Image may contain: 1 person

 ኢትዮጵያ ጠላት የምታሳፍር፤ ተጠቅማ የምትጠቅም አገር ትሆናለች፤
 የእኛ የውስጥ ሌቦችም መደበቂያቸው ትምክህትመና ጠባብነት ነው፤
 ኢህአዴግ ቀጣፊውን በቀጠፈውና ባጠፋው መጠን ለመቅጣት ቆርጧል፤
 ጫካ እያለህና ከተማ ከገባህ በኋላ ነገሮች እኩል አይደሉም፣

አንጋፋው የኢህአዴግ ታጋይና የህወሓት መስራች አቶ ስብሀት ነጋ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ቁልፍ ድርሻ ካላቸው ግለሰቦች መካከል አንዱና ዋነኛው ናቸው። አቶ ስብሀት (በአብዛኛው አቦይ ስብሀት በሚል መጠሪያ ይታወቃሉና እኛም በዚህ መጠሪያ እንቀጥላለን) ከአዲስ ዘመን ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለአገሪቷ ወቅታዊ ሁኔታና መጪው ጊዜ ዘርዘር ያለ መረጃን ሰጥተውናል። ሙሉ ቃለ መጠይቁንም እንደ ወረደ እንዲህ አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- ከኢህአዴግ ታላላቅ ሰዎች መካከል እንደ እርስዎ በብዙ ሚዲያዎች ላይ አስተያየት በመስጠትና በመጻፍ የሚታወቅ ያለ አይመስለኝም። አሁን ከዚያ እርቀዋል ምክንያቱ ምንድን ነው?
አቦይ ስብሃት፡- ማንም ሰው በሚዲያ እንዳይነጋገር የተከለከለበት ነገር የለም። እንዳልከው ግን አሁን ላይ ረዘም ላለ ጊዜ ከሚዲያ እርቄያለሁ፡፡ ኢህአዴግ ስህተቶቹን አስቀምጦ ለመፍታት ገበያ /አደባባይ/ ወጥቷል፤ ህዝብ የሚፈልገው እኔም የምፈልገውንም ነገር እየተናገረ ነው። ስለዚህ የእኔ መናገር አያስፈልግምና ለዚያ ነው ከሚዲያ የራኩት፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሁን አገራችን የገባችበት ጉዳይ ሁሉም የሚያቀው ነው፡፡ የዚህ ችግር መንስኤ በእርስዎ ድምዳሜ ምንድን ነው ይላሉ?
አቦይ ስብሃት፡-መንስኤውም ሆኑ ችግሮቹ ተገልጸዋል።ኢህአዴግ ለዚህ ተጠያቂ እኔ ነኝ ብሏል፡፡ ኢህአዴግ ለቆመለት አላማ ህዝብንና ሀገርን ማዕከል አድርጎ እራሱን እየፈተሸ አልሄደም፡፡ በአንድ ቃል የህዝባዊነት መንፈስ እና ውግንና ላይ ስንፈት ነበር፡፡ ድርጅቱ ሌት ከቀን አልሰራም፤ ይሄንንም እራሱ ለይቶ አስቀምጦታል፡፡
አዲስ ዘመን፡- አቦይ ይህ ችግር የድርጅቱ ወይስ የግለሰቦች?
አቦይ ስብሀት፡- በግለሰብ ወይንም ደግሞ በቡድን ስህተት ከተገኘ ኢህአዴግ ይጠየቃል። ምክንያቱም ድክመት ያሳየው ግለሰብ መወገድ ነበረበት፡፡ ዋናው ተጠያቂ ኢህአዴግ ሆኖ ግለሰቡም ቀጥሎ ተጠያቂ ይሆናል። ድክመቱ የግለሰብ፣ የሁለት ሰው፣ የአራት ሰው የምትለው አይደለም፤ በአጠቃላይ ችግሩ የኢህአዴግ ድክመት ነው፡፡ አንድ ሰው ድክመት ሲያሳይ ሁለት ሶስት ቀን መቆየት የለበትም፡፡ ስርአቱ፣ አሰራሩና አደረጃጀቱ በየጊዜው የሚለካ እንደመስታወት ከሩቅ የሚታይ መሆን አለበት፡፡ እንደምገነዘበው ግን የአንድ ሰው ስህተትም ይሁን የመንግስት አካል ሳይታወቅ ወይም እየታወቀ ሳይታረም ቆይቷል፡፡ አብዛኛው ግን እየታወቀ ይመስለኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ምክንያት ካሉት በተቃራኒው ሀገሪቷ ለገባችበት ወቅታዊ ችግር ምክንያቱ የፌደራሊዝም ስርአቱ ነው የሚሉ አሉ፡፡ እዚህ ላይ ምንድን ነው የእርስዎ ሀሳብ?
አቦይ ስብሃት፡- ፌዴራሊዝሙ በባህሪው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን ማዕከል አድርጎ የተዋቀረ ነው፡፡ ይሄ ህዝቡ እራሱ ፈልጎ ለዘመናት ታግሎ ያመጣው እና የህብረተሰብ ዴሞክራሲ መሰረት ነው፡፡ ይሄ ስርአቱን ያጠናክራል፣ በእኩልነት የተመሰረተ አንድነት ይፈጥራል፣ ህዝብን ነፃ አድርጎ እንዲንቀሳቀስ እድል ይፈጥራል እንጂ ለግጭትም ይሁን ለሌላ ችግር እድል የሚፈጥር አይደለም፡፡ ህዝቡ ሲፈልገውና ሲታገልለት የነበረ ስርዓት ነው የተዋቀረው፡፡ ለምሳሌ የኦሮሞም በለው የሲዳማ ነጻ አውጪ ግንባሮች የጠራ ፕሮግራም ባይኖራቸውም ሲታገልሉት የነበረው ይሄንን አይነት ስርዓት ለማዋቀር ነው፡፡ ፌደራሊዚሙም ይህንን ነው ያረጋገጠው፡፡ ስለዚህ ፌዴራሊዝሙ ፀጋ ነው እንጂ ጉድለት የሚፈጥር፣ ለጉድለት በር የሚከፍት አይደለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንግዲያውስ ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ እንዳስቀመጠው የችግሩ መንስኤ ራሱ መንግስት የፈጠረው የመልካም አስተዳደርና የውስጥ አሰራር ችግር ነው በሚለው ነው የሚስማሙት ማለት ነው፡፡ እንደዛ ከሆነ ለችግሩ መፍትሄ ሆኖ የቀረበው ተሀድሶ ማድረግ፤ በጥልቅ መታደስ የሚል ነው። ሀገራችን ከገባችበት ችግር አንፃር ተሀድሶ መፍትሄ ይሆናል ብለው ያምናሉ?
አቦይ ስብሃት፡- አዎን። በ1993 እና 1997 ዓ.ም ላይ ችግሮች ነበሩን፡፡ ያን ጊዜ የችግሮቹን መንስኤና መፍትሄ አሟጠን አስቀምጠን አባልና ህዝቡን አሰልፈን ብንሄድበት ኖሮ አሁን ተሀድሶ ውስጥ መግባት አይጠበቅብንም ነበር። እራሱን እያስተካከለ የሚሄድ፣ ሁሉንም ህብረተሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ ስርዓት ገንብተንም ቢሆን ኖሮ ወደ ሌላ ተሀድሶ መግባት ባላስፈለገንም ነበር፡፡ ለ15 አመት የተጠራቀሙ ችግሮች ናቸው ወደዚህ ያስገቡን።
በጥልቀት መታደስ ማለትም እኔ እንደሚገባኝ ከእንግዲህ ወዲህ ተሀድሶ የሚባል ነገር የለም ማለት ነው፡፡ ኢህአዴግ እንዳለው ፈጣን፣ የማያቋርጥ፣ ሁሉም በየደረጃውና በየአካባቢው ተጠቃሚነቱን የሚያረጋገጥበት ስርዓት ይገነባል ማለት ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግስት /DDS/ ማለትም ይሄው ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደ ኢህአዴግ ተመልሳችሁ ወደ ተሀድሶ ላለመግባታችሁ ምን ዋስትና አለ? ምክንያቱም ከ15 አመት በፊትም ተሀድሶ ተካሂዷልና?
አቦይ ስብሃት፡- ወደ ተሀድሶ ተመልሰን ላለመግባታችን መቶ በመቶ ዋስትናችን ህዝቡ ነው፡፡ ህዝቡ ለልማት፣ ለሰላምና ለዲሞክራሲያዊ እድገት ተሳትፎ ይፈልጋል፡፡ ኢህአዴግ ችግር የለብኝም ብሎ አያውቅም። ዋና ዋስትናችን ህዝቡ ነው፤ ኢህአዴግ ደግሞ ህዝብን ማሰለፍ ይችልበታል፡፡ ሌላ ዋስትና የለንም። ህዝቡ ስል ሰፊው ህዝብና ጥራት ያለው ካድሬንና አመራርንም ይጨምራል፡፡ ኢህአዴግ ህዝቡን ይዞ በማያዳግም መልኩ ችግሮች ከመፍታት ውጪ ሌላ አማራጭ የለውም፡፡ እተማመናለሁ ይሄን ያደርገዋል፡፡ ይሄ ካልተደረገ ግን በአንድ ሀገር ተሰባስቦ የመኖር ነገር አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ካልሆነ እንዳለፈው እየተንገዳገድን እንኖራለን ወይም እንበታተናለን። ኢህአዴግ ጠያቂ ህዝብ ፈጥሯል። ስለሆነም ከዴሞክራሲያዊነትና ከልማታዊነት ውጭ ዝም ብሎ የሚቀመጥ ህዝብ አይኖርም፡፡ ኢህአዴግ ይህንን አይነት ህዝብ መፍጠሩ ታላቅ ድሌ ነው ብሏል፤ እውነትም ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርስዎም እንዳሉት ኢህአዴግም ህዝቡን በያዘበት በትግሉ ዘመን ተፈቃሪና ተወዳጅ ፓርቲ ነበር የሚሉ አሉ፡፡ በራሱ ነፃ ግዛቶች ላይም ፍትህን በማስፈን ደረጃ በጣም የተዋጣለት ፓርቲ ነበር፡፡ መንግስት ከሆነ በኋላ ግን ያንን መድገም አልቻለም። የህዝብ ቅራኔና ተቃውሞ ተነስቶበታል። ምክንያቱ ምንድን ነው? በፊት የነበረውን ህዝባዊነት ለማምጣት ምን መሰራት አለበት ይላሉ?
አቦይ ስብሃት፡- እንዳልከው በትጥቅ ትግሉ ያሸነፈው ብረት አይደለም። ያሸነፈው፣ ብረት እንዲመጣም ያደረገው የሕዝቡ መንቃት፣ መደራጀት# ማስታጠቅና ማሰማራት ነበር፡፡ አሁን ላይ ይሄ ቀንሷል፡፡ ጫካ እያለህና ከተማ ከገባህ በኋላ ነገሮች እኩል አይደሉም፡፡ ከተማ ብዙ የሚያዳክምና የሚያታልል ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ሙስና ላይ ትግል ሁኔታውን የሚመጥን ትግል አልተደረገም፡፡ ህዝባዊነትን የሚፈታተነው ግላዊነት ነው፡፡ ለግለኝነት አመቺ ሁኔታ ያለው ደግሞ ከተማ ነው፡፡ ከተማ ውስጥ ይሄንን ሁኔታ ተገንዝቦ ችግሩን የሚመጥን የፖለቲካ ትግል አልነበረም፡፡ ኢህአዴግ መንግስት ከሆነ በኋላ ያንን የሚመጥን ትግል አላዳረገም፡፡ ግለኝነት ህዝባዊነትን ተፈታተነው፡፡ ለህዝባዊነትና ሀገራዊነት የሚመጥን ትግል ነው መደረግ ያለበት። ትግሉም ተቋማዊ ሆኖ መሄድ አለበት፡፡ አሁንም ሁኔታውን የሚመጥን ትግል መደረግ ይገባዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢህአዴግ በታሪኩ የገጠመው ትልቁ ፈተና አሁን ያጋጣመው ነው ማለት እንችላለን? በኢህአዴግ ዘመን እንደ አሁኑም ኢትዮጵያ ከዳር ዳር ሰላሟ ተናግቶ አላየንም።
አቦይ ስብሃት፡- አሁን ያለንበት ሁኔታ ፈታኝ ነው፡፡ አሁን የተፈጠረ ሳይሆን እየተጠራቀመ የመጣ ነው፡፡ አሁን እሱን ይዘን የማንቀጥልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ እንዳልከው በኢትዮጵያ የሠላም ማጣት ይኖራል የሚል ግምት አልነበረም፡፡ ክልሎቻችንን የምናስተዳድርበት የሠላም ማጣት ይኖራል የሚል ግምት በውስጥም በውጭም አልነበረም። በኢህአዴግ ታሪክ ይሄ አይነት ችግር የመጀመሪያው ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከምርጫ 97 በኋላ ተነስቶ ከነበረው ሁከት ጋር ሲነፃፀር ከባዱ የትኛው ነው? ለስርአቱስ አደገኛ የነበረው የትኛው ነው?
አቦይ ስብሃት፡- ያንጊዜ የነበረው ይሄን ያህል ስፋት አልነበረውም፡፡ በልማቱና በሌሎች ነገሮች ያለመርካት በከተሞች በተለይም በወጣቶች ላይ ነበር። ያም ሆኖ ሁከቱን የቀሰቀሱት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ነበሩ፡፡ የ1993ቱም የውስጥ ችግር ነው፡፡ ስለዚህ ከዘጠና ሰባቱ የአሁኑ ይከፋል፤ ውስብስብም ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እውነት ነው ፡፡ ያኔ ወደ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅም አልገባንም ነበር፡፡ ምን አልባት ኢህዴግን ጠንካራ ፓርቲ የሚያስብለው 1997 ዓ.ም ላይ ያንን ያህል የህዝብ ተቀባይነትን አጥቶ /በተለይ በከተሞች/ በምርጫ 2002 ዓ.ም ላይ መልሶ ያንን የህዝብ ይሁንታ ማግኘቱ ነው የሚሉ አሉ። ከዚህ ተነስተን አሁንም ያስኮረፈውን ህዝብ ልብ መልሶ የማግኘት ተስፋ አለው ማለት እንችላለን ?
አቦይ ስብሃት፡- ኢህአዴግ ማህበራዊ መሰረቶች አሉት። ሙሁሩ፣ ገበሬው፣ ወዛደሩና ትናንሽ ባለሃብቱ የፓርቲው መሰረቶቹ ናቸው፡፡ ልማታዊ ባለሃብቱም መተክያ የሌለው የኢህአዴግ አጋር ነው፡፡ እነዚህን መሰረቶቹን አደራጅቶ ወደስራ እንደሚገባና ወደፊት እንጂ ወደ ግራ ወደ ቀኝ የማይልበት ደረጃ ላይ እንደሚደርስ አምናለሁ፡፡ አንተ እንዳልከው ሳይሆን ካልከውም በላይ ካሁን በፊት ወዳልነበረበት ጥንካሬ እንደሚመጣ መቶ በመቶ እተማመናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ኢህአዴግን በቅርብ የሚያውቁ ሰዎች «የኢህዴግ ድርጅታዊው ጉባኤው ብዙም ጠንካራ አይደለም፤ ብሄራዊ ድርጅቶቹ ያሉበትን ሁኔታ የሚፈትሽም አይደለም፤ ተቻችሎ የማለፍ ነገር ነግሷል። ማሳያውም 10ኛው የኢህአዴግ ድርጅታውዊ ጉባኤ በተካሄደ በወራት ውስጥ በአማራና በኦሮሚያ ክልል ህዝቡ ለተቃውሞ አደባባይ መውጣቱ ነው» ይላሉ። የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ መፈተሽ የለበትም ይላሉ?
አቦይ ስብሃት፡- ያልከው ትክክል ነው፡፡ ተቻችሎ መኖር፣ ህዝባዊነት መሸርሸር እና ነገሮችን አስቀድሞ ያለማየት ችግር አለ፡፡ ኢህአዴግም የእያንዳንዱን አባል ድርጅት በአጠቃላይ ደግሞ የኢህአዴግ ጉባኤ መፈተሽ እንዳለበትና የሚፈትሹት መሆኑንም ነው እኔ የምገምተው፡፡ አንድ አጀንዳ ሆኖም እንደሚፈትሹት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ መፈተሸ አለበት? አዎ መፈተሸ አለበት።ያለፈውም መገምገም አለበት፡፡ ይሆናል ወይ? እንደሚሆን ነው የምገምተው፡፡ ይሄ አቋሜ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርሶ ጋር የድሮው የትግል መንፈስ አለ ብዬ ስለማምን በትክክል ጉባኤው ምን አይነት ቢሆን ብለው እንደሚመኙ እንዲነግሩኝ እፈልጋለሁ።
አቦይ ስብሃት፡- የትግሉ መንፈስ ባብዛኛው አሁንም አለ፡፡ በተለይ በሰፊው አባልና በኢህአዴግ ማህበራዊ መሰረቶች አሁንም የትግል ስሜቱ እንዳለ ነው። አንዱና ዋነኛው በጥልቀትም በስፋትም መታደስ ያለበት የጉባኤው ሂደትና ይዘት ይመስለኛል፡፡ ዝግጅቱ ረዘም ያለ ጊዜ መውሰድ አለበት፡፡ አጀንዳዎቹ ሃገራዊም# ድርጅታዊም ሆነው ሁሉም በየደረጃ የሚወያይባቸውና በየጉባኤው እየተስተካከሉ የሚሄዱ የረጅም ዘመን አቅጣጫ የሚያመላክቱ ቢሆኑ እመርጣለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ጥሩ፤ በጉባኤው አዳራሽ ውስጥ ያለው መንፈስ ምን መምሰል አለበት? በቀደመው ዘመን የኢህአዴግ የመታገል መንፈሱ እና አንተ እንደዚህ ነህ አንተ እንደዚያ ነህ የመባባሉ ነገር በጣም ጠንካራ እንደነበር ይነገራል። በሂደት ግን ይሄ ነገር እየጠፋ ነው የሚባል ትችት ይቀርባል። በዚህ ዙሪያ ምን ይላሉ?
አቦይ ስብሃት፡- እየጠፋ ሳይሆን እየቀነሰ መጥቷል። ያለ ምንም ምህረት ማን ምንድንነው የሚለው ነገር በደንብ መታወቅ አለበት። ጉባኤተኛ የማያውቀውን እየመረጠ አልመጣም ለማለት አይቻልም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በጉባኤው ላይ ብሄራዊ ድርጅቶች በሪፖርታቸው ትክክለኛውን ገፅታቸውን ያቀርባሉ? ይሄንን ልጠይቅ የቻልኩት በ10ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ ድርጅቶቹ ህዝቡ ኢህአዴግ ብቻ ነው ያለኝ የሚል አይነት ሪፖርት ባቀረቡ በወራት ውስጥ ነው በአማራም ይሁን በኦሮሚያ የተፈጠረው ሁሉ ሁከት የተፈጠረው። እንዲያው ይሄንን ሲያዩ የሚቀርበው ሪፖርት የውሸት ነገርም ያለበት አይመስልዎትም? ይሄ የእኔ ድምዳሜ ነው። የእርስዎስ?
