ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎችና ብሔራዊ ስሜት ምንና ምን ናቸው?

በገነት ዓለሙ

‘አዲስ ራዕይ’ የኢሕአዴግ የንድፈ ሐሳብ መጽሔት ነው፡፡ የኢሕአዴግ እንደገና በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ ከ”ታወጀ” ወዲህ የወጣውና የመጀመርያው የ2009 ዓ.ም. የገዢው ፓርቲ ይኼ የመጽሔት ዕትም፣ ከሌሎች መካከል ”እንደገና በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄያችን አስፈላጊነት ይዞታና ፋይዳ” የሚል ጽሑፍ ጨምሮ ወጣቶችንና ሶሻል ሚዲያዎችን የሚመለከቱ ሦስት ወቅታዊ ጉዳዮችን ያካተተ የትንታኔ ጽሑፎችን ይዞ ወጥቷል፡፡ ሁሉም ጽሑፎች የወቅቱን ችግሮች በኢሕአዴግ ዓይንና በአዲስ ራዕይ በራሱ ቋንቋ ‹‹ሰፊ ማብራሪያና ትንታኔ›› ይዘው የቀረቡ በመሆናቸው፣ መጽሔቱ በቀጥታ ባለ አድራሻ ያደረጋቸው አባላትና አመራር ብቻ ሳይሆኑ ሌላው ዜጋ ጭምር ሊያውቃቸውና የተቻለውን ያህል ሊመረምራቸው የሚገባ ይመስለኛል፡፡

በተለይም የመጀመርው ጽሑፍ እንደገና በጥልቀት የመታደስ የድርጅቱ ንቅናቄ ፍኖተ ካርታ (Road Map) ተብሎ የተጠራ በመሆኑ የህዳሴውን መንገድ ብቻ ሳይሆን፣ አካሄድ ጭምር ማየት የሚፈልግ ሰው ሲጠብቀውና ሲጠይቀው የቆየ ምላሽ በመሆኑ መልሱ ከተገኘ የግድ ሊታይ የሚገባው ጽሑፍ ነው፡፡ ሌሎችም ጽሑፎች በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄው ውስጥ በዋነኛነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዳንዶቹን ሰፋና ገፋ አድርገው የሚመለከቱ በመሆናቸው፣ ማንንም ሰው ቢሆን ባያመልጡና ቢነበቡ ምኞቴ ነው፡፡

በእኔ በኩል ሁሉንም ጽሑፎች ከዳር እስከ ዳር አንብቤያለሁ፡፡ ዓይን አዋጅ የሆነብኝ የምጽፍበትን እንጂ የማነበውን በመምረጥ ላይ አልነበረም፡፡ በዚህ መካከል ከጽሑፎቹ መካከል ‹የወጣቶችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እናረጋግጥ›› በሚለው ጽሑፍ ርዕስ ውስጥ ስለአገር ፍቅርና ስለብሔራዊ ስሜት የተነሳው ነገር ይበልጥ ከሩቅ የሚጣራ፣ የሚያንገዳግድ፣ የሚገፈታትርና ጠልፎ መጣልም የሚዳዳው ስበትና ይዘት ያለው ጉዳይ ገጠመኝ፡፡

ይኼ ጉዳይ እንዴት እንደ ገረመኝ መጀመሪያ ትንሽ ላስረዳ ወይም መግቢያ ቢጤ ላቅርብ፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ ኢሕአዴግም ሆነ ይኼ መንግሥት ጥሎበት ከ‹‹አገራዊ ፍቅርን ማሳደግ››፣ ከ‹‹አገር ወዳድነት››፣ ከ‹‹ብሔራዊ ስሜት›› ጋር ይዛመዳል፣ ይተዋወቃል የሚል ተማሪ የለም፡፡ ተማሪ ያልኩት ጥያቄው በፈተና መልክ ቢቀርብ እንኳን ብዬ ነው፡፡ ተማሪዎች በግራ በኩል ያሉትን ቃላት ወይም ሐረጎች በቀኝ በኩል ካሉት ቃላት ወይም ሐረጎች ጋር አዛምድ ተብለው ቢጠየቁ፣ ብሔራዊ ስሜትን ከገዢው ፓርቲ ጋር አፈላልገው ያገኛሉ ብዬ አልጠረጥርም፡፡ ከ‹‹አገር ፍቅር ትዝታው›› ጀምሮ ‹‹ኢትዮጵያ አገራችን መመኪያችን››፣ ‹‹አገሬ ኢትዮጵያ ተራራሽ አየሩ›› ማለት ዘፈኖች ሁሉ እንኳን አቧራቸውን አራግፈው በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን መዘፈን የጀመሩት በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ምክንያት ነበር፡፡ የኢትዮ ኤርትራ ግጭት መጥቶ እስኪያባንነን ድረስ ታዳጊዎችን እንኳ የአገር መውደድ ስሜት የማነፅ ዕይታ ጠፍቶን ነበር፡፡ እንዲያውም አገር ወዳድነትን ከነፍጠኝነት ጋር አንድ አድርገው የሚጠየፉ ገዢዎች ባለቤት ሆነን፡፡

ሌላው ኢሕአዴግን ከብሔራዊ ስሜት ጋር የማይደራረስ አድርጎ ወይም አስመስሎ ያቀረበው ‹‹በብሔሮች አሠፋፈር ላይ በመመርኮዝ›› ብሔራዊ የክልል መስተዳድሮቹ ሲቋቋሙ ነው፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በተፈጠረው ውዥንብር ምክንያት ጥበትና ትምክህት ከግራ ቀኝ እያገዙትና እያንገላቱት ‹‹ብሔራዊ ክልላዊ መስተዳድር››፣ ‹‹የኦሮሞ ልዩ ብሔራዊ ጥቅም›› ማለት አንፃሩ ከነባሩ ‹‹ብሔራዊ ባንክ››፣ ‹‹ብሔራዊ ትያትር››፣ ‹‹ብሔራዊ ሎተሪ›› ትርጉምና አንድምታ ጋር እየተምታታ ነፃ ሆኖ ነግሶም ቀጠለ፡፡ የማዕከላዊው የሽግግር መንግሥት የአገር የመከላከያ ሠራዊት ሥምሪት ጉዳይ በተወሰነበት በ1984 ዓ.ም. ሕግ ሳይቀር (አዋጅ ቁጥር 8/1984) ዛሬ በኩራት “National Deference Force” ብለን የምንጠራው አካል ያኔ “State Defence Army” ነው የተባለው፡፡ አሁን ሁሉም ከተረጋጋና ከሰከነ በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት (አዋጅ ቁጥር 257/94) ብሔራዊ ተጠባባቂ ኃይል (ናሽናል ሪዘርቭ ፎርስ አዋጅ ቁጥር 327/95) ማለት ተጀምሯል፡፡ በ1987 ዓ.ም. የወጣውን ሕገ መንግሥትና በ2006 ዓ.ም. ተሻሽሎ የወጣውን የአገር መከላከያ ሠራዊት አዋጅ ለተመለከተ ብሔራዊ ዓርማ፣ ብሔራዊ መዝሙር፣ ብሔራዊ ደኅንነት፣ ብሔራዊ ልማት፣ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ፣ ብሔራዊ ባንክ፣ ብሔራዊ ጥቅም፣ ብሔራዊ ፖሊስ ማለት የመላው ኢትዮጵያ ማለት ነው፡፡ የአገር መከላከያ ሠራዊታችንም በ1984 ዓ.ም. ውስጥ ገብቶበት ከነበረው የስያሜ ችግር “State Defense Army” ወጥቶ “National” ተብሏል፡፡

ከላይ የጠቀስኩት የስያሜ መምታታት የችግር ምንጭ ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች አገር መሆኗ፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብት መከበር ያለበት መሆኑ በጭራሽ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ባለ ብዙ ብሔር ብሔረሰብ አገር መሆኗን ተቀብሎ ይኼንን እውነትና መብት ከአገራዊ ትስስር ጋር የሚያግባባ ዴሞክራሲያዊ አመለካከት ይዞ ወደ ሕዝብ መቅረብ ስላልተቻለ ነው፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ የመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አጠቃላይ የዴሞክራሲ ጥያቄ አካል መሆኑን፣ የሁሉም ብሔር/ብሔረሰቦች የትግል አስኳል ዴሞክራሲያዊ ነፃነት መሆኑን አለመቀበል ነው፡፡

በብሔሮች አሠፋፈር ላይ የተመሠረተው የክልሎች ይዞታ ከአገራዊ ትስስር ጋር እንዳይግባባና እንዳይደራረስ በመደረጉና የብሔረሰቦች የትግል አስኳል ከሆነው ከዴሞክራሲዊ ነፃነት ጋር ባለመጣጣሙ፣ የክልሎች ይዞታ የየብሔር ብሔረሰቡ የግዛት ድርሻ ተደርጎ ተወሰደ፡፡ ሁሉም በየክልሉ እንዲወሰንና እንዲሰባሰብ፣ የልማት ጥረትም በክልላዊ ደረጃ እንዲጠብ የሚገፋፋ አስተሳሰብ ሰፈነ፡፡ የብሔር ሀብት ለብሔር የሚል ብሔርተኝነት አገራዊ ዕይታን ጋረደው፡፡ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ሄዶ የመሥራትና የመኖር ነባር ማኅበራዊ እንቅስቃሴ መረበሽና መደናቀፍ ውስጥ ገባ፡፡ ‹‹ስደተኛ በአገሬ መጥቶ›› የሚሉ ጥበቶችና ትምክህቶች እየጋረዱን፣ በየትኛውም ሥፍራ ዜጎች እየሠሩና ካፒታላቸውን እያንቀሳቀሱ ልማታችንን እንዳያንደረድሩት አጠቃላይ አገራዊ ስሜቱ እንቅፋት ገጠመው፡፡

ወደ ዝርዝሩ ከመግባቴ በፊት ኢሕአዴግ አገራዊ ፍቅርን ማሳደግ በሚል ንዑስ ርዕስ ሥር ያለንንና የነገረንን በጥሞና እንመልከት፡-

‹‹ወጣቱ ትውልድ አገር ተረካቢ ነው ሲባል የእኔ የሚለው ተወልዶ ያደገበትና የሚኖርበት አገር እንዳለው ታሳቢ ያደርጋል፡፡ ቢወለድና ቢያድግበትም ሊኖርበት የማይፈልግ ትውልድ አገር ተረካቢ አይሆንም፡፡ እንደዚህ ያለ ትውልድ ያለበት አገር የወላድ መካን በመሆኑ ቀጣይ መድረሻው ለዕድል የተተወ ይሆናል፡፡ ወጣቱ ትውልድ በእርግጥም አገር ተረካቢ እንዲሆን የመጀመርያው ጉዳይ አገሩን የሚወድ መሆን ይኖርበታል፡፡ የአገሩን ታሪክ የሚያውቅ፣ አገሩ ያላትን ተስፋና ተግዳሮት የሚገነዘብ፣ ከዚህም በመነሳትም ከእሱ የሚጠበቀውን ሁሉ ለማድረግ የተዘጋጀ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ አገር ወዳድነት ብሔራዊ ስሜትን (Nationalism) ማዳበር ማለት ነው፡፡ ብዙዎቹ አገሮች ብሔራዊ ስሜትን ለአገራቸው ግንባታ ተጠቅመውበታል፡፡ በኢትዮጵያም ብሔራዊ ስሜት አገርን ከውጭ ወራሪዎች ለመከላከል በተካሄዱ ጦርነቶች ሁሉ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ አገራችን ሌላ ጦርነት፣ ከድህነትና ኋላቀርነት ነፃ ለመውጣት ሌላ ክተት በጠራችበት በአሁኑ ወቅት ከወራሪዎች ጋር እንደተደረገው ጦርነት ሁሉ፣ የአገራችን ወጣቶች በታላቅ ብሔራዊ ስሜት እንዲከቱ ይጠበቃል፡፡

‹‹ይሁንናም የሚጠበቀውን ያህል ጠንካራ የአገር ፍቅርና ብሔራዊ ስሜት ተገንብቷል ለማለት የሚያስደፍር ሁኔታ ላይ አንገኝም፡፡ በዚህ ረገድ ኢሕአዴግና የሚመራው መንግሥት የሠሩት ሥራ ደካማ እንደሆነ ይቀበላሉ፡፡ በትምህርት ቤቶች የሚሰጠው የሥነ ዜጋ ትምህርት የታሰበውን ያህል ውጤታማ አልሆነም፡፡ የመንግሥትም ሆነ የግል ሚዲያዎች ዜጎች ብሔራዊ ስሜትና የአገር ፍቅር እንዲያጎለብቱ የረባ አስተዋጽኦ አላደረጉም፡፡ ይልቁንም አሉታዊ አስተዋጽኦቸው የሚያይልበት ሁኔታ ይታያል፡፡ በአሁኑ ወቅት በወጣትነት ዕድሜ ያለው በኢሕአዴግ በምትመራው ኢትዮጵያ ያደገ በመሆኑ በታላላቅ ወንድሞቹና እህቶቹ የነበረውን ብሔራዊ ስሜትና አገራዊ ፍቅር ሊወርስ ላለመቻሉ ዋነኛው ተጠያቂ ኢሕአዴግ እንደሆነ አያከራክርም፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ወጣቱም በዓይኑ ከሚያየውና ከነጉድለቱም ቢሆን ተጠቃሚ ከሆነበት አገራዊ ለውጥና ዕድገት እንዲሁም በቀጣይ ከፈነጠቀው ተስፋ በመነሳት በአገሩ ላይ ፍቅርና እምነት ማሳደር ይገባዋል፡፡

Related stories   የአውሮፓ ህብረት የይስሙላ ምርጫዎች ሲታዘብ ቆይቶ አሁን አልታዘብም ያለበትን ምክንያት ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያሳውቅ ተጠየቀ

‹‹የዛሬዋ ኢትዮጵያ ሊኖሩባት የሚያስጎመዡ በርካታ ዕድሎች የሚታዩባት አገር ሆናለች፡፡ በአገራቸው የተፈጠሩትን ዕድሎት በመጠቀም ሠርተው ለመኖርና ኑሮአቸውን ማበልፀግ የጀመሩ በርካታ ወጣቶች አሉ፡፡ ወደ ውጭ አገር የመሄድ ዕድል አግኝተው የማይጓጉ፣ በውጭ አገር አድገውና ተምረው ያላቸውን ሙያና ሀብት ይዘው ወደ አገራቸው በመመለስ ሠርተው የሚኖሩ፣ ለሌሎችም አርዓያ የሚሆኑ አገር ወዳድ ወጣቶችም ጥቂት አይደሉም፡፡ ይሁንና ብሔራዊ ስሜትን ከማጎልበት አንፃር በወጣቱ ዘንድ ያሉትን ጉድለቶች በዝርዝር እየፈተሹ ሁኔታውን ለመለወጥ መንቀሳቀስ ይገባል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የሚታየውን በአገር ውስጥ ለመኖር ያለመፈለግ፣ በአገር ውስጥ ሥራ ላይ ቢውል ብዙ ጥቅም ሊያስገኝ ይችል የነበረ ከፍተኛ ገንዘብ ድረስ ወጪ በማድረግ ስደት መሄድ የመሳሰሉ ችግሮች ተገቢ ትኩረት ሰጥቶ መታገል ያስፈልጋል፡፡ በውጭ አገርም ምን ዓይነት አስቸጋሪ ኑሮ እንደሚገፉ በመደበቅ፣ ሌሎችም እንዲሰደዱ የሚቀሰቅሱ ዳያስፖራዎች እንዲሁ ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ወጣቱ በቃችሁ ሊላቸው ይገባል፡፡››  

ይኼ ሁሉ ኢሕአዴግ ስለብሔራዊ ስሜት ያለው ነው፡፡

ጊዜው በዴሞክራሲና ግንባታ ላይ መረባረቢያ ቢሆንም ከብሔርተኝነትና ከኢብሔርተኝነት መስመር የሚመጡ ችግሮች እየተፈታተኑን ነው፡፡ በብሔርተኝነት መስመር ውስጥ ብዙ ልዩ ልዩ ነገሮች አሉ፡፡ የብሔር ብሔረሰቦችን ተፈቃቅዶ መተሳሰር አምናለሁ የሚለው ራሱን ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኛ ብሎ የሚጠራው አለ፡፡ የብሔር ሀብት ለብሔሩ የሚል ብሔርተኝነትም አለ፡፡ ከባሰም መገንጠልን የሚጠይቅ ከዚህ ከመረረም በኢትዮጵያዊነት ላይ ጥላቻ ያዳበረ ወገን ያጋጥማል፡፡ በቀድሞ ‹‹ግፍ›› ተከፍቶ ለመነጠል መፈለግን የሚመርቅ፣ ቂምና ጥላቻን ወደ መነጠልና ወደ በቀል መሄጃ መንገድ ማድረግን፣ የግፍ ባለተራ መሆንን የማይቆጣ ወግም ሰፍኗል፡፡

በኢብሔርተኝነት መስመር ውስጥ የሚታዩ አዝማሚያዎች በአጠቃላይ የኢትዮጵያዊነት ብሔርተኝነትን የተመረኮዙ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ዝርዝራቸው ብዙ ነው፡፡ እስቲ አንድ ሁለት ብለን እንጥራቸው፡፡

1) የሚደረገው አንዱም የማይጥመው፣ ኢትዮጵያ አንድም ወዳጅ የሌላት በሆዷ ያቀፈችውን ሀብት አውጥታ እንዳትጠቀም ሁሉም የሚመቀኟት፣ የምታምነው ቢኖር ፈጣሪዋን ብቻ የሚል ከሰማያዊ ተስፋ በቀር በሐዘንተኝነትና በጨለምተኝነት የተጨበጠ አመለካከት ያለው አንደኛው ዓይነት ነው፡፡

2) ሌላው የኢትዮጵያ የቀድሞ ሥልጣኔና ገናናነት ውዳሴ የሚያጠብቅና የተቀነሰ ግዛትን ሁሉ አስመልሶ ኢትዮጵያን እንደ ነበረች ለማቆየት የሚያስብ፣ ያለውን መንግሥት ከጠላት የሚቆጥር፣ ፅንፈኝነቱ ከፍ ካለም በብሔርተኝነትና በብሔር መብት ላይ ጥላቻ ያዳበረ ነው፡፡

3) ለአፉ የብሔሮች መብት መሟላትን የሚቀበል፣ ግን የተረሳ ባህል ሕይወት እንዲያገኝ መደረጉን ወደ ኋላ መሄድና ሥልጣኔን መቃረን አድርጎ የሚያይ፣ የሌሎች የመብት አተገባበር የማይጥመው አለ፡፡

4) ከመገንጠል በመለስ የብሔሮች መብት ታውቆ በእኩልነትና በዴሞክራሲ ተከባብሮ መኖር ይቻላል የሚል እምነት የያዘም አለ፡፡

5) ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ከተከበሩ ሌላው ችግር ሁሉ ይፈታል የሚልም አለ፡፡

6) ባሉት አስተሳሰቦችና ሲከሰቱ በነበሩ ተሞክሮዎች እየተረበሸ ከየት እንደሚሆን ግራ ተጋብቶ ብቻ ምንም ሆነ ምንም አገር ተጠብቃና ሰላም ሆና የሚኖርበትን እየተመኘ ያለም በርካታ ነው፡፡

እነዚህ በብሔርተኝነትም ሆነ በኢብሔርተኝነት መስመር ውስጥ የሚታዩት አዝማሚያዎች የጠራና የጠጠረ ወሰን የሠሩ አይደሉም፡፡ እንደ ፈሳሽ የመዋለልና የመቀላቀል ፀባይ የሚታይባቸው ናቸው፡፡ ሁለቱም የከረሩና ጥላቻ የጠገቡ የተገንጣይነትና የትምክህተኝነት ዋልታዎች ያሏቸውና ከእነዚህ ሁለት ዋልታዎች በኩል እንደ ገመድ ጉተታ የሚሳሳቡ ናቸው፡፡ እንደ ቡድኖች ወይም ፓርቲዎች ግንኙነት ዓይነትና እንደ ሁኔታዎች ገርነትና መራራነት ከአዝማሚያ አዝማሚያ ያለው የድጋፍ ክምችትና የስበት ኃይል ለውጥ ያሳያል፡፡ በአንድ ወቅት ደንዝዞ የነበረ ዝንባሌ በሌላ ወቅት ተነቃንቆ ሲዛመት ይታያል፡፡ ወደ ዴሞክራሲያዊነትና ወደ መቻቻል እያጋደለ ነው የተባለ ብሔርተኝነት ወይም ኢብሔርተኝነት በተቀየረ ሁኔታ ወደ ኢዴሞክራሲያዊነት፣ ወደ ጥላቻና ወደ ጠበኝነት ሊንሸራተት ይችላል፡፡ ሲጣሉ፣ ሲያጣሉና ሲያጋጩ የምናገኛቸው ብሔርተኝነትና ኢብሔርተኝነት አንዳቸው ለአንዳቸው ሳቢና አበልፃጊ በመሆንም የሚረዳዱ ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ ለብሔርተኝነት የምንሰጠው የጠባብነት ባህርይ በኢብሔርተኝነትም ውስጥ እናገኘዋለን፡፡

በቅርፁ ሰፊ አገራዊ ዕይታ ያለው የሚመስለው፣ ግን በዕይታው ውስጥ ብሔርተኞችና መብታቸውን ማስተዋል የሚፀናወተው፣ ከነበረው የተለየ አደረጃጀት መምጣትን እንደ አገር መናድ የሚቆጥረው፣ ለአንድነት እታገላለሁ ቢልም ከእናት ቋንቋው ውጪ የሌላ ብሔር ቋንቋ ማወቅ ለአንድነት ያለው ጥቅም የማይገባውና ለብሔር ብሔረሰቦች አክብሮትን በመንሳት፣ የሚጮህለትን አንድነት የሚቦረቡረው ዝንባሌ የግልብነትና የጥበት ቋት ነው፡፡ በሆነ ነገር (በታሪክ፣ በሥልጣኔ፣ በሀብት፣ ወዘተ) ላይ የተመሠረተ ኩራት ወደ ትዕቢትና ሌላውን ወደ መናቅ ሲሸጋገር ትምክህት ይሆናልና የብሔርተኛ አስተሳሰቦችን ቀረብ አድርገን ከተመለከትንም ከትምክህት ጋር የሥጋ ዝምድና ሊኖራቸው እንደሚችል እናጤናለን፡ እንደሁም በአንድ ብሔር/ብሔረሰብ ውስጥ ትክክለኛው ወይም ዋናው የብሔሩ ክፍል እኔ ነኝ የሚል መታበይ ከክልልተኝነት ጋር ተጣብቆ ይገኛል፡፡ ከዚያም አልፎ ዋናው የሀብት ምንጭ ወይም የሥልጣኔ መሠረት እኔ ነኝ የሚል ትምክህት ከብሔርተኝነትም ጋር ተዛምዶ ሊታይ ይችላል፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት በወጣትነት ዕድሜ ያለው በኢሕአዴግ በምትመራው ኢትዮጵያ ያደገ በመሆኑ በታላላቅ ወንድሞቹና እህቶቹ የነበረውን ብሔራዊ ስሜትና አገራዊ ፍቅር ሊወርስ ባለመቻሉ፣ ዋነኛው ተጠያቂ ኢሕአዴግ እንደሆነ አያከራክርም፤›› የሚለውና ኢሕአዴግ የሰጠው የእምነት ቃል ዝርዝሩና እውነቱ በሙሉ ግን መታወቅ አለበት፡፡ ‹‹ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት›› የሚባለው አስተሳሰብና አደረጃጀት የትምክህትንና የብሔርተኝነትን በጥባጭነት ሊያመክንና ጉዳታቸውን ሊያደርቅ አልቻለም፡፡ ይልቁንም ብሔርተኝነትና ትምክህተኝነት እየተጫጫሩ ጉዳት ማድረሳቸው ቀጥሏል፡፡ የብሔርተኝነትን ንጠት ከፍና ዝቅ እያለ አገሪቷን እያወዛወዛትና እየገዘገዛት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትም የተናጋበትን የዳር ድንበር፣ የሃይማኖተኝነትና የአንድ ሕዝብነት አመለካከት በአዲስ ራዕይና ግንዛቤ የማደስ ዕርምጃው ቢደክምም ገና አልተሸነፈም፡፡ በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ዛሬም በታሪክ ሀብቶች ራስን ከማሞጋገስ አልተሻገረም፡፡ ዛሬም የሄደ ግዛትን በግድም ሆነ በውድ ወደ ማስመለስ አስተሳሰብ ከመገስገስ አልተመለሰም፡፡ ዛሬም በተለያየ ሥፍራ የሚገኙ ውህዳን የሚባሉ ወገኖች ባልታወቀ አንድ ጎደሎ ቀን ያልተጠበቀ ግጭት ተከስቶ መዘረፍ፣ መባረር፣ መገደል ይደርስብን ይሆን? ወይስ ሳይሰማን በአንድነት ኑሯችን ይቀጥል ይሆን? የሚል ጥያቄ አብሯቸው እየኖረ ነው፡፡

ከአፍ እላፊ ጨዋታ ተነስተው በብሔር ወደ ተቧደነ ጥል የሚቀየሩ የከፍተኛ ተቋማት ተማሪዎች ውዝግቦች በኅብረተሰባችን ማኅበራዊ አብሮነት ውስጥ ያልተጠገነ ስንጥቃት መፈጠሩን፣ ይኸውም በአንድ ግለሰብ ላይ የተሰነዘረ ዘለፋ በሌሎች የብሔር ባልደረቦች ላይ የተሰነዘረ ያህል እየመሰለ፣ የአንድ ግለሰብ የአፍ እላፊ ጥፋትም በአጥፊው ሰው ብሔር ወገኖችም የተፈጸመ ያህል ተደርጎ እየታሰበ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ የዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ባይኖር የግለሰብ ፀብ በግለሰባዊነቱ በታየ ነበር፡፡ እንዲህ ያለ እስከ ግለሰብ ፀብ የወረደ ብሔረሰባዊ ወገንተኝነት በተለያየ ሥፍራ እያዳገመ መንፀባረቁ፣ በጥበትም ይሁን በትምክህት የሚመጣ ተንኳሽነትን ለማሳፈርና ወጣቶችን ለመግራት የቻለ የፖለቲካ ኃይል አለመኖሩን ያሳያል፡፡

Related stories   “ጣልያኖችም ሆኑ እንግሊዞች ቅኝ ግዛትን ለማስቀጠል ህዝቡን በዘር መከፋፈልን እንደ አንድ ስልት ይጠቀሙ ነበር” -አቶ ታቦር ገረሱ ዱኪ

የኢሕአዴግ አዲስ ራዕይ መጽሔት ያለብልኃትም ቢሆን የትምህርት ቤቶችንና የመገናኛ ብዙኃንን ችግሮች ገልጿል፡፡ ስለተደራጀ ተሳትፎም ይናገራል፡፡ ስለዴሞክራሲያዊ ባህልም አውርቷል፡፡ እነዚህ ሁሉ ኢሕአዴግ ራሱ መሣሪያና ፖሊሲ ያደረጋቸው ድክመቶች ናቸው፡፡ እነዚህን ‹‹ፖሊሲ››ዎችና ድክመቶች ተጠግተው፣ ይልቁንም እነሱ ተመችተዋቸው ጠባብ ብሔርተኝነትና ትምክህት የኅብረተሰቡን መልካም ግንኙነትና ብሔራዊ ስሜት ቆረጠሙት፡፡ በዚህ ምክንያት የታደሰ ብሔራዊ ስሜት አልገነባንም፡፡ ለዚህም የታደሰ ኢትዮጵያዊነት የግድ ያስፈልገናል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ተሃድሶ ማግኘቱና የአገሪቱን ሕዝቦች እንደ ሲሚንቶ ሊያያይዝ መቻሉ ለመፃኢ ዕድላችን ወሳኝ ነው፡፡ ይኼንን ያሳካሉ የሚባሉ አንዳንድ ቁም ነገሮችን እናስቀምጥ፡፡

እስከዛሬ ባለን የአገር ፍቅር ስሜት ውስጥ የሚንፀባረቀው ብሔርተኛ የያዘውን ነገር የመራቅና ከትምክህት ጋር የመሳሳብ ግንኙነት የግድ መስተካከል ይኖርበታል፡፡ በብሔርተኝነት ውስጥ የሚወናገረው የብሔር ብሔረሰቦች መብት ተጣርቶ የኢትዮጵያዊነት አንድ ዋልታ መሆኑ ግድ ነው፡፡ በንቀትና በሽሙጥ የሚገለጽ እኔ እበልጥ ባይ አላዋቂነት ተሰብሮ የሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች ማንነት፣ ባህልና ቋንቋ የማክበር ሥልጡንነት ጥብቅ መሠረት ማግኘት ይኖርበታል፡፡ ከጥንታዊ ቅርሶች ጋር የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ቋንቋዎች፣ ባህሎችና የኪነ ጥበብ ሀብቶች የኢትዮጵያ መመኪያ መታወቂያ ሆነው እንዲያድጉ ማድረግ፣ የመላ ብሔር ብሔረሰቦች ታሪክ ከየተጓዝንበት ዘመን የዕድገት ደረጃና የንቃት ህሊና እውነት ሳይነጠል ከተረቶች እየጠራ ተሰናድቶ የኢትዮጵያዊነት ግንዛቤ እንደሆነ ማድረግ፣ ብሎም የዛሬን ችግሮች ለመወጣት ኃይልና ብርታት አድርጎ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡

ኢሕአዴግ በ‹‹አገራዊ ፍቅርን ማሳደግ›› ጽሑፉ፣ ‹‹ብዙዎች አገሮች ብሔራዊ ስሜትን ለአገራቸው ግንባታ ተጠቅመውበታል፤›› ይላል፡፡ ሌላም ሌላም፡፡ ይህንን ሁሉ ‹‹ድስት ጥዶ ማልቀስ›› ያመጣው አስቀድሞ ካልተሠራው ሥራ ይልቅ አስቀድሞ የተሠራው አፍራሽ ሥራ ነው፡፡

ወደ ብልፅግና ለመሸጋገር ከተፈለገ በልማት ራዕይ የታደሰ ኢትዮጵያዊነትን እንደ ኃይል መያዝ፣ አገር የምትጎዳባቸውንና የምትጠቀምባቸውን አቅጣጫዎችና ሁኔታዎች ዜጎች ያወቁበትን አጠቃላይ ንቃተ ህሊና መገንባት የግድ ያስፈልጋል፡፡ ይህ የማይቀር የማይታለፍ ጉዳይ ነው፡፡ በሥራ ፈጣሪነትና ፍቅር የተቀረፀ በየዋህነት ወይም በማይረባ ጥቅም የአገሩን ውድ ቅርስ የማያስመነትፍ፣ ለአገሩ ሀብት እንክብካቤና ልማት የሚቆረቆር፣ ከውጭ ዕቃ አፍቃሪነትና ከአገር ውስጥ ዕቃ ናቂነት ነፃ የወጣ፣ በመጤ ሸቀጦች የተጨናነቀ አኗኗርን ጎጂነት የተረዳ፣ የውጭ ምንዛሪና እውቀት ወደ አገር እንዲገባና እንዲስፋፋ መጣር የልማት ተጋድሎ መሆኑ የገባው ዜጋ ያስፈልገናል፡፡ በላኪነትና በአስመጪነት መስክ በግላዊም ይሁን በመንግሥታዊ አካል የሚደረጉ የግብይይት ሙስናዎች፣ የኮንትሮባንድ ንግድ፣ የብር ምንዛሪ ግሽበት፣ የውጭ ሸቀጦችና የነዳጅ ዋጋ ንረት፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ የሚጎዱና ምንዛሪ የሚያስመልጡ መሆናቸውን ያወቀ፣ ከኋላ ቀር የአስተሳሰብና የአሠራር ማነቆዎች የተላቀቀ፣ በዘመናዊ እውቀትና ክህሎት የሚተጋ ኢትዮጵያዊን ልማታችን ይፈልጋል፡፡ ትምህርትና ሥልጠናችን የአኗኗርና የአሠራር ባህላችን ሁሉ በተሃድሶ አብዮት ውስጥ መግባቱ የግድ ነው፡፡

ኢሕአዴግ በአዲስ ራዕይ ጽሑፍ በአገሩ ‹‹. . . ሊኖርበት የማይፈልግ ትውልድ አገር ተረካቢ አይሆንም፤›› እያለ ክፉኛ ተስፋ በቆረጠ ስሜት የጀማመረውን የወጣቱን የፍልሰት (እሱ ‹‹ስደት›› ይለዋል) ጉዳይ በጽሑፉም ላይ ‹‹አርሰዋለሁ የሚለው አለባብሶ›› ነው፡፡ ‹‹የዛሬዋ ኢትዮጵያ ሊኖሩባት የሚያስጎመዡ በርካታ ዕድሎች የሚታዩባት አገር ሆናለች፡፡ ወደ ውጭ አገር የመሄድ ዕድል አግኝተው የማይጓጉ፣ በውጭ አገር አድገውና ተምረው ያላቸውን ሙያና ሀብት ይዘው ወደ አገራቸው በመመለስ ሠርተው የሚኖሩ ለሌሎችም አርዓያ የሚሆኑ አገር ወዳድ ወጣቶችም ጥቂት አይደሉም፤›› ይልና በአሁኑ ጊዜ የሚታየውን በአገር ውስጥ ለመኖር ያለመፈለግ፣ ‹‹በአገር ውስጥ በሥራ ላይ ቢውል ብዙ ጥቅም ሊያስገኝ ይችል የነበረ ከፍተኛ ገንዘብ ድረስ ወጪ በማድረግ ስደት መሄድ የመሳሰሉት ችግሮች ተገቢ ትኩረት ሰጥቶ መታገል ያስፈልጋል፡፡ በውጭ አገር ምን ዓይነት አስቸጋሪ ኑሮ እንደሚገፋ በመደበቅ ሌሎችም እንዲሰደዱ የሚቀሰቅሱ ዳያስፖራዎች፣ እንዲሁም ሕገወጥ አዘዋዋሪዎችን ወጣቱ በቃችሁ ሊላቸው ይገባል፤›› በማለት ጉዳዩንና ችግሩን የሴራ የግንዛቤ ዕጥረት አደርጎ ‹‹ይገላገለዋል››፡፡

የኢትዮጵያውያንን ፍልሰት የፈጠረው ግን ከውጭው ስበት፣ አማላይነት፣ ሰበካና ቅስቀሳ ወይም አታላይነት ይልቅ አገር ቤት ያለው ገፊ እና ገፍታሪ ኃይል ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ‹አገር ለቀህ ውጣ፣ ብረር ብረር አለኝ› የሚለውን አማራጭ በአደባባይ ላይፈሩ ላይቸሩ በመንግሥት ፊትና ለመንግሥትም ጭምር የሚናገሩት እንዲሁ በተራ በሰላም ጊዜ ብቻ ሳይሆን፣ ሰላሳ ያህል ዜጎቻችን የታረዱበት ሐዘን ላይ ቁጭ ብለው ነው፡፡ ይህንን የውስጥ ግፊትና ግፍተራ በውጭው ‹‹ሴራ›› እና ማጭበርበር በማመካኘት ወይም በስብከት መመከት አይቻልም፡፡ መፍትሔው ኢትዮጵያን የምትመች አገር ማድረግ ነው፡፡

ኃላፊነት የተዋሀደው የአገር ፍቅር መገንባት እስከተቻለ ድረስ (ዋናው ችግር ግን ይኸው ነው) ብዙ ባለሙያም ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ መፍለሱ አያስፈራም፡፡ አያሳፍርም፡፡ አንዱን አንቋሾ ‹‹ስደተኛ›› ሌላውን አሽሞንሙኖ ‹ኤክስፓት› (Expat) የሚያሰኘው ከአገር መውጣት ሳይሆን ተፈላጊነቱ ነው፡፡ መፍትሔ ብሎ የተያዘውም የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ መከልከልና የኮንትራት ቅጣት መጣል ትክክለኛው ጎዳና አይደለም፡፡ ይልቅስ የኢትዮጵያ ሙያተኛ በውጭ በመፈለጉ ተደስተን በተሻለ የችሎታና የሥነ ምግባር ብቃት ገበያውን ለመሙላትና ለማስፋት፣ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ፍላጎትም ለመሸፈን የሚችል የሰው ኃይል በየጊዜው ማፍራት የምንረባረብበት አንድ የልማት ዕቅዳችን መሆን አለበት፡፡ የውስጥ ፍላጎት ሲባልም መታሰብ ያለበት ዜጋችን ብቻ አይደለም፡፡ ዛሬ ጥራትና ደረጃቸው ከለሙት አገሮች ጋር የተመጣጠኑ አገልግሎቶችን (የሕክምና የመዝናኛ፣ ወዘተ) በቀላል ዋጋ ማቅረብ አንዱ የውጭ ምንዛሪ መሳቢያ ነውና በዚህ በኩል መዘጋጀትም ይጠበቅብናል፡፡

ያለንን ሀብት ሳናባክን፣ ለኢኮኖሚ ግንባታችን መሣሪያ ማድረግ ካወቅንበት ሥራዎች አያልቁብንም፡፡ በትግራይና በአማራ አካባቢ ያለው ከትናንሽ ጌጦችና ከእምነት ምልክቶች ያላለፉ ደንጋይ ነክ ዕደ ጥበቦች በቅርቧ ጎረቤት ኬንያ ውስጥ የሚታየው ዓይነት ዘመናዊ ለውጥ ቢካሄድባቸው በሥራ ዕድገትና በቱሪዝም ገቢ ጉልህ ለውጥ የሚያመጡ ናቸው፡፡ በመካከለኛና በረዥም ርቀት ሩጫ የተገኘነውም ዓለም አቀፋዊ ዝና ወደ ልማት መሣሪያነት ሊቀየር ይችላል፡፡ የሩጫ ሜዳዎች፣ የጂምናዚየም፣ የሆቴሎችና ሳቢ የመዝናኛ አካባቢዎችን በአግባቡ አደራጅቶ ዓለም የኢትዮጵያ ሯጮችን የድል ሚስጥር እንዲቋደሱ በመጋበዝ መነገድ እንችላለን፡፡ ታሪካዊና አርኪዮሎጂያዊ ሀብቶቻችንና መገኛ ሥፍራዎቻቸው ከቱሪዝም ገበያ አኳያ ገና አልተሠራባቸውም፡፡ የከረዩና የቦረና ኦሮሞዎች ያልተነካ ውብ አዘፋፈን፣ በጌዴኦና በሌሎች በርካታ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሙዚቃ ውስጥ የምናገኛቸው ድንቅ ኅብረ ዝማሬ፣ ገና ዘመናዊ መነካካት ሳያርፍበት ሐበሻና ፈረንጅን ያስደነቀው የደራሼዎች ዓይነቱ የእግር የምት ሥልት፣ ሁሉ የሚያጋፍርባቸውን የሙዚቃ ሀብቶቻችን የሚያዳብር ካገኙ ዓለም ሊሰማው የሚችለው አልማዝ ነው፡፡ ፈረንጆቹ ሰርቀውና ከራሳቸው ጋር አጣጥመው በእኛው ላይ ከመነገዳቸው በፊት መፍጠንም ይጠበቅብናል፡፡

የእኛ ‹‹ዘመናዊ›› ሙዚቃ ግን የሮክ፣ የህንድ፣ የላቲን፣ ወዘተ. የተባለ ሥልት በመቀዳት ልቃሞነት ውስጥ እየዋተተና አፍ እስከ ማኮላተፍ በደረሰ ፈረንጅ የመሆን ምኞታዊነት ተጠምዶ ይገኛል፡፡ አንድ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደን ለታሪክ ያህል ይዞ እንደቀረ ሁሉ፣ ብዙ ሙላቱ አስታጥቄዎችና ተስፋዬ ለማዎችን መውለድ ቸግሮታል፡፡ ጮርቃው የኢትዮጵያ የፊልም ጥበብ የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦችን ሰፊ ባህልና ሌሎች የቱሪስት መስህቦችን ቢያንስ በድባብነት መጠቀም ቢያውቅ፣ ርኩስና ቅዱስ መንፈስ ጣልቃ እየገቡ ታሪክ የሚሾፍሩበትን ውዳቂ ሥልት ከመቃረምና ከምኞች ማሟያነት ዘለል ብሎ ከአገራችን ሕይወት ጋር እትብቱን ቢያገናኝ፣ መንግሥትም ፊልም በትውልድ እነፃ በኩል የሚኖረውን ኃያል ጥቅምና በአፍሪካ ውስጥ ሊያገኝ የሚችለውን ያልተነካ የገበያ ዕድል ቢያስተውልና ለዕድገቱ ቢጨነቅ፣ ልማታችንን የሚደግፍበት አንዱ ምንጭ ሊሆን በቻለ ነበር፡፡ ለአገልግሎታዊ ገቢ ዝቅተኛ ግምት የሚሰጡ ቢኖሩ ይህ  ዘርፍ (ፊልምን ጨምሮ) በህንድ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ብልጫ ድርሻ ቢያጤኑ ትምህርት ያገኛሉ፡፡

Related stories   ሀገሪቷን ከጥፋት ለመከላከል ፣ ህግን ለማስከበር ፌዴራል ፖሊስ ተግባሩን ያጠናክራል

ይኼን ሁሉ ማድረግ የምንችለው ግን በየብሔር ብሔረሰብ ድንኳን ውስጥ እየተሮጠና የብሔራዊ ክልሎች የግንብ አጥር እየተበጀ፣ ድንገት መገንጠል ቢመጣ እየተባለ ግዛት ቆጠራ ውስጥ እየተገባ፣ የአንድ ወረዳ ወይም ቀበሌ በሌላ ክልላዊ አስተዳደር ውስጥ መግባት መሬትን በመነጠቅ እየተተረጎመ፣ የብሔራዊ ክልላዊ መስተዳድር መዋቅር ተስማምቶ ለመተዳደርና ዕድገትን ለማምጣት ሳይሆን በመሬት ድርሻ ማረጋገጫነት እየታየና እየተመዘነ አይደለም፡፡

ከላይ ከጌጣጌጥ ጀምሮ በሩጫው መስክ በአርኪዮሎጂ፣ በሙዚቃ በፊልም ዘርፍ ያሉ ምሳሌዎችን አንስተናል፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ዝርዝር መነሻ ግን ዋናውና ትልቁ የኢትዮጵያ ጥያቄ ነው፡፡ ይህ ትልቅ ጥያቄ ምንድነው? ልማት፣ ፍትሕ፣ ዴሞክራሲና እኩልነት ለኢትዮጵያ ሕዝቦች የማይታለፉ መብቶች ስለመሆናቸው ሲወራና ሲነገር ብዙ ጊዜው ነው፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ በምትገኝበት ሁኔታ ውስጥ እነዚህን የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በአንድ ላይ የሚያስገብር ትልቅ ጥያቄ አለ፡፡ የመኖር ወይም ያለመኖር ጥያቄ፡፡ የሁላችንም ማነጣጠሪያ መሆን ያለበት ይህ ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡ የትግሎቻችን አስፈላጊነትና ፋይዳም በዚሁ በትልቁ አደራ ውስጥ መስተዋል ይኖርበታል፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ፓርቲዎችና ንቅናቄዎች አስተሳሰብና ተግባር በዚህ አገራዊ አደራ እየተመራ ነው ወይ? የአገር መውደድና የብሔራዊ ስሜት መፍለቂያና መፍለቅለቂያ ምንጭ ይህ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ትግሎችና ንቅናቄዎች፣ ፓርቲዎች/ቡድኖች ከጠላትነት ግንኙነት ወጥተው በአገራዊ ተልዕኮና ኃላፊነት ላይ መዛመዳቸው፣ የመቀዋወምና የሥልጣን ትግላቸውም በዚህ ትልቁ አገራዊ የጋራ ግብ ውስጥ ዋይና አዳሪ መሆኑ፣ የአገሪቱ የመንግሥት አውታራት (በማዕከልም ሆነ በክልል) ከአንድ ውስን ቡድን/ቡድኖች ተቆጣጣሪነትና ከእከክልኝ ልከክልህ አሠራር ተላቀው ለሕግና ለሥራ ኃላፊነት መታመንን መጎናፀፋቸው፣ ከየትኛቸውም ፓርቲ የሥልጣን አፍቅሮት የማይወዳደር ጥንካሬና የአገር ፍቅር ስሜት ምንጭ  ነው፡፡ አገር መውደድን፣ የአገር ፍቅርንና ብሔራዊ ስሜትን ጉድ የሠሩት፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ትንንሽ ቅዳጅና ጥብቆ ዓላማዎች ናቸው፡፡ ይኼንን በውጤትነት ያስከተለው ደግሞ በ1966 እስከ 1969 ዓ.ም. ኅብረ ብሔራዊ ትግል ላይ የወረደው ፍጅትና ይህም ኅብረ ብሔራዊ ትግል ተንኮታኩቶ በተቃውሞ መድረክ ላይ፣ በክልልተኝነት የተጣበቡ ብሔርተኛ ቡድኖች ብቻ ተዋናዮች መሆናቸው ነው፡፡ በዚህ ላይ የተመሠረተውና ከሃያ አምስት ዓመታት በላይ የቀነጨረው አሠራር በአንድ አገር ውስጥ እየኖሩ ካሉበት ውስን አካባቢ ውጪ መምጣትን ባዕድነት መለያ እያደረገ፣ በሌላ በኩል ራስንም ለቀሪዎቹ ወገኖች ወይም ብሔሮች ባዕድ እያደረገ መጣ፡፡ ዝንባሌው በርክቶ አገራዊ ዝምድናው የስም ብቻ ሆነ፡፡ ባይተዋር የሆኑ ትናንሽ ምድሮች ተፈጠሩ፡፡

አገራችን ብዙ የውኃ ሀብት እያላት ግን ያላለማች፣ የሰማይ ዝናብ ከመጠበቅም ያልተላቀቀች፣ ውኃ እያላት የሚጠማት፣ ለም መሬት እያላት ረሃብ ዛሬም ያልተለያት አገር ናት፡፡ ረሃብን የማሸነፍ ትግሏ (የግብርና የኢንዱስትሪ ልማቷ)  ዞሮ ዞሮ የውኃ ሀብቷን መሠረት ከማድረግ አያመልጥም፡፡ የኢትዮጵያ የውኃ ልማት ደግሞ ውስብስብ ፈተና ያለበት ነው፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያን ልማትና ዕድገት ለህልውናችን አደጋ ነው የሚሉ ተቀናቃኞች/ጠላቶች አሉባት፡፡ ተቀናቃኞች ሌላው ቢቀር ኢቀጥተኛ አሰናካይነት ውስጥ እጃቸውን መክተታቸው የኖርንበትና ወደፊትም የሚጠበቅ ነው፡፡ የውስጥ ችግሮችን ከጎረቤት አገር ጋር ማጠላለፍ፣ አዳዲስ የአካባቢ ቅራኔ ውስጥ ለመክተት መሞከር፣ የውስጥ ተቃዋሚን ተንተርሶ የውስጥ ችግሮችን ማባባስ፣ የሃይማኖት ሰላምን ማደፍረስ ሁሉ ለዚህ አገልግሎት ይውላሉ፡፡ የአሰናካይነትና የበጥባጭነቱ ውጤታማ መሆን አለመሆንም ኢትዮጵያ ካለችበት የውስጥና የአካባቢ ሁኔታ ምቹነት ጋር በእጅጉ የተያያዘ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ለመልማት እየጣረች ቢሆንም፣ አካባቢያዊ አፈናንና ጥቃትን ተከላክሎ የማደግ አቅሟን የሚቀንሱና የሚታገሉ የውስጥ ችግሮች አሉባት፡፡ በውስጧ ያሉት በድህነት ላይ የተደረቡት ከፖለቲካ ቡድኖች ግብግቦች ጋር የተዋረሱና ሕዝብን ያጣቀሱ ቅራኔዎችና ውዝግቦች፣ ለእሳት አላኳሾና ለኳሾች የሚያጋልጡ መሆናቸው ክርክርና ማብራሪያ የሚያስፈልገው አይደለም፡፡

ኢትዮጵያውያን በተለይም ወጣቶች በታላቅ ብሔራዊ ስሜት ውስጥ እንዲከቱ ከተፈለገ፣ ኢሕአዴግ ጠንካራ የአገር ፍቅርና ብሔዊ ስሜት መገንባት ግን አልቻልኩም ያለውን የእምነት ቃል ከልብ የሚያምንበት ከሆነ፣ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ኃይሎች ተፋራሽ የሆነ ግንኙነት መለወጥ ‹‹መፍቀድ›› አለበት፡፡ የገዛ ራሱን ተቃውሞን የማስተናገድና የሥልጣን ትግሉንም ታላቁና አገራዊው የጋራ ግብ እንዲገዛው ማድረግ አለበት፡፡ የአገራችን የፖለቲካ ኃይሎች ከጠላትነት ግንኙነት ካልወጡ፣ በጋራ አገራዊ ተልዕኮና ኃላፊነት ላይ ካልተዘማመዱና ካልተዋወቁ፣ የመቃወምና የሥልጣን ትግላቸውንም በዚህ ታላቅ አገራዊ የጋራ ግብ ውስጥ ዋይና አዳሪ ካልሆነ የልማት መሣሪያ የአንድነት ማሰሪያ የሚሆነን ያ ስሜትና ፍቅር ዛሬም እንደራቀን ይኖራል፡፡ የዚህ መንገድ ከመጠማመድ ፖለቲካ መውጣትና ወደ ዴሞክራሲ ማምራት ነው፡፡ የአገርን ዕድልና ተስፋ ከአንድ ወይም ከሌላ ፓርቲ ብቸኛ ሥልጣን ውጭ ማየት መቻልና መብቃት ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከድህነትና ከትርምስ የማውጣት ተልዕኮን ከቡድናዊ ግብግብ በላይ ማስበለጥ የአገር እምነት ሲሆን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ባለ ብዙ ብሔር ብሔረሰቦች መሆኗን ተቀብሎና ተገንዝቦ፣ ይህንን እውነት ከአገራዊ ትስስር ጋር የሚያግባባና ዴሞክራሲያዊ ነፃነትን ማረጋገጥ ነው፡፡

የአንድ ብሔር ብሔረሰብ አባል ሆኖ ማኅበረሰባዊ ማንነትንና መብትን ማወቅ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ኅብር ብሔራዊ የአገር ትስስር እውነታ እስካለ ድረስም የአካባቢ ልዩነቶችን አልፎ በአገር ልጅነት የመተሳሰብ ተዛምዶ ማበጀትም ተፈጥሮአዊ ነው፡፡

በዛሬዋ ኢትዮጵያ የእነዚህ የሁለቱ እውነታዎች መጣጣም ለዕድገታችንም ለህልውናችንም ወሳኝ ነው፡፡ አንዱ ሌላውን ካደበዘዘ ወይም ከተካ ችግር ነው፡፡ በጠባብ ብሔርተኝነትና በብሔራዊ ንቃት፣ በአገራዊ ንቃትና በትምክህተኝነት መካከል ያለው ልዩነት ትልቅ ነው፡፡ የሕዝቦችን ብሔራዊ ማንነትንና የእኩልነት መብትን ማክበር የተሳናቸውና ዳፍንታም ንቀትን የሚረጩ ትምክህተኞች ሺሕ ጊዜ ‹‹ኢትዮጵያ›› እያሉ ቢጮኹ፣ የአገራዊ ተዛምዶው ቀበኛ ከመሆን የተሻለ አስተዋጽኦ አይኖራቸውም፡፡ ኅብረ ብሔራዊ እኛነትን መቀበል ትምክህተኛ መሆን የሚመስላቸውንና ሽብልቅነት የያዙ ብሔርተኞችም ዛሬ ስለጠቅላላ ምድሪቷ፣ ስለመላው የሰው ልጅ ደኅንነትና ስለዓለም አቀፋዊ ዜግነት ማሰብ ከያዘው ሥልጣኔ የቱን ያህል እንደራቁ ቆም ብለው ማስተዋል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሁለቱም ኢትዮጵያን ጎድተዋታል፡፡ ጉድ አድርገዋታል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

ከሪፖርተር ጋዜጣ የተወሰደ

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0
Read previous post:
ከሶርያ ምስቅልቅል ኢትዮጵያውያን ምን እንማራለን?

በአክሊሉ ወንድአፈራው - መግቢያ - በኢትዮጵያ ውስጥ በአገዛዙና በህዝብ መካከል የሚታየው ግብግብ እጅግ እየተካረረና ብዙ...

Close