፣ ያለምንም ደም..፣ተነሳ ተራ.መድ፣ ቦንድ፣ ግንድ፣ ህዳሴ፣ ውዳሴ፣መታደስ፣ ጥልቅ ተሃድሶ… ………..ያበደው መፈክር ጠሩ ነው። ለትውውቅ ያህል ነው። ሰላም ሁኑ! ሰላም ክረሙ! ሰላም፣ ሻሎም፣ ሰናይ ሳምንት። ያበደው በሳምንት እሁድ የእሁድ ወግ ያቀርባል። እሁድን ከ-ያበደው ጋር

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *