“Our true nationality is mankind.”H.G.

2017ም ለእርስ በርስ ፍልሚያ ወደፊት!!

አዋጁ አንዲህ ነበር ፤ የኢትዮጵያ ዘመን ያሳስባል። አሁን ጊዜው ራስንና ህሊናን የመግዛት ነው። የመነጋገር ነው። የመደማመጥ ነው። የመስማማት ነው። ያልሆነላችሁ አቁሙ። ቢቻላችሁ ” አልሆነልኝም” በሉና ንስሃ ግቡ። ለማትችለቡበት የምትዘባርቁ ” እኔ እየረበሽኩ ነው” በማለት ውጡ፤ በስድብ ፖለቲካ የተለከፋችሁ ተመለሱ፣ “ያለ እኛ አገር አትመራም የምትሉም” አለዝቡ፣ ህዝብን በተስፋ የምትሞሉ ይብቃችሁ፤ ታመነም አልታመነም ታመናል። ይብቃ!! በቃ !! በክብር!!

ዘመን ይሄዳል፣ ዘመን ይተካል። አዲሱ አሮጌ ይሆናል። ሌላ አዲስ ዘመን ይመጣና ያረጅብናል። በአዲስ ዓመት አቅደው የሚከውኑ ጥቂቶች እንዳሉ ሁሉ በየዓመቱ ያቀዱትን በከበርቻቻ አጅበው የሚነጉዱ እቅድ አልባዎች የትየሌሌ ናቸው። ራሱ ማቀድ የሚባለው ጉዳይ ሳይገባቸው እንዲሁ በልማድ የሚኖሩ… ብቻ ምን አለፋችሁ ሁሉም ዓይነት ነዋሪዎች አዲስ ዓመትን ተቀብለዋል። 2017!!
ያበደው በውጪ አገር አዲስ ዓመት ለሚያከብሩ እንኳን አደረሰችሁ ይላል። ” እንኳን ደረስን ” የምትሉ ስልጡኖችም ካላችሁ ይሁንላችሁ። እግዚአብሄርን ማወቅና ማምለክ ለተምታታባቸው አዲሱ ዓመት እንዲገልጽላችሁ ያበደው ጸሎቱ ነው። በራስ በጎ ፈቃድ የሚከናወነውን ሁሉ ለፈጣሪ አደራ እየሰጡ በዝግ አእምሮ ለሚኖሩ ያበደው ያዝናል። ስሜትን ሁሉ ” እምነታዊ ጥላ” በመስጠት ፈጣሪ ፊታቸውን አጥቦ፣ ቁርስ ሰርቶ እንዲያጎርሳቸው የሚመኙ ፣የተለየ ባል/ ሚስት ጠፍጥፍፎ እንዲሰራላቸው የሚጓጉ፣ ስርዓት እንጂ እምነት ባጠገባቸው ያልዞረ… ደረቆች!! አዋቂ ነን ባዮች!! የልምድ ባሮች!! ማስተማር ወይም መማር የማይችሉ…ራሳቸውን ችለው የማይቆሙ፣ በልመና ሌላውን መስለው የሚኖሩ፣ ትህትናና “ፍቅር” መለየት የማይችሉ፣… ተንታኝ የሚመስሉ፣ እንደ ከበሮ የሚጮሁ፣…. ያበደው ይህን ሁሉ መታዘቡ ቀፈፈው። የዚህ ዘመን” ነብስ ያለው ሃውልቶች” የሚባሉትን አሰበ። ደንቁረው የሚያደነቁሩ…. እሱ አንዱ ፈጣሪ ፍቅርና ሩህሩህ እንደሆነ ያልገባቸው ደርቅ አሶች… እንዲህ ዓይነቶች ካልገጠሙዋችሁ ከብክነት ድናችኋል!! ያበደው ብዙ የሚረግማቸው አጋጣሚዎች አሉ!!
ቦሰና ስለ እምነት ክርክር አትወድም።” ሁሉም በገባው መጠን” የሚለው አካሄድ ይመቻታል። ንትርክ ደስ የሚላት ፖለቲካ ሲሆን ነው። እምነት ራሱ የፖለቲካ ያህል ቀኝና ግራ እንደሆነ ተመራምራ አልደረሰችበትም። ያበደው … ከሃሳቡ ሲነቃ የ2016 ያለመቻቻልና ያለመደማመጥ ጉዞ ታወሰው። በዳያስፖራ ዓለም ውስጥ ያለው የፖለቲካ አዙሪትና የደመ ነፍስ ጉዞ መቼ እርቃኑንን እንደሚቀር ናፈቀው።
የራስን ሰራ ከመስራት ይልቅ እርስ በርስ መቧቀስ፤ ከመነጋገር ይልቅ እንደ ጋለሞታ አደባባይ ወጥቶ መዣለጥ፣ ከመመካከር ይለቅ ቦታ እንኳን ሳይመርጡ መታኮስ… ያበደው የስህተቶች ደራሽ ጎርፍ ናላውን ይንደው ጀመር። ምን ያልተበላሸ ነገር አለ? ጠየቀ!! ሰዎች ቁጭ ብለው መነጋገር የማይችሉት ለምንድን ነው? መልስ የሌለው ጥያቄ!! መነጋገር ካልቻሉ ለምን ልዩነታቸውን አክብረው የራሳቸውን ስራ አይሰሩም? ለዚህም መለስ የለም!! ካልሆነ ለምን አይተውትም!! ያበደው ጮኸ….
ላብ አደር- ውዝ አደር፣ እናቸንፋለን – እናሸንፋለን… ምሊኒየም- ሚሌኒየም… በአንድ ቃል ስንት ውዝግብ ነበር። ተሸክሞ የሚኖር ወዝ አደር ተባለ ላብ አደር… ሰዎቸ ከዘይትና ከአሳ የቱ እንደሚመርጡ ድምጽ በሚሰጡበት ዓለም … እኛ ገና በስያሜ እንናረታለን። ያበደው አቅለሸለሸው። በእምነት ደጅ ውዝግብ፣ “እዛኛው ቤት ያለው እየሱስ ይቅርብህ፤ እዚህ አዲስ እየሱስ አለ ና፣ ነይ፣ ኑ..” ምዕመኑን ዥጉርጉር ማድረግ!! “የእነ እገሌ ብሄር ደብር አትሂድ፣ አትሂጂ፣ አትሂዱ…” መላዕክትን በብሔር በልቶ አምነት፤ ፖለቲካው ” እኔን ተከተል፣ አትተንፍስ፣ አትቃውም፣ አትጠይቅ…” የሚል አባዜ የተጠናወተው አመራሮችና ጋሻ ጃግሬዎች የተሰገሰጉበት፤ ለመተቸት የሚሞከሩም ሲገኙ – ዝንጠላ፣ ስድብ፣ አብረው ሲሰሩ የሰሙትን ማዝረክረክ፣ ጥላቻ፣ ክፋት….
አሁን 2016 አለቀ። 2017 ተጀመረ፤ “እስኪ ወደ ልቡናችን እንመለስ” ትላለች ቦሰና። ቦሰና የእምነተዋን ማተብ እያማተበች ” እናቴ አስቢን” አለች። አዎ!! ብንታሰብ ደግ ነበር። ግን ለመታሰብም የሚያደርስ ልቡና ይኖረን ይሆን? ያበደው ጠየቀ!! ምን አልባትም አሁን የደረስንበት ደረጃና አገዛዝ ” የሚገባን ይሆን?” አሰበ። ከተቀመጠበት ተነሳ…. “አዋጅ… አዋጅ…. አዋጅ ” አለና በፍጥነት እየተራመደ ለፈለፈ። አንድ ወዳጁን አገኘ!! እንዲረጋጋ ተንገረውና እያጉረመረመ ዝም አለ። ተፋ!! አረፋ የሚመስል…..
አዋጁ አንዲህ ነበር ፤ የኢትዮጵያ ዘመን ያሳስባል። አሁን ጊዜው ራስንና ህሊናን የመግዛት ነው። የመንጋገር ነው። የመደማመጥ ነው። የመሰማማት ነው። ያልሆነላችሁ አቁሙ። ቢቻላችሁ ” አልሆነልኝም” በሉና ንስሃ ግቡ። ለማትችለቡበት የምትዘባርቁ ” እኔ እየረበሽኩ ነው” በማለት ውጡ፤ ብስድብ ፖለቲካ የተለከፋችሁ ተመለሱ፣ ያለ እኛ አገር አትመራም የምትሉም አለዝቡ፣ ህዝብን በተስፋ የምትሞሉ ይብቃችሁ፤ ታመነም አልታመነም ታመናል። ይብቃ!! በቃ !! በክብር!!
የአገሪቱን ፖለቲካ ወደ እርቅ እንመራለን ለሚሉና ሃሳብ ላላቸው በር ይከፈት፤ የሚበጀው እርስ በርስ መነጋገርና በሰላማዊ መንገድ ችግሮችን መፈታት ነው። አሁን የተያዘው የቅርጫ ጉዞ የትም አያደርስም። ተበጣጥሰናል፤ ተበልተናል፤ ተነጣጥለናል፤ ተፈረካክሰናል፤ በተስቦ ውስጥ ነን፤ ተስቦው ማጭድ ሳይጀምር የተዘራውን የቂም ዘር እናጽዳ… ያበደው ጥሪው አንድ ነው… የመንፈስ ልዕልና ይሏል ይህንን መረዳት ነው። ገዢ ተገዢ ሳይባል ሁሉም ልብ ይበል… ታመናል፤ ከታመምን ቆይቷል፤ ሀመሙ የጸና ነው፤ ገጀራም ሊኖርበት ይችላል፤ ኢትዮጵያ ለሁሉም ቤት ትሆን ዘንድ ሃላፊዎቹ ሁሉም ናቸው!! ያበደው እንባው ቀረረ አገር… አገር… እስኪ ልቡና ይስጠን፣ እስኪ የእርስ በርስ ፍልሚያ ይቁም ….  በ2017 ለእርስ በርስ ፍልሚያ ወገባችሁን ያጠበቃችሁ ግፉበት… ለሁሉም  መልካም አዲስ ዓመት!!

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0