May 9, 2021

ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

ሳንቼዝ – የፕሪምየር ሊጉ ተኳሽ!!

ሳንቼዝ ሲጫወት መመልከት ያስደስታል። የሚሰራው ስራ ሁሉ ግብታዊ አይደለም። ለሚያድረገው ነገር ሁሉ ምክንያታማ ነው። ቀድሞ ያስባል። ፍጥነቱንና የሰውነት ብቃቱን በወጉ የሚጠቀም አስተዋይ ተጫዋች ነው። ያሉትን ቴክኒካዊ ብቃቶች የሚጠቀምባቸው ከአእምሮ ጋር ነው።
ዌስት ሃም ላይ ያስቆጠራቸው ጎሎች በፍጹም ብቃቱን የሚያሳዩ ናቸው። ለኦዚል ያለቀለት ጎል ሰጠ። ከሙስታፊ የተላከለትን ኳስ እግሩ ሲያስገባ ወዲያውኑ ተከላካዩን ሚዛኑን አስቶ በሰውነቱ በመሸፈን ያስቆጠራት ግብ ብቃቱን ያስመሰከረች ናት። ሁለት ተከላካዮች ተከታትለውት በሸርተቴ ሊያጨናግፉት ሲሞክሩ ሁለት ጊዜ የሚመታ እየመሰለ እያሸማቀቀ አካላቸውን አስቶና አቋማቸውን አበላሽቶ አስቆጠረ።
ዋልኮት ተመሳሳይ ኰስ አግኝቶ ነበር። አስቦ ሳይሆን ዝም ብሎ ወደ ጎል ሞከረና ተደረበች። ያቺን ኳስ አንዴ እንኳን አሸማቆ ያዝ ቢያደርጋት ጎል የማግባት እድሉ በሰፋ ነበር። በተመሳሳይ የመጨረሻውን ኳስ ሲያገባም በረኛው ስለወጣ አሸማቆ ሚዛኑን ካሳተው በሁዋላ ነው መረቡን የደነሰበት። አርሰናል 5- 1 ባሸነፈበት በዚህ ጨዋታ አሌክሲስ ሳንቼዝ የእለቱ ምርጥ ነበር።

Related stories   የመረጃ መንታፊዎች ዋትሳፕን እንደ ጥቃት ማድረሻ መሳሪያ እየተጠቀሙ መሆኑ ተገለጸ
Alexis Sanchez of Arsenal scores and celebrates 0 2 during the Premier League match between West Ham
Alexis Sanchez of Arsenal

ለዚህም ይመስላል ዌንገር ” ምርጥ” ሲሉ ያደነቁት። በዘንድሮው ሲዝን ኦዚል ያንቀላፋውን ያህል የሳንቼዝ ታታሪነት አርሰናልን እጅግ እየጠቀመ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ኦዚል አሁን በሚያሳየው ብቃቱ መቀየርና መውጣት ሲገባው ዌንገር ተሸክመውታል። ቀደም ሲል እንደሚያደርገው ኳስ ማዘጋጀት እንኳን እየተሳነው ነው። በዚህም ላይ የሚነጠቃቸው ኳሶችን መልሶ ለመቆጣጠር የሚያሳየው ዳተኛነት በተደጋጋሚ የሚታይበት ችግር ነው።
አሌክሲስ እንደዛ እየተሯሯጠ ኳስ ለመንጠቅ የሚያደርገውን ትግል ለሚያይ የኦዚል ዳተኛነት ከምን የመጣ እንደሆነ ግልጽ አይደለም። አሁን ተወደደም ተጠላም የአርሰናል እንቁ ሳንቼዝ ነው። በጥቅል ግን አርሰናል አሁንም ጥልቀት የሚቀረው ቡድን ነው። ለዋንጫ የሚጫወት ቡድን ኳሊቲ የላቸውም። አንዳንዴ ቶሎ ይፈርሳሉ። ተከላካይ ክፍሉ የተሻለ መሆኑ እንጂ መካከል ላይ ያለው የኖረ ችግር አንዳንዴ ሲያወዛግባቸው ይታያል። እንደ እኔ ሃሳብ አርሰናል ኦዚልን አስቀምጦ ሳንቼዝን ተደራቢ አጥቂ በማድረግ አንድ አጥቂ አስገብቶ ቢጫወት በርግጠኛነት የበለጠ ፈርጣማ ይሆናል።
የሞላ ቤት በመግባት የብልጣብልጥ ጨዋታ የሚጫወተው ጋርዲዮላ ከፊትለፊቱ በርካታ ሽንፈቶች የሚገጥሙት ይመስላል። ጋርዲዮላ ባየርን ሲረከብ ቡድኑ የአገሩ ሻምፒዮን፣ የቻምፒዮን ሊግ አሸናፊ ነበር። እሱ ከባርሳ ወደ ባየር ሲመጣ ተጨማሪ ተጫዋቾች ቢገዛም ለሁለት ዓመት የቻምፒዮን ሊግ ውድድር ላይ ሊሳካለት አልቻለም። አሁን ደግሞ በሲቲ የተዘባረቀበት ነው የሚመስለው። ቼለሲ አሳምሮ ነው የቀጠቀጠው። ኮንቴ ቡድኑን ከቀን ወደ ቀን እያረመ አጠንክሮታል። አሁን በጥር ደግሞ ተከላካይ ይገዛና የሁዋላ ደጀኑን ግምብ ያደርጋል።
አርሰናል ተከላካይ ክፍሉ እንዳይጎዳበት፣ ሳንቼዝ እክል እንዳይገጥመው እየጸለየ ከመኖር ከወዲሁ ብቁ ተጠባባቂ ተጫዋቾችን መያዙ ደግ ይሆናል። እንደ ካርል ጃክሰን አይነት ደንባራ ተጫዋች ይዞ ለዋንጫ መጫወት ህልም ነው የሚሆነውና። ለሁሉም ግን ሳንቼዝ እንቁ ነው። ሲጫወት ሌሎችን እያበላሸና ሚዛን እያሳተ መሆኑን ልብ ላለ የእሱን ሃያል ተጫዋች መሆን ለመቀበል ይገደዳል። ሙሉ ተጫዋች ማለት ሳንቼዝ ነው!! ፖግባ የምትሉ ኑ እንከራከር። በነገራችን ላይ ዩናይትድ ችግራቸው ነጻ የሚለቃቸው አሰልጣኝ አለማግኘታቸው ብቻ ነው። ጆሴ ቴክኒካል ተጫዋቾችን የሚመች ዘዴ አያውቅም። ታክቲካል ጉዳዮች ላይ ስለሚያተኩር ኳስ የሚችሉ ተጨዋቾች ይምታታባቸዋል።

0Shares
0
Read previous post:
የስስታሙ ነጋዴ ታሪክ

በአንድ ወቅት አንድ ፈጣሪ በሰጠው ፀጋ አመስግኖ የማያውቅ ስስታም ነጋዴ ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ለንግድ...

Close