…ያበደው ” እመኑኝ” ይላል። አዲስ አበባን የሚመቻት በልኳ የሚሰፋ ፖለቲካና ፍልስፍና ከልተበጀ  አትነቃነቅም። ሁሉን ስላቀፈች ለሁሉም ቤት እንዳትሆን ለሚጎትቷት መልስ የላትም። የሁሉ እናት ሆና በረከቱን ስላየች ጎንደሬ፣ ኦሮሞ፣ ሲዳማ፣ ኦጋዴን፣ ሶማሌ፣ አፋር፣ ትግሬ… በሚሉ ሃይሎች ለመበለት አትፈቅድም። ግን ለውጥ ትፈልጋለች። መለወጥ ያምራታል። ሁሉንም ታውቃለች። አትሸወድም። ንቃቷ ከሁሉም በላይ ነው። ችግር ቢያንተከትካትም ” ብልኬ” ባይ ነች። ልኳ የሁሉም ቤት ሆኖ የመኖር እምነቷ ነው። እምነት !! በቦስና ቋንቋ  ማተቧ አብሮነት ነው!!…

አዲስ አበባን ጅል የሚያደርጉ አሉ። ግን አዲስ አበባ አዋቂ ነች። የነቃች ነች። ዝም ብላ አታብድም። የማያዋጣት ጨዋታ ውስጥ አትገባም። በጎሳ ፖለቲካ ውስጥ ሳትንቦጫረቅ ሩብ ምዕት ኖራለች። ያም ሆኖ ህመም ቢኖርባትም ዋስትና ትፈልጋለች። ለውጥ ፈላጊ ብትሆንም እሷን የማያካትት ከሆነ ይደብራታል። “በራ” ማለትን ትወዳለች። ግን ሁሉም ሆኖ የኑሮ ምላጭ ውጣ እየሸረካከታት ነው። አይ አዲስ አበቤ!! አይ አዲስ አበባ!! ስምሽ ደግ አዳርና ውሎሽ ቀለሙ የማይታወቅ….. አዱ ገነት ዥጉርጉር!!

እንደምን ከረማችሁ? ገና ነበር። በገና እሱ ተወለደ። ቦታ ጠፍቶ በረት ውስጥ ተገኘ። አዋቂዎች፣ አጥባቂዎች፣ መምሮች፣ ባለጠጎች፣ አገልጋዮች፣ የተከበሩ… እያሉ ለእረኞች ተከሰተ። ንጉሱን እረኞች ለመጀመሪያ ጊዜ ሰገዱለት። ለተከበሩት ለነዛ ምናምንቴዎች ንጉሱን አበሰሩ።ከሁሉም መርጦ ለነሱ ተገለጠ!! ብስራቱን በእረኞች በኩል አደረገው… ይገርማል። ደቀ መዝሙሮችን ልኮ ያቺን፣ ያቺን የተገፋች፣ ” የመንጻት ህግ” የሰለጠነባት ሳምራዊ አገኘ። አናገራት። ጠየቃት። በመጠየቅ አዳናት / ነፍሷን!! አይሁድ ከሳምራዊ ወሃ ለመነ። “እኔ ነኝ” አላት። ስለ እራሱ መናገር ባይወድም ለእርሷ እሱነቱን ገለጠላት። ከዛም ሰበከችው። የተናቀችው አዳኙን አወጀች… መታደል!!  ገና- ሽብሸባ፣ ድግስ፣ ጋጋታ፣ እስክስታ፣ ቀረርቶ… አይደለም። ጥሞና ነው።  እሱ በቤታችሁ፣ በልባችሁ፣ በህሊናችሁ የተወለደ ታድላችኋል። በልታችሁ ያገሳችሁ ተሸውዳቹሃል። ደስታው ደግ ቢሆንም ያን ዘመን ለሚያስቡ ገና መወለጃ ቦታ የሚፈልግና፣ እንዲወለድ ለሚፈልገው ቦታ በሚፈቅዱ መካከል የሚደረግ ቃል ኪዳን ነው!! በቃ!!

ያበደው ቀና። እረኛ ወይም ሳምራዊቷን መሆን ተመኘ። አይሁድ በመጠየቀ ይፈውሳል። በመጠየቅ ውስጥ ፈውስ አለ።  እሱ ሲጠይቅ የማንሰማ “ቴሌዎች” በዛንና ህይወት የሌለው ድግስ አድማቂ ሆን… ያበደው የተነሳበትን ረሳው። አዲስ አበባ ” ተኝታለች” ይላሉ። አዲስ አበባ በማንኮራፋት ሳይሆን በኩርፊያ ውስጥ እንዳለች ግን ሳታሳብቅ አላረፈችም። ኑሮ ልጆቿን እየለበለበባት ነው። ቦሰና እያለቀሰች የሰማችውን ተረከች። ” መማር ከንቱ” ስትል መሬት ጫረች። አዲስ አበባ የአንዱን ልጇን የኑሮ መልክ አሳየቻትና “አዬ” ስትል አንጋጠጠች። “የገናው ንጉስ አንተ መላ ፈልግ እንጂ” ስትል በየዋህነት የእናቶቻችን ልቡና ማመልከቻዋን ወደ አርያም ላከች።

ለጁ ተመራቂ ነው። ዘመዷ!! ባለ ዲግሪ ነው። አሁንም ጡረተኛ ነው። እየሰራ የሚጦር!! አዲስ አበባ የሰራተኛና የስራ አልባ ጡረተኞች፣ የእድሜ ጡረተኞች፣ የተፈጥሮ ጡረተኞች…. ብዙ አይነት ጡረተኞች ተሸክማለች። ቦሰና የተፈጥሮ ጡረተኞች የምትላቸው በጸሎት በልተው፣ በጸሎት የበሉትን ከፍለው፣ በጸሎት ማረፊያ ፈልገው፣ በጸሎት ላረፉበት ከፍለው፣ ሲነጋም ሲመሽም ሁሌም አዲስ ነገር የማያዩ… እንዲሁ ኖረው፣ ኖረው እድር በሳጥን አድርጎ በደማቅ ስነስርዓት የሚሸኛቸውን ነው። ከቁም ኑሯቸው ሞታቸው የሚስብ!! አይ እኛ… ከኗሪ ለሟች የምናነባ፣ የምናዝን፣ የምንነፈርቅ፣ ደረት የምንደቃ፣ በቃ ከቆመው፣ ከሚወለደው፣ መኗሪው ይልቅ ለአስከሬን የምንዘምር፣ የምንገበር፣ ኢንቨስት የምናደርግ ጉዶች!! ግን ሁላችንም አይደለንም!!

ቦሰናን አሁን አንጀቷን የበሏትና ያሳሰባት “እየሰሩ የሚጦሩት” ናቸው። ይህ ዘመዷ 2000 ብር ያገኛል። 2000 የተመራቂዎች የመነሻ ደሞዝ ነው። ደሞዙ የተተመነው ኑሮውን አጉኖ እላይ የሰቀለው የሃይለማርያም፣ ይቅርታ የእነ መለስ፣ አሁንም ይቅርታ የእነ… አስተዳደር ነው። የአገራችን ኢኮኖሚ በድርብ አሃዝ አደገ ሲባል ” ሌሊት ሌሊት ህዝብ ሲተኛ ነው?” ብሎ መጠየቁን ቦሰና አትረሳም። አንዳንዴ ሲነሽጣት ” ይሄ እድገት አይታይም” ትላለች። ኪስ ውስጥ ካልገባ “ምን ዋጋ አለው?” ለማለት ነው። እናም ይህ ዘመዷ 2000 ይጣልለታል። ትራንስፖርት ችሎ ፣ በልቶ፣ ጠጥቶ፣ ለብሶና ተጫምቶ አይበቃውም። መዝናናት አይታሰብም። ፍቅረኛውን በሻይ ሲቀቀላት ጥላው ሄዳለች።

ለካ ክህደቱ፣ ማምታታቱ፣ ስርቆቱ፣ የቀደመው ፈሪሃ እግዜሩ የከሰሙት በዚሁ የተነሳ ነው። አዎ አዲስ አበባ ኑሮ ባደመባቸው ስለተሞላች እምነትና መተማመን ሸሽቷታል። ምን ይደረግ ጠኔ አደገኛ ነው። እያዩ መሞት የለ፤ መመነተፍ ነው። “አዲስ አበባ የሁሉም ነች” ሲባል እንዚህንም ያካትታል። የፍቅር መሰረቱ ሆድ ሆኗል። የትዳር መሰረቱ ገቢ ሆኗል። የሌለውን ማን ይፈልገዋል። ምኞት ለያውም የተፈጥሮ ደግሞ አባይ/ አቅል የለውም። ራስን ያስረሳል። እናም ….. ግን አዲስ አበባ መቼ ነው የትራንስፖርት ወረፋ የሚቀረው? ያበደው ጠየቀ? ለነገሩ የሁሉም ጥያቄ ነው።

ነገርን ነገር ያነሳዋልና ፣  ባቡር ተዘረጋ ፣ አውቶቡስ ተጨመረ፣ የከተማ ውጪ ሚኒ ባሶች በተደራቢነት ተመደቡ፣ ችግሩና ስልፉም የዛኑ ያክል ያድጋል። ለምን? አሃ ኑሮ አድጎ በመኪና የሚሄዱ በዙ። በግር መሄድ ቀረ። ስኳር ሲጠፋ “ገበሬው ሁሉ ስኳር መብላት ጀመረ” እንደተባለው። ጤፍ ሲወደድ ” ገበሬው ጤፍ መብላት ስለጀመረ” እንደተባለው… ሚኒ ባስ ቢባል አሁን ያሉት ሚኒባሶች እንዴት ነው ምርመራ የሚያልፉት? ከርክሰዋል። መብራት እንኳን በወጉ የሌላቸው አሉ። መቀመጫቸው በጊዜ ብዛት ራሱን ወደ ታጣፊነትና ቆርቋሪነት የቀየረ፣  እንዲህም ሆኖ የትራንስፖርት ችግር የሚቀረፈ አልሆነም። ሳናድግም፣ አሁን ” አድገንም” ችግሩ ሲሰፋ እንጂ ሲጠብ አይታይም። … ያበደው ሃሳብ በዝቶበት አንዱን እያነሳ ሌላውን  ጣለ። ቤት ተከራይቶ የሚኖር የ2000 ሺህ ብር ጡረተኛ ይቅርታ ደሞዝተኛ እንዴት ይኖራል? አባት ልጆቹን እንዴት እንዳሳደገ ሲጠየቅ ” በታምራት” እንዳለው ካልሆነ በቀር።

አንድ ተራ ሽሮ 30 ብር  ነው። 2000 የሚያገኝ ሰው ቤት ተከራይቶ 30 ብር ከፍሎ ሽሮ የመብላት ድፍረት የለውም። ዲግሪ ይዞ ሽሮ ለመበላት የሚሸማቀቅ ሰራተኛ፤ ከበላም የግድ ” ኪራይ ስብሳቢ” ሆኗል ማለት ነው።  እና አሁን አሁን “ስራ አለኝ” ማለት ደባሪ … በወሩ መጨረሻ ስንት ስንት ይጨመር የሆን? የደሞዝ ጭማሪ በወሩ መጨረጫ እንደ ጸበል እንደሚረጭ ተነግሯል። ያበደው አንድ መልዕክት አለው። ደሞዝ ሲጨመር የሽሮውን ዋጋ ፍሬን ግጥም አደርገው እንዲይዙት!! እንደው የሰራተኞቹ ጉዳይ ተነሳ እንጂ አዲስ አበባ በየስርቻው ያቀፈቻቸው የተማሩ ስራ ፈቶች እንዴት ይኖሩ ይሆን? አሳሳቢ…

ቦሰና ዘመዷ ጠዋት ተጣጥቦ፣ በቆሮቆንዳ የታጠበ ሸራ መስሎ ወደ ሰራ ሲሄድ የሚሰማውን ነግሯት ውስጧ አዝኗል። እሱ ብቻ አይደለም ሰሞኑንን አደገኛ ወሬ ለቃሚ ሆናለች። ቀረጥና ታክስ አደገኛ ጉዳይ መሆኑንን ሰማታለች። የሂሳብ ሰራተኛ ሲሳሳት ባለቤት ወደ እስር ቤት ይቅርታ ” ወደ መመረቂያ” ቤት ይላካል። ማስተማር የለም። ” ተሳስቷልና አስተካክለህ አምጣ” አይባልም። አንዳንዶች በመቶ ሺህ የሚቆጠር በጀት እያላቸው በሚሊዮን ታክስ ይጣልባቸዋል። እንዲህ አይነት ስህተት የሚሰሩ ምንም አይባሉም። አምስት መቶን አንድ ዜሮ ጨምሮ ያሳሳተ አለቀለት!! ይህም የመልካም አስተዳደር ሳይሆን የመልካም አስተሳሰብ ችግር ነው።

አዲስ አበባ አሁን አንዳንዶቹን አራዳ እያደረግች ነው። ንቃቷን እያካፈለቻቸው ነው። ቤት ለጋራ መከራየት ተጀምሯል። ጠበሳ ሲኖር በስምምነትና ” በመፈቃቀር ላይ በተመሰረተ” ይከናወናል። እቅድ ይወጣል። …. በተጻራሪው 2000 እየወሰዱ የሚሊዮን ኑሮ የሚኖሩ አሉ። የቶጀሩ አሉ። ኑሮን ሌሎችን ሲያንጠባጥባቸው ኑሮን የሚያንቀረቅቡ አሉ። የጥልቁ ተሃድሶ ዘመቻና የአዲስ አበባ መዥጎርጎር በቀለም የሚገለጸው አይደለም። አዱ ገነት የገንዳ፣ የገዳም፣ የጎዳና፣ የቱቦ ውስጥ፣ የህንጻ ላይ… ሁሉም አይነት ህይወት ይፈስባታል። አዲስ አበባ ብትነፍርም አላመጸችም። የአመጹ አይነት የተስማማት አትመስልም። ጎሳና ጎጥ ውስጥ መወሸቅ አትወድም። ንቃቷ ይህን አይቀበልም። ብችግር የምትነፈረው አንሷት በጎሳና በቀበሌ አሳብ መናጥ አልመረጠችም። በሄርና ጎት ውስጥ መቀርቀር አልፈለገችም።

ያበደው ” እመኑኝ” ይላል። አዲስ አበባን የሚመቻት በልኳ የሚሰፋ ፖለቲካና ፍልስፍና ከልተበጀ  አትነቃነቅም። ሁሉን ስላቀፈች ለሁሉም ቤት እንዳትሆን ለሚጎትቷት መልስ የላትም። የሁሉ እናት ሆና በረከቱን ስላየች ጎንደሬ፣ ኦሮሞ፣ ሲዳማ፣ ኦጋዴን፣ ሶማሌ፣ አፋር፣ ትግሬ… በሚሉ ሃይሎች ለመበለት አትፈቅድም። ግን ለውጥ ትፈልጋለች። መለወጥ ያምራታል። ሁሉንም ታውቃለች። አትሸወድም። ንቃቷ ከሁሉም በላይ ነው። ችግር ቢያንተከትካትም ” ብልኬ” ባይ ነች። ልኳ የሁሉም ቤት ሆኖ የመኖር እምነቷ ነው። እምነት !! በቦስና ቋንቋ  ማተቧ አብሮነት ነው!! ቸር እንሰንበት!! ገና የገባችሁ ተባረኩ። ያልገባቹህ ድፎ ጋግሩ፣ ድግስ አድምቁ፣ ንጉሱ ከመወለጃ ስፍራ እንጂ ከግር ግር ጋር ጉዳይ የለውም!! አሜን!!አሜን ጌታ ቦታ ላዘጋጁለት ተወልዷል። ለሚወዱት ሁሉም ቀን ልደቱ ነው። አሜን ሁሌም !!

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *