* ኢህአዴግ እስረኞችን “አሰልጥኜ” አስመረኩ አለ፤ እስረኞቹ “ በፍፁም፣ አይደገምም፣ የቀለም አብዮት፣ ህገ መንግስት እና የኢትዮጵያ ህዳሴ” የሚሉ ኮርሶች የወሰዱ ናቸው።

ዛጎል ዜና- መንግስት አምስት ሺህ የሚጠጉ እስረኞችን “ተመራቂዎች” በሚል መፍታቱን ይፋ ባደረገበት ቀን በተመሳሳይ አምቦ ተማሪዎች ተቃውሞ ማሰማታቸው ተሰማ። ተማሪዎቹ የአስቸኳይ አዋጁን በመጣስ ” መረራ ይፈታ” እያሉ ተቃውሞ መጀመራቸው ነው የተሰማው። ከትምህርት ቤት ወደ ትምህርት ቤት የሰፋው ተቃውሞ ብህይወት ላይ አደጋ ባያስከትልም በንብረት ላይ ግን ጉዳት አድርሷል። መኪና ሲቃጠል ያዩ የአይን ምስክሮች ተቃውሞውን በጀመሩት ላይም ሆነ ዘግይተው በተቀላቀሉት ላይ እንደ ቀደሞው ያለ የሃይል እርምጃ አልተወሰደም። የኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ወርክ እንዳለው ደግሞ በርካታ ሰዎች ታስረዋል።

ለወትሮው ህገ መንግስቱን በሃይል ለመናድ የተነሱ፣ የነውጥ ሃይሎች፣ አተራማሾች፣ የጥፋት ሃይል ተላላኪዎች በሚል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል  4035 የሚሆኑት ሲፈቱ እስረኞቹ “ስድስት ኮርስ ወስደው ተመረቁ” ነው የተባለው።

የኦሮሚያ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ኮሚሽነር ፀሃይ በላይን ጠቅሶ ፋና እንደዘገበው ጦላይ ተሃድሶ ማዕከል ከገቡ 5 ሺህ 600 ሰልጣኞች መካከል 4035 ያህሉ በስድስት ዋና ዋና ጉዳዮች ሥልጠና ወስደው ተመርቀዋል። ኮርሶቹም በፍፁም አይደገምም፣ የቀለም አብዮት፣ የኢትዮጰያ ህገመንግስት እና የኢትዮጵያ ህዳሴ ሚሉ ርዕሰ ጉዳዮችን የተካተቱባቸው ነው።

አበምርቃቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ተገኝተው “ ሽኝት” አደርጉላቸው ተብሏል። በርካታ ቃል ተገብቶላቸዋል። መስመርም ተሰምሮላቸዋል። “በደምና በአጥንት የተጻፈውን ሕገመንግስት፣ ዋጋ የተከፈለበትን ህገመንግስት” በማለት አቶ ሃይለማርያም በሃይል ለመናድ መሞከር አይቻልም በለዋል። “ ልክ እናንተ አይደገምም እንዳላችሁት፣ እኛም አይደገም እንላለን” ብለዋል። የፋና ዘገባ እንዲህ ይነበባል።

“አይደገምም” – በኮማንድ ፖስቱ በቁጥጥር ስር የነበሩና ወደ መጡበት የተመለሱ ሰልጣኞች

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 12 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረው ሁከት ውስጥ ተሳትፈው በማሰልጠኛ ጣቢያዎች የተሃድሶ ስልጠና ሲወስዱ የነበሩ ዜጎች ወደ መጡበት እየተመለሱ ነው። በአዋሽ፣ አላጌና ብር ሸለቆ ማዕከላት የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ ዜጎች ናቸው ወደ አካባቢያቸው እየተመለሱ ያሉት። በጦላይ ለአንድ ወር የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ 4 ሺህ 35 ዜጎችም ሥልጠናቸውን አጠናቀው ነገ ወደ መጡበት አካባቢ ይመለሳሉ ተብሏል።

Related stories   ኦነግ ሸኔና ህወሃት ከሃጫሉ ሁንዴ ግድያ ጀርባ መጠርጠራቸው ይፋ እየሆነ ነው!! በሽሬ የሻዕቢያ ተቃዋሚዎች ልምምድ

በጦላይ የተሃድሶ ማዕከል የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት ሰልጣኞች ወደ መደበኛ ህይወታቸው እንዲመለሱ መንግሥት ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል። ሠራተኞች ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ የሚደረግ ሲሆን ተማሪዎች ደግሞ ትምህርታቸው እንዲቀጥሉ ይደረጋልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም።

ሥራ አጥ የሆኑ ወጣቶችም በራሳቸው መንገድ ሥራ እንዲፈጥሩ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ የማይነጣጡ የአንድ አገር ህልውና መሰረት መሆናቸውን ወጣቱ ተገንዝቦ እነዚህን እሴቶች የመጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል። ወጣቱ ጥያቄ እንኳ ቢኖረው ሕገ-መንግሥቱ በሚፈቅደው መሰረት የማቅረብና መልስ የማግኘት መብት እንዳለው ገልጸዋል። ባለፉት ወራት እንደታየው ጥያቄውን በአመጽና ግርግር መጠየቁ ዋጋ እንዳስከፈለ ለማሳያነት በማንሳት።

እንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንዳይደገም መንግሥትም የራሱን ስህተት ለማረም ጥልቅ ተሃድሶ እያደረገ መሆኑን ገልጸው ወጣቱም የራሱን ስህተት በማረም ከመንግሥት ጋር በመሆን ሠላሙን እንዲጠብቅ መልዕክት አስተላልፈዋል። የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው በክልሉ የሰፈነውን ሠላም ለማስቀጠል ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ጋር በቅንጅት ሥራዎች ይሰራሉ ብለዋል።

ከወራት በፊት በተፈጠረው ሁከትና ግርግር ህይወት የጠፋ መሆኑን ገልጸው ለዘመናት የተለፋባቸው የህዝብ ኃብቶችም መውደማቸው አግባብ አለመሆኑን ተናግረዋል። ክልሉ ሊለወጥና ሊለማ የሚችለው የክልሉ ወጣቶች ለሠላም በጋራ ዘብ ሲቆሙ እንደሆነም አስምረውበታል።

አሁን ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ የሚደርስባቸው ነገር እንደማይኖር ገልጸው ተረጋግተው መደበኛ ህይወታቸውን እንዲቀጥሉ አሳስበዋል። የኦሮሚያ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ኮሚሽነር ፀሃይ በላይ እንደገለጹት ጦላይ ተሃድሶ ማዕከል ከገቡ 5 ሺህ 600 ሰልጣኞች መካከል 4 ሺህ 35 ያህሉ በስድስት ዋና ዋና ጉዳዮች ሥልጠና ወስደው ተመርቀዋል። ሰልጣኞቹ በቆይታቸው በፍፁም አይደገምም፣ የቀለም አብዮት፣ የኢትዮጰያ ህገ-መንግስት እና የኢትዮጵያ ህዳሴበሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሥልጠና ወስደዋል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *