ያበደው ሳቀ። ደስ አለው። አዲስ ነገር ሰማ። እስረኞች አዲስ ስም ወጣላቸው። ” ሰልጣኞች” ተባሉ። ሰልጠና ብቻ አይደለም ምርቃትም ተደርጎላቸዋል። የመረቋቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው። አቶ መለስ ይህንን ወግ አላገኙም። አስረው ለማሰለጠንና ለማስመረቅ ሳይበቁ እጣ ወጣባቸው። ያበደው አሁን መለስ ላይ ቢፈትል አይፈራም። ራሱ ህወሃት ” አብሎቹን ሰብስቦ ” መለስ እያላችሁ አታላዝኑ” መባሉን ሰምቷል። ይህ እድገት ነው….. “አሻም አሻማ” ትላለች ቦሰና!!
“ በፍፁም፣ አይደገምም፣ የቀለም አብዮት፣ ህገ መንግስት እና የኢትዮጵያ ህዳሴ” የሚሉ ኮርሶች ወስደዋል አሉ ታሳሪዎቹ፤ ይቅርታ ” ሰለጣኞቹ ተመራቂዎች” ያበደው ሃሳብ አለው። ኮማንድ ፖስቱ እንዲህ ዓይነት ትጋትና የስራ ቅልጥፍና ካለው የኢትዮጵያ ህዝብ በየተራ ስልጠና እስኪጨርስ አስቸኳይ ጌዜ ይራዘም። ኮማንድ ፖስት የማይነቀል የመንግስት ማዕረግ ይሰጠው። በክፉ የሚያነሱት…
ነውጠኞችን አስሮ፣ ገርፎ፣ አድቅቆ፣ አራግፎ፣… እስር ቤት የሚደረገውን ሁሉ አደርጎ… የማስመረቅ ፓኬጅ የሚፈልጉ ብዙ አገሮች አሉ። ኢህአዴግ በነካ እጁ ሲሪያ ገብቶ ” ያመጹትን ቢያሰለጥንና ቢያስመርቃቸው” ስትል ቦሰና ሃሳብ አቅርባለች። አዋጪ የኢንቨስትመንት መስክ ሊሆን ይችላል። ጋቦን፣ ኮንጎ፣ ሊቢያ፣ ናይጀሪያ… ዳግም ከተሳካ ሶማሌ ይህንን አገልግሎት እንደሚፈለጉት ቦሰና ታይቷታል።
ሰላም ወገኖች። መልካም ዜና አስፈነደቀኝና ሰላምታ ዘነጋሁ። ቦሰና ” አይደገምም” የሚለው ኮርስና ቃለ መሃላ ተመችቷታል። ደጎል ምንም እንኳ ውሻ ቢሆንም ” አይደገምም ” የሚለው ንግግር አልገባውም። ምኑ ነው የማይደገመው? አመጽ፣ ሽብር፣ ተቃውሞ፣ ሰላማዊ ሰልፍ፣ መሰብሰብ፣ መደራጀት፣ መታገል፣ ማታገል፣ ማሳመጽ… አቶ ሃይለማርያም ” ህገ መንግስቱ በደምና በአጽም የተጻፈ ነው፤ ዋጋ ተከፍሎበታል” ብለዋል ለካ!!
ያበደው አሁን ጥያቄ አለው። “ህገ መንግስቱን መጣስ አይደገምም” መባል አለበት። ሰዎች የመናገር ተፈጥሯዊ መብታቸው ከተከበረ፣ መምረጥ፣ መመረጥና ሾመው ማውረድ ከቻሉ፣ መሰብሰብ፣ መሰለፍ፣ መቃወም፣ ማውገዝ፣ መደራጀት፣ ማደራጀት… ህገ መንግስቱ ላይ ያለው ሁሉ ከተከበረላቸው ለምን ያምጻሉ? ለምን ንብረት ያወደማሉ?…… ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው።
ሰዎች ድምጻቸውን ሲሰረቁ ቢያምጹ ጥፋተኛው ማን ሊሆን ነው? ያበደው ሰነድ አየ። ወደ ሁዋላ አሰበ። ” ድምጽ ሰርቀን እንጂ ተሸንፈን ነበር” ሲሉ ምስክር የሆኑትን አደመጠ። እናም በሰላማዊ መንገድ መርጠው፣ በህጋዊ ተቋም አማካይነት ሰዎች ድምጻቸው ከተሰረቀ ምን ያድርጉ? ያበደው አሁንም ይጠይቃል፤ ስልጠናው የህገመንግስት ኮርስን ያካተተ ነበር። ታዲያ አሁን ” ሰልጥነው የተመረቁት” እንደ ቀድሞው “ህገ መንግስት ይከበር ቢሉስ?” እንደውም አቶ መለስ ባሉበት ነብስያቸው እንድትፋፋ ” እስከመገንጠል” ድረስ የሚሄዱ ቢነሱስ?… አይደገምም!! ያበደው ደጎልን መሆን ተመኘ።
የኢትዮጵያ ነገር ግራ ያጋባል። ግራ ያልገባችሁ እድለኞች ናችሁ። ያበደው በእናንተ ይቀናል። ሌላም ነገር አለ። አሁን በየቦታው ቃል እየተገባ ነው። በብዛት ቃል ሲገባ ይሰማል። ስራ መስጠት፣ ገንዘብ መስጠት፣ ምቹ ሁኔታ መፍጠር…. ወዘተ… ይነጋል። ይህ ወጣት ነገ ይጠይቃል። ድሆች ነን። ገና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በቀን አንዴ መብላት ያልቻሉባት ደሃ አገር ይዞ ተስፋ ደግ አይደልም። ከጥልቅ ተሃድሶ የዘለለ መሃላ ሊኖር አይችልም። ከዚህ ሁሉ የፖለቲካውን ሜዳ ሰፋ ማድረጉ፣ አማራጭ አለን ለሚሉ እድል መስጠቱ፣ መመካከሩና ተጋግዞ መስራቱ ይመራጣል ሲል ያበደው ጥሪ ያሰማል።
ግልገል ጊቤ ተመረቀ የሳምንቱ ዜና ነው። ሃሪፍ ዜና ነው። ያበደው ጸሎት አለው። ” ግልገል ጊቤን አንድዬ በተዓምርህ ጠብቀው፣ ዝናብ ይፈልጋልና ሙላው፣ ግን አታጥለቅልቀው፣ ቅድሚያ ለወገኑ ያበራ ዘንድ እርዳው፣ ቅድሚያ ለጎረቤት ብሎ እንዳይሸፍት ልቡና ስጠው… አሜን” መልካም ነገር ሲሰራ ደስ ይላል። የሚከፋችሁ ካላችሁ ታከሙ። ታስራችሁ ” ተመርቃችሁ” ለወጣችሁት ኮንግራ!! እነሱን ተክታችሁ ወደ ” ስልጠና ማዕከል” ለምትጋዙ… ያበደው ከንፈሩን መጠጠ። ብዙ አይነት ብርሃን ታየው። የሚያቃጥል፣ የሚነተከተክ፣ የሚለበለብ… ግን እንስማማ። ዳግም ጀማሪ፣ አፍርሶ አዳሽ፣ አውድሞ ጠጋኝ ከመሆን ይጠብቀን። የሰላም ቀን ያምጣልን፤ አሜን!! ያበደው ተነሳ፣ ደጎል ጭራውን ቆላ፣ ቦሰናም ሸብረክ አለች። “ድንግል ሆይ” ስትል እንደ ልማድዋ አነባች። አገሪቱ ” በሚያነቡ” ጸሎት እንዳለች የታመነ ነው!! በስድስት ኮርስ ፓስተር፣ ነብይ፣ ዲያቆን፣ መምህር… በመሆን ጥበብ የትም አይደረስም። አቋራጭ… ሰላም ሁኑ!! መልካም የጌቶቻችን ገና!! እስኪ እናንተ ልበ ብርሃኖች ጸልዩ ለኢትዮጵያችን !! የዋሃንን ይሰማልና!! በድጋሚ አሜን አልን!! አሜን!!

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *