ወዮልሸ አዲስ አበባ!! ከመቆርቆሯ ጀምሮ… እስከ አሁን ድረስ ለምታ ላትለማ አድጋም ላታድግ…በየፎቆቿ እና መንገዶቿ ስር የቀበረችው ላብ ደም እና እንባ ተጠራቅሞ ከከርሰ ምድር ፈልቆ ቢያጥለቀልቃት…
.
በጊዮርጊስ በኩል እምዬ ምኒሊክን ከነፈረሳቸው እያንከባለለ (ይጋልቡት ይሆናል የሳቸው ነገር) ወስዶ ራስመኮንን ድልድይ… ሰባ ደረጃን… እንደ በቆሎ ጥብስ በየተራ እየተፈለፈለ ባናታቸው!…የልደታ ኮንዶሚኒየም ከሰሚቱ ጋር ድብልቅልቅ!…ናኒ ህንጻ በቁሙ ተገንድሶ ግዮን ሆቴል መዋናኛ ገንዳ ውስጥ ቦርጨቅ! ባጃጆች ታክሲ ሆድ ውስጥ ሲደበቁ…. አንበሳ አውቶ ቡሶች እንደ መቶ እግር በጎርፉ ላይ ሲንሳፈፉ…ሳርቤት ያለው የካርል ሃውልት በቄራ በወሎ ሰፈር በቦሌ አድርጎ እየተንከባለለ ሄዶ የቦብማርሊን ድሬድ በጠቋሚ እና አውራ ጣቱ ጉትት!
ምናለፋችሁ ከተማዋ 2012 ፊልም ላይ እንዳያችሁት በጎርፍ ስትዋጥ ስትናጥ… እዛ ቦሌ የተደረደሩ አውሮፕላኖች ‘የኢትዮጵያ’ በሚለው አርማቸው ምትክ ከታክሲ በር ላይ የተገነጠለ ‘ጦርሃይሎች ዞን ሰላም የታክሲ ባለ ንብረቶች ማህበር’ ወይም ‘ከመገናኛ በሲግና ካሳንቺስ’ የሚል ታፔላ ልጥፍ!! ብሄራዊ ጋ ያለው አንበሳ አጠገቡ ያለውን ግራር ላይ ተጠምጥሞ እየተንሳፈፈ ቃሊቲ …የአንዋር መስኪድ ግራማፎን ራጉኤል ቤተመቅደሱ መሃል ዱብ… የድል ሃውልት እንደ ምሰሶ ተገንድሶ እየተንከባለለ የአፍሪካ ህብረት ስር ዘፍ… እሱም ትንሽ ተንገዳግዶ በመካኒሳ ከጀሞ ኮንደሚኒም ጋር ድብልቅ! ኢንተር ኮንቲኔንታል ያደረው ቱሪስት በበር ጉማጅ እየተንሳፈፈ ፎቶ ለማንሳት ሲጣጣር የኢሲኤ ጣሪያ አናቱ ላይ ክድን! የፓርላማው ሰኣት ‘ዋተር ፕሩፍ’ በመሆኑ መቁጠሩን ቀጥሎ እየተንከባለለ መገናኛ ዘፍመሽ ሸዋ ሱፐር ማርኬት አይቶ ከማያውቃቸው እቃዎች ጋር ድብልቅልቅልቅልቅ…ከሲኤም ሲ ጦር ሃይሎች የተዘረጋው የባቡር ሃዲድ እንደ ጠላ ቂጣ ከመሬት ተፈቅፍቆ እንኩሮ… የብረታ ብረት እና የኮንክሪት እንኩሮ…
.
ይህቺ ስም ብቻ ‘አዲሰ አበባ’ … የአፍሪካ መዲና …. የርዕሰ ብሄሩ መቀመጫ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ… የእኛም መቀመጫ የአንዳንዶች መጎለቻ…ምንጥርሶ ቅብርጥሶ … ሸገር… ፊንፊኔ …አዱ ገነት …ድንቄም ገነት…ምንድን ናት አዲስ አበባ? ማናት አዲስ አበባ? ለመሆኑ አዲስ ባባዊ ብልጫው ምንድነው?
.
የአዲስ አበባ ልጅኮ…
እንደ ባቄላ ተፈልፍሎ ከእናቱ ማህፀን በኦፕራሲዮን ይወጣል… ትንሽ ከፍ ሲል ቢራ በጡጦ ይጠጣል…ከጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ፓውደር ቀድሞ የሲጋራን አመድ ያውቃል…
ሙዝ መላጥ ይደክመዋል…(ምናለ ያለ ልጣጭ ቢፈጠር ሲልም ይመኛል) የተቀቀለ እንቁላል… የተቀቀለ ድንች ለመላጥ ያልበዋል..(አንዳንዶች ከነልጣጩ አይተው አያውቁም)… የእንጀራ ጠርዝ ይቆርጠዋል…ጥሬ ጤፍ አይቶ አያቅም (ያየ ቀንም … ወይኔ ጤፍ እንደዚህ ትንሽ ነው እንዴ?)…ከሱም ብሶ እንጀራ ይበላል…(ሩዝ ምናምን ሞክር እንጂ ጀለስካ)
ተማር ሲሉት 4ዓመት ብዙ ነው ይላል… በብረት የታሰረ ጥርሱ ለማስፈታት 4 ዓመት ይጠብቃል … ሁለተኛ ፎቅ ድረስ ለመሄድ ሊፍት ይሳፈራል … ቺዝ የወተት ተዋፆኦ መሆኑን አያውቅም ስፔሻል ፒዛ ግን ያዛል… ‘ድንች እንደ ማንጎ ከዛፍ ይቀጠፋል’ ብሎ እየተወራረደ ‘ፍሬንች ፍራይስ’ ያዛል…ካቻፕ ቲማቲም እና ስኳር መሆኑን ስለማያውቅ…ልዩ ነገር መስሎት ገበታው ላይ በገፍ ያዝረከርካል… ‘ወንድይራድ እና አብዲሳ አጋ ነው የተማርኩት’ ስትለው ትምህርት ቤቱ ጥቁር አንበሳ ከሊሴ ገ/ማርያም አጠገብ በመሆኑ ይመፃደቃል
… ሽሮሜዳ ነኝ እንዳይልህ አሜሪካ ኢምባሲ ይልሃል … ሱሉልታን ሳያውቅ ሲያትልን ይናፍቃል …ሳሪስ ቁጭ ብሎ ስለ ፓሪስ ይተርካል … አቦል፡ ቶና ፡ በረካ የሌለው ቡና በየበረንዳው ያንቃርራል …የድጎማ ዶላሩን በብላክ ማርኬት መንዝሮ ኤድናሞል ሲኒማ ይገባል…ሲወጣ በሁለቱም ጆሮው ነጭ ኢርፎን ሰክቶ አስፓልት ያቋርጣል … ሐይቅ ፡ ወንዝ እና ፏፏቴ የመሳሰሉትን የውሃ አካላት ለማየት ቢያንስ 50ኪ.ሜ.ይጓዛል…አማረኛ አለማወቅ ስልጣኔ መስሎ የመልክአምድር ተመሳሳይ ሲሉት ‘አይነምድር’ ይላል … አሁንም የድጎማ ዶላር መንዝሮ ኮንደሚኒየም ይከራያል …ቢጤውን ያገባል … DSTV ቤት እያመሸ ከሚስቱ ጋር ይነታረካል…ንፁሕ አየር…የባህር ምግቦች…ፍሬሽ ኦርጋኒክ ምግቦች ስለማያገኝ (የዕድሜውን ግማሽ በሳህን የተቋጠረ ምሳ …ከዛም የቆርቆሮ እሽግ እየከፈተ እየበላ)እንዲሁም በቂ የአካል እንቅስቃሴ ስለማይኖረው(በየቱ ሜዳ ተጫውቶ?በምን ሐይቅ ዋኝቶ?) ሳያረጅ ይሞታል በመጨረሻም … ዮሴፍ ይቀበራል!
ታዲያስ አዲስ አበባዊ ብልጫው ምንድነው?

Teym Tsigereda Gonfa

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *