በአክሊሉ ወንድአፈራው –
መግቢያ – በኢትዮጵያ ውስጥ በአገዛዙና በህዝብ መካከል የሚታየው ግብግብ እጅግ እየተካረረና ብዙ ህይወትም እያሰገበረ በመጣበት በአሁኑ ጊዜ፣ እነሆ ብዙ ሰዎች የሀገራችንና የሕዝቧ መጻዒ እድል ምን ይሆናል በማለት ያስባሉ፣ ይጨነቃሉም።
መጭው ጊዜ ምን ሊሆን እንደሚችል ሙሉ በሙሉ በእርግጠኛነት መናገር ባይቻልም፣ የሌሎች ሀገሮችን ልምድ መገምገምና ከሀገራችን ሁኔታ ጋር በማመዛዘን ከነዚህ ልምዶች “ምን እንማራለን?” ብሎ መጠየቅ በጣም ጠቃሚ ነው። ከዚህም አንጻር፣ የዚህ አጭር ጽሁፍ አላማ የሶርያን የቅርብ ጊዜ ልምድ በመመርመር ይህ ልምድ ሀገራችን ለገጠማት ፈታኝ ሁኔታ የሚቸረው ትምህርት ምንድነው? ሀገራችን ከቀጣይ ጥፋት ለመዳንስ ምን መደረግ አለበት? በሚሉት ጥያቄዎች ላይ ተጨማሪ የውይይት ሀሳቦችን ለማቅረብ ነው።
የአረብ ጸደይ አብዮትና በሽር አልአሳድ
በአውሮፓ አቆጣጠር በዲሰምበር 2010 የተቀሰቀሰውና የአረብ ጸደይ ( Arab Spring ) እየተባለ የሚጠራው የመካከለኛው ምስራቅ ህዝቦች አምባገነኖችን አይናችሁን አንይ ብለው በቁጣ ያርበደበዱበትና ያፍረከረኩበት አርድ አንቀጥቅጥ የሆነው የህዝቦች አመጽ ሶሪያ ውስጥ የተከሰተው ትንሽ ዘግየት ብሎ ነበር።
የአረብ ጸደይ እንቅስቃሴ በብዙ ሀገሮች በዋናነት “መንግስት ሰልጣኑን ይልቀቅ” ( Ash-sha`b yurid isqat an-nizam) በሚል መሪ መፈክር ስር ሲካሄድ፣ ሶርያ ወጣት፣ የተማረና ምናልባትም የተሻለ ስርአት ተግባራዊ ያደርጋሉ ተብለው በተጠበቁት መሪ ፣ በበሽር አልአሳድ ስር ይተዳደሩ ነበር። ለ40 አመት በፈላጭ ቆራጩነት ይገዙ የነበሩትን ሀፊዝ አልአሳድን ሞት ገላግሏቸው የተደሰቱት ሶርያውያን ከእርሳቸው የባሰ አይመጣም ብለው በመገመት በአዲሱ ፕሬዝዳንት ላይ ተስፋ የጣሉ እጅግ ብዙዎች ነበሩ።
ምንም እንኳ በህዝብ ፍላጎት ሳይሆን በአምናገነኑ አባታቸው ውሳኔ ስልጣን ላይ ቢወጡም አዲሱ መሪ በሸር አልአሳድ ሰላማዊ ለውጥ ያስከትላሉ የሚል ታላቅ ተስፋ ቢያንስ ከላይ ከላይ ሲናፈስ ይስተዋል ነበር። ያ ሳይሆን ቀርቶ ግን ሶሪያ በአጭር ጊዘ ውስጥ እጅግ የተካረር ባለብዙ ገጽታ የፖለቲካ ምስቅልቅል ውስጥ ገባች። እጅግ ለማመን በሚከብድ ሁኔታም በዓለም ዋናዋ የስደተኛ መፍለቂያ ሀገር ሆነች። ከተሞቿ፣ የታሪካ ቦታዎቿ፣ ቅርሶቿ መጋየት ጀመሩ። የሟች ሶርያውያንን ቁጥር ማወቅ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደረሰ። ሁሉም ታላላቅ ከተሞች፣ ዋና ከተማዋ ደማስቆን ጨምሮ በሁለትና ሶስት ተፋላሚ ድርጅቶች ስር መውደቅ ጀመሩ። በሶርያ የውስጥ ጉዳይም ዋናዎቹ ተደራዳሪወችና ተናጋሪዎች ሶረያውያን ሳይሆኑ እጅግ ብዙ የባእድ መንግስታትና የውጭ ድርጅቶች ሆኑ::
ለውጥ ያመጣሉ የተባሉት ወጣቱ መሪ፣ የሚመሩትም መንግስት ይሁን እርሳቸው ከተኳቸውና በጭካኔያቸው ከታወቁት አባታቸው ብሰው ተገኙ፤ ስርአቱን የሚቀናቀን ማንኛውንም ሰው ያለርህራሄ መጨፍለቅ የእለት ተእለት ተግባራቸው ሆነ። ፎሬይን አፊርስ (Foreign affairs) የተሰኘው መጽሄት አንድ ዘጋቢ በቅርቡ፡እንደጻፈው የበሽር አልአሳድ አገዛዝ፣ ጭካኔው፤ ንቅዘቱ፣ ወገንተኛነቱ፣ የማፊያ አይነት የአሰራር ስልቱ… ወዘተ ሲታይ በሽርና መንግስታቸው ከአረመኔያዊው አባታቸው፣ በብዙ እጥፍ እንደሚብሱ አሳይተዋል ነበር ያለው።
ታዲያ ሶርያ ለምን ወደዚህ አይነት የጥፋት ጉዞ ገባች? አዲሱ መሪና መንግስትስ እንዴት ከተጠበቁት በተጻራሪው ሆነው ተገኙ?

Related stories   “ጣልያኖችም ሆኑ እንግሊዞች ቅኝ ግዛትን ለማስቀጠል ህዝቡን በዘር መከፋፈልን እንደ አንድ ስልት ይጠቀሙ ነበር” -አቶ ታቦር ገረሱ ዱኪ

ጡንቻንና የከፋፍለህ ግዛን ተንኮል ዋና መመሪያው ያደረገ ስርአት ያሰከተለው እዳ
በአውሮፓ አቆጣጠር በኖቨምበር 1970 በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ለስልጣን የበቁትና ለአርባ አመታት ያክል በስልጣን ላይ የቆዩት ሀፊዝ አላአሳድ እና የሚመሩት ሶሻሊስት ቀመሱ የአረብ ብሄረተኛ ፓርቲ በሀገር ውስጥ ይከተሉት የነበረው ፖሊሲ የህዝባቸውን ይሁንታ በማግኘትና ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር በሚደረግ ጥረት ላይ ያተኮረ ሳይሆን፣ የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍልን ወዳጅ፤ ሌላውን ደግሞ እንደጠላት በመፈረጅ፤ የተወሰነውን ክፍል በማቅረብ ሌላውን ደግሞ የማራቅና የማጥቃት ፖሊሲን መሰረት ያደረገ ነበር። በዚህም መሰረት በተለይም የሱኒ እምነት ተከታዮችን፤ 10% የሚሆኑትን ክርስቲያኖችና፣ 3% የሚሆኑትን ድሩዞች (Druze) እንዲሁም የራሳቸው የሀፊዝ አልአሳድ ወገንና ተወላጆች የሆኑትን 10% የሚሆኑትን አላዋዮችን (Alawi) የቅርብ ወዳጅ በማለት ያቀርቧችው ነበር::
በአንጻሩ 15% የሚሆኑትን የሶርያ ኩርዶችን፤ ቀደም ሲል በስልጣን ላይ የነበሩትን የሱኒ እምነት ተከታይ የነበሩትን ባለስልጣኖችና ወገኖቻቸውን፤ “ጨቋኝ” ብለው የመደቧቸውን የመሬት ባለሀብቶችና ነጋዴወችን፤ እንዲሁም ስርአቱ የሚመራበትን የአረብ ሶሻሊስት ራእይና ፖሊሲን የተቃወሙትን ሁሉ ከፖለቲካውም ሆነ ከኢኮኖሚው ምህዳር እንዲገለሉ አድርገዋል:: ህብረተሰቡንም ከላይ በተመለከተው ሁኔታ እርስ በርስ የወዳጅና የጠላትነት ስሜት እንዲኖረው እየቀሰቀሱ ነበር የገዙት። ሀፊዝ አልአሳድ በህብረተሰቡ ውስጥ የነበረውን የኢኮኖሚና የተለያዩ ማህበራዊ ብሶቶችን በማራገብ፣ ህዝቡን ከሚያመሳስሉ እሴቶች ይልቅ በሚያለያዩት ጉዳዮች ላይ በማተኮር ነበር ክፍፍሉ ስር እንዲሰድና አንዱ በሌላው ላይ የመረረ ቂም እንዲይዝ ያደረጉት።
ሌሎቹ የህብረተሰብ ክፍል አባላት እርስ በርስ ሲናቆሩ፣ ከ1970ወቹ ጀምሮ በተለይም በሀገሪቱ ፖለቲካና፣ ወታደራዊ ስልጣን የበላይነትን አጠናክረው የተጓዙት 10% ከሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል የተውጣጡት አላዋዮችን (Alawi) ናቸው። ይህ ደግሞ በአጋጣሚ የተፈጠረ ሳይሆን በእቅድ ደረጃ በደረጃ ተግባራዊ የተደረገ ጉዳይ ነው።
በሀፊዝ አልአሳድ የሚመራው ባአዝ ፓርቲና (Arab Socialist Ba’ath Party) መንግስቱ ፖለቲካውን ለብቻው ሙጥኝ ብለው መቆየት ብቻ ሳይሆን እጅግ ዘግናኝ የሆነ ጭፍጨፋም በሶርያውያን ላይ በተደጋጋሚ አካሂደዋል። ከነዚህም ውስጥ በአውሮፓ አቆጣጠር ከ1977 ጀምሮ እያደገ የመጣውን ተቃውሞ ለማፈን የተደገረገው ጭፍጨፋ፣ በጁን 1979 የተደረገውን የመንግስት ግልበጣ ሙከራ ተከትሎ 50 የሚሆኑ ወታደራዊ መኮንኖች ላይ የተካሄደው ግድያ፤ በ1980 ፕሬዚደንት አሳድን ለመግደል የተደረገውን ሙከራ ተከትሎ በእስር ላይ ይገኙ የነበሩ የ250 ሰወች መረሽን፣ በፌበርዋሪ 1982 የተነሳውን አመጽ ተከትሎ በሃማ ከተማ ከ10 እስከ 25 ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ላይ የተካሄደው ጭፍጨፋ፤ እንዲሁም ከ1982 እስከ 1992 በሽዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ እስር መወርወራቸው እስከ 10 ሺህ የሚደርሱ ሌሎች መገደላቸው የስርአቱን ግፍ በከፊሉ ያሳያል።http://foreignpolicy.com/2011/08/05/massacre-city-2/
አዲሱ ፕሬዚዳንት በሽር አልአሳድ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ 2000 አመተ ምህረት ስልጣኑን ከአባታቸው ከሀፊዝ አልአሳድ ሲወርሱ አብረው የወረሱት ደግሞ ሰጥ ለጥ ያለ የሚመስል ሁኖም ግን ውስጥ ውስጡን በምሬት የተቃጠለና እርስ በርስም እጅግ የተቃቃረ ህብረተሰብን ነበር። ከዚህ በተጨማሪ በሽር አዲስ ፕሬዚዳንት ይሁኑ እንጂ የወረሱትና ከሞላ ጎደል እንዳለ ያስቀጠሉት ግን 40 አመት ሙሉ በጭቆና ህዝብን ያስተዳድር የነበረውን ፖለቲካ ፓርቲ ከነባለስልጣናቱ ነበር።
ባጭሩ የተካሄደው ለውጥ በፕሬዚዳንቱ ወንበር ላይ እንጂ በገዥው ፓርቲና በስርአት ደረጃ አልነበረም። አዲሱ መሪ ያስቀጠሉትም የተለየ ራእይና አካሄድ ሳይሆን የአባታቸውን ሌጋሲ ነበር።
በደል ገደብ እንዳለውና የህዝብን በቃኝ ማለት ለመረዳት ያልቻለ ስርአት ውጤት …. ሙሉውን ለማንበብ ሊንኩን ይጫኑ

Related stories   “የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች አለመምጣት የሚያጎለው አንዳችም ነገር የለም፤ እኛም አንጠብቃቸውም” ፕሮፌሰር በየነ

the-case-of-syria-lesson-for-ethiopiajan62017

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *