ኢህአዴግ አደገኛ ደረጃ ላይ ደርሷል ያለውን የሙስና ወንጀል ለመመርመር በአሜሪካኑ የኤፍቢአይ ቅርጽ የተደራጃ የምርመራ ቢሮ ማቋቋሙን አስታወቀ። ዜናው ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ሃይመለማሪያም የሆነውን የፌደራሉ የስነ ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን ምን ሊስራ ነው የሚል ጥያቄ እንደሚያስነሳ ይጠበቃል።
ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው መርጃ የሰጡት አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ እንዳሉት በየትኛውም ደረጃ ያለ ባለስልጣን በሙስና ወንጀል የሚያስከሠው መረጃ ከተገኘ ህግ ፊት ይቀርባል። አቶ ሃይለማርያም ይህንን ያሉት “ኢሕአዴግ እንደ ገዢ ፓርቲና እንደ መንግሥት ባደረገው ተሃድሶ ሙስና ፈጽመዋል በተባሉ ግለሰቦች ላይ በቂ እርምጃ አልወሰደም የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው በሰጡት ምላሽ ነው።
“መንግሥት ሙስና ፈጽሞ ማስረጃ በሚቀርብበት ማንኛውም ግለሰብ ላይ ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ ይወሰዳል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ፤ ሙስና በባህርይው ውስብስብና ፊት ለፊት የሚደረግ ባለመሆኑ መረጃዎችን በቀላሉ ለማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነ አልሸሸጉም። ያም ቢሆን በተቻለ ሁሉ መረጃ በቀረበባቸው ላይ ርምጃ መወደሰዱንና ይህ እርምጃ ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።
“ማስረጃ ቀርቦበት በሕግ ተጠያቂ ከመሆን የሚድን አንድም ሰው አይኖርም” ሲሉ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ሃይለማርያም ” በባህሪው ውስብስብ ” ያሉትን ችግር ለመመርመር በፌደራል ፖሊስ ስር በኤፍቢአይ ቅርጽ የተደራጀ የምርመራ ቢሮ መደራጀቱን አመልክተዋል። የተጠናከረ መሆኑንን የመሰከሩለትን የጠቅላይ አቃቤ ህግን፣ በጨረፍታ የፌደራሉን የጸረ ሙስና ኮሚሽን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህዝብ ተሳታፊ እንዲሆን የሚያስችል አሰራር መዘርጋት አስፈላጊ በመሆኑ ቢሮው እንደተቋቋመ አመልክተዋል።ከዚህ አኳያ መንግሥት የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ማዕከል በማቋቋም ህዝቡ በየጊዜው መረጃ የሚሰጥበትን ሁኔታ ለማመቻቸት መወሰኑን ይፋ አድርገዋል።
“መንግሥት ባገኘው መረጃ ልክ ሙስና ፈፃሚዎችን ሕግ ፊት እያቀረበ ቢሆንም በቂ ነው ብሎ ግን አያምንም” ሲሉም አፈጻጸማቸው በዙ እንደሚቀረው ገልጸዋል። መንግሥት የችግሩን ውስብስብነት ተገንዘቦ ሙስናና የሥነ-ምግባር ብልሹነትን ለመታገል በጥናት የተደገፈ ሥራ በመስራት ላይ እንደሚገኝ አመልከተዋል።
በሌላም በኩል የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ኃብትና ንብረት ለህዝብ ይፋ እንደሚሆን ያመለከቱት አቶ ሃይለማርያም፣ ከተመዘገበው ውጭ በግል፣ በዘመድ፣ በወዳጆች ወይም በተለያየ መንገድ የተያዘ ተጨማሪ ኃብት “አለ” የሚል አካል ካለ ይህን እንዲጠቁም የማመቻቸት ሥራ መንግሥት እያከናወነ መሆኑንን ጠቁመዋል። ይሁንና ይህ መቼና እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን አላብራሩም። ሟቹ አቶ መለስም በተመሳሳይ የባለስልጣናት ሃብት ምዝገባ ይፋ ይሆናል በማለት ለዓመታት ሲናገሩ ነበር። በተጨማሪም ህዝቡ በኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ የተደገፈ ጥቆማ እንዲያደርግም ሁኔታዎች እንደሚመቻቹ ተናግረዋል። ” ሙስና የአመለካከት መሸርሸር ውጤት እንደሆነ መረዳት ይገባል” ሲልም ተደምጠዋል።
አቶ ስብሃት ነጋ አሁን ያለው ሙስና ርምጃ ካልተወሰደበት አገር ያፈራርሳለ ሲሉ ከሳምንት በፊት ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ መናገራቸው አይዘነጋም። በሌላም በኩል ህዝብ ስማቸውን የሚያነሳቸው ባለስልጣናት እስካልተነኩ ድረስ የሚባለው ዘመቻ የማስመሰል እንደሆነ የሚገለጹ በርካታ ናቸው። ይህ በአገር ቤት ሚዲያዎችም በስፋት ውይይት የሚነሳ ጉዳይ ነው።

Related stories   “ዶላር እናወርዳለን” የውጭ አገር ዜጎችን የዝርፊያ ድራማ ፖሊስ አለሳልሶ ይፋ አደረገው

በቅርቡ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 130 ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ይታወቃል። ኮሚሽኑ የሙስና ወንጀሎችን መመርመር ከጀመረ በኋላ ከህዝብ፣ ከመንግሥትና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት 260 የሙስና ወንጀል ጥቆማዎች ደርሰውታል።

በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 125 ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን መግለጹ የሚታወስ ነው። በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል 22ቱ አመራሮች፣ 99ኞቹ ሠራተኞች ሲሆኑ አራቱ ደግሞ ተገልጋይ ግለሰቦች መሆናቸው በወቅቱ ተገልጿል።
በመግለጫቸው አቶ ሃይለማረያም አካባቢያዊ ጉዳዮችን አንስተዋል። ከግብጽ ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑንና ቀጣይ ውይይት ለማድረግ ቀጠሮ መያዙን ጠቁመዋል። “በየመን የተፈጠረውን ቀውስ ተከትሎ በቀይ ባህር ላይ እየተከማቸ ያለ ሀይል አለ፤ ይሄ ሀይል እነ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ እና ኤርትራ ያሉበት ነው፤ በዚህ ሀይል የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ እና ሳኡዲ አረቢያ መኖራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ባላቸው ስትራቴጂካዊ አጋርነት ምክንያት ይህ ሀይል ለደህንነታችን አስጊ አይሆንም” ሲሉ መናገራቸውን ፋና ዘግቧል። “የሻዕቢያ መንግስትን በተመለከተ ግን እየተከታተለን የሚወስደውን እርምጃ ምላሽ እየሰጠን እንቀጥላለን” ማለታቸውንም አመልክቷል።
ዜናው የተጠናከረው ከተለያዩ የመንግስት ሚዲያዎች ነው፤ ፋና ዘግይቶ የሚከተለውን ዘግቧል

ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላትን ጥቅም የሚወስነው ህግ የመጀመሪያው ረቂቅ ተዘጋጅቷል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ።

Related stories   ደመቀ መኮንን በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሚመራ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ጋር ተወያዩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ዛሬ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ በረቂቁ ላይ የሚመለከታቸው አካላት ተወያይተውበት ይጸድቃል ብለዋል። ጉዳዩ ህገ መንግስታዊ ስለሆነ መውጣቱ አከራካሪ አይሆንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ህጉ በበሰለ ሁኔታ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ የምታገኘውን ጥቅም በሚያሳይ መልኩ መውጣት እንዳለበት ተናግረዋል። ረቂቅ ህጉ በቀጣይ ከህዝቡ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ይደረግበታልም ብለዋል።

የውጭ ምንዛሬ እጥረት

ከአመታዊ አጠቃላይ ምርቷ 40 በመቶውን ለኢንቨስትመንት በምታውል ሀገር የውጭ ምንዛሬ እጥረት ቢኖር አይደንቅም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ አሁን ላይ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንዳከማቹ የሚነገርላቸው እነ ቻይና እና ደቡብ ኮርያ በኢትዮጵያ የእድገት ደረጃ ላይ በነበሩበት ወቅት የሴቶቻቸውን ጸጉር ለውጭ ምንዛሬ ሲሉ እንደሸጡ አስታውሰዋል። ኢትዮጵያ ላለፉት ሶስት አመታት የውጭ ምንዛሬ ግኝቷ የቀነሰው የምትልካቸው የግብርና ምርቶች መጠንም ጨምሮ ነው።

ምክንያቱም የአለም የግብርና ምርቶች ዋጋ ከኢትዮጵያ ቁጥጥር ውጭ ነው፤ ኢትዮጵያ ግን የሚጠበቅባትን የምርት ጭማሬ አድርጋለች፤ ስለዚህም ነገሩን በትክክለኛው መነጽር ማየት ይገባል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም። የአምራች ኢንዱስትሪው አሁንም የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ተስፋ የተጣለበት መሆኑንና እንደ ሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ያሉትን ማስፋፋት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል ።

በሌላ በኩል የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ከፍ ለማድረግ የባህረ ሰላጤው ሀገራትን የመሳሰሉ የኢትዮጵያ ወዳጆች ገንዘባቸውን በኢትዮጵያ እንዲያስቀምጡ በማድረግ ረገድ ባለፈው አመት ስኬታማ ስራ ተሰርቷልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ግኝቷ እንዲያድግ ተመኗን ትቀንስ የሚሉ ምሁራን ሙሉ ለሙሉ ተሳስተዋል ማለት አይቻልም፤ ምክንያቱም ይህን ማድረግ በጥቂቱም ቢሆን የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ስለሚያሳድግ ነው ብለዋል ።

ሆኖም የውጭ ምንዛሬ ተመን እንዲቀንስ ቢደረግ ግን ከውጭ የሚገቡ እቃዎች የሀገር ውስጥ ዋጋቸው ከፍ ስለሚል የሀገር ውስጥ ባለሀብቱን ይጎዳዋል፤ ስለዚህ ምርጫው ተመኑን አለመቀነስ ይሆናል የሚል ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል። በሁለቱ ጽንሰ ሀሳቦች መካከል አማካኝ የሆኑ ጉዳዮች ከተገኙ ግን መንግስት ሊያየው እንደሚችል ነው የተናገሩት።

Related stories   Egypt-Sudan alliance shifting in row with Ethiopia over Nile dam

የስራ እድል ፈጠራ

መንግስት አሁን ላይ የተከለሰውን የወጣቶች ፓኬጅ ለክልሎች እንዲተገብሩ ልኮላቸዋል። ፓኬጁ ወጣቱ መንግስት በመደበው ገንዘብ ተገቢውን ስራ እንዲያከናውን ያደርጋል፤ ወጣቱም በጉዳዩ ላይ አምኖበት እንዲሰራ ይጠበቃል ብለዋል አቶ ኃይለማርያም።

ከዚህ ቀደም መንግስት ለስራ ፈጠራ ብሎ ብዙ ገንዘብ ቢመድብም የማሳመን ስራ ባለመከናወኑ የተሳካላቸው ቢኖሩም ያልተከካላቸውም ጥቂት አይደሉም ነው ያሉት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወጣቶች ለሚገቡበት ስራ ድጋፍ እንዲሁም የፕሮጀክት ቀረጻ ያስፈልጋቸዋል፤ የገንዘብ ብክነት እንዳይኖርም አሰራር ተዘርግቷል ብለዋል።

ሰፋፊ እርሻዎች

ከሰፋፊ እርሻ ባለሀብቶች ጋር በተያያዘ መንግስት ያጋጠመው የፖሊሲ ሳይሆን የአፈጻጸም ችግር መሆኑን ጠቁመዋል። በዚህ ዘርፍ ላይ 46 ባለሀብቶች ብቻ በጥሩ አፈጻጸም የቀጠሉ መሆናቸውን አንስተው፥ 220 ባለሀብቶች ግን መንግስት ዘርፉ ላይ ስኬታማ እንዲሆኑ ያቀረበላቸውን ድጋፍ ለግል ጥቅማቸው እንዳዋሉት ተናግረዋል።

አሁን ላይ መንግስት ቀድሞ የነበረው የግብርና ኢንቨስትመንትና የመሬት አስተዳደር ኤጀንሲን በመተካት በዘርፉ ላይ ሰፊ ቁጥጥርን የሚያደርግ የግብርና ኢንቨስትመንት ባለስልጣንን አቋቁሟል። ባለስልጣኑ የሙያ ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን፥ የባንክ ብድራቸውን በአግባቡ እየተጠቀሙበት መሆኑን ይከታተላል ብለዋል።

ባለሃብቶች ከቀረጥ ነፃ ያስገቧቸውን ሀብቶች በአግባቡ እየተጠቀሙባቸው መሆኑንም ይቆጣጠራል ነው ያሉት። በሌላ በኩል ለመንግስት ሰራተኞች በዚህ አመት አጋማሽ ይደረጋል የተባለው የደሞዝ እና የጥቅማጥቅም ጉዳይም በጥር ወር መጨረሻ ምላሽ እንደመኪያገኝ ይጠበቃል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም።

በሌላ ዜና  የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ መጨመሩ ተገልጿል። በዚሁ መሰረት  ቤንዚን በሊትር 16 ብር ከ61 ሳንቲም የነበረው በተከለሰው ዋጋ 17 ብር ከ92 ሳንቲም፣ ነጭ ናፍጣ 14 ብር ከ16 ሳንቲም የነበረው 15 ብር ከ18 ሳንቲም፣  ኬሮሲን በሊትር 13 ብር ከ65 ሳንቲም፣ ቀላል ጥቁር ናፍጣ 13 ብር ከ57 ሳንቲም፣ ከባድ ጥቁር ናፍጣ 12 ብር ከ93 ሳንቲም ሲሆን የአውሮፕላን ነዳጅ ደግሞ በሊትር 15 ብር ከ49 ሳንቲም መደረጉን ንግድ ሚኒስቴር አመልክቷል። የዋጋ ማስተካከያው ከጥር 2 እስከ ጥር 30 2009 ዓ.ም ድረስ ተግባራዊ የሚሆን ነው።

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *