Skip to content

“ከኢትዮጵያ ጋር ትብብር ለማድረግ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎች እየተከበሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንፈልጋለን” የካናዳ ው/ጉ/ሚ

የካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስቴፈን ዲዮን ከሰሃራ በታች ወዳሉ አገሮች ኦፊሴላዊ ጉብኝት ሲያደርጉ የመጀመርያቸው ነው፡፡ በናይጄሪያና በኬኒያ ያደረጉትን ጉብኝት አዲስ አበባ ላይ የቋጩት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ፣ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ከአዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁና ከሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው ተነጋግረዋል፡፡

ጉብኝቱን አስመልክተው በካናዳ ኤምባሲ የሰጡት መግለጫ እንደሚያመለክተው፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ፣ በአፍሪካ ቀንድ ስላለው የፀጥታና የፖለቲካ ሁኔታ፣ እንዲሁም በሁለትዮሽ የኢኮኖሚ ትብብር ላይ አንዳንድ ጉዳዮችን አንስተው ምክክር አድርገዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስቴፈን ዲዮን፣ በተለይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምና ከውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር ባደረጉት ሰፋ ያለ ውይይት ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ውስጥ ተከስቶ ስለነበረው ሁከት፣ ችግሩ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይወጣ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተመለከተ መነጋገራቸውን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በተፈጠረው ሁከት ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች ሐዘናቸው የገለጹ ሲሆን፣ አገሪቱ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በምታደርገው ጥረት ከአገራቸው ካናዳ የሚጠበቀውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡ አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎች ግን ያስቀመጡ ይመስላል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር በነበራቸው ቆይታ በቅርቡ በኢትዮጵያ ስለታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ አዋጁን እያስፈጸመ ስላለው ኮማንድ ፖስት፣ እንዲሁም የአዋጁን አፈጻጸም በተመለከተ በዝርዝር መነጋገራቸው የታወቀ ሲሆን፣ በተለይ ሁለት ጉዳዮች ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

Related stories   አለቃ አጽመ ጊዮርጊስ – የተሳሳተውን የውጫሌ ውል የመረመሩ ጀግና ኢትዮጵያዊ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ያነሱቸው ነጥቦች ችግሩን ለመፍታት መንግሥት እየወሰደ ስላለው ዕርምጃ ነው፡፡ ችግሩን በተመለከተ ከሞላ ጎደል ኢትዮጵያውያንን ያካተተ ሰፊ ሰላማዊ ውይይት እንዲካሄድና ባለድርሻ አካላት በሙሉ ተሳታፊ እንዲሆኑ ካነሱቸው ነጥቦች የመጀመሪያው ነው፡፡ በዚህ ውይይት በተለይ ወጣቶች ልዩ ትኩረት እንዲያገኙ አጽንኦት ሰጥተውበታል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በውይይት ተሳትፎ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ሊያካሂዳቸው ያሰባቸውን ማሻሻያዎች በተመለከተም በተለይ የወጣቶችን ተሳትፎ ከፍ የሚያደርጉና ፋይዳ እንዲኖራቸው ጠይቀዋል፡፡

የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት መሪ ድርጅቱ ኢሕአዴግ በጥልቀት ከመታደስ አንስቶ፣ በመንግሥት ደረጃ የተለያዩ አሳሪ የተባሉ ሕጎችን ለማየትና የሕገ መንግሥቱን አንቀጾች ጭምር ለማሻሻል ቃል ገብቷል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስቴፈን ዲዮን ማሻሻያዎቹን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ በሚጠቅም መንገድና ወቅቱን ያገናዘበ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡

‹‹ባደረግናቸው ውይይቶች ሕዝቡ በሚደረጉ የዴሞክራሲ ውይይቶች ተሳታፊ እንዲሆንና ገንቢ ማሻሻያ እንደሚያስፈልግ እምነቴን ገልጫለሁ፤›› ብለዋል፡፡

በካናዳ ኤምባሲ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ከጋዜጠኞች ለቀረቡባቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ፣ ጉብኝቱ በተለይ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የፖለቲካ አለመረጋጋት ለማሻሻል ካናዳ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ በመሥራት መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ በተለይ በሶማሊያና በደቡብ ሱዳን ስለሚሰማሩ የሰላም አስከባሪ ኃይሎች በጋራ ለመሥራት ማሰባቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹በሰላምና በፀጥታ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ መሥራት እንፈልጋለን፤›› በማለት፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ብሎም በአፍሪካ ሰላምን በማስከበር ወደር የሌላት አገር በመሆኗም አገራቸው በጋራ ለመሥራት እንደምትገደድ አስረድተዋል፡፡

Related stories   አለቃ አጽመ ጊዮርጊስ – የተሳሳተውን የውጫሌ ውል የመረመሩ ጀግና ኢትዮጵያዊ

የአካባቢውን ሰላም፣ መረጋጋትና የኢትዮጵያን የውስጥ ጉዳይ በተመለከተ በተለይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር ባደረጉት ውይይት የሴቶችና የወጣቶችን እኩል ተጠቃሚነት፣ የውኃ አጠቃቀም፣ የሥራ ፈጠራ፣ የቴክኖሎጂ፣ የማዕድን ፍለጋ፣ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ከምትተባበርባቸው መካከል ግንባር ቀደም መሆናቸውን በመግለጫቸው ወቅት አብራርተዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በወሳኝ የፖለቲካና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ላይ አጽንኦት ሰጥተው መክረዋል፡፡ በተለይ ደግሞ የጋዜጠኞች፣ የጦማሪያንና የተቃዋሚዎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብታቸው እንዲከበር ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም መነጋገራቸውን አስረድተዋል፡፡

‹‹ከኢትዮጵያ ጋር ትብብር ለማድረግ እነዚህ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎች በውል እየተከበሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንፈልጋለን፤›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተገኘውን ልማትና ዕድገት ለማስቀጠል ካናዳ የበኩሏን እንደምታደርግ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ‹‹የሕዝቡ ነፃነት የበለጠ በተከበረ ቁጥር ልማቱ የበለጠ ይጨምራል፤›› ብለዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከዴሞክራሲ ግንባታ ጋር በተያያዘ ያነሱዋቸውን ሥጋቶችና የሰጡዋቸውን አስተያየቶች በተመለከተ፣ ከአንዳንድ የሲቪክ ማኅበረሰቦች ጋር ባደረጉት ጥልቅ ውይይት ማንሳታቸውንም ማወቅ ተችሏል፡፡

Related stories   አለቃ አጽመ ጊዮርጊስ – የተሳሳተውን የውጫሌ ውል የመረመሩ ጀግና ኢትዮጵያዊ

በተለይ ደግሞ የዴሞክራሲውን ምኅዳር ማስፋት፣ የሐሳብ ነፃነትን ማክበርና የሰዎች መሠረታዊ ነፃነቶች መጠበቅ ለሚታሰበው የፖለቲካ ውይይት ጠቃሚ ቅድመ ሁኔታዎች መሆናቸውን መግለጫቸው ያትታል፡፡

በአካባቢው ሰላምና ደኅንነት፣ በሽብርተኝነት፣ በንግድና በኢንቨስትመንትና በመሳሰሉት ኢትዮጵያ ከካናዳ ጋር ያላት ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ለሚኒስትሩ እንደገለጹላቸው በመንግሥት ሚዲያዎች የተዘገበ ሲሆን፣ ከዴሞክራሲና ከሰብዓዊ መብቶች ጋር ተያይዞ ከሚኒስትሩ ስለተነሱ ሥጋቶች የኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ ምን እንደሆነ ማወቅ አልተቻለም፡፡

የሁለቱ አገሮች ግንኙነት እ.ኤ.አ. ከ1956 የሚጀምር ነው፡፡ ካናዳ ኢትዮጵያን ከሚረዱ ግንባር ቀደም ለጋሽ አገሮች መካከል ነች፡፡ ካናዳ በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን የከፈተችው እ.ኤ.አ. በ1957 ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በካናዳ ኤምባሲዋን እ.ኤ.አ. በ1962 ከፍታለች፡፡ እ.ኤ.አ በ2007 ካናዳ ለኢትዮጵያ የሰጠችው ዕርዳታ 90.52 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ይህ ዕርዳታ ከኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ዕርዳታ ሰጪዎች አራተኛዋ አገር ያደርጋታል፡፡

እንዲሁም ደግሞ ከኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ግጭት በኋላ፣ በሁለቱ አገሮች ድንበር ከተሰማሩት የተመድ የሰላም አስከባሪ ወታደሮች መካከል 450 ያህሉ የካናዳ ወታደሮች እንደነበሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

source reporter 16 Nov, 2016

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Copyright - zaggolenews. All rights reserved.

Read previous post:
“የሰው ልጆች ጥላቻን ለመሸከም አይመጥኑም”

ኦባንግ፦አቶ መለስ ህወሓትን ከፊት አድርገው አዲስ አበባ ሲገቡ እውነተኛ ብሔራዊ እርቅ አድርገው ቢሆን ኖሮ ዛሬ ተገፍተን በስደት ያለን ሁላችን በየሙያችን...

Close