አቦይ ስብሃት፡- የእኔም ድምዳሜ እንደሱ ነው፡፡ ይሄን አምኖ የሚመጣ ጉባኤ መሆን አለበት፡፡ ጉበኤ መደምደሚያ ነው፡፡ በጉባኤው ዋዜማ ይህን የእርካታ በሽታ መኖሩን እያመነ የሚመጣ ጉባኤተኛ መሆን አለበት፡፡ ያስቀመጥናቸው ችግሮች በአንድ ላይ ችግሮቻችን ለመቅረፍ ይቅርና በአንድ ላይ ለመሆንም አያስችሉንም። እንደ ኢትዮጵያ ህዝቦች በአንድ ላይ በሰላምና በእድገት ዘላቂ ጐዳና ለመኖር የማያስችለንን በሽታ ተሸክመናል ብለው የሚያምኑ ድርጅቶች መሆን አለባቸው፡፡ ጉባኤው ህዝቡን ማዕከል አድርጎ አንድነት በዲሞክራሲያዊ እኩልነት ላይ የሚፈጥር መሆን መቻል አለበት፡፡ ይሄ ብቸኛው ኢትዮጵያን አንድ አድርገን የምንሄድበት መንገድ ነው። እያንዳንዱ ድርጅትና ጉባኤተኛ በዚህ መንፈስ መንቀሳቀስ አለበት። አጋር ድርጅቶችም ጭምር። ስለዚህ ያለፈው ጉባኤም መገምገምና መስተካከል አለበት፡፡የፖለቲካል ፓርቲ ምንነት ባጠቃላይና በኢትዮጵያ ደግሞ በተለይ የራሱ የሆነ ጥናት የሚያስፈልገው ቢሆንም በጥልቅ መታደስና የበሰለ ጉባኤ ማድረግ በኢትዮጵያ ማህበራዊ መሰረታቸው የታወቀ የፖለቲካል ፓርቲዎች እንዲመሰረቱ መንገድ ይጠርጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ወደ ሌላ ጉዳይ ልውሰድዎ፤ የስርዓቱ አደጋ ተብለው የተለዩትን ትምክህት፣ ጠባብነትና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማክሰም መንግስት እየተጓዘበት ያለው መንገድና ስልት ምን ያህል አስተማማኝ ነው ብለው ያምናሉ? በቀጣይስ ምን መሰራት አለበት ይላሉ?
አቦይ ስብሃት፡- በእኔ ግምት በዝግጅት ደረጃ እንጂ የተሰራ ነገር የለም ነው የምለው፡፡ ድክመቶቻችንን የመለየት ስራ ተሰራ እንጂ ለማስወገድ የተጀመረ ስራ የለም፡፡ ዝግጅት እንዳለ ግን እገነዘባለሁ፡፡ ለማስወገድ የተሰራ ነገር ግን የለም፡፡ እነዚህ ተለይተው የተቀመጡ ሀጢያቶች ለሁሉም ነገር ዳገት ናቸው። ኢህአዴግ እነዚህን ለማስወገድ በዝግጅት ላይ እንዳለ ግን እገነዘባለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ይሄን ያህል አመት በዝግጅት ላይ ማለት ይቻላል አቦይ?
አቦይ ስብሃት፡- ምንድን ነው መሰለህ፤ አሁን ያለው ችግር ጠባብነትና ትምክህት በሁለት ወር ወይንም በሶስት ወር ይወገዳል የሚባል አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ተሀድሶ የጀመረው ነሀሴ ይመስለኛል፡፡ ይሄ የችግሩን ምንነት፣ ስፋት እና መጠን አጥንቶ የማን ፖለቲካ እንደሆነ ወ.ዘ.ተ ለመለየት ቀጣይነት ያለው ስራ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ኢህአዴግ በጥልቀት ለመታደስና ህዝብንና አገርን ከጠላት አመለካከት ነፃ ለማውጣት በዝግጅት እንዳለ አውቃለሁ፡፡ ይሄ አዋጅ አይደለም፤ ሂደት ነው፡፡ ይሄ ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል? ጊዜ ላስቀምጥ አልችልም፡፡
ሳይነካ የቆየ አመለካከት ነው። ጉዳዩ እራሱ ገፍቶ ስለመጣ ኢሀአዴግ ችግሮቹን አንድ ሁለት ብሎ ለይቶ አስቀምጧል፡፡ በጥልቀት መታደስ ማለት ችግሩን በጥልቀት መረዳት ማለት ነው፡፡ ይሄን ሳንፈታ ዴሞክራሲያዊት አገር መፍጠር አንችልም፡፡ እኔ የምጠይቀው የህዝቡን ትዕግስት ነው። ኢህአዴግም ጊዜ ሳያጠፋ ችግሮቹን እየበጣጠሰ መሄድ አለበት። በሁለት አመት እና በሶስት አመትም የሚያልቅ አይመስለኝም፡፡ በዚህ ሂደት የሚገኙ መጠናዊ ለውጦች ግን ይኖራሉ፡፡ ወደ ጠራ አይነታዊ ለውጥ ለመግባት ግን ጊዜ የሚወስድ ይመስለኛል፡፡ አንዱ ወሳኝ መድረክ ጉባኤው ነው፡፡ ህዝቡም ለዘላቂ ሀገራዊ ጥቅም በትእግስትና በሰላም መታገል አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ እነዚህ ችግሮች አብረውን ይቀጥላሉ ማለት ነው?
አቦይ ስብሃት፡- እየተቃለሉ እየተቃለሉ አደጋነታቸውም እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ የስርአቱ ዋና አደጋ መሆናቸውም እየተዳከመ ይሄዳል፡፡ መታወቅ ያለበት ህዝብ ህዝብን እንደማይጨቁን ነው። ይህን የሚያመጣው ስርአቱና አንተ ትበልጣለህ ሌላው ግን ሌላ ነው የሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ናቸው። በቀደመው ጊዜም ስርዓት ይሁን አሁንም የእነሱ ቅሪቶች አንተ ትበልጣለህ የሚል ያመጣብን ጣጣ ነበረ። ህዝቡ የእነዚህን ጠንቅነት ማመን አለበት፡፡ አሁን ግን ይሄን የሚያስተናግድ በር የለም፡፡ አንዱ በአንዱ ላይ የበላይነቱን የሚያረጋግጥበት ስርአት የለም፡፡ ኢህአዴግ ይሄንን ሳልፈታ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት የለም ብሎ ያመነ ስለሆነ እንደሚፈታው እርግጠኛ ነኝ፡፡ በዚህ አስተሳሰብ ለመኖር የሚፈልጉ ፓርቲዎችም ሌቦችም አሉ። የእኛ የውስጥ ሌቦችም መደበቂያቸው ይሄ ነው። በአጭሩ እነዚህን አስተሳሰቦች እያሸነፉ መሄድ ያስፈልጋል። ሰልፍ ማለት የአመለካከት የህዝብ ጠላትን እያስወገድክ ወዳጅህን የምትሰበስብበት ነው፡፡ ህዝብ ህዝብን አይጨቁንም፤ አይበድልም፤ አይጠላም፡፡
አዲስ ዘመን ፡-እርስዎም እንዳሉት ዛሬ አንዱ በአንዱ ላይ የበላይ የሚሆንበት እድል ዝግ ነው። ስለሆነም አማራ ክልል ላለው ህዝብ መጨቆንና መበደል ተጠያቂው ብአዴን፤ ለኦሮሚያው በደልም ኦህዴድ፤ ለትግራዩም ህወሓት፤ ለደቡብ ህዝብ በደል ደግሞ ደኢህዴን ናቸው፡፡ እውነታው ይሄ ቢሆንም አሁን በጥልቀት መታደሱ ላይ በየብሄራዊ ድርጅቶች ላይ የህወሓት የበላይነት አለ፤ ለችግሮቹ ተጠይቂው ህወሓት ነው የሚሉ ሀሳቦች እየተደመጡ ነው፡፡ እዚህ ላይ የእርስዎ ሀሳብ ምንድንነው አቦይ?
አቦይ ስብሃት፡- በአመለካከት ደረጃ ከሆነ ዲሞክራሲያዊ ብሄርተኝነትን የማስፈኑ ስራ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ነው፡፡ በአንድ ብሄር ጠባብነት ካለ ኢህአዴግ ነው መጠየቅ ያለበት፡፡ ምክንያቱም ኢህአዴግ የሁሉም ድርጅቶች ግንባር ነው፡፡ በትግራይ ትምክህት ካለ ኢህአዴግ እንደ ግንባር መታገል አለበት፡፡ ሌላውም ጋር ትምክህትም ሆነ ጠባብነት ካለ ኢህአዴግ መታገል አለበት፡፡ ልማት በዋናነት የክልሉ መንግስት ጉዳይ ሊሆን ይችላል።ፖለቲካው ግን ድንበር ያለው ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ ጠባብነትን፣ ትምክህትን አብረን መመከት አለብን፡፡ ይሄ በየትኛውም ብሄር ሲታይ መመከት መቻል አለብን፡፡ እያንዳንዱ የኢህአዴግ አባል ድርጅት ኢህአዴግ ሆኖ ማንኛውንም የተዛባ የፖለቲካ አመለካከት መመከት አለበት፡፡
አንተም እንዳልከው ህዝቡ ማወቅ ያለበት አንዱ ብሄር ሌላውን ሊጨቁን ክፍት ቦታና እድሉ አለ ወይ? የሚለውን ነው። የትግራይ ህዝብ ኦሮሚያ ውስጥ የተሰበሰበን ገንዘብ ላኩልኝ ይላል ወይ፤ መሬቱን ላስተዳድር፣ ቋንቋዬን ባህሌን አስተምሩ ይላል ወይ፤ በምን አልፎ ነው አንድ ብሄር ይሄንን በሌላው ብሄር ላይ የሚያደርገው። ይሄ ዝም ብሎ ግንዛቤ ነው እንጂ በተጨባጭ የለም። ህዝቡ የለም ብሎ ማመን አለበት። ይሄ የሌቦች መደበቂያ ስልት ነው።
የሚቀጠቅጠው የሚዘርፈው እራሱ ሆኖ ሳለ እንትና ወሰደብህ ይላል። አንተን የመሰለ የለም እያለ እያደነዘዘ የሚዘርፈው እሱ እንደሆነ፤ ፍትህ የሚያጓድልበት የራሱ ልጆች እንደሆኑ፣ ብሄር ከብሄር ጋር የሚያጋጨው አንተን የሚመስል የለም እያለ የሚያቆረቁዘው ራሱ መሆኑን ማወቅ አለበት።
እኔ የትግራይ ህዝብን አንተን የመሰለ የለም ካልኩት ገድየዋለሁ ማለት ነው። እንደዚህ ካልኩ ከእኔ በላይ ገዳይ የለውም፤ በመንግስት ላይ ባለፈው ስርዓት ባጉረመርም ውሸት፤ ዋናው ጠላቱ ካንተ በላይ የለም ያልኩት እኔ ነኝ። ህዝቡ ማወቅ ያለበት ይሄንን ነው። አዕምሮውን እየሰለቡ ሌላ ነገር እንዳያስብ የሚያደርጉት የራሱ ዘራፊ ልጆች ናቸው።
አዲስ ዘመን፤ ስለዚህ የህዝቡ ጠላት አጠገቡ ያለው ነው እያሉኝ ነው?
አቶ ስብሀት፤ ተራ ጠላትም ሳይሆን ከባድ ጠላት። አዕምሮህን ከሰለበህ ምን ታደርጋለህ? አገርህ የውጭ ጠላት ቢያዝብህ ነገ ታግለህ ታወጣዋለህ። አዕምሮህን ከተያዝክ እኮ በድን ነህ። ምንም አዲስ ነገር ልትቀበል አትችልም። ስለ ሳይንስም ስለቴክኖሎጂም ወዘተ ልታስብና ልትይዝ አትችልም፡፡ ስለአለፈ እንጂ ስለወደፊት አታስብም፡፡ ምክንያቱም አዕምሮህን ተሰልበሃል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ወደሌላ ርዕሰ ጉዳይ እንሂድ፤ ብሄራዊ መግባባት ተፈጥሯል ብለው የሚያምኑ እንዳሉ ሁሉ፤ እዚህም እዚያም የሚነሱ ጉዳዮችን በመጥቀስ ብሄራዊ መግባባት ቢፈጠር ኖሮ ይሄ ግጭት ባልተፈጠረ የሚሉ አሉ። እርስዎ ብሄራዊ መግባባት ላይ ተደርሷል ብለው ያምናሉ?
አቦይ ስብሃት፡- ብሔራዊ መግባባት የሚባለው ቃሉም ብዙ አይገባኝም። ቀደም ብለን የጠቀስነው የአስተሳሰብ ሰለባ ካለ ብሄራዊ መግባባት አይመጣም። ህገመንግስቱም በየብሄራችን ሆነን አንድ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ማህበረሰብ እንፈጥራለን ነው የሚለው፡፡ ይሔ ደግሞ የሚፈጠረው እያንዳንዱ ብሄር ሌላውን ብሄር በመሬቱ የሚያስተናግድ ከሆነ ነው፡፡ የሶማሌ ሀብታም፣ የአማራ ሀብታም፣ የኦሮሞ ሀብታም፣ የትግራይ ሀብታም ሌሎቹም ሀብታሞች ወደሌላው ክልል ቢሄዱ ወገኖቼ ናቸው ብሎ መቀበልና እኩል ማየት አለ ወይ? እኔ አይመስለኝም። ካለ ግን ብሄራዊ መግባባቱ ተፈጥሯል ማለት ነው። በፕሮግራም ደረጃ ግን አለ። መግባባት በአየር ላይ የሚፈፀም አይደለም፡፡ የአንተ ትርጉም እንደሱ ከሆነ ለእኔ ብሄራዊ መግባባት ያለ አይመስለኝም። አሁን ያለው ትምክህት፣ ጠባብነትና እና አክራሪነት ነው።
ብሔራዊ መግባባት የሚተገበረው በሁለት ነገሮች ይመስለኛል፡፡ አንዱ ያው ስንለው እንደነበረው በፖለቲካ ይመስለኛል፡፡ ሁለተኛው ግን ነፃ የካፒታልና የሰራተኛ እንቅስቃሴ ሲኖር ነው የሚመስለኝ፡፡ ለምሳሌ ትግሬው የኦሮሞ ሌባንና የትግራይ ሌባን አንድ አድርጐ ያያቸዋል? የኦሮሞ ልማታዊ ባለሃብትና የትግራይ ባለሃብትስ አንድ አድርጐ ያያቸዋል? ሌላውም ሌላውም እስቲ እንፈትሽ፡፡
አዲስ ዘመን፡- መንግስት ሀገሪቷ ከገባችበት ቀውስ ለመሻገር ከተሀድሶ ባሻገር ካቢኔውን በአዲስ መልክ ማዋቀር መፍትሄ ነው ብሎ ጥቅምት 2008 ዓ.ም የተቋቋመውን ካቢኔ በዓመቱ ህዳር 2009 ዓ.ም አፈርሶታል። ያኛውም ተስፋ የተጣለበት ካቢኔ ተብሎ ነበር፡፡ የአሁኑ ካቢኔም በምሁራን የተዋቀረ ነው ተብሏል፡፡ እርስዎ በአዲሱ ካቢኔ አወቃቀር ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድን ነው? ለችግሩስ ይሄ እርምጃ መፍትሄ ይሆናል ብለው ያምናሉ?
አቦይ ስብሃት፡- እኔ ስለ አዲሱ ካቢኔ አወቃቀር የራሴን አመለካከት ነው ልነግርህ የምችለው፡፡ ምክንያቱም ብዙ አላውቅም፡፡
አዲስ ዘመን፤ ላያውቁ ይችላሉ፤ ግን የኢትዮጵያን ፖለቲካ ጥንቅቅ አድርገው ከሚያውቁና እንዲያውም የኢትዮጵያ ፖለቲካ አባት አድርጌ ከማያቸው ሰዎች መካከል አንዱ እርስዎ ነዎት፤ ብዙ ዘመንዎንም በፖለቲካው ላይ ነው ያሳለፉት፤ ስለዚህ ይሄ ካቢኔ ማየት የሚፈልጉትን አይነት ስርዓትና አገር ለመፍጠር ወደዚያ ይወስዳል?
አቦይ ስብሀት፤ አባት ወዘተ የሚለው ይቅርና እኔ ይሄንን በአጭሩና በግሌ ነው የምመልስልህ። የካቢኔ ማፍረስ እና መገንባት ነው ወይ የተካሄደው? ሶስት ነገሮች አሉ፤ ቀጣይነት፣ መሻሻልና መለወጥ የሚባሉ፡፡ አንድ ስርአት እደዚህ እያደረገ ካልሄደ መቀጠል አይችልም። የአሁኑ የካቢኔ ለውጥ ነው ወይ ብትለኝ አይደለም፡፡ የካቢኔ ማሻሻያ ነው የምልህ፡፡ አዲስ የተሾመው ነው የሚበዛው ነባሩ ነው ብትለኝ እውነቱን ለመናገር አላውቅም፡፡ ይሄ ለውጥ ያመጣል ወይ? ሰው ማስቀመጥ በራሱ ለውጥ አያመጣም። ማስቀመጥና በተቋሙ ተጠያቂ ማድረግ፤ ተቋማዊ ሁነው ተጠያቂነት ያለበት ስርአት ፈጥረው ይሄዳሉ ወይ ብዬ ራሴን ብጠይቅ ቀላል አስተያየት እሰጣለሁ፡፡
ተሿሚው ወደ ተቋሙ ሲሄድ ጥሩውን ማስቀጠል፤ የነበረው መጥፎውን ማሻሻል አዲስ ጥሩ ነገር ማስገባት ነው ወይንስ በጅምላ መርገም ነው የሚያስበው? አንዳንዱ የነበረችውን ይዞ የሚቀጥል አለ ሌብነትም ቢሆን፡፡ ሌላው ደግሞ የነበረውን ሙሉ ለሙሉ ደምስሶ በአዲስ የሚቀይር አለ፡፡ ሌላኛው ደግሞ የነበረውን እያሻሻለ የሚሄድ አለ፡፡ ጥያቄህን በትክክል መልሼ ከሆነ አላውቅም፤ ለእኔ የሚመስለኝ ግን የተደረገው የካቢኔ ማሻሻያ ነው እንጂ ለውጥ አይደለም፡፡ ማሻሻሉስ ጥሩ ነው ወይ? ብትለኝ ጥሩ እንዲሆን ተስፋ አለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ካቢኔው በምሁራን የተዋቀረ ካቢኔ ነው ይባላል፡፡ በእርግጥ በኢህአዴግ ዘመን ኢትዮጵያ እደዚህ አይነት በምሁራን የተዋቀረ ካቢኔ አልነበራትም ማለት ነው? ይሄንን ሲሰሙ እርስዎ ምን ይሰማዎታል?
አቦይ ስብሃት፡- እኔም አንተ እንደሰማኸው በምሁራን የተዋቀረ ካቢኔ ሲባል እሰማለሁ፡፡ በመጀመሪያ በኢትዮጵያ ታሪክ እንደ ኢህአዴግ በተማረ ሀይል የተደራጀ የለም፡፡ የቀበሌ አመራር እንኳን ዲፕሎማ የሌለው የለም፤ የወረዳ ካቢኔም ዲግሪ የሌለው ሰው ያለ አይመስለኝም፤ የክልል ካቢኔም እንደዚያው። የፌዴራል ካቢኔውም በሙሉ የተማሩ ነበሩ። ቁጥራቸው ጨምሮ ሊሆን ይችላል። የወጡትም የተማሩ ዶክተሮችም ናቸው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በዶክተሮች የሚለው ውሸት ነው፡፡ ቁጥራቸው ግን ጨምሮ ይሆናል። ትምህርት ግን በራሱ ብቻውን ፀጋ ነው የሚባለው ውሸት ነው መለኪያው ያንን ትምህርት ተምሮ የሚያመርተው እውቀት ለማን ይጠቅማል ነው? ትምህርት ደግሞ እዳም ሊሆን ይችላል፡፡ መለኪያው ወገንተኝነት መሆን አለበት። ፕሮፌሰር ሆነው እኮ ያን የጨለማና የእልቂት ዘመን ደጉ ዘመን ብለው የሚናፍቁ አሉ፡፡ እና ትምህርት በራሱ ጥሩ ነው አይባልም፡፡ ጥሩ ነው የሚባለው ባሰላለፉ ነው፡፡ መታወቅ ያለበት ትምህርት እዳም ነው፤ ፀጋም ነው። ዋናው አሰላለፉ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከካቢኔው ጋር በተያያዘ አብዛኛው ወደ አመራር ውስጥ የገቡት በቁጥርም ካየነው መምህራንና ለፖለቲካው እንግዳ ናቸው። የኢህአዴግ ፖለቲካ ደግሞ ሲበዛ ጠንካራና ከባድ ነው፡፡ ፖለቲካ በራሱ መሰጠትን ይፈልጋል። እነዚህ አዳዲስ የካቢኔ አባላት ፖለቲካው ገብቷቸው ወደ ስርዓቱ ቅኝት እስኪገቡ ድረስ ጊዜ ይወስዳል። ህዝቡ ደግሞ ከሚያዲውም ከፖለቲካውም ቀድሞ ሄዷል። እና ይሄ ካቢኔ የማህበረሰቡን ጥያቄ በሚፈለገው ፍጥነት ይመልሳል ይላሉ?
አቦይ ስብሃት፡- ሰው የነበረበት ሙያ መሀንዲስም ይሁን መምህር ፖለቲካዊ ማንነቱን አያሳውቅም፡፡ ዋናው ነገር ወገንተኝነቱ ነው። ሰው የሚፈጠረው በተቋም ነው፡፡ የፓርቲም ይሁን አሊያም የመንግስት ተቋም መሪውን ህዝባዊ መሪ አድርገው ይፈጥሩታል ወይ? ተቋሞቻችን መሪ ያፈራሉ ወይ? ይሄ ነው ዋናው ነገር። እናም ወገንተኝነቱ ማለት በመሰረቱ ህዝባዊነቱና ሃገራዊነቱ ካለ የፓርቲውም የመንግስቱም የተቋማት ብቁ ያደርጉታል፡፡ የሚሻሻል የሚቀጥል የሚለውን ለማድረግ የበቃ ይሆናል፡፡ ኢህአዴግ አሁን በሚያደርገው ጥልቅ ተሃድሶ ብቁ ሰዎች እንደሚፈጥር አምናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኢህዴአግ ምክር ቤትና የድርጅቶቹ ማእከላዊ ኮሚቴ አካባቢ ያለመነካካት ነገር እንዳለ ይሰማኛል። ምክንያቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀር የመንግስትን ስልጣን ለግል የማዋል ዝንባሌ ተግባር ነገር አለ ብለው ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ይሄ ነገር ተመንዝሮ እከሌ ይሄን አድርጓል እከሌ ይሄ ነው ጥፋቱ የሚል ነገር እስካሁን አልተሰማም፤ አልታየም። እዚህ ላይ ምን ይላሉ? ህዝቡ የሚጠብቀው በዚህ ጉዳይ የሚወሰደውን እርምጃ ማየትና መስማት ነው።
አቦይ ስብሃት፡- ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ ብሄርተኝነት አንዱ ችግር ነው፤ ሌላው ሙስናና ብልሹ አሰራር ነው። እነዚህ ደግሞ የጥልቅ ተሀድሶው አጀንዳዎች ናቸው፡፡ ስልጣንን ለግል ጥቅም ማዋል የሚለው አንዱ ስርዓት ለማስያዝ እየተበጀለት ያለ ጉዳይ ነው። የጥልቅ ተሀድሶው አካሎች ናቸው፡፡ እንዳልከው ህዝብም በጣም የሚጠብቀው ይሄንን ነው፡፡ ይሄ እንዴት ይሄዳል? መቼ ይጀምራል? ከማን ይጀምራል? የሚለው ጥያቄ ነው ያለኝ እንጂ ኢህአዴግ ታጥቆ የተነሳበት ቀጣፊውን በቀጠፈውና ባጠፋው መጠን የሚቀጣበት፤ ይሄ ተቻችሎ መሄድ የሚያበቃበት ስርአትን ለመገንባት ቆርጧል። ጠባብነትንና ትምክህትን የሚያመጣውም ይሄው ተሸፋፍኖ መሄዱ ስለሆነ ገና ያልተጀመረ የሚጀመር አድርጌ ነው የምወስደው። ጠቅላይ ሚኒስትሩም አስቀምጦታል፡፡ ኢህአዴግም እንደ ድርጅት አስቀምጦታል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ግን ተግባር የለማ አቦይ።
አቦይ ስብሀት፤ ተግባር የሚጀምር ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፤ እንጠብቅ? እርስዎ የቅርብ መረጃ አለዎት?
አቦይ ስብሃት፡- እኔ አሁን የቅርብ መረጃ የለኝም፡፡ አሁን ኢህአዴግ የሚታማው ይናገራል እንጂ አያደርግም አይደለም? አሁን ግን ይደረጋል፡፡ ሲያደርግ ደግሞ ከላይ በከፍተኛ አመራር በስርዓት የሚጀምር ይመስለኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ ቀደም ባሉት አመታት ወደ ማረሚያ ቤት የገቡትን ሚኒስትሮች የሚቀላቀል ሚኒስትር ይኖራል?
አቦይ ስብሀት፤ የእነሱም ቢሆን ስርዓቱ ሳይስተካከል ነው የሄዱት። ሰው መልቀምም ብቻውን ዋጋ አይደለም። ኢህአዴግ ያንን የቅጥፈት ሁኔታ የፈጠረውን ስርዓት እያስወገደ እያስተካከለ እንደሚያደርገው፤ በምሬትም እንደሚሄድበት ነው ያለኝ ግምት።
አዲስ ዘመን፤ ካልሄደበትስ?
አቦይ ስብሃት፡- ችግሩ እየተባባሰ ይቀጥላል፤ ሀገር ይፈርሳል፡፡ እንደሌሎች የአፍሪካ አገሮች እየሰረቅንና እየተንገዳገድን ለመቀጠልም እድል የለንም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ ጨዋታው በሀገር እና በግለሰብ መሀከል ነው ማለት ይቻላል?
አቦይ ስብሃት፡- ስራ አጥነት፣ ህብረተሰብን በአግባቡ አለማገልገል ችላ ተብሎ እንደማይታለፍ ነው የእኔ ግንዛቤ። ይሄ ካልተቀረፈ ደግሞ ስራ ፈጠራ፣ ዲሞክራሲ፣ ሰላምና እድገት የሚባል ነገር አይኖርም። ስለዚህ ባሁኑ ጊዜ ለሰው ታስቦ ሀገር የሚካድበት ሁኔታ የለም፤ ለግለሰቦችም ተብሎ ተቻችሎ መሄድ የኢህአዴግ ቁመና እንዳልሆነ ነው የእኔ ግንዛቤ፡፡
አዲስ ዘመን ፡- ውጤቱ ምን ይሆናል ?
አቦይ ስብሃት፡- መጠበቅ ነው፡፡ ህዝቡ በጉጉት መጠበቁ ትክክልና ምክንያታዊ ነው። ኢህአዴግ ለግለሰቦች ሲል ህዝቡን ይከዳል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ካልሄደበት ይሄ አገርንም ህዝብን መክዳት ነው፡፡ ኢህአዴግ ሕዝቡ የሚጠብቀውን ጉዳይ ወደኋላ ይላል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ይሄን ካላደረገ ህዝብን መክዳት ነው፡፡ ሀገር ማፍረስ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- አቦይ የበፊቱን ዘመንና ፖለቲካ በደንብ ያውቁታል፤ በተመሳሳይ የዛሬውንም አሉበት። እስኪ ዛሬ ላይ ሆነው ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን ይታይዎታል?
አቦይ ስብሃት፡- ህዝቡ የሚምጠብቀው ይታየኛል። ባሁኑ ጊዜ ለሰላምም ይሁን ለልማት፣ ለብልፅግና ልቡን አጥፍቶ ሊሰራ የሚፈልግ ህዝብ ስላለ ኢትዮጵያ እንደ አዲስ እራሷን ሆና እራሷን የምትጠቅምና ከአካባቢዋም አልፎ ለዓለም የምትጠቅም ሀገር ትሆናለች፡፡ ጊዜ የማያመልጣት ሀገር ትሆናለች፡፡ ጠላትን የምታሳፍር፤ ተጠቅማ የምትጠቅም ሀገር ትሆናለች፡፡ ጊዜ የማያመልጣት ሀገር እንድትሆን እመኛለሁም ብቻ ሳይሆን ትሆናለች፡፡
አዲስ ዘመን፡- ግን ይሄ የሚሆነው ቅድም ባስቀመጡልኝ ልክ የስርዓቱ አደጋዎች ተብለው የተጠቀሱት ከተወገዱና እርምጃውም ከተጀመረ ብቻ ይመስልኛል አቦይ።
አቦይ ስብሀት፤ አዎን። እነሱ ካልተወገዱ፤ መሆን ያለበትና መሆን የሚገባው ሁሉ ካልሆነ አይሆንም። እንደሚወገዱ ግን አምናለሁ። ይሄ ከሆነ ጠላትን የምታሳፍር ወዳጅንም የምትጠቅም አገር እንደምትሆን አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- አቦይ ወደ ኋላ እንዲሄዱ እድል ቢሰጥዎት እንደ አንድ ፖለቲከኛ ወደ ኋላ ሄጄ ባስተካክለው የሚሉት ነገር ይኖርዎት ይሆን?
አቦይ ስብሃት፡- እንደሰው ያጠፋኋቸው ጊዜዎች አሉ፡፡ ለመጥፎ ያዋልኩት ጊዜ የለም። ለጥሩ ያላዋልኩት ጊዜ ግን አለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለምሳሌ እስቲ ይጥቀሱልኝ?
አቦይ ስብሃት፡- ለምሳሌማ የፖሊስ ጥያቄ ነው። ማህበረሰቡን በሚጎዳ ተግባር ያሳለፍኩት ጊዜ የለኝም፡፡ ነገር ግን በማንበብ እና በመወያየት ማሳለፍ የሚገባኝ ጊዜ ነበር፤ ያንን ሳላደርግ ያሳለፍኩት አለ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለምሳሌ በ1993 የህወሓት ተሀድሶ ወቅት የነበረዎትን ሚና ያስታውሳሉ፤ ከኤርትራ ጋር የነበረንን ግጭት በተመለከተ የያዙት አቋም አለ፤ ሌላም ሌላም በዚህ ዙሪያ መለስ ብለው ያስተካክሉ ቢባሉ የሚያስተካክሉት ነገር ይኖር ይሆን?
አቦይ ስብሃት፡- በ1993 ዓ.ም. በህወሓት ከፍተኛ አመራር ያጋጠመው ችግር ብዙ ሰው የሚያውቀው ነው፡፡ የችግሩ መንስኤ በውስጣችን የነበረው ከፍተኛ ተቻችሎ የመኖርና አብዮታዊነት የጐደለው አካሄድ ነው፡፡ እኔም ሌሎችም ተገማግመን አብረን ለመቀጠል ነበር ፍላጐታችን፡፡ አንጃዎች የውስጣችን የሁላችን ብልሽት ለቡድናዊ ጥቅማቸው ለማዋል ፈልገው ስላልተሳካላቸው በሌላ መንገድ ሊተገብሩት ረግጠው ወጡ፡፡ ከወጡ በኋላ ይህ አደገኛ ሁኔታ የተፈጠረበት ምክንያት ያለምህረት ሌላ ጊዜ እንደማይደገም እንገምግመው የሚል አመለካከት ነበረኝ፡፡ ለአንድ ሁለት የህወሓት ከፍተኛ አመራርም አካፈልኩ፡፡ ግን በሚገባ ገፍቼ ባለመያዜ ይቆጨኛል፡፡ ምናልባት ቀጥለው የመጡ ከዚያኛው የማይተናነሱ ተከታታይ አደጋ እየፈጠሩ የመጡ ከአብዮታዊነቱ በጣም የራቁ ግንኙነቶች ላይከሰቱ ይችሉ ነበር የሚል ግምት አለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፤ ስለዚህ ወደ ኋላ እንዲሄዱና እንዲያርሙ እድል ቢሰጥዎት የሚያስተካክሉት ይሄንን ነው ማለት ነው።
አቦይ ስብሀት፤ አዎን ያ ቢሆን ኖሮ የ1997 ችግርም ባልመጣ የአሁኑም ተሀድሶ አይመጣም፤ ቀጥ ብለን እንጓዝና እንቀጥል ነበር። የሚል ግምት አለኝ፡፡ ውጣ ውረድ የሌለው መቀጠል፣ ማሻሻልና የሚጨመር እየጨመርን ወደማያቋርጥ ዕድገት እንገባ ነበር፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ማብራሪያ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ።
አቦይ ስብሀት፡- እኔም አመሰግናለሁ።

Related stories   “የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች አለመምጣት የሚያጎለው አንዳችም ነገር የለም፤ እኛም አንጠብቃቸውም” ፕሮፌሰር በየነ

በአርአያ ጌታቸው /በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል የእለተ ረቡዕ ዝግጅት አስተባባሪ/ Mob.+251 911 15 42 54

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *