የዛሬ ዓመት በዚህ ሳምንት፣ የሰማይ ኩስ ድፍን ሳር ቅጠሉ ነጭ አድርጎታል። የቅዝቃዜው መጠን አይታወቅም። ሰማይና ምድር በበረዶ ተጣብቀዋል። ፍጡራን ጭራሹኑ የሉም። ጸጥ ረጭ …. ብቻ ሰማይ እዳሪውን ያለማቋረጥ ይለቀዋል። በረዶ እንደ ባዘቶ ጥጥ በውሽንፍር ተመስሎ እየበነነ ይነሰሰነሳል። አንዳንዴም ይጋረፋል። ሲኦል ለምን በእሳት ተመሰለ ያሰኛል። በደፈናው የቅዝቃዜ እቶን ነው። ክፉ ቀን ነበር። ማስታውስ የሚቻለው ከሞት በፊት ያለውን ብቻ ነው። ኦፕላንድ ፣ ዎላ የስደተኞች መጠለያ!! ተራራ ላይ የተሞሸረ ማቀዝቀዣ!!

ሰላም ሻሎም … ያበድው ለሁሉም ሰላምታ አለው። ግን ለሰላምታ እንዲያመች በብሄር ብትደራጁ ደስተኛ ነው። በፌስ ቡክ “የነጻነት አርበኞች” ለናንተም ሰላም። ከድል በሁዋላ ቢያንስ በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ” የጥቃቅን ጉዳዮች ሃላፊ ሚኒስትር” እንድታደርጉት ያበደው ከወዲሁ አደራ ይላል። “መከሩ ጥቂት ሰራተኛው ብዙ” አለ መጣፉ!! ያበደው እየተቅለሰለሱ” ሰላም ይብዛላቹህ” የሚሉትን ያልፋቸዋል። ሳኡዲን አስቦክተው ለተመለሱት፣ 20 የመዝናኛ አውሮፐላኖችን ላገቱት ሃይለማርያምም አሻም!! ያበደው ሰው ረሳ ” አብዮታዊ ይሁን ጀሃዳዊ” በውል ለማይታወቀው አዲሱ መሪ ጁሃር መሃመድ በገ ጅርቱ !! ለአርበኛ ብርሃኑም ሰላም!! ማን ቀረ?? ራሱ ፈጣሪ፣ ሁሉን ቻይ !! ከሞት ወደ ህይወት የመለሰ!! ያበደው ከጌታው ጋር የሚግባቡት በከንፈር አይደለም።3653823749_2776862a

ያበደው ባለመሞቱ ማስታወሻውን መከተብ ቻለ። እናንተዬ በረዶ ወረደ ብሎ መጨፈር ምን ማለት ይሆን? ያበደው በረዶን የሰማይ ኩስ ይለዋል። የሰማይ እዳሪ ይለዋል። እዚህ አውሮጳ ያበደው በተዛወረባቸው አገሮች  ምድር አረንጓዴ ለብሳ አይቷል። ውሃ ኩል መስሎ  ሲንጣለል አስተውሏል። ይህንን ውበት ሊያከስል በረዶ ኩስ ሆኖ ሲመጣ ጭፈራ… ያን የመሰለ እርንጓዴ ምድርና ደን አክስሎ ጸያፍ የሚያደርገውን የሰማይ ኩስ ማምለክ… ስለ አረንጓዴ ምድር ሲነሳ ያበደው ያቅለሸልሸዋል። ሳይኖረን በመዝሙር መኖራችንን ያበደው ይረግማል። ” ለምለም መስክሽ፣ ተራራሽ፣ አየርሽ፣ ሸንተረርሽ… ሲባል ያበደው ተፈጥሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ያለ ይመስለው ነበር። ያበደው ተናደደ “በመፋክርና በመዝሙር መኖር” አለና ምራቁን ተፋ። በባዶ ቂጥ ጉራ!! አገሩ አልወቀሰም። ቦሰና ” አገሪቱ ምን ታድርግ” ትላለች። እውነቷን ነው። ያ ሁሉ ወንዝ እያለ ውሃ ይጠማናል። ወንዝ የሚያስጠልፍልን መሪ አጥተን በቆሎ አሮብናል። በቀን ሶስቴ መብላት ቀርቶብን አንዴውም ቅንጦት ሆኖብናል። ረሃብ መሳቂያና ማልቀሻ አድርጎናል። ችጋር ቤቱን ገንብቶብን በሄድንበት “ረሃብተኛ” እንባላለን… ያበደው አለቀሰ። ከዚህ በሽታ ተረዳድተን እንዳንወጣ የራበው ገበሬ፣ የራበው ወንድሙን ገበሬ ጨቆነ እያልን እናላዝናለን። ኤጭ!!

ከእግዜሩ ቀጥላ ኢትዮጵያ ሁሉን ቻይ ናት። መሪዎቿና አዋቂዎቿ ሳይጨምሩላት ያላትን እየቆረጠሙ እዚህ አደረሷት። ራቁት አደረጓት። ሌሎች ከባዶ ተነስተው ሲመነጠቁ እኛ ያለንን እያወደምን እንፎክራለን። መሪ አልባ አገር። ያበደው ተቆጣ። አፉ ምራቅ አኮረፈ። አዎ እውነት ነው። መሪ የሌላት አገር። መሪ ያጣ ህዝብ። መምረጥ ያልቻለ ህዝብ። የመምረጥና የመሻር መብቱን ለዘመናት የተገፈፈ ህዝብ…. የተደፈረ ህዝብ፣ በባርነት የተያዘ ህዝብ፣ በማያውቃቸውና ባልመረጣቸው የሚመራ፣ ያበደው ጮኸ። ” ምንድን ነው የጎደለን” ሲል ጠየቀ… መልስ የሚሰጥ የለም። ከደም የምንጸዳው መቼ ይሆን?? ያበደው ጠየቀ። ደጎልን አየው። ደጎል ያበደው ሲናደድ ይገባዋል። “ ጌታው ሲናደድ “ አየና አይኑን ከፈት ዘጋ እያደረገ ጭራውን ቆላ። የለሆሳስ ድምጽ እያሰማ…

ያበደው ማስታወሻውን አየ። የዛሬ ዓመት እንዲህ ብሎ ጽፎ ነበር “ ሰው መኖር ያለበት አምላኩ እንዲኖር በፈጠረው ቦታ ብቻ ነው “ በዛ ቅዝቃዜ ያለ ከብርድ ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ለብሶች ደርቶ ወደ ከተማ ለመውጣት ጋራ ላይ ከተተከለው መጠለያ ወረደ። አውቶቡስ ለማገኘት ቁልቁል 15 ደቂቃ ያስኬዳል። መንገዱ በረዶ ሞለቷል። ብርዱ ከታች ሽቅብ እየተነሳ ላንቃ ያደነዝዛል። አፍንጫ ያቆረዝዛል። ፊት እንደ እሳት ያቃጥላል። ጆሮ ፍጥረቱም አኞ ነገር ስለሆነ እንደ ሸክላ ይደርቃል። ጓንት ዘልቆ የሚገባው ቅዝቃዜ ጣቶችን ለይቶ ይገላቸዋል።

ያበደው ቁለቁለቱን ጨርሶ አውቶቡስ ማቆሚያ ደረሰ። አውቶቡስ የምትመጣው በየሁለት ሰዓት በመሆኑ 45 ደቂቃ መጠበቅ ግድ ነበር። መብራት አብርተው ውሽንፍራማውን በረዶ እየቀደዱ የሚሮጡ ውስን መኪናዎች ብቻ አልፎ አልፎ ውልብ ይላሉ። ከዚያ ውጪ የሚሆን ነገር አልነበረም። ሁሉም ነገር ሙት ነው። ፈጡራን ስራ ላይ ያሉ አይመስልም።  ያበደው እንቀስቃሴ አቁሞ አውቶቡስ ሲጠብቅ ቆፈኑ ቀስ እያለ ልቡን ነሳው። አይኑ ማየት ደከመው። ጣቶቹ ቀስ በቀስ እየደረቁ በድን ሆኑ። የአውቶቡሷ መምጣት የምጽአት ያህል ሆነበት። የእግሩ ጣቶች እየሞቱ ስሜት አልባ ሆኑ። ቀስ እያሉ እንቀሰቃሴ አቆሙ። ራሱን ወረረው። ምንም ነገር አስቦ የማድረግ አቅም ከዳው። ከንፈሮቹ ደርቀው መንቀሳቀስ አቁመዋል። ወገቡን ይሰማው የነበረው ስሜት ጠፋ… በየደረጃው ያበደውን በረዶ በላው። አሁን አውቶቡስ መጣች። ለመራመድ ሲሞክር አቃተው። እግሮቹ ጉድጓድ ውስጥ ገብተው የተጠቀጠቁበት መሰለው። የህልም ያህል ሾፌሩ ወርዶ እንደረዳው ያስታውሳል።

ከሶስት ሰዓታት በሁዋል ያበደው ሲነቃ በሚያምር ክፍል ውስጥ ነው። ክፍሉ ውስጥ የሚያስጠሉት ያበደውና ልብሶቹ ብቻ ናቸው። እንደ እንቁላል በሙቀት ያበደው ዳግም ተወለደ። በኢንኩቤተር ከሞት አፋፍ ተመልሶ ኖረ። ዛሬ በስድሰት ዓመቱ ላልሰሙ አሰማ።….. በረዶ አገራችን ቢኖር እንዴት እንሆን ነበር? በዚህ ስንፍናችን፣ በዚህ ሁዋላ ቀርነታችን፣ በዚህ ድህነታችን….. ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ ሆነ። የጎዳና ተዳዳሪ ወንደሞቻችን የተባረካችሁ ናችሁ!!

ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት ይህ ሆኖ ነበር። ዛሬ ያበደውና በረዶ ተላምደዋል። ብዙ ገጠመኞች አሉ። ያበደው አሁን ቦሰና ታስፈለገዋለች። ኪኒኑ ናት። ቦሰና ፍቅር ናት። ሲነሳባት ኤሌክትሪክ ናት። ነዝራ ታስነዝራለች። “አከሲ” ካለች አለቀ። ያበደው ፈገግ አለ። ከሞት ያመለጠበትን ቀን ሊቀልድበት ወስኗል። አከሲ!!የሰላሌ ቆንጆ!! ሰላም እንሰንብት!! መላካም ሰንበት!! ነገ ብቻ ሳይሆን ከሰኮንዶችና ደቂቃዎች በሁዋላም ብዙ ሌላ ነገሮች አሉ። ይኖራሉ… ሰው በተፈጠረበት ይኑር!! አበቃሁ… ለዛሬ!!

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *