“Our true nationality is mankind.”H.G.

የመንግስት አመራሮችን ጨምሮ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 130 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ፤በመቀሌ ከተማ በተካሄደ ግምገማ 49 አመራሮች እና ሰራተኞች ላይ እርምጃ ተወሰደ

የመንግስት አመራሮችን ጨምሮ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 130 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 130 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

መንግስት የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ እና ለመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት የሆኑ አመራር እና ፈጻሚ አካላትን ለማረም የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ እያደረገ ይገኛል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንም የመንግስት ጥልቅ ተሃድሶን ተንተርሶ ባለፉት ጥቂት ወራት ከህዝብ፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጥቆማዎች     ደርሰውታል።  በዚህም ፖሊስ ከህብረተሰቡ የደረሱትን 260 ጥቆማዎች ተቀብሎ እንዲጣሩ ማድረጉን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀኔራል ልዩ አማካሪ ኮማንደር ደስታ አስመላሽ ተናግረዋል።

በእንዲሀ መልኩ የህብረተሰቡን ጥቆማዎች ተቀብሎ ማጣራት የጀመረው ኮሚሽኑ፥ አሁን ላይ ከ130 በላይ ተጠርጣሪዎችን በከባድ የሙስና ወንጀል ተገቢው ማስረጃ ቀርቦ እንዲጣራ ተደርጓል ብለዋል። ተጠርጣሪዎቹ የመንግስት አመራሮች፣ ባለሙያዎች እና የተለያዩ ግለሰቦች መሆናቸውንም ነው ኮማንደር ደስታ የተናገሩት።

ተጠርጣሪዎቹ ከመንግስት እቃ ግዥ፣ የቤቶች ልማት፣ መሬት ልማት፣ ባንክ ስራዎች እና ከአክሲዮን  ኩባንያዎች፥ የታክስ ማጭበርበር እና የሙስና ወንጀል ፈፅመዋል በሚል በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ገልጸዋል።  ይህን ተከትሎ ፖሊስ በወሰደው እርምጃ 13 የሃብት እና ንብረት እገዳ ማድረጉን ይገልጻሉ።

ስምንት ትላልቅ የአክሲዮን ኩባንያዎች፣ ሁለት ፋብሪካዎች፣ አራት ህንፃዎች፣ 22 መኖሪያ ቤቶች እና 49 ተሽከርካሪዎች ላይ በተጨማሪነት እገዳ ተጥሏልም ነው ያሉት። ኮሚሽኑ ከህብረተሰቡ ከደረሱት ጥቆማዎች ባሻገር በፌደራል ስነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በኩል ተይዘው የነበሩ ከ102 በላይ መዝገቦች ምርመራ ተካሂዶባቸው ለፍርድ ቤት መለላካቸውንም አስረድተዋል።

Related stories   “የግድቡ ግንባታ ውሃ ይቀንስብኛል የሚለው የግብጽ ጩኸት የማጭበርበሪያና የተለመደ የሃሰት ክስ ነው››

ከባድ የሙስና ወንጀሎች በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ቀለል ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር ፖሊስ ኮሚሸን፥ በውክልና ጥቆማዎችን ተከትለው መረጃዎችን የማጣራት እና የመመርመር ስራዎችን እየሰሩ ነው። በቅርቡም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከህብረተሰቡ የደረሰውን ጥቆማ ተከትሎ በወሰደው ዘመቻ 125 በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን፥ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ በማካሄድ ክስ እንዲመሰረትባቸው መደረጉን ልዩ አማካሪው አስታውሰዋል።

ኮሚሽኑ ሙስናን በተመለከተ ለሚደርሰው ጥቆማ ተገቢውን ምላሸ ለመስጠት፥ የአደረጃጀት እና የሰው ሃይል ምደባውን በተገቢው መንገድ እንዳጠናቀቀም ገልጿል። በቀጣይም ህብረተሰቡ የሙስና ወንጀሎችን ለማጋለጥ በአካል በመቅረብ ወይም በኮሚሸኑ ስልክ ቁጥሮች ደውሎ በመጠቆም አጋርነቱን እንዲሳይም ጠይቋል። በተያያዘ ዜና በመቀሌ ከተማ በሁሉም ዘርፎች የሚታዩ የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች እንዲፈቱ የተጀመረው ጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባ የከተማዋ ነጋዴዎች ተናገሩ።

የመቀሌ ከተማ አስተዳደር ከከተማዋ ነጋዴዎች ጋር በመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች ዙሪያ ውይይት አድርጓል። በውይይቱ ላይ ነጋዴዎች የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማው የዘመቻ ብቻ ሆኖ እንዳይቀር ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል። እንደ ነጋዴዎቹ ገለጻ ግምገማው መልካም ቢሆንም እየተወሰደ ያለው እርምጃ ግን በቂ አይደለም። በግምገማው የመልካም አስተዳደር ችግር በመፍጠር የተለየ አመራር ላይ ጠንካራ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ በሽግሽግ ማለፉም አግባብ አይደለም ነው ያሉት።

Related stories   “ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን በአንድነት በመከባበር፤ በመተሳሰብ እና በመረዳዳት ሊያከብር ይገባል”

ከዚህ ባለፈም አንዳንድ ተቋማት በደላሎች እየተመሩ መሆኑን ጠቅሰው፥ በአብዛኛዎቹ ደግሞ ውሳኔ የመስጠት እና የአመራሩ የብቃት ማነስ ችግር መሆኑን ጠቁመዋል።ምየከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ በተለያየ ደረጃ ግምገማ ማድረጉን ነው የገለጸው።

ከዚህ ጋር ተያይዞም እስከታችኛው አመራርና ሰራተኞች ድረስ በተካሄደው ግምገማም፥ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ 49 አመራሮች እና ሰራተኞች ላይ እርምጃ ተወስዷል ብሏል። በዚህም 18 መካከለኛ እና ከፍተኛ አመራሮች ከስራ ገበታቸው ሲነሱ፥ የ17 ባለሙያዎች ጉዳይ ደግሞ በህግ እንዲታይ መደረጉንም ገልጿል።

በነጋዴዎቹ የተነሱትን ቅሬታዎችና የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚሰራም ነው አስተዳደሩ የገለጸው። በቀጣይ መሰል ግምገማዎች ይቀጥላሉ ያለው አስተዳደሩ፥ ነጋዴዎች ሙስና ባለመስጠትና ሙሰኞችን በማጋለጥ ሙስናን ለመዋጋት የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙም ጠይቋል።

በሌላ ዜና ደግሞ ተቀጥረው የሚሠሩበትን የመንግሥት ሥራና ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው፣ የራሳቸውን ጥቅም በማስቀደም ሙስና በመፈጸምና ለመልካም አስተዳደር እንቅፋት በመሆን የተጠረጠሩ በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች የነበሩ 22 አመራሮች፣ በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው፡፡

Related stories   የኢትዮዽያ የቁርጥ ቀን ልጅ "ስለአባይ እውነቱን እንካችሁ" – መካ አደም አሊ

በአዲስ አበባ ከተማ የልማት እንቅስቃሴዎች በአግባቡ እንዳይከናወኑ እንቅፋት በመሆንና በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ኃላፊ ሆነው ሲሠሩ፣ በተለያየ ደረጃ የሙስና ተግባር የፈጸሙ መሆናቸውን ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን ለፍርድ ቤት ሲያቀርብ አስረድቷል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ከታኅሳስ 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ባደረገው ዘመቻ፣ በተለያዩ የከተማው አስተዳደር መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ከተፈጸሙ የሙስና ወንጀሎች ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ 125 አመራሮችንና ሠራተኞችን መያዙም ታውቋል፡፡

በሕገወጥ መንገድ የተሽከርካሪ ሰሌዳ በመስጠት፣ በሌሎች ሰዎች ስም መንጃ ፈቃድ በመስጠት፣ የመንግሥትን ቤቶች ወደ ግል በማዞር፣ የመንግሥት ገንዘብ በማጉደል፣ ያለጨረታ ከሕግ ውጪ ጨረታዎችን በመስጠትና በሌሎች የወንጀል ድርጊቶች ተጠርጥረው መያዛቸውን ፖሊስ ገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ዕርምጃውን እንደቀጠለ፣ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸውን ፍርድ ቤት እያቀረበ እንደሆነና ሌሎች ያልተያዙ ተጠርጣሪዎችን በመከታተል ላይ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

በቁጥጥር ሥር የዋሉትን ተጠርጣሪዎች ከታኅሳስ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ፍርድ ቤት በማቅረብ የ14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ ጠይቆ በምርመራ ላይ መሆኑም ታውቋል፡፡

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 21 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ)

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0