ኦቦ ቃሲም ሁሴን አባናሻ፣ ኦቦ ነጋ ጃላ በሊቀመንበርነት፣ ጀነራል ሃይሉ ጎንፋ በም/ሊቀመንበርነት የሚመሩት የተባበሩት የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ ናቸው። ላስ ቬጋስ የሚገኘው የሕሊና ራዲዮ ላይ ቀርበው ነበር።

ቃለ አቀባዩ ስሜን ጠቅሰው መጠነኛ ትችት አቅርበዋል። ትችት ቢሆን ለሰጡት አስተያየት አክብሮቴን በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እወዳለሁ። በተለይም በለንደን እና በአትላንታ ኮንፍራንስ የተሰባሰቡ ወገኖች፣ በምንም መስፈርትና ሚዛን የኦሮሞዉን ማህበረሰብን አይወክሉም በሚል፣ በዚሁ ራዲዮ ላይ የሰጠሁት አስተያየት ላይ ይመስለኛል አቶ ቃሲም ቅሬታ ያደረባቸው። እንደርሳቸው አባባል በጉብዬው የተገኙት ኦሮሞውን የሚወክሉ ናቸው። ከታላቅ አክብሮት ጋር አቶ ቃሲም በጣም ተሳስተዋል። እንኳን በአሥር ሚሊዮን የሚቆጠረዉን የኦሮሞ ማህበረሰብ ቀርቶ ዉጭ ያሉት ጥቂቶቹን እንኳን አይወክሉም። አንድ ሰው ይሄ ማህበረሰብ እወክላለሁ የሚለው ሲመረጥ ወይንም በተመረጠ አካል ሲመደብ ነው።፡ያ ባልሆነበት ሁኔታ ራስን ላይ መስቀል ትንሽ ያስገምታል።

አቶ ቃሲም ሁሴን ከተናገሩት በግሌ እንደሰበር ዜና ሊቆጠሩ ይችላሉ የምላቸውን ሶስት ነጥቦች ላይ አሁን በስፋት ማተጆር እፈልጋለሁ።

1) ቃለ አቀባዩ “ኦሮሚያ የኦሮሞዎች ናት ከማለት ለምን ኦሮሚያ የነዋሪዎቿ ናት ?” አይባልም የሚል ጥያቄ ቀረበላቸው። የመለሱት መልስ በግሌ የምደገፈውና እንዲሆን ስጠይቀው የነበረ ጉዳይ ነው። እንደሚታወቀው አሁን ያለው የኦሮሚያ ሕገ መንግስት የኦሮሚያ ባለቤት ኦሮሞው ብቻ እንደሆነ ነው የሚደነግገው። ሆኖም አቶ ቃሲም “ኦሮሚያ የነዋሪዎቿ ናት፤ በኦሮሚያ የሚኖሩ ሁሉም እኩል ናቸው” የሚል ምላሽ መስጠታቸው አስደስቶኛል።

ሌላው ማህበረሰብ በተለይም አማርኛ ተናጋሪው አገር አይደለም እየተባለ የዘር ማጥፋት ወንጀል ላለፉት 25 አመታት ሲፈጸምበት ነበር። አቶ ቃሲም እንደ ትልቅ ስኬት የቆጠሩትን፣ እኔ ግን የኦርሞዎችን እንቅስቃሰ ያንኮታኮተው የምለው የአትላንታ ኮንፍራንስ አዘጋጅ ከሆኑት መካከል አንዱ ጃዋር መሐመድ ነው። ጃዋር መሐመድ ከጥቂት አመታት በፊት “Ethiopians out of Oromia” እያለ በአደባባይ መፈክር ሲያሰማ እንደነበረ እና በቅርቡ ደግሞ፣ ሌላው በኦሮሚያ የሚኖረዉን ኦሮሞ ያልሆነውን ማህብረሰብ፣ ኬንያ እንደሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን በኦሮሞው ፍቃድና አዎንታ የሚኖር እንግዳ ( alien) እንደሆነ አድርጎ ማቅረቡ የሚታወቅ ነው። ሆኖም አቶ ቃሲም ከነጃዋር የተለየ አቋም ማንጸባረቃቸው ” Oromia for the Oromos” ሳይሆን “Oromia for Oromians (የኦሮሚያ ነዋሪዎች) መሆኑን መግለጻቸው ማለፊያ (ይሄን ስል ለኦሮሚያ እውቅና መስጠቴ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ)

2) “እኛ የምንታገለው ሕዝብ እንዲመርጥ ነው። ህዝብ ከፈለገ ከኢትዮጵያ ጋር መቀጠል ካልፈለገ መለየት ይችላል” ያሉት አቶ ቃሲም ሬፈረንደም እንደሚደረግ ገልጸዋል። “ረፈረንደም የሚደረግ ከሆነ ማን ነው የሚመርጠው? ማን ነው ካርድ የሚሰጠው ? ማን ነው ኦሮሞ የሚባለው ?” የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው የ DNA ምርመራ እንደማያደርጉ ነው የገለጹት። “አፋን ኦሮሞ የሚናገር ኦሮሞ ነው ማለት አይደለም” ሲሉ ያከሉት የኦነጉ ቃል አቀባዩ፣ አንድ ሰው አፋን ኦሮሞ መናገሩ ኦሮሞነቱን አይገልጽም ብለዋል። ማንም ሰው አፋን ኦሮሞ ይናገር አይናገር ኦሮሞ ነኝ እስካለ ድረስ ኦሮሞ ነው ሲሉ ነው በግልጽ ያስቀመጡት።

ከዚህ ጋር በተገናኘ ፣ እነ ጃዋር ኦሮሞ አይደለም ብለው ዘመቻ ሲያደርጉበት የነበረው የአቶ ገበየሁ ወርቅነህ ጉዳይተነስቶ ነበር። “ታዲያ በዚህ ሁኔታ ዶር ገበየሁ ወርቅነህ ኦሮሞ ነው ማለት ነው ? ” ተብለው የተጠየቁት አቶ ቃሲም፣ ምላሽ አልነበራቸው። ይሄም የሚያሳየው ምን ያህል ነገሩ የተወሳሰበ እንደሆነ ነው።

3) አቶ ቃሱም የራስን እድል በራስ መወሰኑ የዲሞክራሲ መርህ ጉዳይ ነው በማለት ሌላው ለምን እንደሚቃወመው እንደማይገባቸው ነበር የገለጹት። “ታዲያ የመርህ ጉዳይ ከሆነ ለምሳሌ የምስራቅ ሸዋ ዞን ከኦሮሚያ እገነጠላለሁ ካለ፣ በዞን ደረጃ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ይኖረዋል ወይ ?” የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። አቶ ቃሲም መልሳቸው “አዎን በሚገባ” የሚል ነበር።

ከዚህ ጋር በማያያዝ እስቲ አንድ ጥያቄ ላንሳ። ኦሮሚያ ተገነጠለች እንበል። ከዚያ አዲስ አበባ፣ አዳማ፣ የምስራቅ ሸዋና የሰሜን ሸዋ ዞኖች ከኦሮሚያ ተገንጥለው ከኢትዮጵያ ጋር መቀጠል ፈለጉ። ይሄ እንግዲህ እንደ አቶ ቃሲም አባባል ችግር አይኖረዉም። የዲሞክራሲ መብት ጉዳይ ስለሆነ። ኦሮሚያ የምትባለው ለሁለት ተከፈለች ማለት ነው። የኦሮሞ አክራሪዎች “እንገጠል” ሲሉ ይሄንን አስበዉት ይሆን ?

በኔ ግምት የመገንጠል ጥያቄ እንኳን ባይነሳም፣ አሁን ያለው የኦሮሚያ ክልል ለአስተዳደር አመች ነው የሚል እመንት የለኝም። አቶ ቃሲም በመጥቀስ የራስን እድል በራስ መወሰን የመርህ ጉዳይ ነዉና፣ ለአንዱ ተሰጥቶ ለሌላው የሚከለከል አይደለምና፣ የምስራቅ ሸዋ ዞን፣ የቡራዩ፣ የአዳም ልዩ ዞኖች ከኦሮሚያ ክልል ወጥተው ከአዲስ አበባ ጋር የመቀላቀል ሙሉ መብት አላቸው።

በመሆኑም አዲስ አበባ እና በአካባቢዋ ያሉ ዞኖች(ቢያንስ ቡራዩ፣ አዳማ፣ ሰሜን እና ምስራቅ ሸዋን፣ ምን አልባትም አርሲ ጨምሮ) የሚኖሩ ነዋሪዎች፣ በህዝብ ዉሳኔ ከኦሮሚያ በመዉጣት የራሳቸውን ክልል ቢመሰርቱ ጥሩ ነው። የዚህ አዲስ ክልል የሥራ ቋንቋ አማርኛ እና አፋን ኦሮሞ ሆኖ፣ በዚህ ክልል በሁሉም ትምህርት ቤቶች አፋን ኦሮሞ፣ አማርኛ እና እንግሊዘኛ እንደ ትምህርት እየተሰጠ፣ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ ሳይባል ሁሉም በሰላም የሚኖርባት ይሆናል። ድሬዳዋ፣ ሐረረን እና አካባቢዉን ያካተተ አንድ ሌላ ክልል ቢኖር ጥሩ ይሆናል።

ግርማ ካሳ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *